ኢትዮጵያ ከ127 ዓመታት በፊት በዓድዋ በወራሪው የጣሊያን ሠራዊት ላይ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ድል የተቀዳጀችበት በዓል፣ እየተገባደደ ባለው የዓድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ለማክበር መታሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲስ አረጋይ ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደገለጹት፣ የዓድዋ ድል በሚዘክርበት በዚህ ፕሮጀክት የዘንድሮው ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ከፍ ባለ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለማክበር እንዲቻል፣ በሙዚየሙ ውስጥ ተካቶ ያለውን የበዓሉን ማክበሪያ ሥፍራ ለማጠናቀቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡
የዓድዋ ሙዚየም ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ2,000 እስከ 4,000 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የተለያዩ ቢሮዎች፣ ካፍቴሪያና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች፣ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የአውቶቡስና የታክሲ መናኸርያ፣ እንዲሁም ከሕንፃው ውጪ የቴአትርና የዓውደ ርዕይ ማሳያ ቦታዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡
4.6 ቢሊዮን ብር የተበጀተለትና ግንባታው በመስከረም 2012 ዓ.ም. የተጀመረውን ይህን ፕሮጀክት በተቋራጭነት ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ኩባንያና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት በባለቤትነት እያከናወኑት የሚገኝ ነው።