- ሁላችንም የጉብኝት ቡድኑ አባላት ባየናቸው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ተደንቀናል። ቢሆንም ግን…
- ቢሆንም ምን? የሚያሳዝን ጉዳይ ገጠማችሁ?
- ጥሩ ጅምሮችን ዓይተን ብንደሰትም አንድ ጉዳይ ግን አሳዝኖናል።
- ምንድነው?
- አንድ ከውጭ ክር አስመጥቶ ጨርቅ አምርቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ፋብሪካ ተመልክተን አድንቀን ስናልፍ ባገኘነው ፋብሪካ ደግሞ አዘንን።
- ለምን?
- ምንክንያቱም ይህ ፋብሪካ ከውጭ ጨርቅ አስመጥቶ ልብስ የሚሰፋና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ነው።
- ታዲያ ለምንድነው ያዘናችሁት?
- እንዴት ልብስ ሰፍቶ ለውጭ ገበያ ያቀርባል?
- ታዲያ ምን ማድረግ ነበረበት?
- እንዴ! አገራችን የሚለብስ ጠፍቶ ነው? ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለበት አገር ጥሩ ገበያ አይደለም?
- እሱማ ነው። ግን…
- አለቃ በነገሩ ተበሳጭተው ያሉትን አልሰማህም?
- ምን አሉ?
- ያልገባን ነገር አለ። ልብስ ሰፍተን እያመረትን ለውጭ ገበያ እየሸጥን እንደገና ከውጭ ገበያ ልብስ ለመግዛት የምንሰደድ ከሆነ ያልገባን ነገር አለ ሲሉ በቁጭት ነው የተናገሩት፡፡
- እንዴት እንደዛ ይላሉ?
- ለምን አይሉም ትክልል አይደሉም እንዴ?
- መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሲገነባ ኤክስፖርትን ለማስፋፋትና የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለማሳደግ አቅዶና አስልቶ አይደለም እንዴ?
- እሱማ ነው፡፡
- ይህንንም በፍጥነት ለማሳካት የገበያ ትስስርና ልምድ ያላቸው የውጭ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ማስገባት የተሻለ ነው ተብሎ ታቅዶ አይደለም እንዴ?
- እሱማ ነው።
- አጎዋ የተባለው የአሜሪካ የገበያ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆንን፣ እርካሽ የሰው ኃይል፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዳለን አስተዋውቀን አይደለም እንዴ እነዚህን ኩባንያዎች የሳብናቸው?
- እሱማ ነው።
- ታዲያ ለምንድን ነው አለቃ ‹‹ያልገባን ነገር አለ›› ያሉት?
- እኔም አልገባኝም!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ቢገቡም ጸሐፊያቸው ዛሬም በሰዓት ቢሮ አልተገኘችም፡፡ በነገሩ መደጋገም ተናደው ቢሮ ውስጥ እየተንጎራደዱ ሳለ ጸሐፊዋ እየተጣደፈች ወደ ቢሮ ገባች]
- ውይ ክቡር ሚኒስትር ዛሬም ቀደሙኝ?
- እኔ ቀድሜሽ አይደለም።
- እህ… ነው እንጂ ይኸው ቢሮ ቀድመውኝ ገብተው?
- ቀድሜሽ ሳይሆን የሥራ ሰዓት እያከበርሽ ባለመሆኑ ነው።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር ዛሬስ አርፍጃለሁ።
- ዛሬ ብቻ አይደለም። ታስተካክያለሽ ብዬ ዝም ብልሽም ከመደጋገም አልፎ በዛ፡፡
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር… ወድጄ አይደለም እኮ?
- ስንት ዓመት እዚህ ቢሮ ስትሠሪ ያላየሁብሽን ባህሪ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየሁ ያለሁት፡፡ የሆንሽው ነገር አለ?
- በፊት መኖሪያ ቤቴ መሀል ከተማ ውስጥ ስለነበር ትራንስፖርት አልቸገርም ነበር ራመድ ብዬም መድረስ እችል ነበር። አሁን ግን…
- አሁን ግን ምን?
- መሀል ከተማ ላይ የመኖሪያ ቤት ኪራዩ ከበደኝና ትንሽ ራቅ ብዬ ተከራየሁ… እዚያም ሲጨምር ለቅቄ ራቅ ብዬ ሌላ ቤት ተከራየሁ።
- እሺ…?
- እዚያም ዋጋው አልቀመስ አለና ለቅቄ የከተማው ጥግ ወጥቻለሁ። ለዛ ነው በሰዓቱ ቢሮ ለመድረስ የተቸገርኩት ክቡር ሚኒስትር?
- አሁን የት አካባቢ ነው መኖሪያሽ?
- ኮዬ ፈጬ፡፡
- ከዚህ ከመሀል እዚያ ሄድሽ?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር። ለነገሩ እኔ ብቻ አይደለሁም።
- እህ…?
- አብዛኛው ነባር የከተማዋ ነዋሪ እኮ እንዲሁ የቤት ኪራይ ዋጋውን አልችል ብሎ ከመሀል ከተማ ቀስ እያለ ወጥቶ አሁን ወይ ኮዬ ፈጬ ነው አልያም ደግሞ…
- እህ…?
- የካ አባዶ ወይም ከዚያ አልፎ እየተከራየ ነው።
- ወይ ጉድ…?
- እናንተ ግን የአርሶ አደሩን መፈናቀል ብቻ ይዛችሁ ፖለቲካ አደረጋችሁት።
- እናንተ ማለት?
- ውይ ይቅርታ መንግሥትን ማለቴ ነው።
- እሺ ይሁን… አርሶ አደሩ መፈናቀሉ እውነት አይደለም እያልሽ ነው?
- እንደዛ ማለቴ አይደለም።
- ታዲያ?
- የከተማ ዕድገት ሲመጣ አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን ከተሜውም ይፈናቀላል ማለቴ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ….
- የከተማ ዕድገትና ከተሜነት እስካልቆመ ድረስ መፈናቀልን ማቆም አይቻልም። መቆም ያለበት ሌላ ነገር ነው፡፡
- ምን? እስኪ ቀጥይ…?
- ሥልጣንና ገንዘብ ያላቸው በአርሶ አደር ስም ፖለቲካ መሬት እየተቆጣጠሩ፣ ከተሜውም የሚፈናቀልበት አሠራር መቆም አለበት። ካልሆነ ግን ከተሜውም መጠየቁ አይቀርም።
- ምን? ተፈናቃይ ነኝ ብሎ?
- እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- ሌላ ምን ሊል ይችላል?
- የአርሶ አደር ልጅ ነኝ!