Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተግዳሮቶችና እየቀረቡ ያሉ መፍትሔዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግንባታዎችን በሚያካሂዱና በግንባታው ባለቤቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በርከት ብለው መታየት ጀምረዋል፡፡ በመካከላቸው የሚደረገው ውል አልፀና ብሎ ግንባታዎች እየተስተጓጎሉ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ግንባታ ዘርፍ በአስገንቢና በገንቢ መካከል ያለመግባባቶች ሊፈጠሩ የሚችሉበት ሁኔታዎች ያሉ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ያለመግባባቱ በርከት ብሎ እየታየ ነው፡፡ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለመፍታት አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፈጠራቸው፣ የኢንዱስትሪው ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን የዘርፉ ተዋናዮች ያመለክታሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከሌላው ጊዜ የተለየ ችግሩ እንዲጎላ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ በእጅጉ መናርና ያልተቋረጠ የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ ግንባታዎችን መጀመርያ በተፈረመ ስምምነት ላይ በተቀመጠ ዋጋ መቀጠል የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው፡፡

በተለይ ካለፉት አራትና አምስት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አሳማኝና አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የግንባታ ግብዓቶች በእጅጉ ዋጋ በመጨመራቸው ብዙዎቹ ፕሮጀክቶችን እንገነባበታለን ብለው በተስማሙበት ዋጋ ማስቀጠል አለመቻሉ የውለታ ሰነዶችን እያስቀደደ ነው፡፡

የባሰ እንዳይመጣ ብለው ከኮንትራክተሮች ጋር ተስማምተው የዋጋ ማስተካከያ አድርገው ግንባታውን ማስጨረስ እየታተሩ ያሉ ቢኖሩም፣ በአብዛኛው ግን በግንባታ ፕሮጀክቶቹ ባለቤቶችና በኮንትራክተሮች መካከል ያለመግባባት እየተፈጠረ ነው፡፡ ከዋጋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ያለመግባባት መፍታት ያልቻሉ ደግሞ ጅምር ሥራቸው ባሉበት እንዲቆሙ አስግድዷቸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ ኢንዱስትሪውን እየፈተነው ነው፡፡ እያንዳንዱ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ እስካሁን ባልታየ ሁኔታ ጨምረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ በ300 እና በ400 በመቶ ዋጋቸው የጨመሩ ዕቃዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ እንደ አልሙኒየም ያሉ ምርቶች ደግሞ በአንድ ዓመት ውስጥ በ360 በመቶ ዋጋቸው ጨምረዋል፡፡ እነዚህ ምርቶች አሁንም ዋጋቸው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ባለመሆኑ ኢንዱስትሪውን በጠቅላላ ችግር ውስጥ ስለመክተቱ አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ያለው ግልጽ እውነታ እየታየ ግንባታዎችን ከአንድና ከሁለት ዓመት በፊት ለመገንባት ያስችላል ተብሎ ውል በተገባበት ዋጋ መጨረስ ፈጽሞ የማያስችል ደረጃ መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁን በአስገንቢዎችና በገንቢዎች መካከል ተፈጠሩ የተባሉ ልዩነቶችም ጎልተው እንዲታዩ ያደረጋቸው፣ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ነባር የግንባታ ሥራዎችን በቀደመ ዋጋቸው ማስጨረስ የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡  

በኢትዮጵያ ትልቁ የግንባታ ባለቤት መንግሥት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት ያስከተለው ችግር ብዙ ፕሮጀክቶች ባሉበት እንዲቆሙ አስገድዷል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ተጀምረው የነበሩ ግንባታዎች ለመታጎላቸው አንዱ ምክንያት ይኼው የዋጋ ንረት የፈጠረው ችግር ስለመሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የዲዛይን ማስተካከያ የኮንትራክተሮች አቅም ማነስ፣ በጊዜ ክፍያን አለመክፈልና የመሳሰሉት ችግሮች ለግንባታ መዘግየት ምክንያት ሊሆኑ ቢችሉም፣ አሁን እየታየ ያለው ዋና ችግር የዋጋ ንረትን ተከትሎ የመጣው የግንባታ ዋጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ነው፡፡  

የዋጋ ንረቱ የፈጠረውን ችግር በቅርብ ተከታትሎ የዋጋ ማስተካከያ ዕርምጃ ያለ መውሰዱ ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው አቶ ግርማም ሆኑ በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የምሕንድስና የግንባታ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አጠቃላይ ችግሩ ውስብስብ እየሆነ ስለመምጣቱ ያመለከቱት አቶ ግርማ፣ ችግሩ ከመንግሥት ውጪ ባሉ የግል ኩባንያዎች የሚያስገነቧቸው ፕሮጀክቶች ላይም እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ኮንትራክተሮች መጀመርያ በገቡት ውል መሠረት ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደማይችሉ በማሳወቅ ሥራውን ለማቆም የሚገደዱበት ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ በማገናዘብ የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግላቸው ባለመቻሉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

እንዲህ ያለ ችግር ከገጠማቸው ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የንብ ኢንሹራንስ ዋና መሥሪያ ቤት አንዱ ነው፡፡ በዋጋ ይስተካከልልኝና ሥራው ከተጀመረ በኋላ በተጨመረ ሥራ ዋጋ ላይ የተፈጠረ አለመግባባት ግንባታውን ሲያካሂድ የቆየው የቻይና ኮንትራክተር ሥራውን አቁሟል፡፡ ንብ ኢንሹራንስ በቅርቡ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ በ810 ሚሊዮን ብር ለማስገንባት ተዋውሎ የነበረውን የግንባታ ሥራ ተቋራጩ አሁን ካለው የግንባታ ዋጋ አንፃር በተዋዋለበት ዋጋ ግንባታውን ለመጨረስ የማይችል መሆኑን ገልጾላቸዋል፡፡ የተቋራጩን ጥያቄ የተመለከተው የኩባንያው ቦርድና ማኔጅመንት ግን የቀረበው የዋጋ ማስተካከያ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ እንዲቀንሱለት ያቀረበው ሐሳብ አዎንታዊ መልስ ባለማግኘቱና አሁንም ድረስ ስምምነት ላይ ባለመድረሱ 30 ወለል ያለው የኩባንያው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ አሁን ዘጠነኛ ወለል ላይ ደርሶ ቆሟል፡፡ የምሕንድስና ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ ችግሩን በቶሎ ያለመቋጨት ግንባታ ወጪውን በእጅጉ የሚጨምር መሆኑን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ችግር የገጠማቸው አስገንቢዎች ለረዥም ጊዜ የቆመን ግንባታ ለማስቀጠል ከዚህም በኋላ ከተቋራጮች ጋር ቢስማሙና ሥራው ቢቀጥል የግንባታ ወጪውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያንርባቸው ይሆናል ይላሉ፡፡ ለሌሎች ትልልቅ የሚባሉ ግንባታዎችም ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የግንባታ ሥራቸው  መጠናቀቂያቸው ላይ የደረሱ ፕሮጀክቶች ሳይቀሩ የዋጋ ንረቱ የፈጠረው ችግርና ተጨማሪ ክፍያ ጥያቄው ግንባታዎችን አጠናቅቆ ለማስረከብ እንቅፋት እስከመሆን ደርሷል፡፡

ያልታሰበና የተጋነነ የግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ ሲኖርና በኮንትራክተሮችና የአስገንቢ መካከል ያለ መግባባት ቢፈጠር ሥራው ቢታጎል ሊከሰቱ በሚችሉ ችግሮች ዙሪያ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ግርማ፣ ፕሮጅክቶችን አቋርጦ መልሶ ለማስጀመር ወይም የቀድሞውን ውል በማቋረጥ ለአዲስ ኮንትራክተር መስጠት እጅግ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ የግንባታ ውሉ ላይ የሰፈረው ስምምነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚመከረው ግን በስምምነት ነባራዊ ሁኔታ ላይ በመስማማት ግንታውን ማስቀጠል ነው፡፡ ውል አቋርጦ ለአዲስ ኮንትራክተር መስጠት የግንባታ ወጪውን ያንረዋል፡፡ አንዳንድ አስገንቢዎች ደግሞ ከውል ማቋረጥ ቀጥሎ የሚገጥማቸውን ችግር በማሰብ የዋጋ ማስተካከያ አድርገው ሥራውን አስቀጥለዋል፡፡

