ከሃና ማርያም ወደ መገናኛ ለመሄድ በማለዳ ትራንስፖርት ጥበቃ የተሠለፉ ሰዎች ተሽከርካሪዎች ከታች ላይ ባለፉ ቁጥር ዓይናቸው ሲንከራተት ይታያል፡፡ ረዥም ሠለፍ ከተሠለፉት መካከል ወጣት ዮናስ ዘገየ ይገኝበታል፡፡
ወጣት ዮናስ ከሃና ማሪያም ወደ መገናኛ ለመሄድ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ መሠለፉንና 2፡00 ሰዓት ሆኖም ትራንስፖርት አለማግኘቱን ያስረዳል፡፡
አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች መኪናቸውን እዚያው አቁመው አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ያለመስመራቸው እየሠሩ የሚገኙ መኖራቸውና መንግሥት በዘርፉ ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ያሰማራቸው ሠራተኞች ተገቢውን ክትትል አለማድረጋቸው ችግሩን አባብሶታል ብሏል፡፡
አብዛኛው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ኅብረተሰብ የሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ላይ ትራንስፖርት እንደሚቸገርና ረዣዥም ሠልፎችን ማየት እየተለመደ መምጣቱን የሚናገረው ወጣቱ፣ በተለይም የመንገድ መዘጋጋት የትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ያክላል፡፡
ወጣት ዮናስ፣ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች መንግሥት ካስቀመጠላቸው መስመር ውጪ የሚሠሩት አጫጭር ርቀት ተጉዘው የሚያገኙት ገንዘብ የተሻለ ስለሆነ ነው ይላል፡፡
ከሃና ማሪያም መገናኛ ወደ ሥራ ለመሄድ በተጓዘባቸው ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ገበታው ላይ አርፍዶ እንደሚደርስና በቂ የትራንስፖርት አማራጭ አለመኖሩም ለሥራው ትልቅ ችግር እንደሆነበት ያስረዳል፡፡
ከሃና ማርያም መገናኛ፣ ከሃና ማርያም አቦና ቃሊቲ የሚሠሩ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች፣ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ 4፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደማይሰጡና ኅብረተሰቡም ላልተፈለገ ወጪ መዳረጉን ይገልጻል፡፡
ከሥራ ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች ከቦታ ቦታ በሚዘዋወርበት ጊዜም ረዥም ርቀት ከሆነ መንግሥት ካወጣላቸው ታሪፍ በላይ እንደሚያስከፍሉ ይህም በራሱ ላይ ደርሶ ማየቱን አስታውሷል፡፡
በሌላ በኩል አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን የትራንስፖርት አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ መሆን አለበት የሚለው ወጣቱ፣ ይህንንም ለማድረግ መንግሥት ከሌሎች ፕሮጀክቶች በተለየ የትራንስፖርትና የመንገድ ፍሰቱ ላይ የተሻለ መሥራት ይኖርበታል ይላል፡፡
በአዲስ አበባ አብዛኛው ኅብረተሰብ የሕዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ በመሆኑ፣ በሥራ መውጫና መግቢያ ወቅት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች ለትራንስፖርት ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
መንግሥት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን በተሻለ መንገድ በማሳለጥ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ይኖርበታል የሚለው ወጣቱ፣ ይህ ካልሆነ ግን አንድም የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሌላ በኩል ደግሞ የከተማዋ የውበት ገጽታ ሊጠፋ እንደሚችል ያምናል፡፡
በአዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከባድ ችግር እየታየና ረዣዥም ሠልፍ ማየት እየተለመደ መምጣቱ፣ መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል የምትለው ደግሞ ወጣት ቃልኪዳን መንገሻ ናት፡፡
እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በየጊዜው አዳዲስ ነገር ይታያል፡፡ በተለይም ደግሞ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የተባሉ አሽከርካሪዎች ከመስመራቸው ውጪ በመጫን ተጠቃሚውን እያንገላቱ ይገኛሉ ብላለች፡፡
መንግሥት ከሰጣቸው ታፔላ ውጪ ጭነው የሚገኙ አሽከርካሪዎችን ወጥ በሆነ አሠራር መቅጣት እንዳለበት፣ የመደባቸውን ተቆጣጣሪዎችም መከታተል እንደሚገባው ወጣት ቃልኪዳን ትናገራለች፡፡
ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚሆኑ መሠረተ ልማት ምቹ ባለመሆናቸው የተነሳ አብዛኛው ተሽከርካሪዎች እንደልባቸው ተመላልሰው ለመሥራት ሲቸገሩ ይታያልም ብላለች፡፡
