Tuesday, February 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው መሰሪነት ሲወገድ ነው!

‹‹ፍቅራችሁም ሆነ ጠባችሁ በልክ ይሁን›› የሚለውን ዕድሜ ጠገብ አባባል ባለመገንዘብ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ጥፋቶች ከደረሱ በኋላ የሚስተዋሉ ፀፀቶችና ምን ነክቶን ነበር የሚሉ መብሰልሰሎች፣ ትውልዶች በተፈራረቁ ቁጥር የሚያጋጥሙ የዘመናት ችግሮቻችን መሆናቸው ያስቆጫል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ብሔርም ሆነ እምነት ውስጥ ሆነው ካካበቷቸው አኩሪ ባህሎችና እሴቶቻቸው መካከል፣ ማንኛውም ችግር ሲያጋጥም የሚፈቱበት የዕርቅ ወይም የሽምግልና ሥርዓት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በዕለታዊ አለመግባባት ከተጣሉና ከተኳረፉ ጀምሮ እስከ ደም አፋሳሽ ግጭትና ሕይወት ሕልፈት ድረስ፣ በአራቱም ማዕዘናት በእዚህ አኩሪና ምሥጉን ሥርዓት መፍትሔ ማበጀት የየዘመኑ ኢትዮጵያውያን ተግባር ነበር፣ ዛሬም አለ፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የጋሞ የአገር ሽማግሌ አባቶችን አርዓያነት ያለው ተግባር ደጋግሞ ማውሳት የግድም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ታላቅነት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ገላጋዮች አማካይነት የሁለቱ ዓመት አውዳሚ ጦርነት እንዲያበቃ ተስፋ ሲሰነቅ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕፎይ ብሎ ሰላምን እንዲያጣጥም ሲባል ይሁን ብሎ መቀበል የግድ ነው፡፡ ይልቁንም የሰላም ተስፋው በመሰሪዎች ሴራ እንዳይከሽፍ ነው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡

መሰንበቻውን እንደ ዶፍ ዝናብ በተከታታይ ሲለቀቁ የነበሩ ሰላም የሚነሱ የክፋት አጀንዳዎች ጋብ ብለው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሚመራ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ልዑክ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ አቅንቷል፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ያስከተለ ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ፋታ አግኝቶ፣ በስምምነቱ መሠረት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቆይተው እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ ይበል ማለት ተገቢ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በአፍሪካ ኅብረት ባለቤትነት በሌሎች የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ለማስቆም የተሄደበት ርቀት ከባድ ቢሆንም፣ አሁን ነገሮች መልክ እየያዙ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ልዑክ መቀሌ መሄዱ ሲሰማ ዘላቂ ሰላም ለማግኘት ተስፋ ይሰነቃል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ግን፣ በሌሎች ሥፍራዎች የሚሰሙ የተቃውሞ ድምፆችም ሲደመጡ ጭምር ነው፡፡ ያጋጠሙ ችግሮችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን የሚጠቅመው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠመው የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት እንዳይከሰት ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ይረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መጎናፀፍ የሚያስችሏት በርካታ አማራጮች አሏት፡፡ ከእነዚህም መካከል የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስተካከል፣ ለአድልኦ በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር፣ የምክክር መድረኮችን በማስፋት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የግብይት ሥርዓቱን ፈር በማስያዝ የኑሮ ውድነቱን ማቅለልና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ እያስተናገዱ በጋራ ችግሮች ላይ መነጋገር እየተቻለ፣ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ቂምና በቀል የሚያስከትል አውዳሚ ጦርነት ውስጥ መግባት አሳዛኝ ነው፡፡ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ፈፅሞ ሊከሰት የማይገባው አውዳሚ ጦርነት በሕዝብ ላይ ያደረሰው ዕልቂትና በንብረት ላይ ያደረሰው ውድመት መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ ከዚያ አሳዛኝ ክስተት በኋላ አንፃራዊ ሰላም ተፈጥሮ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ልዑክ ትግራይ ሄዶ ግንኙነት ሲፈጠር፣ ያለፉት ሁለት ዓመታት ዓይነት መከራና ሰቆቃ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች እንዳይደገም ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ አሁን የተገኘው ፋታ የበለጠ ተጠናክሮ ዘለቄታዊ ሰላም መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቧ ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ሞት፣ መፈናቀል፣ ውድመትና ሌሎች ሥቃይ አባባሽ ችግሮች ከመጠን በላይ ታይተዋል፡፡ ሰላም ሲጠፋና ጦርነት ውስጥ ሲገባ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚሸከመው በላይ የዕዳ ጫና ይፈጠርበታል፡፡ ከቀላል እስከ ከባድ መሣሪያዎችና ተተኳሾች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ነዳጅና ቅባት፣ የምግብ አቅርቦት፣ አልባሳትና ሌሎች ወጪዎች ኢኮኖሚውን ያንገዳግዱታል፡፡ በዚህ ላይ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የሚከሰቱ ዕልቂቶችና የመሠረተ ልማት ውድመቶች ሲታከሉበት ለአገር ከባድ ኪሳራ ነው፡፡ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ማቃለል የሚገባው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት ሲውል፣ ምንም ጥቅም እንደማይሰጥ የወረቀት ተረፈ ምርት እሳት ውስጥ እንደገባ ነው የሚቆጠረው፡፡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቧ ልማትና ዕድገት መዋል ያለበት ሀብት ከእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ውድመት ሊገታ የሚችለው፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ ወገኖች የተጀመረው የሰላም ሒደት ግቡን እንዲመታ ዕገዛ ሲያደርጉ ነው፡፡  ከዚያ ውጪ ያለው ትርክት ለማንም አይረባም፡፡

በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተጀመረው የሰላም ሒደቱን አስተማማኝ የማድረግ ጥረት፣ በሌሎች ወገኖችም ድጋፍ ተችሮት ኢትዮጵያ ከገባችበት ማጥ ውስጥ ትውጣ፡፡ በዚህ ጥረት ትግራይም፣ አማራም፣ አፋርም ሆኑ ሌሎች የተቀሩት ክልሎች ሰላም አግኝተው ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ በመሆን የጥፋት ምዕራፍ ይዘጋ፡፡ ማዶ ለማዶ ሆኖ ከመወጋገዝና በቂም በቀል ለመተላለቅ ቀጠሮ ከመያዝ ይልቅ፣ በሠለጠነ መንገድ ተነጋግሮ የጋራ አማካይ መፍጠር ይበጃል፡፡ በአጉል ትዕቢትና ጀብደኝነት በመወጣጠር ትከሻ መለካካት ያተረፈው ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ በደረሰው ዕልቂትና ውድመት በመፀፀት ካለፈው አደገኛ ስህተት መማር ይገባል፡፡ የሐሳብ ልዩነት ለክርክር ማዘጋጀት ሲገባው ጦር መማዘዝ የለየለት ዕብደት መሆኑን፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት አውዳሚ ጦርነት መማር ተገቢ ነው፡፡ አጉል ትዕቢትና ጀብደኝነት የሚኮራበት ሳይሆን የድንቁርናን ጥግ ማሳያ ነው፡፡ ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሦስቱ ክልሎችም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የመከራ ገፈት ቀማሽ ምስኪን ኢትዮጵያውያን፣ ጦርነቱም ሆነ ግጭቱ ያተረፈላቸው ዕልቂትና መፈናቀል ነው እያሉ ነው፡፡ በእነዚህ ወገኖች ደም መነገድ ይቁም፡፡

ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ነገር ስለሌለ የፖለቲካ ችግርን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይለመድ፡፡ እልህ፣ ግትርነት፣ አጉል ጀብደኝነትና ማናለብኝነት ይወገዱ፡፡ በሕዝብ ስም እየተነገደ እነዚህን ኋላቀር ባህርያት አገር ማፍረሻ ማድረግ ይብቃ፡፡ ማንም ፖለቲከኛም ሆነ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ኃይል፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን የፖለቲካ ቁመና ይኑረው፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ለሐሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ቦታ ስለሌለው፣ በዘመነ መሣፍንት አስተሳሰብ ላይ የተቸነከራችሁ በሙሉ አስቡበት፡፡ ሰላም በኢትዮጵያ ምድር መስፈን ስላለበት የግልና የወል የጥፋት ፍላጎታችሁን ግቱት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም በማጣቱ ብቻ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ተቀምጦ እየተራበ ነው፡፡ ሰላም አግኝቶ በምግብና በሌሎች ምርቶች መትረፍረፍ ሲገባው፣ ለምፅዋት ጠባቂነት የተዳረገው በእናንተ ዕርባና ቢስ የፖለቲካ መገፋፋት ምክንያት ነው፡፡ አሁን ጊዜው የዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሆን ይኖርበታል፡፡  ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው ደግሞ መሰሪነት ሲወገድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት ዕግድ ተጠየቀ

የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተካተዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...