በጦርነት ቀጣና ውስጥ የቆዩት አምራች ኢንተርፕራይዞች በከፊል አገግመው ሥራ ቢጀምሩም፣ የገበያ ዕጦት እየፈተናቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል በደሴ፣ በኮምቦልቻና በወልድያ ከተሞች በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ምልከታ ማድረጉን ያስታወቀው ተቋሙ፣ በምልከታው ኢንተርፕራይዞች በጦርነቱ ወቅት በጥሬ ዕቃ፣ በምርት ዘረፋ፣ በመሥሪያ ማሽኖችና በመሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ከገለጻቸው መረዳቱን አስታውቋል፡፡
ምልከታ የተደረገባቸው አምራቾች በጦርነቱ ወቅት ከደረሳባቸው የጥሬ ዕቃ፣ የማሽን፣ እንዲሁም የምርት ዝርፊያ በተጨማሪ፣ እንደገና ወደ ምርት በገቡበት ወቅት የገበያ ችግር ፈተና እንደሆነባቸው ተገልጿል፡፡
በጦርነቱ ውስጥ የቆየው ኅብረተሰብ በማገገም ሒደት ውስጥ ያለው ፍላጎት ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ሌሎች ከኢንተርፕራይዞች ተመርተው የሚወጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ገዝቶ የመጠቀም ፍላጎቱ አናሳ ስለሆነ፣ ገበያ ማግኘት ላይ ክፍተት መፍጠሩን፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
አምራች ኢንተርፕራይዝ የሚባለው ዘርፍ በተለይም የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የጌጣጌጥና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ እንዲሁም የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤቶችን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ ሥራዎች ላይ የተሰማሩትን ያካትታል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ አምራች ኢንተርፕራይዞች ብቻ ሳይሆኑ ድጋፍ ሰጪ የሚባለው የመንግሥት መዋቅር በራሱ ድጋፍ የሚፈልግ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በማገገም ላይ ያሉት ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅና መሸጥ እንዲችሉ እየደገፈ ነው ተብሏል፡፡
በጥር 2015 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት እንዲሳተፉ ከሚደረጉ አካላት ውስጥ፣ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሾች መሆናቸውን አቶ አሸናፊ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎች፣ እንዲሁም የካፒታል ፋይናንስ ድጋፍ የሚባለውንና ማሽኖችን በብድር እንዲያገኙ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገልጿል፡፡
አቶ አሸናፊ እንዳስታወቁት፣ በአማራ ክልል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ከ500 በላይ ዘርፉን የሚመሩ ኢንተርፕራይዞችንና አስፈጻሚዎችን የሥነ ልቦና ማገገሚያ ሥልጠና ከዚህ ቀደም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሥልጠናውንም መሠረት በማድረግ ብዙዎቹ ወደ ምርታማናት እንደተመለሱ፣ ከዚህ ባሻገር ለቢሮ መገልገያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን መደረጋቸውን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ከጦርነቱ አስቀድሞ በኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴ ተጠቃሽ የነበረ መሆኑን ያወሱት አቶ አሸናፊ፣ ጦርነቱ በክልሉ በተለይም በኢንተርፕራይዝ ዘርፉ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ያለውን እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስና የሰላሙ ሁኔታ በሚፈቅደው ልክ ለመደገፍ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አክለዋል፡፡