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለዚህ ምሳሌ ነው፡፡ እያስገነባ ያለውን ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በዋጋ ማስተካከያ ምክንያት ሥራውን ያቆመውን ኮንስትራክተር በማግባባትና ዋጋ አስተካክሎ ሥራውን አስቀጥሏል፡፡ ኩባንያው ከብዙ ድርድር በኋላ ግንበታውን ማስቀጠል ባይችል ኖሮ፣ ግንባታውን ለሌላ ኩባንያ መስጠት የሚያስከፍለውን በመገንዘብ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የሚፈጠር አለመግባባት የሚፈታው በውለታው ውስጥ በተደነገገ ስምምነት መሆኑን የገለጹት የምሕንድስና ባለሙያ ደግሞ፣ አንድ ኮንትራክተር አምስትና አሥር በመቶ የዋጋ ጭማሪን ተቋቁሞ ሥራውን ለመጨረስ ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ የሚደረግበት አጋጣሚዎች እንዳሉም አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን የዋጋ ጭማሪው ከዚህ በላይ ከሆነ ግን አሁን ያለውን የዋጋ ጭማሪ ተሸክሞ ሥራውን ለመቀጠል እጅግ ከባድ ይሆናል ይላሉ፡፡ እንዲህ ሲሆን የግድ የዋጋ ማካካሻው ያስፈልጋል፡፡ የዋጋ ንረቱ ግልጽ ነውና አስገንቢውም ይህንን መገንዘብ ይኖበታል፡፡ ስለዚህ የገንቢውና ያስገንቢው ስምምነትና መረዳዳት አንድ መፍትሔ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ግን ኮንትራክተሮች እየጠየቁ ያሉት ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ተከትሎ የመጣውን ልዩነት ነው፡፡ ይህ በግልጽ የሚታወቅ ከሆነ በስምምነታቸው መሠረት ማካካሻውን አድርጎ መቀጠል ለሁለቱም ወገኖች የሚጠቅም መሆኑን አቶ ግርማም ይስማሙበታል፡፡ መንግሥት የሚያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል ተብሎ ይኼ እየተሠራበት ስለመሆኑ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በወቅቱ የዋጋ ማስተካከያ አድርጎ ግንባታውን በቶሎ ማስጨረስ ካልተቻለ፣ መንግሥትንም ከፍተኛ የሚባል ወጪ የሚያስወጣው በመሆኑ፣ በተሰጠው የዋጋ ማስተካከያ ኮንትራክተሮች እየሠሩበት ነው ይላሉ፡፡ ዋጋ ንረቱ የዕቃ እጥረቱ ለሠራተኞች የሚከፈለው ክፍያ እያደገ መምጣቱን የግንባታ ወጪን አሁንም እያናረው ስለሆነ፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ዓይቶ ሥራውን የያዘው ኮንትራክተር የፕሮጀክቱን ግንባታ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ለማንኛውም ገንቢ አካል በጣም ጠቃሚ መሆኑን አቶ ግርማ ያምናሉ፡፡ ‹‹በተረፈ ግን ውል አቋርጦ ለሌላ ተጫራች ከተሰጠ አደጋው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ መንግሥትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ ይችላል፤›› በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡ የአቶ ግርማ እምነት የተናገሩት ቢሆንም አንዳንድ ፕሮጀክቶች ግን ውላቸው ተቋርጦ ለአዲስ ገንቢ እየተሰጡ መሆኑ የሚያስከትለውን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ለማየት ከሰሞኑ መንግሥት ከእያንዳንዱ ኮንትራክተሮች ነጥቆ ለሌላ የሰጣቸውን ፕሮጀክቶች አስታውሰዋል፡፡  

ያለውን ችግር ለማሳየት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያስገነባ ያለውን አንድ ፕሮጀክት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከሦስት ዓመታት በፊት አፍሮ ፂዮን ኮንስትራክሽን በ1.1 ቢሊዮን ብር ሥራውን የተረከበ ቢሆንም፣ ከጠቅላላ የግንባታ ሥራው ወደ 15 በመቶ አካባቢ ካጠናቀቀ በኋላ፣ የተወሰነ የዋጋ ማስተካከያ ጠይቆ ምላሽ በማጣቱና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የግንባታ ውሉ ይቋረጣል፡፡ የአፍሮ ጺዮን ውለታ ከተቋረጠ በኋላ፣ በቅርቡ በተደረገ ጨረታ ለሌላ ኮንትራክተር ሥራውን እንዲያጠናቅቅ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 4.5 ቢሊዮን ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በ1.3 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል፡፡ አንድ ፕሮጀክት የቀደመ ውለታው ተሰርዞ ለአዲስ ኮንትራክተር በሚሰጥበት ጊዜ የሚያስወጣው ወጪ ቀላል ያለመሆኑን ለመረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡ በዚህ አንድ ፕሮጀክት በቻ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ መጠየቁ ያለውን ችግር እንደሚያሳይ እኚሁ ያነጋገርናቸው የምሕንድስና ባለሙያ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

 እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው አንድ የግንባታ ውል አቋርጦ ለአዲስ መስጠት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መጠነኛ የዋጋ ማስተካከያ አድርጎ ሥራውን ማስቀጠል ያለመቻል ራሱ በግንባታ ሒደቶች ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑን ነው፡፡

