Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ላወጣነው ሕግ ተገዥ ካልሆንን በስተቀር ፓርላሜንታዊም ሆነ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በመከተል የተለየ ነገር አይኖርም›› ዘሪሁን ሞሐመድ (ዶ/ር)፣ የጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ ፣ የምስራቃዊ አፍሪካ ቢሮ ኃላፊ

ጉድ ገቨርናንስ አፍሪካ (መልካም አስተዳደር በአፍሪካ) የተሰኘው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2012 በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የተመሠረተ ሲሆን፣ ተቋሙ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ላይ በመልካም አስተዳደር ላይ ይሠራል፡፡ ይህ ተቋም በኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ቢሮውን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘውን ይህ ተቋም በበላይነት የሚመሩት ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሒዩማን ጆግራፊ የዶክትሬት ተመራቂ የሆኑትና በዘርፉ በርካታ ልምዶችን ያበረከቱት ዘሪሁን ሞሐመድ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ይህ ተቋም በሚሠራቸውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- መልካም አስተዳደር በአፍሪካ የተባለው ተቋም መቼ ተቋቋመ? ምን ዓላማ አንግቦ ተነሳ?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ ሲቋቋም መነሻው በአብዛኛው የአፍሪካ ችግሮች ኢኮኖሚያዊ ይሁን ማኅበራዊ ችግሮች ከመልካም አስተዳደር የመነጩ በመሆናቸው፣ እነዚህን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ብንፈታ አብዛኛውን መሠረታዊ ችግር ማቅለል ይቻላል የሚል ዕሳቤ ይዘን ነው፡፡ የመጀመሪያ ቢሮውን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ አድርጎ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ እንግዲህ አፍሪካ ውስጥ ያሉ አገሮች ችግሮቻቸው የተለያዩ በመሆናቸው፣ ለሁሉም ተመሳሳይ መፍትሔ መስጠት አዳጋች ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ለመሥራትና ለአሠራርም እንዲያመች በሚል፣ የተለያዩ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ እንዳልኩህ የመጀመሪያውን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ፣ በምዕራብ አፍሪካ በጋና አክራ ቢሮ ከፈተ፡፡ በሌላ በኩል ናይጄሪያ ትልቅ አገር በመሆኑና ብዙ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ስለሆነ፣ እዚያም ቢሮ ተከፍቷል፡፡ በመቀጠል በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ቢሮ እንዲከፈት ፈቀዱ፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ እንዲከፈት ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ በአገሪቱ ሲካሄድ በነበሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና ዴሞክራሲ ለመፈንጠቅ የነበረውን ተስፋ በማየት ነው፡፡ በተለይም የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት አፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ብዛትና ሥራ በመመልከት፣ በአዲስ አበባ ቢከፈት የተሻለ ነው በሚል እዚህ ተከፍቶ እንቅስቃሴውን እ.ኤ.አ. በ2020 ጀመረ፡፡ ዋና ተቋሙ መዳረሻውን መልካም አስተዳደሮች አድርጎ ይሠራል፡፡ ይህንን ሥራ ስንሠራ በጥናትና ምርምር አዳዲስ ዕውቀቶችን በመፍጠርና በማሠራጨት፣ እንዲሁም የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት በተለይ ቀና አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ ውይይትና ባህል እንዲዳብር ብለን ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙን እነማን መሠረቱት?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– ይህ ድርጅት በትንሽ በጎ አሳቢ ግለሰቦች ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው የተመሠረተው፡፡ የተወሰኑት ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በቦርድ ይመራል፡፡ ቦርዱ ውስጥ ከግሉ ዘርፍ መምህራንና ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተውጣጡ አካላት ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡– የፋይናንስ ምንጫችሁ ምንድነው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– በአብዛኛው አሁን ባለንበት ሁኔታ እኛ ገቢ ማመንጨት አልጀመርንም፡፡ ነገር ግን ዋና ተቋሙ ከሚያሰባስበው ገቢ በሚሰጠን ገንዘብ ላይ ተመሥርተን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የገቢ ምንጭ የሚሆኑ የጥናት ጽሑፎችን በማዘጋጀት ራሳችንን እንደግፋለን፡፡

