Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአፍሪካውያን የጤና ባለሙያዎች የተባበሩበት የቴሌሜዲስን ኔትዎርክ

አፍሪካውያን የጤና ባለሙያዎች የተባበሩበት የቴሌሜዲስን ኔትዎርክ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ዓለማችን ለቴክኖሎጂ እጅን ሰጥታ ከየብስ እስከ ጠፈር ከባህር እስከ ጨረቃ ጓዳ ጐድጓዳው በቴክኖሎጂ እየተሳሰረ እንደሆነ የመስኩ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንደር በማቀራረብ ሰዎች በብዙ ማይል ርቀት ላይ ሆነው ልክ አብረው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚወያዩ፣ እንደሚሠሩና እርስ በርስ እየተያዩ ደስታም ሆነ ሐዘናቸውን እየተጋሩ እንዲኖሩ ማድረግ ከጀመረም ሰነባብቷል፡፡ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችም ዓለምን ወደ መንደርነት እየቀየሩ ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምናልባትም አፍሪካውያን በተናጥል ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመሄድና በቴክኖሎጂው መስክ በመሰማራት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ችለው ይሆናል እንጂ አሁን ላይ ግን እነዚህን እይታዎች ሊቀይሩ የሚችሉ ጅምሮች በየአቅጣጫው ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ የአፍሪካ ቴሌሜድሲን ኔትዎርክ ነው፡፡

የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ በአኅጉሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘና የጤናውን ዘርፍ ሊያዘምን የሚችል ነው፡፡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል፣ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂን ለማዘመንና የአፍሪካን የጤና ባለሙያዎች ወደ አንድ መድረክ ለማምጣት የሚያግዝ ነው፡፡

ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ ከአሜሪካ ሜዲካል ሴንተር ጋር በመተባበር ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ጉባዔ በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው አፍሪካን ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ ከኢትዮጵያ አልፎ የአኅጉሪቱ የጤና ተቋማትንና ባለሙያዎች ዘመኑ ያመጣውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ኅብረተሰቡን ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻች ነው፡፡

ቴሌሜዲስን እንደ ኮምፒዩተር፣ ካሜራ፣ ሽቦ አልባ የመገናኛ ዘዴዎችንና የቪዲዮ ኮንፈረንስ መድረኮችንና የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጤና አገልግሎቶችን ከርቀት ማድረስ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው የቦታዎች ርቀት ሳይገድበው በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው የጤና ተደራሽነትን ለማዳረስ እጅግ ተመራጭ ዘዴ እንደሆነም በመድረኩ ተነግሯል፡፡

በአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ ጥላ ሥር በየአገሮች ውስጥ ዲጂታል የጤና አቅምን ለመገንባት የሚያገለግሉ ኢትዮጵያ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ፣ ሩዋንዳ ቴሌ ሜዲሲን ኔትዎርክ፣ ኬንያ ቴሌሜድስን ኔትዎርክና ሌሎችም ድርጅቶች ይኖራሉ ተብሏል፡፡

የቴሌሜዲስን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ መመርያዎችንና ደንቦችን ለማውጣት ከአገር ውስጥ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከጤና ባለሥልጣናትና ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን በቅርበት እንደሚሠራም የአሜሪካ ሜዲካል ሴንተር መሥራችና የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ ሰብሳቢ አከዛ ጣዕመ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ጠንካራ የቴሌሜዲስን ማኅበረሰብ ለመገንባትና በአኅጉሪቱ ለማስፋፋት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

 ኢትዮጵያም ሆነች የአፍሪካ አገሮች ወደ ዲጂታል ጤና አገልግሎት ለመግባት በሙከራ ላይ መሆናቸውንና ዘርፉን ለማዘመን በየቦታው ያሉ ጅምሮች እንዳሉ ያነሱት አከዛ (ዶ/ር)፣ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ሊያሻግሯቸው የሚችል ጠንካራ ማዕከላዊ ድርጅት አለመኖሩን መነሻ በማድረግ አፍሪካን ቴሌሜዲሲን ኔትዎርክ የተባለ ድርጅት እንዳቋቋሙ አብራርተዋል፡፡

ማንኛውም ሰው አገልግሎቱን ለመጠቀም ሀባሪዶክ (HabariDoc) የተባለውን መተግበሪያ ከጉግል አፕ ወይም ከጉግል ስቶር ማውረድ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

በመጪዎቹ ሳምንታት ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና የተለያዩ አገሮች መተግበሪያውን በማውረድ አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚጀምሩ፣ ኢትዮጵያውያን ለሁለት ሳምንታት ያለምንም ክፍያ መጠቀም እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ማንኛውም የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ አገልግሎቱን ከሚሰጠው ዶክተር ጋር መግባባት በሚችሉበት ቋንቋ እንዲጠቀሙ እንዲችሉ ተደርጎ መተግበሪያው መዘጋጀቱን አከዛ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ዶክተሩ በእጅ ስልኩ በኩል የመጣለትን ታማሚ ከርቀት ሆኖ ከተመለከተ በኋላ በአሜሪካ ይሁን ካናዳ በኢትዮጵያ ይሁን ደቡብ አፍሪካ በርቀት ሳይገደብ የላብራቶሪ ምርመራ ካስፈለገው ማዘዝ የሚችልበት ዘዴ ነው ሲሉ ሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሕክምና ወጪን ከማስቀረቱም ባሻገር የጊዜንና በሕክምና ወቅት የሚታይን የተራዘመ ቀጠሮና መጉላላት እንደሚቀርፍ አስታውሰዋል፡፡

በመጪዎቹ ስድስት ወራት አገልግሎቱን ለመስጠት ከ2,000 በላይ ባለሙያዎች ይሳተፋሉም ተብሏል፡፡

አፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ አገልግሎቱን ከገጠር እስከ ከተማ የሚያዳርስ እንደመሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነቱ እስከምን ድረስ ነው ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አከዛ (ዶር) እንዳሉት፣ በመሆኑና ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ከገጠር እስከ ከተማ ሰፊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ለጊዜው ችግር ቢኖርም ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው በመሥራት የሚያሻሽሉት ይሆናል፡፡  

በጉባዔው የተገኙት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ከጤና ተደራሽነት አኳያና በአሁኑ ጊዜ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኢንተርኔትን በእጃቸው ላይ የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው መጠን የጤና አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት የኢንተርኔት ተደራሽነቱን ማስፋፋት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ሥራው ሰፊ ጉልበትና ገንዘብ እንደሚጠይቅ በማንሳትም የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን እንደ አገር የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እንዳልተቻለ አንስተው፣ ለዚህም የቴሌሜድስን ቴክኖሎጂን መጠቀም አገልግሎቱን ለሚሰጡ ዶክተሮች ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...