Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት ምርትን በመሸሸግ እጥረት በሚፈጥሩ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ይውሰድ!

ዛሬም በግብይት ሥርዓታችን ውስጥ ሥር እየሰደደ ያለን አንድ ህፀፅ እናነሳለን፡፡ በአጭሩ ምርት በመሸሸግና እጥረት በመፍጠር የሚፈጸሙ ሸፍጦችን ይመለከታል፡፡

ሆን ብሎ አንድ ምርትን በመሸሸግ የሚፈጠር እጥረት የግብይት ሥርዓቱ መገለጫ ከመሆን አልፎ በአቋራጭ የበለፀገበት ተግባር ሆኗል፡፡ ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦችና ኩባንያዎች ይህንን ክፉ ተግባር በተለያየ መንገድ የሚያከናውኑት እንደሆነም ይታመናል፡፡

ምርት በመሸሸግና እጥረት በመፍጠር ገበያው እንዲወጣጠር አድርገው ከልክ በላይ ትርፍ ይዘው ኪሳቸውን ከሚሞሉበት መንገድ አንዱ ተመሳሳይ ምርቶችን የሚያመጡ አስመጪዎች ትብብር ይፈጸማል የተባለው ተግባር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ይህም ምርቱን አስመጥተው በውድድር ከመሸጥ ይልቅ ተራ በተራ ገበያውን በመያዝ ዕቃቸውን ይቸበችባሉ፡፡ በየተራ ገበያውን መያዛቸው ደግሞ በገበያ ውስጥ እጥረት የተፈጠረ በማስመሰል እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለገበያ ለመሸጥ ይረዳቸዋል፡፡

እንዲህ ያለው አደገኛ አሠራር አንዳንድ ተፈላጊ ምርቶች ዋጋቸው በየጊዜው እንዲያድግ ምክንያት ከመሆን አልፎ፣ ተገልጋዩ በአማራጭ ዋጋ አወዳድሮ የመሸመት መብቱንም እንዲነጠቅ እያደረጉት ነው፡፡

ከገበያ ሕግ ባፈነገጠ መልኩ በመቧደን ተራ በተራ ምርት በማስገባት ገበያውን በሞኖፖል መያዛቸው የሚነገርላቸው አስመጪዎች፣ አንዱ የያዘውን ሸጦ እስኪጨርስ ተመሳሳይ ምርት ጉምሩክ ቢደርስ እንኳን ወደ ገበያ እንዳይሠራጭ በማድረግ የምርት እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋሉ እየተባለ ነው፡፡ 

አንዳንድ ምርቶች ከገበያ ዋጋ በላይ የሚሸጡትና እጥረት ተፈጠረ ከሚባልበት ምክንያት አንዱ፣ ይኸው በመቧደን የሚፈጸም እጅግ አደገኛ አሠራር ነው፡፡

እንዲህ ባለው ክፉ ምግባር ተሳስረው እየሠሩ ያሉ ተጓዳኞች ድርጊታቸውን ከውንብድና ጋር የሚያያይዘው ሌላው መገለጫ ደግሞ፣ በእነርሱ ከሚያስመጡት ምርት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምርት የሚያስመጣ ነጋዴ ወይም አስመጪ ካለ፣ በዚያ ቢዝነስ እንዳይገፋ የሚያደርጉበት መንገድ አላቸውም ይባላል፡፡ ገበያውን በሞኖፖል ይዘው ዋጋ እንደፈለጉ በመተመን የሚያገኙትን ጥቅም ላለማስነካት በእነርሱ ቢዝነስ ውስጥ ለመግባት መሞከር ለኪሳራ ሊዳርግ ይችላል፡፡ ወይም ኪሣራ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በግፍ ያሰባሰቡትን ገንዘብ በመርጨት ጭምር ዓላማቸውን ያሳካሉ፡፡

አንድ ምርት ወደ አገር ለማስመጣት የመጀመርያው የሆነ አንድ አዲስ አስመጪ ገጠመኝ ብሎ ያጫወተኝ ነገር፣ ሕገወጥ ሥራው ስለመኖሩ ማረጋገጫ ሆኖልኛል፡፡ አንዳንድ ቢዝነሶች ወይም የተወሰኑ ምርቶች ገበያ በጥቂቶች ብቻ የተያዙ መሆናቸውንም እንድረዳ አድርጎኛል፡፡ አዲሱ አስመጪ በቀላሉ በጥሩ ትርፍ ይሸጣል ያለውን ዕቃ አምጥቶ ለመሸጥ ያየው ፍዳ በእነዚህ ተጓዳኞች በተፈጸመ ደባ መሆኑንም አጫውቶኛል፡፡

ስለዚህ የአገራችን የግበይት ሥርዓት እንዲህ ያለውንም አደገኛ አካሄድ እየተለማመደ ብቻ ሳይሆን በተግባር እያሳየ ነው፡፡ አንዳንድ ምርቶች በገበያ ዋጋ ለመሸጥ ወይም የተመጠነ ትርፍ ይዞ ሸማቹን ለመታደግ የሚሻ ቢኖር እንኳን፣ ጡንቸኛ ‹‹አስመጪዎች›› አያፈናፍኑንም ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች በእኛ ሥራ አትግቡ እኛ ብቻ እንሽጥ ሳይሆን እንዝረፍ የሚሉ በዝምታ የሚታለፉ ከሆነ፣ ሕገወጥነት ነገሠ ማለት አይደል? የድርጊቱን ሕገወጥነት ተገንዝቦ መፍትሔ ካልተበጀለት ሥርዓት ያለው ግብይት መፍጠር ዘበት ይሆናል፡፡

የምርት እጥረት በመፍጠር የሚፈጸሙ ሸፍጦች ብዙ ናቸው፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ በተዋረድ የሚፈጽማቸውም ናቸው፡፡ ከትላልቆቹ አስመጪዎች ሌላ መለስተኛ አከፋፋዮች ደግሞ አንድን ምርት ሆን ብለው ሸሽገው እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ፣ በአቅማቸው ያልተገባ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ በቀናት ልዩነት ዋጋ ይጨምራሉ፡፡

ስለዚህ የዚህ አገር የገበያ ችግር ሰው ሠራሽና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው ነው የሚባልበቱ አንዱ ምክንያት፣ በእጅ ያለ ምርትን ሆን ብለው ሸሽገው በማቆየት እጥረት እንዳለ አስመስሎ ገበያውን ማወጣጠር ነው፡፡

የሲሚንቶ ገበያ ጉዳይም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ሲሚንቶ ገበያ በኔትወርክ በተሳሰሩ አካላት የሚፈጸም ነው፡፡ እጥረቱም በዚህ በቡድን ከሚፈጸም ምዝበራ ጋር ይያያዛል፡፡

መንግሥት የሲሚንቶን ገበያ ለማስተካከል ነጋ ጠባ ማስተካከያዎችንና ዕርምጃዎችን ወስጃለሁ እያለ የሚያወርደው መመርያና የማሳሰቢያ ጋጋታ አልሰምር ያለው ደካማ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ኔትዎርክ መበጣጠስ ስላቃተው ነው፡፡