ሪፖርተር፡–  ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ምን ሠራችሁ?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– እንዳልኩህ እ.ኤ.አ. በ2020 ነው በሲቪክ ማኅበራት ባለሥልጣን ተመዝግበን ሰርተፍኬት አግኝተን መንቀሳቀስ የጀመርነው፡፡ እንግዲህ ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተከሰተበት ስለነበር ሠራተኛ መቅጠር አልቻልንም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያው ዓመት ኮቪድ-19 ላይ ያጠነጠነ የሕዝብ ውይይት አካሂደናል፡፡ በተለይም ኮቪድ-19 ያስከተላቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ እንደ አገር የተከተልነው ፖሊሲ ያመጣቸውን ውጤት የሚዳስሱ አራት ተከታታይ የውይይት መድረኮች አዘጋጅተን ነበር፡፡ በጤናው ዘርፍ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበን በጊዜው የነበረው የጤና ሁኔታ፣ እንዲሁም ኮቪድ-19 ያስከተለው ምንድነው? መንግሥት ምን ዕርምጃ ሊወስድ ይገባዋል? የሚሉትን ዓይተናል፡፡ በተመሳሳይ በማኅበራዊ ዘርፍ ላይ ኮቪድ-19 ያስከተላቸው ችግሮችና ልንከተለው የሚገባ የፖሊሲ አማራጭ እንዲሁ በጥናቱ ዳሰናል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያስ ምን ጉዳት አደረሰ የሚሉትን ዳሰን መጨረሻ ላይ ጽሑፎችን በሚዲያ እንዲሠራጩ አድርገናል፡፡ ቆይተንም በኅትመት ለሚመለከታቸው አካላት አድርሰናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ሥራችን ያተኩር የነበረው በአገራዊ ምርጫ ላይ ነበር፡፡ ይህ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን በሚል በተከታታይ ገዥው ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና ሌሎች አካላትም የተሳተፉበት የፓናል ውይይት አድርገናል፡፡ በተለይም የምርጫ ሕግን በተመለከተ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ሁኔታ በመዳሰስ፣ ከምርጫ ቦርድና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በመመካከር ይሆናሉ በተባሉ ርዕሶች ላይ ውይይቶችን አካሂደናል፡፡ ሌላው የሠራነው ምርጫና ሚዲያ ላይ ሲሆን፣ በተለይ ሚዲያው ምን ዓይነት የሥነ ምግባር መርህ መከተል ይኖርበታል? ሚዲያው ራሱ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች ምን ይጠብቃል? ምንስ መደረግ አለበት? የሚዲያ ተቆጣጣሪው አካልስ ይህ ምርጫ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን በሚል የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡

ሌላው የነበረው የሲቪክ ማኅበራት ሚና በምርጫው ምን ሊሆን ይገባል ነው፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ጭምር በተገኙበት ውይይቶችን አካሂደናል፡፡ በመጨረሻ ምርጫና ወጣቶች በሚል ያካሄድነው ውይይት ነው፡፡ በዚህም እንደምታውቀው ወጣቱ በአንድ በኩል ይወቀሳል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በምርጫው የወጣቱ ቁጥር ከፍተኛ እንደ መሆኑ መጠን ተሳተፎ ላይ ወሳኝ ውይይት አድርገናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በጊዜው የነበረው ብዥታ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምርጫው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለው ነው፡፡ በተለይም ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ ምሁራን የተሳተፉበት ነበር፡፡ በተቻለ መጠን ለአንድ ወገን ያላደላና ሚዛናዊ የሆነ ጥሩ ውይይት አድርገን ነበር፡፡ በዚህም የምርጫው ግልጽነት እንዲጨምር የበኩላችንን ተሳትፎ አድርገናል፡፡ ከዚያ በኋላም የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ አዲሱ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ፣ ከአዲሱ መንግሥት ምን እንደሚጠበቅና የምርጫ ኃላፊነት በሚሉ ርዕሶች ተከታታይ ውይይት አካሂደናል፡፡ በተለይም በምርጫ ቃል ገብቶ ያሸነፈው አካል፣ የገባውን ቃል በምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጽማል በሚል በመጀመሪያ ላይ እናያለን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ታወጀ በእርግጥ ይህ አዋጅ ይህንን ውይይት እንድናደርግ አይከለክለንም፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን ትንሽ ስሜት በተሟሟቀበትና ጥሩ መንፈስ ባልሰፈነበት ሁኔታ ምን ያህል ሚዛናዊ የሆነ ውይይት ማድረግ አጠያያቂ ስለነበር ቀኑን አዛውረናል፡፡ በየካቲት 2014 ዓ.ም. አዳዲስ ርዕሰ ጉዳዮች በተለይም ሰላምና መረጋጋት ላይ ምን መደረግ አለበት በሚልና አገራዊ መግባባትን እንዴት መፍጠር እንችላለን? ከየትስ መጀመር አለበት? በሚል በምሁራን የመነሻ ጽሑፍ ተነስተን ውይይት አካሂደናል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የታችኛው የመንግሥት እርከን ላይ ያሉ አሠራሮችን እንዴት ማስተካከል ይቻላል የሚል፣ በተለይም አሁን ካየህ በአብዛኛው ትልቁ የመልካም አስተዳዳር ችግር ምንጭ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ነው፡፡ ከቀበሌ መታወቂያ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ኅብረተሰቡ የሚያገኘው የታችኛው የአስተዳዳር እርከን ላይ በመሆኑ፣ ቅሬታ የሚመጣውም በእዚህ አካል ላይ በመሆኑ ምን ዓይነት ቅሬታ በምን ዓይነት መልክ መስተካከል አለበት የሚል የጥናት ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የመጨረሻው የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ያለው ጉዳይና አስተሳሳብ ምን መደረግ አለበት በሚል የጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት፣ መጨረሻ ላይ እነዚህ የጥናታዊ ጽሑፎቹ ታትመው ለኅብረተሰቡ እንዲደርሱ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በዚህ ዓመት በተለይም ከመልካም አስተዳዳር ጋር ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ብዙ ጊዜ በጣም ያልተማከለ የአስተዳዳር አወቃቀርን የተሻለ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያልተማከለ አስተዳዳር ለሥርዓት አልበኝነት የሚያጋልጥ ነው ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ የአገራችን የአስተዳደር አወቃቀሮችን ስንመለከት የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያልተማከ አወቃቀርና የታችኛው የመንግሥት እርከን ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ምን መልክ አለው የሚለውን የሱዳንን፣ የኢትዮጵያን፣ የሩዋንዳን፣ የኬንያንና የኡጋንዳን ልምድ በመውሰድ ከእነዚህ አገሮች በተወጣጡ ባለሙያዎች የጥናት ጽሑፍ በማዘጋጀት ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡ የዚህም ውይይት ውጤት ታትሞ እንዲቀርብ እየሠራን ነው፡፡ ይህም የጥናት ጽሑፍ የታችኛው የመግሥት እርከን ላይ ያለውን አሠራር አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ብለን እናስባለን፡፡  

ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ በታችኛው የመንግሥት እርከን ውስጥ መልካም አስተዳዳርን ጠንካራ አድርጎ ማስቀጠል የሚቻለው እንዴት ነው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– የታችኛው የመንግሥት እርከን የመንግሥት ፊት ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ መንግሥትን የሚያገኘው ቀበሌ ሲሄድና አገልግሎት ሲፈልግ በሚሄድበት ወቅት እንጂ፣ የላይኛው እርከን ላይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብና የመንግሥት ግንኙነት የሚካሄደው እዚህኛው እርከን ላይ ነው፡፡ በመሆኑም እዚህ ቦታ ላይ የሚሰጠው አገልግሎት ጤናማ ካልሆነ የመንግሥተና የዜጎች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፣ የመንሥትና የዜጎች ግንኙነትን ያበላሻል፡፡ ስለዚህ ይህንን እንዴት እናስተዳድር ሲባል ተቋማዊ አወቃቀር ራሱን የቻለ ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የታችኛው የመንግሥት እርከን በራሱ የቆመ አይደለም፡፡ ከላይ ጀምሮ የወረደ ነው፡፡ በአሠራር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ስለታችኛው የአስተዳዳር እርከን ስናወራ የላይኛውን ትተነው የምንሄደው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያልተማከ አስተዳደር ምንድነው? ጥቅሙና ጉዳቱ? የተማከለውስ የቱ ላይ ነው? ጉድለቱ? የሚሉትን? በጥናቶቻችን ዳሰናል፡፡