አቶ ግርማ እንደገለጹት፣ በወቅቱ በቶሎ ማስተካከያ አለመደረጉና ግንባታውን አንድና ሁለት ዓመታት ማዘግየት ወይም ባለመግባባት ሥራ ውል አቋርጦ ለሌላ መስጠት እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም ብዙ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ችግር ሲቆሙ በቀጣይ የሚጠብቃቸው እጅግ የተጋነነ ዋጋ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ችላ ሊባሉ እንደማይገባም ይመክራሉ፡፡ በተለይ ውል አቋርጦ ሥራን ለሌላ መስጠት የፕሮጀክቱን ወጪ ሁለትና ሦስት እጥፍ፣ አንዳንዴም ከዚያም በላይ ሊሰቅለው የሚችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለውን ችግር ሊያስቆም የሚያስችል ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ባደረጉት ግፊት የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል በተወሰኑ የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ማካካሻ እንዲደረግ ተወስኖ ይህ እንዲተገበር እየተደረገ መሆኑን ከአቶ ግርማ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በመልካም የሚታይ ሲሆን፣ የዋጋ ማካካሻው የሚደረገውም ከየካቲት 2013 ዓ.ም. በፊት ውል ተገብቶላቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ከተጨማሪው ወጪ ግን መንግሥት 60 በመቶውን፣ ኮንትራክተሩ 40 በመቶውን በመሸፈን ሥራው እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  

አራትና ስድስት ዓመት የቆዩ ያላለቁ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ ግርማ፣ የዋጋ ማካካሻውን በአግባቡ ለመተግበር ግን አስቸጋሪ ነገሮች የሚያጋጥሙ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ሆኖም የዋጋ ማካካሻው እስከ ጉድለቱም እየተሠራበት ነው፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት ኮንትራክተር ግን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግንባታዎችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን የዋጋ ማካካሻን በተመለከቱ እየተወሰነዱ ያሉ ዕርምጃዎች በችግሮች የታጨቁ ናቸው ይላሉ፡፡ አሁን ትልቁ ችግር ያለው መንግሥት ጋ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ መንግሥት የፈለገውን ፕሮጀክት ይነጥቃል፡፡ ለፈለገው ፕሮጀክት ደግሞ የዋጋ ማካካሻ ይከፍላል፡፡ የፈለገውን ፕሮጀክት ደግሞ ፕራይስ ሪቫይዝ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ማካካሻ ተደርጓል ይባል እንጂ ወጥ የሆነ አሠራር እንዳለ የሚያመለክት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ በጅምር ያሉ ፕሮጀክቶች በጊዜ እንዳይጠናቀቁ ከማድረጉም በላይ ከፍተኛ የሆነ ወጪ እንዲያወጣባቸው እያስገደደ ነው፡፡

የዋጋ ማካካሻው በቶሎ አለመፈቀዱ ወጪውን ማናሩ ሳያንስ ግልጽ የሆነ አሠራር ባለመኖሩ ችግሩን ማባባሱን ያመለክታሉ፡፡  አሁን እየተደረገ ያለው የዋጋ ማካካሻ (ፕራይስ ስካሌሽን) ራሱ ብዙ የግንባታ ግብዓቶችን የሚሸፍን ስላልሆነ የግዴታ የግንባታ ስምምነት ክለሳ መደረግ እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ለምሳሌ የሠራተኞች ክፍያ፣ አሸዋና የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ ዋጋቸው ጨምሮ ሳለ በዋጋ ማካካሻው ውስጥ የማይገቡ በመሆኑ፣ አሁን ለተወሰኑ ምርቶች የተሰጠው ማካካሻ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ብለው ያምናሉ፡፡  

የዋጋ ማካካሻው (ፕራይስ ስካሌሽን) እየታሰበላቸው የሚገኙ ምርቶች ብረት፣ ሲሚንቶ፣ ናፍጣና የሴራሚክ ምርቶች መሆናቸውን የሚገልጹት እኚሁ ኮንትራክተር፣ እነዚህ ምርቶች ደግሞ ለፕሮጀክቱን ከ30 በመቶ በላይ ሽፋን የላቸውም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የተጀመሩ ሕንፃዎች ብዙዎቹ ስትራክቸር ስላለቀ የብረት ማካካሻ ሳይከፈላቸው የሚቀር በመሆኑ ማካካሻውን የይስሙላ ያደርገዋል በማለት ይሞግታሉ፡፡  

ስለዚህ ማካካሻው ብዙ ኮንትራክተሩን የሚያግዝ ስላልሆነ መንግሥት ወጥ የሆነና በመርህ የታገዘ አዲስ አሠራር ቢዘረጋ ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ የዋጋ ማካካሻው በቂ አይደለም በሚለው የኮንትራክተሩ ሙግት ላይ አቶ ግርማ ከየካቲት 2013 ዓ.ም. በፊት ውለታ ለተገባላቸው የግንባታ ፕሮደክቶች ላይ የማካካሻ ፎርሙላው መሠረት እየተሠራበት መሆኑን ገልጸው፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ የሚወሰድ ከሆነ፣ ፎርሙላው የሚፈለገውን ነገር ሊያስገኝ ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡

በመንግሥት በኩል በብሔራዊ ደረጃ ለሁሉም የሚሆን የዋጋ ማስተካከያ ሊወጣ ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸው ኮንትራክተሩ፣ ኢንፍሌሽኑም ሆነ ዲቫሉዌሽኑ የሚታይ ነገር ስለሆነ፣ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሁሉንም በእኩል የሚያይ አሠራር የማይዘረጋ ከሆነ፣ አሁን እየታየ ያለው ችግር ይቀጥላል የሚል ሥጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ ያስከተለውን ችግርና ኮንትራክተሮች የጀመሩትን ሥራ ከመቀጠል እስካሁን የከሰርኩት ይበቃል ወደሚል መደምደሚያ የሚሄዱት በግልጽ የሚታየውን የዋጋ ንረት ዓይቶ ተገቢው ማካካሻ ስላልተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ ነዳጅ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ25 ብር እስለ 60 ብር መግባቱ፣ ወደ 300 በመቶ ዋጋ ልዩነት መኖሩን ያሳያል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከሦስት እስከ 5 ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረ አሸዋ 20 ሺሕ ብር መግባቱ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ አንድ ገልባጭ መኪና አሸዋ ከዓመት በፊት 12 ሺሕ  ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከ30 እስከ 35 ሺሕ ብር መግባቱ፣ እንዲሁም ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ ሁለት ሺሕ ብር እየተሸጠ ባለበት ሁኔታ ለተወሰኑ ምርቶች ማካካሻ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም ብለዋል፡፡

ስለዚህ አሁን ኮንትራክተሮቹ እያነሱ ያሉትን ጥያቄ መንግሥት በቅጡ ሊያየው እንደሚገባ የሚያምኑት እኚሁ ኮንትራክተር፣ ለዚህም ራሱን የቻለ አንድ ታክስ ፎርስ መቋቋም አለበት ይላሉ፡፡ በተለይ ትልልቅ የቆሙ ፐሮጀክቶችን ለማስቀጠል የተፈረሙ የግንባታ ውሎችን ብቻ መሠረት በማድረግ ሳይሆን፣ ያለውን ችግር በማየት ሥራው እንዲቀጥል መነጋገር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ተግባብቶና ተስማምቶ መሥራት የማይቻል ከሆነ ግን ሁሉንም ወገን እንደሚጎዳ ፕሮጀክቶቹም ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንዲያመዝን ያደርጋል፡፡

ከወቅታዊው ችግር አንፃር አንድ አገር አቀፍ ታክስ ፎርስ ይቋቋም በሚለው አመለካከት ላይ አቶ ግርማ የሚስማሙ ሲሆን፣ ይህንን ማድረግ አገርን ከውድቀት ማዳን ነው ብለውም ያምናሉ፡፡ አሁን ላይ ኮንትስትራክሽን ኢንዱስትሪው ማስታመም ሳይሆን ተገቢ ሕክምና የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የምሕንድስና ባለሙያው በበኩላቸው የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ብዙ ኮተት ያለበት በመሆኑ ይህንን ማጥራት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ሁሉ ለመፍታት ያስችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በመጀመሪያ ግን ኮንትራክተሩን እንደሌባ የማየት አመለካከት መቀየር ይኖርበታል የሚሉት የምሕንድስና ባለሙያው፣ ከዚህ በኋላ ግን ለዘለቄታው አሁን ያሉ የኮንትራት በትክክል በድጋሚ ማየትና የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግልጽ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ፕሮጀክቶች የቆሙ በመሆኑ እነዚህን ለማስጨረስ በቅንነት ማሰብና ያለውን ችግር ተገንዝቦ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠቱን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የመቆማቸው ምክንያት ደግሞ የብዙ ችግሮች ድምር ውጤት እንደሆነ የሚጠቅሡት የምሕንድስና ባለሙያው፣ ኢንዱስትሪው ባለቤት የሌላው እየመሰለ በመሆኑ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ትርምስ ለማጥራት ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል በማለት አሁን የሚታየው ችግር የዋጋ ማስተካከያ ብቻ ያለመሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች