የዛሬው መንገድ ከኮተቤ ወደ አራት ኪሎ ነው። ‹‹የሴት ልጅ ሸክሟ በእንስራ ውኃ ነው፣ አንቺን የደም ገንቦ ያሸከመሽ ማነው?›› እያለ ወያላችን አጠገቤ የተቀመጠችውን አንገተ ብርሌ ያደንቃል። ቆንጅት አልዋጥላት ብሎ፣ ‹‹ትንሽ ቆይተህ ጠጋ በይ ለማለት ነው?›› ነቅቼብሃለሁ…›› ትለዋለች። ወያላው በስጨት ብሎ፣ ‹‹ምን ስለሆንሽ ነው የማትጠጊው? ዘለዓለም ከአንቺ ጋር ጭቅጭቅ? ሁሌም ለምን የእኔን ታክሲ መርጠሽ ትሳፈሪያለሽ?›› ብሎ ጮኸባት። የወያላውና የለግላጋዋ ትውውቅ የዛሬ ብቻ አይመስልም። ‹‹አልጠጋም፣ አልጠጋም። ትርፍ መጫን ሕገወጥነት ነው፣ ጨርሻለሁ…›› ብላ በስምንት ነጥብ ዘጋችው። ‹‹አንተ በቃ ተዋት፣ የራስህ ጥፋት ነው። ገና በሩቁ ስታያት አልጭንሽም አትላትም?›› ብሎ ሾፌሩ ሲናገረው ጋቢና ወደ ተሰየሙት ሹክክ ብሎ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ሰው ቆሞ በፀሐይ ሲቀቀል እያየች ምንም አይመስላትም ስላችሁ። እሷም እንዲችው ስትቀቀል ትውላታለች እንጂ ትርፍ ልጫንሽ ብትላት እሺ አትልም። እመኑኝ ሞክሬያታለሁ። አካብዴ ናት…›› ይላል። አታካብዱ አይደል የዘመኑ ወሬ!
ይኼኔ ሰምታው ኖሮ፣ ‹‹አዎ አካብዳለሁ፣ ከተፈቀደው በላይ መጫን የትራፊክ ሕግ አይፈቅድላችሁም። ለምን ትርፍ ትጭናላችሁ?›› ብላ ቱግ አለች። ‹‹ተረፋችኋ፣ እናንተ ስትተርፉ እኛ ምን እናድርግ?›› አለ ወያላው ጣልቃ ገባ። ‹‹አንተን አላናገርኩህም?›› ብላ ስትመናጨቅ ወያላው፣ ‹‹አሃ እኔም ትርፍ ሆንኩብሽ?›› ብሎ አፍ ዕላፊ መናገር ሲጀምር ከፊታችን ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ በቃ ይብቃችሁ፣ አንቺም አንዴ አቋምሽ ታውቋል ዝም በይ። አንተም ገና ለገና በአገሩ አንድ ሰው ዘራፍ አለብኝ ብለህ አትወብራብን። መብቷ ነው። መደራረብ እኮ ለእኛም ቢሆን የውዴታ ግዴታ ሆኖብን እንጂ ፍላጎታችንም፣ ግዴታችንም አይደለም…›› ብለው ውኃ ሲቸልሱበት ነገሩ በረደ። መትረፋችን ሳያንስ ትርፍ የምንነጋገረው ነገር እኮ ባሰ እናንተ!
እናም ጉዟችን አንደኛውን ሩብ እያገባደደ ነው። ‹‹ያዝላቸው!›› ወያላው የታክሲያችንን ገላ በመዳፉ ይጠፈጥፋል። መጨረሻ ወንበር የተሰየመች ባለንቅሳት ታዳምቃለች። ‹‹ወይ ጉድ ይኼ ሁሉ ሰው ምንድነው?›› ትገረማለች። ‹‹ጥበቃ ነዋ፣ አንቺም አሁን እንዲህ ተዝናንተሽ መቀመጥሽን አትመልከቺ። ሁላችንም ጥበቃ ላይ ነን…›› ይላታል አጠገቧ የተሰየመ ወጣት። ሦስት የፊት ጥርሱ እንደ ቀይ አገዳ መሀል መሀል ወገቡ ላይ ተከትክቶ ተሸርፏል። ‹‹የምን ጥበቃ?›› እያለች ታደርቀዋለች። ‹‹የምቾት ነዋ፣ ሌላ ምን ትጠብቂያለሽ ደግሞ ከዚህ ዓለም? ዓለም አንድ ያላት ነገር ተድላና ምቾት ነው። የነፍሱን ነገር ካላሰብሽ ደግሞ ምቾት እዚህ አፍንጫሽ ሥር ነው፣ እመኝኝ…›› ብሎ ተመቻችቶ ተቀመጠና ልብ ብሎ ዓያት። ለከተማው እንግዳ፣ ለሠፈሩ ባዳ፣ ለመንገዱ አዲስ መሆኗን ሲገባው አፉን አሹሎ ጨዋታውን ቀጠለ። ‹‹እስኪ አስቢው አሁን ጠዋት ከእንቅልፍሽ ብድግ ስትይ በቀኝሽ በሙቅ ውኃ የተነከረ ፎጣ ይዞ አንድ አገልጋይሽ ʻእንደምን አደሩ እሜቴʼ ብሎ ፊት ማበሻ ያቀብልሻል። በግራ በኩል ቀኝ እጄ የምትያት ደንገጡር በባዶ ሆድ ሁለት ብርጭቆ የማር ውኃ አዘጋጅታ በፍቅር ታጠጣሻለች። ከዚያማ ተይው። ከአልጋሽ ሳትወርጂ ጁሱ፣ ወተቱ፣ ዕንቁላሉ፣ ዓሳው፣ ፍራፍሬው… ይመጣልሻል። ይኼ ሁሉ ቁርስ ነው እሺ…›› እያለ እያለ ይቀጥላል። ተጀመረ ማለት ነው!
‹‹ይኼ የት ነው? ከአፍሪካ መሰስ ብለሽ ስትወጪ…›› ብሎ ሳይጨርስ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ኢርፎን ጆሮው ላይ ሰክቶ ድምፁን አጥፍቶ የቆየ ጎልማሳ፣ ‹‹ዓይናችን እያየ ጆሯችን እየሰማ አጠገባችን ሕገወጥ ደላላ…›› ብሎ ጮኸ። አማሎ አማሎ ያናወዛት ምስኪንም ከፍዘቷ ነቅታ፣ ‹‹ዞር በልልኝ አንተ…›› ብላ ፊቷን አዞረችበት። የዘንድሮን ጮሌ ፊት በማዞር ብቻ ዝም ካስባልነውም አንድ ነገር ነው። ታክሲያችን ጉዟዋን ቀጥላለች። ማንም እንዳይደረብብኝ ካለችው ሞጋች በስተቀር ሁሉም ወንበር ላይ ትርፍ ሰው ተገጥግጧል። ወያላው በዚህ መሀል እያንዳንዱን ሒሳብ ካላመጣችሁ ብሎ ይተናነቀናል። ‹‹ኧረ እባክህ ፋታ ስጠን? ገና ለገና ወደ አራት ኪሎ ጫንኳቸው ብለህ ነገር ታሸክመናለህ?›› ይለዋል አንዱ። ወያላው ነገር በዝቶበት ነው መሰል ዝም አለ። ይኼኔ ከጎልማሳው አጠገብ የተሰየመች ወይዘሮ፣ ‹‹የራሱን ነገር ያልተሸከመ ሰው ማን አለ? ይኼ እኮ በመፈጠር ዕጣ የሚታደልህ እንጂ ታክሲ ስትሳፈርና ስትወርድ የሚጫንብህ አይደለም…›› አለችው። እንዲያ ስትለው አራት ኪሎን በነገር አዋዝቶ ያነሳው ተሳፋሪ ዝም ብሎ አያት። ዝም አለኝ ብላ ቀጠለች። ‹‹ይህቺ ዓለም እኮ ሰጥቶ በመቀበል ሒሳብ ብቻ ሳይሆን የምታምነው ሒሳብ በማወራረድም ነው። እያንዳንዳችን ሒሳብ ሳናወራርድ ከዚህች ሕይወት ውልፍት ማለት የለ…›› ትላለች። ምን ጉድ ነው!
‹‹አሃ እንዳንቺ አባባል ሕይወት በትርፍ ሰዓቷ ነጋዴ ናት ማለት ነዋ…›› ጎልማሳው ፈገግ ብሎ እያያት ጠየቀ። ‹‹ድብን አድርጋ፣ ያልተወራረደና ያልተመረመረ ሕይወት ደግሞስ ሕይወት ነው እንዴ?›› ስትለው፣ ‹‹መወራረዱን ግድ የለም ይሁን። ወደድንም ጠላንም ራሷ ሕይወት ማወራረዷ አይቀርም። መመርመሩን ግን እንጃ። እንኳን ሕይወትን ገና መቼ የምንናገረውን መመርመር አልጀመርንም እኮ። ዘረኝነት፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ በቀል የሚያጭሩና የሚያበረታቱ ያልታረሙ ንግግሮችን፣ ያልተገሩ አስተሳሰቦችን እያራመድን መስሎኝ ደህና ተስፋ የሰጠን እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲህ ውርጭ የወረሰው…›› ሲላት ፖለቲካ ሊያናግራት መስሏት ወይዘሮይቱ በጥርጣሬ ዓይን አየችው። ‹‹ይኼው አንቺ አሁን ደህና የነበርሽው ሴትዮ ተመልከች በአንዴ ወደ በረዶነት ስትቀየሪ…›› ሲላት ነገሩ ባያስቃትም ለይስሙላ ፈገገችለት። ጥርስ ላይ የታወጀ ቀን ብቻ በምን እንደምንሸነጋገል ተያይተን!