የችግሩን ሥረ መሠረት አውቆ መፍትሔ ለማበጀት ከልብ ያለመሥራቱ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ከፋብሪካ 800 ባልሞላ ብር የሚወጣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ በጥቁር ገበያ እስከ 2,300 ብር የመሸጡ ሚስጥር ገበያውን የሚመጥን ምርት ባለመቅረቡ ብቻ አይደለም፡፡ ይህን ገበያ ለመቆጣጠር የተቧደኑ አካላት የሚፈጥሩት ሸፍጥ ነው፡፡ በጥቁር ገበያ እንደ ልብ የሚሸጠው እነዚህ ገበያውን የያዙት አካላት ምርቱን የሸሸጉበት ቦታ እየታወቀ ዕርምጃ ያለመወሰዱም ጭምር ነው፡፡ በሲሚንቶ ገበያ ደላሎች፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች በኔትወርክ ተሳስርው የሚዘውሩት መሆኑና ባለሥልጣናትም የዚህ የጥቁር ገበያው ተዋንያኖች ስለመሆናቸው ጠቋሚ እውነቶችንም እየታዩ ነው፡፡ ከሰሞኑ በሕገወጥ የሲሚንቶ ንግድ እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪ ሹመኞች ስለመያዛቸው መስማታችን አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ አልማዝ በፍለጋ በውድ ዋጋ እየተቸበቸ ባለው የሲሚንቶ የጥቁር ገበያ ውስጥ ሕግ እጅ ላይ የወደቁት ሹመኞች ከሰሞኑ ተያዙ የተባሉት ብቻ ናቸው አንልም፡፡ የፀጥታ አካላትም ተሸሽገው በጥቁር ገበያ የሚሠሩ ተዋንያኖችና የተሸሸገውን ምርት ዓይቶ እንዳላዩ የመሆናቸው ሚስጥር የዚሁ የሕገወጥ ንግድ እጃቸው ቢኖር አይደል?

በዚህ ገበያ ሌላው እጥረት እንዲፈጠርና የሲሚንቶ ዋጋን ያናረው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች እያመረቱ መሆኑ ነው፡፡ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች የሚያመርቱት ለምንድነው? ብሎ ለጠየቀ እውነታውን ያገኛል፡፡

ነገር ግን ለፋብሪካዎቹ ከአቅም በታች ማምረት የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረትና መሰል ሰበቦች ይቀርባሉ፡፡ ከአቅም በታች የማምረቱ ሚስጥር በኔትወርክ የተያያዘው የሲሚንቶ ገበያ ስላለ መሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ፡፡ ስለዚህ የምርት እጥረትና ከአቅም በታች ማምረት ምርትን ከመሸሸግ የተናነሰ አይሆንም፡፡

ገበያ ውስጥ ያለ ችግር መሸጥ የሚችልና ከፍተኛ እጥረት ያለበትን ምርት በሙሉ አቅም ያለማምረት ጤነኛ ነው ተብሎ ስለማይታሰብ ይህንን ጉዳይ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ ሸፍጦች መኖራቸውን አያውቅም አይባልም፡፡ አንዳንድ ሹመኞችም የዚህ አደገኛ ጨዋታ አካል መሆኑንም በሚገባ ያውቃል፡፡ የሌብነት ስልቱ በየጊዜው የሚቀያየር ቢሆንም የአገሪቱን የዋጋ ንረት ወደላይ ከሰቀሉት ምክንያቶች መካከል እንዲህ ያሉ ሸፍጦች ጭምር መሆናቸውን ማወቅ ይገባል፡፡

ከአቅም በታች ለማምረታቸው አሳማኝ ምክንያት ካለ ይህንን ዓይ’ቶ መፍትሔ መስጠት ቢያስፈልግም አንዳንድ ሁኔታዎች ግን ድርጊቱ ሆን ተብሎ የሚፈጸም መሆኑን ስለሚያመላክቱ ጉዳዩን ጠለቅ ብሎ ማየት ለመፍትሔ ይበጃል፡፡

ስለዚህ ተቧድነው ዋጋ የሚወስኑ አካላት ተገልጋዮች ላይ እየፈጠሩ ያሉት ተፅዕኖዎች እየበዙ ነው፡፡ ድርጊቱ እንደ አገር ከታሰበ አደገኛም ነው፡፡ እንደ ሸማች ደግሞ አንድን ምርት አማርጦ በተሻለ ዋጋ ለመግዛት ያለውን መብት እያሳጡ ነውና መንግሥት ሆይ ከሰማህ እንዲህ ያለም ነገር አለና ዓይንህን ግለጥ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት