- የፌዴራል ፖሊስ በትግራይ ክልል የሚገኙ የፌዴራል ተቋማትን ተረከበ
– የ32 አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች መቀሌን ጎበኙ
በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነትና በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሒደት መሠረት እየተተገበረ ያለው የሰላም ስምምነት ትግበራ ጅማሮ ያለምንም ተግዳሮት እንዲፈጸም፣ የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ትኩረታቸውን በአተገባበሩ ሒደት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነት የደረሰው ዕልቂትና የንብረት ውድመት መሆን ያልነበረበት እንደነበር ያስታወሱት የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች፣ የወገን ዕልቂትና የንብረት ውድመት ምንም ያልመሰላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አሁንም አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የሰላም ስምምነቱ ጫፍ እንዲደርስ እየሠሩ ያሉት ወገኖች ትኩረታቸውን ስምምነቱ ላይ ብቻ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በናይሮቢ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገውን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ውይይት እንዳበቃ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ መቀሌ ተጉዞ፣ ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶና ጉብኝት አድርጎ መመለሱ ይታወሳል፡፡ በመቀጠልም ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ተወካዮችና ዋና አደራዳሪዎች የቀድሞ የናይጀሪያና የኬንያ ፕሬዚዳንቶች ኦሊሴጉን ኦባሳንጆና ኡሁሩ ኬንያታ፣ እንዲሁም 32 የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ወደ መቀሌ ተጉዘው ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ከሁለቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ጋር የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁም (ዶ/ር)፣ መቀሌ ተገኝተው ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሰደርን ጨምሮ የአውሮፓና የአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮችና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መቀሌ ሲገቡ፣ በክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡
አምባሳደሮቹ በመቀሌ ቆይታቸው ከፌዴራልና ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸምን በሚመለከት መወያየታቸው ተነግሯል፡፡
የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የአፍሪካ ኅብረት ቡድን መቋቋሙም ተሰምቷል፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ሁለቱም ወገኖች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የፌዴራል ፖሊስ ከታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል የፌዴራል ተቋማትን ተረክቦ ፀጥታ ማስከበር ጀምሯል፡፡