Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በትግራይ ክልል ለማስጀመር እንቅስቃሴ ተጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቋርጦ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት እንደገና ያስጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በመላው አገሪቱ አገልግሎት ላይ የዋለውን የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት (ቴሌ ብር) በትግራይ ክልል ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ከድምፅ በተጨማሪ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በትግራይ ክልል ከተሞች መቅረብ መጀመሩን ለሪፖርተር ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት የሆነውን ‹‹ቴሌ ብር›› በክልሉ ለማስጀመር የሚመለከተው የሥራ ክፍል እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኔትወርክ መጨናነቅ እየተመለከትን የኢንተርኔት አገልግሎት የምናሰፋበት ሁኔታ ይኖራል?›› ሲሉ የገለጹት አቶ መሳይ፣ በትግራይ ክልል አገልግሎቱን ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከማዕከል በተላኩና በቦታው በነበሩ ባለሙያዎች በተደረገው የመልሶ ጥገና መቀሌን ጨምሮ ሽሬ፣ እንዳባጉና፣ ሰለክላክ፣ ውቅሮ ማሪያም፣ አክሱም፣ ዓድዋ እንዲሁም የማይጨው ከተሞች ካለፈው ሳምንት አንስቶ የድምፅ አገልግሎትን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

እስከ ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላው 86 የቴሌኮም ጣቢያዎች ሥራ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 33 ያህሉ በመቀሌ 47 ደግሞ በማይጨው የሚገኙ መሆናቸውን አቶ መሳይ ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በተወሰነ ደረጃ አስቸጋሪ እንዳደረገው የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም የሚጠበቅበትን የፋይበር ጥገናና ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን በክልሉ በተጠናከረ መንገድ እያከናወነ እንደሆነ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

ክልሉን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስጀመር እያደረጉት ያለው ትብብር በጣም ቀና የሚባል ነው ያሉት ቺፍ ኮሙኒኬሽን ኦፊሰሩ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሌለባቸው ጣቢያዎች ነዳጅ በማቅረብ አገልግሎቱ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሞባይል ጣቢያዎች ወደ ሥራ ከተመለሱ በኋላ ከሲም ካርድ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የገጠሙ ችግሮችን ያወሱት አቶ መሳይ፣ ሲም ካርዶች በጊዜ የተገደበ አገልግሎት ከመስጠታቸው ጋር ተያይዞ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ በርካታ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ጥሪ መላክና መቀበል የማይችሉ አሊያም ከሁለት አንዱ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ሲም ካርዶችን ወይም ስልኮች መገኘታቸው፣ ነዋሪዎች ስልኮቻቸው በተለያዩ አጋጣሚ ከእጃቸው ጠፍተው ስልክ አልባ መሆናቸው አገልግሎቱን በማስጀመር ሒደት ውስጥ ያጋጠመ ችግር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ተጨማሪ አገልግሎቱ ከረዥም ጊዜ በኋላ የተመለሰ በመሆኑ፣ በርካታ ጥሪዎች በአንድ ጊዜ መደረጋቸው የኔትወርክ መጨናነቅ እንደፈጠረ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች