Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዘውዱና የደርጉ ዘመን ወታደራዊ ቅርሶችን የተረከበው ወታደራዊው ሙዚየም

የዘውዱና የደርጉ ዘመን ወታደራዊ ቅርሶችን የተረከበው ወታደራዊው ሙዚየም

ቀን:

የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ታሪኳ ሲነሳ ከሦስት ሺው ዘመን ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚወሳው ገናናው የአክሱም ዘመን ነው፡፡  ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚ ከማኅበራዊ እስከ ጥበባዊ ዘርፎች ብቻ ሳይሆን የጦር ኃይሉም ኃያላኑ አገሮች አንዱ እንደነበር ተመዝግቧል፡፡ በተለይም የአፄ ካሌብ የባሕር ኃይል የአካባቢው ልዕለ ኃያል እንደነበረና ለተገፉ ፈጥኖ ደራሽ ሆኖ ያገለግል እንደነበረ በዓረቢያ ምድር በፈጸመው ገድልም ይወሳል፡፡

በ19ኛው ምዕት ዓመት ተስፋፊው የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት በ1879 ዓ.ም. በራብዓዊ አፄ ዮሐንስ ዘመን ዶግዓሊ ላይ፣ በ1888 ዓ.ም. በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ዓድዋ ላይ ድል የመታችው ኢትዮጵያ፣ ታሪኳ በወርቅ ቀለም የተጻፈው በአውሮፓ ነጮች ላይ ድል የተቀዳጁ ጥቁሮች በሚል ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ገድል ባዕዳን ወራሪዎችን በመግታትና በመርታት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ሥር በመሆን በተለያዩ አገሮች ኮርያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን ከውጊያ እስከ ጸጥታ ማስከበር ተልዕኮዋን መወጣቷ ሲያስመሰግናት ኖሯል፡፡

ይህ የጦር ኃይሎቿ በየዓረፍተ ዘመኑ ያከናወኑት ተግባራት በመጻሕፍት፣ በፊልምና በሌሎች መንገዶች ተቀርሰው ቢገኙም በሙዚየም ደረጃ ክብር ሲጎናጸፉ አልታየም፡፡

የስምንት አሠርታት ያህል ዕድሜ እንዳለው በሚነገርለት የዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚየም ታሪክ ውስጥ ይዘቱና ትኩረቱ በሌሎች ዘርፎች ላይ በማድረጉ፣ ነባሩን የጦር ኃይሉን የሚያሳይ የገዘፈ ክንፍ እንኳን አልነበረውም፡፡ የጦር አልባሳትን፣ የአርበኞችንና የከፍተኛ መኰንኖችን ምስል ከማሳየት ባለፈ፡፡ የኮርያ ዘማቾች ማኅበር ያደራጀው ሙዚየምም ሳይዘነጋ፡፡

በሌላ በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መከላከያ ሚኒስቴር የራሱን የውትድርና ቅርስ ጥበቃ ማዕከልና ወታደራዊ ሙዚየም ለማቋቋም ሲጥር ታይቷል፡፡ በተለይ ዓምና በወርኃ ሚያዝያ ርዕዩን ዕውን ለማድረግ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የውትድርና ቅርስ ጥበቃ ማዕከልና ወታደራዊ ሙዚየም ማቋቋም የአገር ፍቅርን ለማስረፅና ጠንካራ ብሔራዊ ስሜትን በትውልዱ ህሊና ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

የወራት ዕድሜ ያስቆጠረውና ተልዕኮውን ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ ያለው የመከላከያ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም፣ ባለፈው ሳምንት በነገሥታቱና በደርግ ኢሕዲሪ ዘመን የሠራዊት አዛዦች የነበሩ ይገለገሉባቸው የነበሩትን የተከበሩ ንብረቶችን ከቤተሰቦቻቸው ተቀብሏል፡፡

በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደተገለጸው፣ የመከላከያ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም የተረከባቸው ወታደራዊ ቁሳቁሶች የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲኔግዴ እና የሜጀር ጀኔራል ግዛው በላይነህ ናቸው፡፡

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ከ1900 እስከ 1919 ዓ.ም. የጦር ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በጦር ሜዳ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ቁሳቁሶች ገቢ ያደረጉት የባህል ሐኪሟ ወ/ሮ አበበች ሺፈራው ናቸው።

በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) ዘጠነኛው  ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጄር ጀኔራል ግዛው በላይነህ፣ በውትድርና አመራርነታቸው ሲገለገሉባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን እና ሌሎች ማስተወሻዎችን ልጃቸው አቶ ግሩም ግዛው በላይነህ ገቢ ማድረጋቸው የመከላከያ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም አስታውቋል።

የሠራዊቱን ቅርስ በመሰብሰብ ለትውልዱ እንዲተላለፍ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ያሉት፣ በርክክቡ ላይ የተገኙት በመከላከያ ሚኒስቴር ልዩ ስታፎች ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ጥሩዬ አሰፌ ናቸው፡፡

ጄኔራሏ አያይዘውም ትውልዱ ከአባቶቻችን ታሪክ ተምሮ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥና እንዲማርበት ወታደራዊ ቅርሶች ዕድል ይፈጥራሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የመከላከያ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱልቃድር ደበሹ በበኩላቸው የሠራዊቱን ታሪክና ቅርስ በመሰብሰብ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ያለው ሥራ ትውልዱ በተለይ ታሪካዊውን የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በሚገባ እንዲገነዘቡ ያግዛል ብለዋል።

‹‹ታሪክን መሰብሰብ ጀግኖችን እንዲሁም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ፣ ትውልዱ ወደ ሙዚየም የገቡ ቅርሶችን ተመልክቶ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥና የተሻለ ነገር እንዲሠራ ያነሳሳል፤›› ያለው በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘው  ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነው፡፡

‹‹የአበበ ቢቂላና የማሞ ወልዴ ታሪክ እንዳመጣኝ ሁሉ ሁሉም ሰው በየቤቱ ያለውን ወታደራዊ ቅርስ ለመከላከያ በመስጠት የአገራችንን ታሪክ ማስቀጠል አለብን፤›› ማለቱን ወታደራዊው ሙዚየም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋምን በበላይነት የሚመራው ሚኒስቴር ‹‹መከላከያ ሚኒስቴር›› ከመባሉ በፊት፣ በቀደምቱ ዓመታት በተከታታይ ‹‹የጦር ሚኒስቴር››፣ ‹‹የአገር መከላከያ ሚኒስቴር›› እየተባለ ከመጠራቱ አስቀድሞ፣ ‹‹ቀ.ኃ.ሥ የጦር ሚኒስቴር›› (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ሚኒስቴር ለማለት ነው) ይባል እንደነበረ በፈረንሳይኛ ቋንቋም ‹‹MINISTERE GUERRE DE LA›› መሳ ለመሳ ይጻፍ እንደነበረ፤ አንበሶች፣ ጦርና ጋሻ፣ ጎራዴም በአርማነት ይውሉ እንደነበረ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...