ሰላም! ሰላም! እንደ ዋዛ የጀመርነው የዓለም ዋንጫ በአስገራሚ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ያቺ የሸሚዝ ቁልፍ የምታህል ኳታር የምትባል አገር የዓለምን ቀልብ ለአንድ ወር መቆጣጠር መቻሏ በእጅጉ ቢያስገርመኝም፣ እኛ ስንትና ስንት ታሪክ ያለን ኢትዮጵያውያን እያደር ቁልቁል መንሸራተታችን ያበሳጨኛል…›› ነበር ያለኝ፡፡ ይህንን ቁጭት የሰማ አንዱ ወዳጃችን ደግሞ፣ ‹‹በቃ አሁን ነው ልክ እንደ ታላቁ ዓድዋ ድል ዓለምን ማስደመም የሚችል ሥራ ለማከናወን መነሳት ያለብን…›› ሲለን ንግግሩ ስላቅ ቢመስለኝም ነገሩ ግን እውነት ነው የሚያሰኝ ነበር። ‹‹ዓለም ለአንድ ወር ያህል አንድ መንደር ልትሆን የቻለችው በሥራ እንጂ በወሬ እንዳልሆነ ከናይጄሪያ በጣም ያነሰ የነዳጅ ሀብት ያላት፣ ነገር ግን ያላትን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር የቻለችው ኳታር አሳይታናለች። ከዚህ መማር ያለብን እኛ እንጂ ማንም ሊሆን አይገባም፡፡ ለዚህ ደግሞ መነጋገር፣ መከራከር፣ አንዱን ሐሳብ ከሌላው ጋር ማፋጨት ይገባል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦችና ዕውቀቶች የታጨቁባቸውን መጻሕፍት ማንበብ፣ መመርመር፣ ማሰላሰልና የመሳሰሉትን ስናከናውን የጎደለን ምን እንደሆነ ይታወቃል…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ግን ገና ይቀራል!
እኛማ ስንትና ስንት አስደናቂ ታሪኮችንና ክንውኖችን ለዓለም አስተዋውቀን መልሰን የዓለም ጭራ መሆን ሳይቆጨን፣ በቋንቋና መሰል የማያጣሉ ነገሮች እንደ ዝንጀሮ እርስ በርስ እንናጀሳለን፡፡ ሌላውን ተውትና አንድ ሥራ ለመሥራት ዘንድሮ ያለ ዕውቅና የሚሆን ነገር የለም። ‹የምታውቀው ሰው የለም? የሚያውቅህ ባለሥልጣን አታውቅም?› መባባል ከሆነ ቆይቷላ ጨዋታው። ይኼው በየዕለቱ በየጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮቻችን ሳይቀር የምንታዘበው ነገር ነው። ‹‹ዕውቅና ከሌለህ ብትኖርም የለህም› እየተባባልን አይደል እንዴ በብሔር ዝምድና አገር የምናምሰው? ‹‹መሬት ለሚባለው ፈጣሪ ለሰጠን ፀጋ የብሔር ሰሌዳ ለጥፈንለት እርስ በርስ ስንገፋፋ፣ እዚህ ቅርባችን ያሉ አገሮች እየታዘቡን መሆናቸውን እንኳ ልብ አለማለታችን ያሳዝናል። የፈጣሪን ፀጋ በአግባቡ መጠቀም አቅቶን በየዓረብ አገሩ ልጆቻችን እንደ ቆሻሻ ሲጣሉና መድረሻ ቢስ ሆነው ሲባዝኑ ካልተቆጨን ማን ይቆጭልን…›› የሚሉት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ታሪካችንን አክብረን በኩራት ሥራችንን ማከናወን ብንችል ኖሮ፣ ዝናችን ከዳር እስከ ዳር ይናኝ ነበር እንጂ፣ በድህነትና በግጭት የላቆጡ ተብለን መሳቂያ መሳለቂያ አንሆንም ነበር፡፡ ወይ ነዶ!
‹‹እዚህ አገር በኳስና በኑሮ ምን ያልሆነው አለ?›› ያለኝ ድሮ በሠፈሩ በኳስ ተጫዋችነቱ የሚታወቅ ደላላ ወዳጄ ነው። ‹‹አንበርብር በኳስ ምክንያት ያልሆንኩትን አትጠይቀኝ። በአጠቃላይ ድቡልቡል ነገር እስኪያስጠላኝ ድረስ ነበር ተስፋ ቆርጬ የተውኩት…›› ብሎኝ ተክዞ ማዶ ማዶ ያይ ጀመር። እኔም ትካዜውን ለመስበርና ወጉን ለማስቀጠል፣ ‹‹ምን ነበር ምክንያቱ?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ከሙስና ሌላ ምን ምክንያት አለው የእኛ አገር ነገር? ስንቱ ኢትዮጵያዊ ማራዶናና ስንቱ ሮናልዲንሆ እኮ ነው በአጭር የተቀጨው? የዚያ ትውልድ ጡር አልፎ ለዚህ በቃን…›› አለኝ። ከወዳጄ ጋር ስጫወት ከፍ እንዳንል ሲያወርደን የኖረውን በየመስኩ ዕድገታችንን ጨምድዶ ይዞት የኖረውን ሙስናን ለመርገም ቃላት ያጥረኝ ነበር። ምናልባት ሙስና በእርግማን መቆም ከቻለ ብዬ ነዋ፡፡ ሙስናም በሉት ሌብነት በምኞት እንደማይጠፋ እንኳን ለአቅመ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ያልደረስኩት ደላላውን አንበርብር ምንተስኖት፣ ትናንት የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ጭምር በሚገባ ያውቁታል፡፡ ችግሩ ግን ‹‹የዓሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ›› የሚባለውን ዕድሜ ጠገብ ብሂል አለመገንዘባችን ወይም አለመፈለጋችን ነው፡፡ ‹‹አላማጣ ውዬ መልሼ አላማጣ፣ በበሽታዬ ላይ በሽታ ላመጣ…›› የተባለው መቼ ነበር… እንጃ!
እንግዲህ እንዲህ ባለ ውሉ በጠፋበት ዘመን የምትሰሙት ስላቅና ተረብ ተቆጥሮ አያልቅም። እና ምን ተባለ መሰላችሁ? አንዱ ሲሮጥ መጥቶ፣ ‹‹ወንዳታ! ጤፍ ሠራ!›› ብሎ ጮኸብኝ። መጀመርያ ግር ብሎኝ ቆይቼ፣ ‹‹ምን አልክ?›› አልኩት። ‹‹ጤፍ ዘንድሮ ሠራ ነው የምልህ!›› አለኝ ደገመና። ጤፍ በውጭ አገር ተወዳጅ ምግብ መሆኑ በውጭ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲነገር መሰንበቱ ሲታወሰኝ እስኪወጣልኝ በሳቅ ፈርሼ ነበር። እየቆየሁ ግን ሥጋት ይሰማኝ ጀመር። ‹‹የምን ሥጋት?›› አለችኝ ማንጠግቦሽ የተባለውን ስነግራት እሷም አብራኝ ስትስቅ ቆይታ። ‹‹ምን ታውቂያለሽ በዚህ ዓይነት ጤፍ መደነቅና መሞጋገስ ከጀመረ አበቃ፡፡ ነገ ‘ለጤፍ ሃያ ሺሕ አነሰው?’ ይባልልሽና ትገላገያለሽ…›› ስላት የታኅሳስ ቅዝቃዜ አልበቃ ብሎ ቀዝቃዛ ውኃ የደፋሁባት ይመስል ኩስስ ብላ አነሰች። እንዲህ አይደል የእኛ ኑሮ? ድል በዋናው በር ሲገባ በጓሮ በር አያ ጣጣ ይገባል። ማንጠግቦሽ በስጨት ብላ፣ ‹‹እንዲያው እኛ ግን ከሆዳችን ጋር የማይያያዝ ሌላ ጉዳይ የለንም ግን?›› በማለት ጠየቀችኝ። ‹‹በቀን ሦስቴ አሁንም የልማታችን ግብ መሆኑን እያወቅሽ እንዴት እንዲህ ትጠይቂኛለሽ?›› ስላት ንግግር አስጠልቷት ወደ ጓዳዋ ገባች። እኔም አንዳንድ ሥራ ነበረኝና እሱን ልፈጻጽም ከቤት ወጣሁ። ምንም እንኳ መንግሥታችን ሳይቀር በሚታወቅበት የአፈጻጸም ችግር አገሩ በሙሉ ቢታማም፡፡ ደግሞ ለመታማት!
ሳይውል ሳያድር ቅድም እንዳልኳችሁ ያው የተለመደው የጭንገፋ ዜና ጆሯችን ደረሰ። ‹‹መክሸፍ›› ሳይሆን ‹‹መጨንገፍ›› ነው ያልኩት፡፡ በቀደም አንዱ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ለበጋ ስንዴ የሚዘጋጁ ሰፋፊ ሁዳዶችን ዓይቶ መምጣቱን ነገረኝ፡፡ ‹‹ልማቱ መልካም ነበር፣ ነገር ግን የፀጥታው ሁኔታ ግን መላ ካልተበጀለት ምን ዋጋ አለው…›› ብሎም ተቆጨ፡፡ ይህንን ወሬ ሲሰማ የነበረ አንዱ ደላላ ወዳጄ፣ ‹‹ወንድሜ ያልከው ልክ ቢሆንም፣ መላ ካልተበጀለት ያልከው ስህተት አለበት፡፡ የፀጥታው ችግር ያለው እኮ በሌላ ሳይሆን መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሰርገው በገቡ ሰዎች ነው፡፡ እነሱን እያወቀ እሹሩሩ የሚለው መንግሥት አንድ ዕርምጃ ካልወሰደ ነገ ለእሱም አይመለሱለትም…›› ሲል፣ ወትሮም የዘራነውን ለንፋስ መስጠት ነውና ልምዳችን ብዙም ሳልደናገጥ ግን አውቀን የፈጸምነው በሚመስል ስህተት ተገርሜ አደመጥኩት። ወዲያው የባሻዬ ነገር ታሰበኝና እጨነቅ ጀመር። ‘እንባና ሳቃችን ሆነው ቅርብ ለቅርብ፣ ስንስቅ አለቀስን ስናለቅስ ሳቅን!’ ያለው አዝማሪ ትዝ አለኝ። እናንተዬ አሁንስ ከሚዲያው ይልቅ አዝማሪ የልብ አድራሽ ሳይሆን አልቀረም መሰል፡፡ መሰል ነው እንግዲህ!
አዛውንቱ ባሻዬ የዓለም ዋንጫው ከተጠናቀቀ በኋላ እኛን መከራ የሚያሳየንን መጥፎ ልማዳችንን አስመልክተው፣ ‹‹እኔን የገረመኝ አንበርብር ሰላም አገኘን ብለን ዕፎይ ከማለታችን ከየታዛቸው እየተጠራሩ የሚበጠብጡን ጉዶች ነገር ነው። በአገር ውስጥ የለመድነውን ከሕግ በላይ ሆኖ የመኖርና የመሥራት አባዜ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ስንደግመው መታየታችን ነው…›› አሉኝ ኮስተር ብለው። ‹‹እንዴት?›› አልኳቸው ንግግራቸው ከወፍራም ኮስታራ ድምፃቸው ጋር ተደምሮ ጠንክሮብኝ። ባሻዬ፣ ‹‹መቼም የዚህን አገር ነገር ምን ብዬ እነግርሃለሁ አንበርብር? ሁሉም ማለት ትችላለህ ከሕግ በላይ ነው። ሕግ የበላይ ነው ብለህ የመናገር ድፍረቱ እንዳይኖርህ የፍትሕ ሥርዓቱ መዝረክረክ ይከለክልሃል። ሁሉም በዘፈቀደ እንዳሻው ይኖራል፣ እንዳሻው ይከብራል። ፈሪኃ እግዚአብሔር ብሎ ነገር የለም። ማናለብኝነት ነግሷል። ታዲያ እንዲህ ባለው የዘቀጠ አሠራር በተበለሻሸ ሁኔታ ውስጥ ለሕግና መርህ መከበር የሚደነግጥ ዜጋና ማኅበረሰብ ቁጥሩ እጅግ ኢምንት በሆነበት አገር የሚያሳፍር ስህተት ቢሠራ ምን አጀብ ያስብላል?›› ሲሉኝ ነገሩን የጠመዘዙበት መንገድ ገባኝ። የባሻዬ አተያይ ሲደንቀኝ የውስጥ አመላችን እንዲህ በአደባባይ ዋጋ ሲያስከፍለን ማየቴ ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ። ጉድ ሳይሰማ መስከረም የሚጠባው መቼ ይሆን ግን? ለነገሩ ችግራችን መፍታት አቅቶን ፕሪቶሪያ ድረስ የሄድነው በዚህ አባዜያችን መሆኑን ማን ይክድ ይሆን? ማንም!
ሰውን ሰው አላነሳው አለ እንጂ ጨዋታንስ ጨዋታ ማንሳቱ እንደቀጠለ ነው። እንዲያው ግን እንዲህ የሰው መጨካከን አይገርማችሁም? ይገርመው እንደሆን ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ብጠይቀው፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? የክፋት ዘመን ስለሆነ እኮ ነው…›› አለኝ። ክፋት ቢል በቀደም ዕለት የሆንኩትን ላጫውታችሁ። ከመቼው ተጋብተው ከመቼው እንደተፋቱ አላውቅም የማውቃቸው ባልና ሚስት ንብረት እኩል ለመካፈል ቤት ይሸጣሉ። እንግዲህ አሻሻጩ ደላላ እኔው አንበርብር ምንተስኖት መሆኔ ነው (ይቅርታ አድርጉልኝ ስላቋረጥኩ። የዘንድሮ ፍቅርና ኔትወርክ ግን መንታ ወንድማማቾች አይመስሉም? ደርሰው ምጥት ደርሰው ሂድት ሲሉ?)፡፡ አቤት ደግሞ ቤቱን ብታዩት? እዚያ ነበር ተወልዶ አድጎ አርጅቶ መሞት ያስብላል እኮ (የአብዛኞቻችን ኑሮ አንድ ቤት ውስጥ ተወልዶ ማርጀት ስለሆነ ብዬ ነው)፡፡ እናማ በምታውቁት ፍጥነት ታ! ታ! ታ! አድርጌ ቱጃር ነጋዴ ቤት ፈላጊ አገኘሁ። መቼም ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነበር (ነበር ልበል እንጂ በ‘ኔትወርክ’ ምክንያት፣ ነበር እኛ አገር መቼ ርቆ ያውቅና?)፡፡ ምንም እንኳ የእኛ አገር ‘ኔትወርክ’ ‘ፎርሜሽን’ እስካሁን ባይታወቅም። እናማ ቤቱን ከመግዛቱ በፊትና ሰዎቹን ከማነጋገሩ አስቀድሞ፣ ‹‹ለመሆኑ በሰላም ነው ይህን የመሰለ ቤት ሰዎቹ የሚሸጡት? መቼም በዚህ ዘመን ከዚህ የተሻለ ቤት ልሥራ ማለት የሚታሰብ አይሆንም…›› አለኝ ቱጃሩ። እኔም፣ ‹‹የለም በሰላም እንኳ አይደለም። ባልና ሚስቱ ፍቺ ላይ ስለሆኑ ነው…›› ብዬ ዓይን ዓይኑን አየሁት። በቃ የማንፈራው የለም እኮ እኛ ደላሎች። ‘ደግሞ የፍቺ ቤት ገዝቼ ነገ እኔስ ብፋታ?’ እንዳይለኝ ሰግቼ እኮ ነው ዓይን ዓይኑን የማየው። ወይ ጉድ? አጉል ልማድና አስተሳሰብ እንኳን እንዲሁ በገንዘብ መቼ በቀላሉ ይለቃል ብላችሁ ነው። ኧረ ተውኝማ!
ስለምን ነበር የምንጫወተው? አዎ ስለጭካኔ፡፡ የሳምንት ፍቅር፣ የሳምንት ኩርፊያ፣ የሳምንት ጓደኝነት፣ ወር የማይቆይ ሹመት፣ ዓመት የማይቆይ ሽረት፣ አንድም ቀን የማይተገበር መርህ፣ በተግባር የማይታይ ስብከት። ኧረ ምኑ ቅጡ? ጭካኔ በወረት ታጅቦ፡፡ በአንድ ወገን የጓዳችን ወረት አልብቃቃ ሲለን፣ በአንድ ቀን ወረት እያሳሳመ ሲያናክሰን ኑሮን እንደ ቀልድ፣ ዕድሜን እንደ ቀላል ይኼው እንገፋዋለን። ‘መኖር ደጉ ብዙ ያሳያል’ ተብሎም አይደል? እናማ እንዲህ እያሰብኩ ሳላውቀው ይኼን ሁለት ቀን ‘ወረተኛ ነሽ አታዋጭኝም’ የሚለው ዜማ ከአፌ አልጠፋ ብሎ ነበር። እህሳ? ማንጠግቦሽ ጆሮ ደርሶ እርፍ። ያው እንደምታውቋት፣ ‹‹ምነው ሐሳብን ፊት ለፊት የመግለጽ መብት በተከበረበት ዘመን ጥግ ጥጉን ያዞርሃል?›› ብላኝ ቁጭ። እንዲህ የአንጎራጎርነውና የተነፈስነው ሁሉ ፖለቲካ ነው እየተባለ እንዴት መኖር እንደምችል ስታስቡት አያማችሁም ታዲያ? አቤት ዘንድሮማ አባብለን ተናግረን እንዲህ ከተባልን ዴሞክራሲ አለ ብለን የልባችንን ብንዘረግፍ ጉድ ነበር የሚታየው። በተለይ ይህ የልጆቻችን ትምህርት ቤት ድረስ ሰተት ብሎ የገባው የብሔርተኝነት ጉድ ብዙ ሳያባብለን አይቀርም ነበር፡፡ ጉድ ነው ዘንድሮ!
በሉ እስኪ እንሰነባበት! እኔና የባሻዬ ልጅ በአርባ ብር የተገዛ ጭብጥ የሽንብራ እሸት እየጠረጠርን የእግር መንገድ እንጓዛለን። ‹‹ድሮ ቢሆን እኮ እሸትና ቆንጆ አይታለፍም እየተባለ አላፊ አግዳሚው ከእጃችን ላይ ሳብ ያደርግ ነበር…›› ስለው፣ ‹‹አንተ ደግሞ አሁን ያለው ትውልድ እኮ የድሮ አይደለም…›› እያለኝ መንገዳችንን ቀጥለናል፡፡ ‹‹ሰማህ አንበርብር? እውነት ግን እንደዚህች ሕዝቧ ተጠቃሚ ያልሆነባት አገር ዓለም ላይ የቷ አገር ትሆን?›› ብሎኝ ዕርምጃውን ገታ አድርጎ ቆመ። ‹‹ማለት?›› አልኩት ጠጠር ያለው ጥያቄው እንዳሰኘኝ መልስ ለመስጠት አላመች ብሎኝ። ‹‹በቃ፣ የወጠነችው እንዳይሳካ በውስጥም በውጭም ሴራ ሲጎነጎንላት፣ ትንሽ ትልቁ ከፍ ስትል ሊያወርዳት አበሳውን ሲያይ፣ ጠቀምኩሽ ብሎ ያልጎዳት፣ እኔ ነኝ የማውቅልሽ ብሎ ያልገደላት ማን ነው? አቤት ስንቱን ያሳለፈ ብርቱ መሰለህ ይህ ሕዝብ? ከጭቆና አገዛዝ ነፃ ለማውጣት መስዋዕትነት የከፈለላት አንድ ትውልድ ይታሰብሃል? በገዛ ውኃዋ ተጠቃሚ እንዳትሆን የደረሰባትን የዘመናት ፈተና ትረዳለህ?›› ብሎኝ በሐሳብ ነጎደ። ወዲያው ደግሞ ምልስ ብሎ በንዴት እየተንቀጠቀጠ፣ ‹‹የእስካሁኑ ይበቃል፣ ከዚህ በኋላ ማንም በሕዝብ ስም እንዲቀልድ፣ በሕዝብና በአገር ሀብት እንዲደላደል አንፈቅድም። ማንም!›› ብሎኝ እንዳፈጠጠ ቀረብኝ። እኔም ምንም እንኳ ስሜታዊ ቢሆንም የተናገረው እውነት ስለነበር፣ ‹‹አዎ የእስካሁኑ ይብቃ!›› ብዬ መለስኩለት። ፉከራዬ የወረት እንዳይሆን እየተጠራጠርኩ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በላቡ፣ በድካሙ፣ በደሙ የጠበቃት አገር የጃርት መጫወቻ እንዳትሆን ተመኘሁ፡፡ ምኞቴም ከንቱ እንዳይሆን ሥልታዊ የመሆን አስፈላጊነትም ታየኝ፡፡ ሥልታዊ ማጥቃትና ማፈግፈግ የሚባለው ለካ የዋዛ አይደለም! መልካም ሰንበት!