‹‹በየጊዜው ከቤት ስወጣ ቅድሚያ የሚያሳስበኝ የትራንስፖርት ሁኔታ ነው፤›› የምትለው ወጣቷ፣ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ በሥራ ገበታዋ ላይ አርፍዳ በመገኘቷ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣት ታስረዳለች፡፡
የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ፣ ተጠቃሚውና የተሽከርካሪ ብዛት የማይመጣጠን መሆኑ አብዛኛውን ትራንስፖርት ተጠቃሚ ችግር ውስጥ ከቶታል፡፡
መንግሥት የትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ካልሠራና ያሉትን ችግሮች ካልቀረፈ የበርካታዎች ኪስ ሊፈትን ይችላል ብላለች፡፡
ከሁሉ በላይ በከተማዋ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የሚሠሩ ሰዎች ችግር ውስጥ እንደወደቁና በፈለጉት ጊዜ ደርሰው ሥራዎቻቸውን መሥራት እንዳልቻሉ፣ በተለይም አቅመ ደካማ፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እንደ ልብ ተጋፍተው አሊያም ደግሞ ተሠልፈው ትራንስፖርት እንደማያገኙና ከባድ ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደቻሉ ታስረዳለች፡፡
በአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አብዛኛው አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን፣ ይህ ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ እንደሚበዛ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ከላይ ታች የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለስርቆት እንደሚጋለጡና ይህም የበርካታ ሰዎች ምሬት እንደሆነ ታክላለች፡፡
መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል የምለትው ወጣቷ፣ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሰማራቸው ተቆጣጣሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መሥራት ይኖርበታል ብላለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ እፀገነት አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት ሰጥተዋል? የሚለውን ለመቆጣጠር ከ342 በላይ ተቆጣጣሪዎች ተሰማርተዋል፡፡
በተለይም በማኅበረሰቡ በኩል እየተነሱ ያሉ ትራንስፖርት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ ከ100 በላይ አውቶብሶችን ገዝቶ ወደ ሥራ ማሰማራቱን፣ በከተማዋ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከተመደቡበት መስመር ውጪ ሲሠሩ እንደሚታዩና ይህንን ሲሠሩ የተያዙ አሽከርካሪዎች የ500 ብር ቅጣት እንደሚገጥማቸው አክለዋል፡፡
ከመስመር ውጪ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን መቆጣጠር የቢሮው ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ይሁን እንጂ እነዚህን አሽከርካሪዎችም ሆነ ሌሎች በዙሪያው ሕገወጥ አሠራርን የሚከተሉትን ለመቆጣጠር የተመደቡ ሠራተኞች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በከተማዋም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተመድበው የሚሠሩ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ከተያዙ የ1,500 ብር እንደሚጠቀጡ ገልጸው፣ አብዛኛውን ጊዜም ይህን ሥራ የሚሠራው ተቆጣጣሪ በሌሉባቸው ቦታዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የተሰማሩ ሠራተኞች ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅትም ከ600 በላይ ሠራተኞች ለዚህ ሥራ እንደሚያስፈልጉ ወ/ሮ እፀገነት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ማኅበረሰቡ አልከፍልም በማለት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥ የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ተበላሽተው የተቀመጡ አውቶብሶችን እንደ አዲስ በማደስ ወደ ሥራ ማስገባቱን አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ ችግር እየታየ ሲሆን፣ በተለይም ከመስመር ውጪ ተዘዋውረው የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና እዚህ ላይ ቁጥጥር እየተደረገ አለመሆኑን ሪፖርተር በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ ለመመልከት ችሏል፡፡