Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዲላ ማረሚያ ቤት የታይፎይድና የታይፈስ በሽታ መከሰቱ ተነገረ

በዲላ ማረሚያ ቤት የታይፎይድና የታይፈስ በሽታ መከሰቱ ተነገረ

ቀን:

  • እኛ ጋ የነበረው ጉንፋን ነበር አሁን ሰላም ነው እግዚአብሔር ይመስገን

ትዕግሥት ሮቤ የዲላ ማረሚያ ቤት ኃላፊ

በኢዮብ ትኩዬ

በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ የታይፎይድና የታይፈስ በሽታ እንደገጠማቸው የጤና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

ከሁለት ሳምንታት ወዲህ በማረሚያ ቤቱ የጤና ዕክል እንደተከሰተ፣ አሁንም ሙሉ ለሙሉ በሕክምና መከላከል እንዳልተቻለ በማረሚያ ቤቱ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት ባለሙያዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ‹‹ከ1,200 በላይ ታራሚዎች አሉ›› ያሉት የጤና ባለሙያዎች፣ ካለፈው ሳምንት ወዲህ አንዱ ሲያስለው ወደ ሌላኛው እየተዛመተ ታራሚዎች ሲታመሙ፣ ከዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት ጋር ለመናበብ ምርመራ እንዳደረጉ አስረድተዋል፡፡

በምርመራ ውጤትም የተከሰተው በሽታ ታይፈስና ታይፎይድ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ በማረሚያ ቤቱ ያሉ ታራሚዎች በመጨናነቃቸው በሽታው በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላኛው የመዛመት አጋጣሚው ሰፊ ነበር፡፡

ተከሰተ በተባለው የታይፎይድና የታይፈስ በሽታ በየቀኑ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ሰዎች የሚታከሙበት አጋጣሚ እንደነበረም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ በሽታው አሁን ያለበት ደረጃ ምን ላይ እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ከዚህ ቀደሙ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ እንደሆነና በሕክምና መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እንዳልተቻለ ሲገልጹ፣ ‹‹ሙሉ ለሙሉማ እንዴት ይጠፋል? ብዙ ታራሚዎች ስላሉ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ማለት አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም አሁንም ቢሆን ምርመራ ሲደረግ ታይፎይድና ታይፈስ የሚገኝባቸው ታራሚዎች ስለመኖራቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዲላ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ትዕግሥት ሮቤ፣ የማረሚያ ቤቱ የጤና ዕክል መከሰቱን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹እኛ ጋ እግዚአብሔር ይመስገን ሰላም ነው፡፡ ጉንፋን ነው የነበረው፡፡ አሁን ነው ከግቢው የወጣሁት፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት በማረሚያ ቤቱ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት የጤና ባለሙያ፣ ታራሚዎቹ የጤና ዕክል እንደገጠማቸው ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ታይፎይድና ታይፈስ በሽታ እንደተከሰተ በሕክምና አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት ባለሙያዎች መጀመርያ በሽታው ሲከሰት እንደ ወረርሽኝ እንደነበር፣ ምናልባት ኮሮና ይሆናል የሚል ሥጋት እንደነበርና በምርመራው ግን ታይፎይድና ታይፈስ እንደሆነ ተደርሶበት ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ለመቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

የታራሚዎች ቤተሰቦች በበኩላቸው በማረሚያ ቤቱ ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ እንደተከሰተና ከአንዱ ወደ ሌላኛው ሰው እየተዛመተ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የታራሚዎች ቤተሰቦች እንደገለጹት ከሆነ፣ በሽታው በተከሰተበት ወቅት በፍጥነት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡ በእስር ቤቱ ያለው የአኗኗር ሁኔታ ምቹ እንዳልሆነና ከ1,200 በላይ ታራሚዎች ተጣበው በመቀመጣቸው፣ በሽታው በቀላሉ ሊስፋፋ ስለመቻሉም ተብራርቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የተደረገ ነገር እንደሌለ ሲጠቅሱ የነበሩት የታራሚዎች ቤተሰቦች፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሻለ ሁኔታ እንዳለና ሕክምና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ተከሰተ በተባለው በሽታ የከፋ ሕመም ቢከሰትም ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ግን የሞተ ሰው እንደሌለ ማወቅ ተችሏል፡፡  

በሽታ ተከሰተበት የተባለው ማረሚያ ቤት በደቡብ በጌዲኦ ዞን በምትገኘውና ከተመሠረተች መቶ ዓመት እንዳስቆጠረች በሚነገርላት በዲላ ከተማ ይገኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...