የጎርጎርዮሳዊውን ቀመር በሚከተሉ አገሮች የገና በዓልን ከምግቡ ባሻገር ይበልጥ የሚያደምቁት ቤቶችና መንገዶች የሚዋቡባቸውና የሚደምቁባቸው መብራቶች፣ በደማቅ ቀለም በተለይም በቀይ ቀለም የተዋቡ አልባሳት፣ በተለያዩ ቀለሞች በተሽቆጠቆጡ መጠቅለያዎች ተሸፍነው የሚሰጡ ስጦታዎችና ጣፋጮች ናቸው፡፡ በደማቅ ቀለማት ተሽቆጥቁጦ በሚያልፈው የገና በዓል ሰሞን ደግሞ ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ተቋማትም ያሸበርቃሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ስተዲ ኢንተርናሽናል በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ የዘንድሮን ገና ይበልጥ ምትሐታዊ በሆነ መንገድ ያሸበረቁ ዩኒቨርሲቲዎች አራት ናቸው፡፡ እነሱንም በፎቶ አስደግፎ አቅርቧል፡፡ በየዓመቱ በእንግሊዝና በአሜሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የገና ወቅትን (ክሪስማስ) በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉም ይላል፡፡