አሜሪካን ያጥለቀለቃት ጉዳት የሌለው የሚመስል አባባል አለ። ሰዎች ‹‹ደህና ዋል፡፡›› ደህና ሁን፡፡›› ማለትን ትተዋል፡፡ ምንጊዜም ‹‹ጠንቀቅ በል፡፡›› የሚለውን ሳይጨምሩ አይሰናበቱም።
እኔ ‹‹ጠንቀቅ በል›› ‹‹ተጠንቀቅ›› የሚለው አባባል ስህተት ነው እላለሁ። በምትኩ ‹‹ዕድልህን ሞክር፣ ኃላፊነት ውሰድ፣ ሁኔታዎችን ተቆጣጠር፡፡›› ቢባል እመርጣለሁ፡፡ ለምን? ምክንያቱም የሚጠነቀቁ ሰዎች የትም አይደርሱም። ችግርህን በተሳካ ሁኔታ መምራትና መቆጣጠር ከፈለግክ ዕድልህን መሞከር፣ ኃላፊነትን መውሰድና መቆጣጠር ይኖርብሃል፡፡ ዕድልን መሞከር በራሱ አደጋ ነው። ኃላፊነትን ስትወስድ ግን አደጋውን ትቆጣጠረዋለህ። ሁኔታውን ተቆጣጥረህ ስትመራው ደግሞ ችግርህንም ትቆጣጠረዋለህ።
ኃላፊነትን ውሰድ። ሁኔታዎችን ተቆጣጠር። አመራሩን ለውጫዊ ሁኔታዎች አሳልፈህ አትስጥ፡፡ አመራር ወይም መሪነት ማለት ምን ማለት ነው? በአጭሩ እገልጽልሃለሁ። አመራር ወይም ወይም መሪነት ህልምህን የሚመርጥና ግብህን ለመለወጥ የሚያሽከረክረው ኃይል ነው። አብርሀም ሊንከን ስለ አንድ አንጥረኛ የተናገረውን ታሪክ ልንገርህ። አንጥረኛው ረዥም ክብ ብረት ፍም እስኪመስል ድረስ እሳት ውስጥ ይከተዋል። ከዚያ ቅርጽ ማውጫው ላይ አስቀምጦ በመዶሻው መጠፍጠፍ ይጀምራል፡፡ ጎራዴ ለመሥራት፡፡ ሲጨርስ በውጤቱ አልተደሰተም። መልሶ እሳት ውስጥ ከተተውና ጠፍጣፋውን አካል ትንሽ ሰፋ አድርጐ ለአትክልት ቦታ መቆፈርያ አድርጎ ሊሠራው ሞከረ፡፡ አልተሳካም እንደገና እሳት ውስጥ ከተተውና ትንሽ ክብ አድርጎ የፈረስ ኮቴ ለማበጀት ሞከረ፡፡ ይህም ሙከራ በአሳዛኝ ሁኔታ ከሽፈ።
የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ እሳት ውስጥ ከተተው። መልሶ አወጣው። ምንድነው የምሠራበት? እያለ ሲያስብና ሲገረም ቆይቶ፣ ምንም ሊሠራበት እንደማይችል ወስኖ ውኃ የያዘው በርሜል ውስጥ ከተተው። የጋለው ብረት ስስስ የሚል ድምፅ እያሰማ መቀዝቀዙን ሲቀጥል አንጥረኛው፡- ‹‹ደህና! ሌላው ቢቀር ከውስጡ ድምፅ አስወጥቻለሁ።›› አለ። ህልምህ መምከን የለበትም፡፡ ያለ ስኬት መቋጨት የለበትም። በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ የተዘረዘሩትን የአመራር መርሆች ከተማርክ፣ ኃላፊነት ወስደህ ከመራኸው ችግሮችህ ይቃለላሉ። ሕይወትህ ይደምቃል። ብዙዎቹ ‹‹መሪዎች›› ይህንን አለማወቃቸው ይደንቃል። እነዚህን መርሆች ባለማወቃቸው ሁኔታዎችን መቆጣጠሩ ያቅታቸውና በስኬት ሊመሯቸው ይገቡ በነበሩ ችግሮች ይቸነፋሉ።
ወርቁ አበራ (ትርጉም) ‹‹ክፉ ቀን ያልፋል›› ክብሩቡክስ እንደቀመረው