«…….. ሽሮሜዳ አማረም አላማረም ማንም በልቶ ጠግቦ የሚያድርባት ሥፍራ ናት፡፡ ልጆቻችን የረጉ፣ በሳቅ በጨዋታ ነፍሳቸውን የቀለለችና የተኳለች ናት፡፡ አያድርገውና ቢያደናቅፋቸው መሬት አይነኩም፡፡ መሬት ነክተው እንዳይጎዱ ከሚንሳፈፉበት አየር ላይ በወገናቸው በፍጥነት ይለቀማሉ። እዩ እግሮቼንና ክንዶቼን። ሺሕ ጊዜ አደናቅፎኛል፣ ሺሕ ጊዜም ወድቄአለሁ፡፡ ምንም ጠባሳ ግን የለብኝም። እዳሪያችን ድስት፣ መሶብና ማዕድ ነው። የሰውን ተውኝና ባለቤት የሌላቸው ለቅልውጥና የመጡ የሌላ ሰፈር ውሾች እንኳን እዛ እዛ ብለው ቀራርመው የሚመሰጡበት ቁራጭ ሥጋ፣ መቅኒ የለጎመ አጥንት አያጡም።
ንቦቻችን ፍጡር ናቸውና ክብር አላቸው፡፡ ይኼም ንቁ አድርጎአቸዋል። ጌጥ ስለሚወዱና ኪነጥበብ ስለሚያደንቁ በዓይን ማየት የሚያዳግት ቁንዳላቸውን ለማበጠሪያ ክንፎቻቸው ሥር ከሰንደል እንጨት የተበጀች ደቃቃ ሚዶ ይዘው ይበራሉ። ከዚያም አልፎ አይኖቻቸውንም ይኳላሉ፡፡ በየቦታው ሲንዛዙ ወለላ ማጠራቀሚያ ወርቅማ ሙዳዮች በጀርባቸው አዝለው ነው፡፡ ጣፋጭነታችን በአንደበታችን፣ በዘፈናችንና በሽፈነን ቆዳችን ላይ አለ። ልብሶቻችን ለአንድ ሰዓት ያህል እውጭ ቢሰጡ፣ ከላያቸው የሚወርደው ዮጵ የመሰለ ማር ነው፡፡ ጥርሶቻችን ነጫጮች ናቸው። እኔን እዩ (እኝ)፡፡ ከብቶቻችን የሚግጡት የባቄላና የአተር ደን ነው (አለነገር ‹ሽሮሜዳ› ተባለ መሰላችሁ?) ቅቤያችን ያለ አላቢ ከላሞቻችን ግት በራሱ ፈቃድ እተንዠረዠረ ይወጣል። ጀምበር ስታዘቀዝቅ፣ ብዙ ‹እምቧ› ብትሰሙ የሰፈራችን ጥገቶች ‹ወተታችንን ውሰዱ› እያሉ ሲለማመጡን ነው።
ለታሪክ የሚቀመጥ አንድ ነገር እንካችሁ። በዚህች ዓለም ላይ ሽሮሜዳ ብቻ ናት የሚያቀነቅኑ ላሞች ያሉባት፡፡ ይኼ ቀጥሎ የምትሰሙትን ‹እምቧ በይ ላሚቱ› የተባለውን የሙሉቀን መለሰን ዘፈን መጀመሪያ ያንጎራጎረችው ‹ቡራቡሪት› የተባለች የሽሮሜዳ ላም ናት…» (አንድ የሽሮሜዳ ወጣት ስለ ሽሮሜዳ ሰፈር በኢትዮጵያ ሬድዮ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ካነበበው የተቀነጨበ 1963 ዓ.ም.)
- አዳም ረታ ‹‹መረቅ››