አጠገቤ የተቀመጠችዋ አንገተ ብርሌ ቤልኤር አካባቢ ስንደርስ ወረደች። ወያላው፣ ‹‹ሁለተኛ እንዳላይሽ…›› እያለ ይዝታል። ‹‹እንዴ ምን ሊላት ነው ይኼ ወያላ? በገዛ አገሯ? በገዛ መሬቷ?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ እባክሽ ሴትዮ ዝም በይ። ዝም ብለሽ ስለመብቷ ብቻ አትይም። አገር መሬት ቅብጥርስ ምን ያስብልሻል? ልታስወነጭፊብን ነው እንዴ?›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ወጣት ደነፋ። ‹‹በገዛ አፌ ምን አገባህ?›› ብላ ዞራ ልትገጥም ስትል አዛውንቱ፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እናንተ ሰዎች። እርቧችሁ ነው? ሆዳችሁ ባዶ ነው? ከሆነ ንገሩንና ምግብ እንዘዝላችሁ። በተረፈ ሆዳችሁ ካልጎደለ ምንድነው በትንሽ ትልቁ ሽቅብ ሽቅብ የሚላችሁ? እኛም እኮ ያለ መለከፍ መብት አለን…›› ብለው ሲቆጡ ጫጫታው ረጭ አለ። ይሻላል!
አራት ኪሎ ተቃርበናል። መሰላቸታችንና መተፋፈጋችን ጣራ ነክቷል። ይኼን ጊዜ አንድ እንግዳ ድምፅ ከመሀላችን ወጣ። ጎማ ላይ በትርፍነት የተቀመጠ ተሳፋሪ ነው። ገጽታው ክፋት በሞላባቸው የማጣት ኃያላን መናፍስት የተገረፈ ይመስላል። ‹‹እባካችሁ እባካችሁ እርዱኝ?›› አለ ጮክ ብሎ። ‘እግሩ ተቀርቅሮበት ነው?’ ይላል ወያላው። ‘ሞባይሉን ጥሎ ይሆናል’ ወይዘሮዋ ናት። ‘ተሳስቶ ተሳፍሮ ይሆናል’ ከጎኔ ያለው። ልመና ነው ብሎ የገመተ የለም። ‹‹እባክህ ተናገር እንጂ። አንተም እንደ እነ እንትና ያደርግሃል እንዴ? ምን ትንተባተባለህ?›› ወያላው ምሕረት በሌላቸው ደቋሽ ቃላት ሲያዋክበው ሾፌሩ ይቆጣዋል። ‹‹ወንድሜ ታሞብኝ እዚህ ድረስ ላሳክመው አምጥቼው ይኼው ካንሰር ነው ብለውኝ ሳይድን ይዤው ልመለስ ነው። እኔ ገንዘብ አይደለም የምለምናችሁ። እባካችሁ ተለመኑኝ…›› እያለ ዙሩን አከረረው። ‹‹እና ገንዘብ ካልፈለግክ ምን እንርዳህ?›› ወይዘሮዋ ጠየቀች። ‹‹እንዲያው በዓይኔ ዓይቻለሁ፣ ሲሠራ ዓይቻለሁ፣ አምነዋለሁ የምትሉት ፀበል ጠቁሙኝ። እኔ ያልሞከርኩት የለም። ግን ቢጨንቀኝ ነው…›› ሲል የመሀል አዲስ አበባ ልጆች በሳቅ አሽካኩ። ጎልማሳውና ወይዘሮዋ አሽሟጠጡ። አዛውንቱ በአንክሮ ዘወር ብለው አይተውት፣ ‹‹ስማኝ ልጄ እሱ ራሱ ካላመነ በሰው እምነት ማንም አይድንም። የእያንዳንዳችን እምነት የተለያየ ነው። ጨንቆህ ነው አውቃለሁ። ግን ደግሞ ሳታስበው ሌላ ችግር ላይ እንዳትወድቅ። ፈጣሪ ያለውን በፀጋ ተቀበል። ካለለት በራሱ እምነት ይዳን…›› ብለው ሲያበቁ ሁላችንን ተራ በተራ እያዩ፣ ‹‹ዘንድሮ ያስቸገረን ምን ሆነና? ያለ እምነታችን ምኑንም ሳናውቀው በሌላው እምነት፣ በሌላው ዕቅድ፣ በሌላው ሴራና ደባ እየተመራን እኮ ነው የዚህችን ምስኪን አገር ጥርስ የምናነቃንቀው?›› ሲሉ ወያላው ʻመጨረሻʼ ብሎ በሩን ከፈተው። እንዲህ ሒሳባችን እየተወራረደ ይነገረን እንጂ! መልካም ጉዞ!