ሪፖርተር፡– የታችኛው የመንግሥት አወቃቀር ችግር ከሥርዓተ መንግሥት ጋር የሚኖረው ቁርኝትና በተለያዩ ጊዜያት ፈርሶ የመሠራት ጉዳይ እንዴት ሊስተካከል ይችላል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– የተረጋጋ ተቋማዊ ቁመና በጣም ወሳኝነት አለው፡፡ በአወቃቀራቸው ቀበሌን ከወረዳ፣ ወረዳን ከክፍለ ከተማ ለይተን ማየት አንችልም፣ የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህን ልታስተካክለው የምትችለው ከላይ ወደታች በሚወርደው አሠራር መሠረት ነው፡፡ ከላይ የተዘጋጀውን የአገልግሎት ዕቅድ ልታስፈጽም የምትችለው ምን ዓይነት ሲስትም ዘርግተናል? ምን ያህል የሰው ኃይል አለ? በምን ዓይነት አወቃቀርስ ይወርዳል? ምን ዓይነት የተጠያቂነት ሥርዓት ተዘርግቷል? በሚሉ ነው፡፡ በተገቢው ጥራት ደግሞ ካልቀረበ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር የምትቆጣጠርበት ሥርዓት በመዘርጋት፣ ተጠቃሚው የሚደርስበትን የአገልግሎት በደል በተመለከተ ቅሬታ የሚያቀርብበት የተዋረድ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ በታችኛው እርከን ላይ በሚሰጡ አገልግሎቶች የሚነሳው ቅሬታ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ችግሮቹ ሊከሰቱ የቻሉባቸው ምክንያቶች ከአቅም አንስቶ የፖለቲካውን ጉዳይ ጨምሮ ብዙ የሚዘረዘሩ ጉዳዮች አሉበት፡፡ አንዳንዶቹ  ሰፋ ያለ ጥናትም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ግን መናገር የምችለው የታችኛው እርከን ላይ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት አስደሳች ነው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡– የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙና የተዘረጋው የፖለቲካ ምኅዳር ከታችኛው የመንግሥት እርከን ጋር ያለውን ቁርኝት እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– ርዕዮተ ዓለም የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሚሰጠው አገልግሎት ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከኢሕአደግ በፊት በነበሩ ጊዜያት የነበረውን ስታይ አሀዳዊ የሆነና ከላይ ወደ ታች የሚፈስ፣ በጣም በሚባል ደረጃ ማዕከል ላይ ሥልጣን የታቆረበትና ከላይ ወደ ታች ትዕዛዝ የሚወርድበት፣ ግን ደግሞ ከታች ወደ ላይ ሪፖርት የሚፈስበት ሥርዓት ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ግን ያልተማከለ የፖለቲካ አደረጃጀት ነው እየተከተልን የመጣነው፡፡ እያንዳንዱ ሥርዓት በራሱ አደረጃጀት ላይ ጥያቄ የለውም፡፡ በርዕዮተ ዓለም ደረጀ ይኼ ያልተማከለ የፖለቲካ አደረጃጀት ከታችኛው የመንግሥት አደረጃጀት አንዱ ከአንዱ ጥሩ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ብዙም የሚያስኬድ የመከራከሪያ ነጥብ አይደለም፡፡ ከዚህ በተሻለ ጥሩ የሚሆነው ባለውና በተቀበልነው የፖለቱካ አደረጃጀት ውስጥ ምን ዓይነት ተቋምና ሲስተም ዘርግተናል? ተቋማቱንም በምን ዓይነት አዋቅረናል? የሚለውና እነዚህ ውስጥ ደገሞ ተጠያቂነትን ምን ያህል አስፍነናል? እንዴትስ ክትትል ይደረግበታል? የሚለው ጉዳይ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ የምትከተለው የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ቀርቶ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት መከተልን የተሻለ አድርገው የሚወስዱ ስላሉ እርስዎ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– እዚህ ላይ ፕሬዚዳንታዊ ወይም ፓርላሜንታዊ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ አይደደለም፣ አንዱን ከአንዱ ጋር ማወዳዳር ይከብዳል፡፡ እንደ የአገሮቹ ሁኔታ ነው የሚወሰነውና የሚመረጠው፡፡ ነገር ግን ያም ሆኖ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚከተሉ፣ ነገር ግን ቅልጥ ያሉ ፈላጭ ቆራጭ አገሮች ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡ በዚያው ልክ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚከተሉ ጥሩና ይበል የሚያስብል የዴሞክራሲ ሥርዓት ያላቸው አገሮች አሉ፡፡ በተመሳሳይ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት እየተከተሉ ጥሩ የሚባል የፓርላሜንታዊ ሲስተም ያላቸው አገሮችም አሉ፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንታዊ ወይም ፓርላሜንታዊ መሆን በራሱ የሚያመጣው ነገር አይኖርም፡፡ ዋናው ነገር እኛ እነዚህን ሲስተሞች የምንፈጽምባቸው መንገዶች ናቸው ወሳኝ የሚሆኑት፡፡ በእኛ አገር ችግር አለብን፡፡ የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የፉክክር አቅምና የፓርቲዎችን በሳልነት በምርጫ ጊዜ በሚያደርጉት ክርክር የታጠቁት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ያላቸው ፕሮግራም የነጠረ ነው የሚለውን በማየት የሚፈጠረው ፓርላማ የሚሰጠንን የመጨረሻ ውጤት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ አባላት የበላይነት ሲያዝ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጠር ግልጽ ነው፡፡ ፓርላማው የተለያዩ ሐሳብ ያላቸው የፓርቲዎች ስብስብ ሲሆን የተሻለ ይሆናል፡፡

ምክንያቱም በሐሳቦች መካከል የነበረውን ለይቶ ማውጣት ስለሚቻል ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ፓርላማው አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችለው አቅም ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን የአንድ ፓርቲ ሰዎች ብቻ ካሉበት በተመሳሳይ የፖለቲካ ዓላማና ዝንባሌ በአንድ ዓይነት ዕሳቤ ተመርጠው ይገባሉ፡፡ ያኔ አስፈጻሚው ከዚያው ነው የሚመረጠው በመጨረሻ ፓርቲና የመንግሥት ሰዎች ተመሳሳይ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፓርቲ ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ ይህንን ማስተካከል የሚቻለው የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲጠነክሩ በማድረግ ነው፡፡ የተሻሉ ተፎካካሪዎች ወደ ፓርላማው እንዲገቡ በማድረግ የፓርቲ ልውውጥ ስትፈጥርና በማስፋት ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ አስፈጻሚውና ፓርቲው አንድ ዓይነት መሆናቸው ይቀርና ፓርላማው ውስጥ የብዙ ሐሳቦች ስብጥር ይኖራል፡፡ ላወጣነው ሕግ ተገዥ ካልሆንን በስተቀር ፓርላሜንታዊም ሆነ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በመከተል የሚመጣ የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ በምንከተለው ሥርዓት ብቻ የሚመጣ የተለየ ተዓምር አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል ያለውን የእርስ በርስ ተጠያቂነትና ቁጥጥር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡- በሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል ያለውን ቁጥጥር በተመለከተ፣ አሁን ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ አንዳንድ ለውጦችን በተወሰነ ዓይተናል፡፡ ፓርላማውንም በተወሰነ ደረጃ የተሻለ አወቃቀር እንዳለው ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በሒደት ያለ ነው፡፡ ምናልባት አሁን ያሳለፍነው ምርጫ  በተወሰነ ደረጃ ግልጽና ፍትሐዊ ነው ተብሎ የሚነሳለት የመጀመርያው ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመርያ ምርጫ ላይ ተዓምር መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ የአሁኑ ፓርላማ በአንድ ፓርቲ የበላይነት የተያዘ ነው፡፡ ያ ማለት ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዘው የገቡ ናቸው ማለት ነው፡፡ አስፈጻሚውም ከዚያ ፓርቲ የወጣ ነው፡፡ ስለዚህ የፓርቲው ሊቀመንበር የፓርላማው አለቃ ሲሆን፣ ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ እንግዲህ የመንግሥትን አወቃቀር ስንመለከት ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ ፓርቲው እንዴት ይመሠረታል? ከፓርላማው በኋላ መንግሥት እንዴት ይመሠረታል? የሚለውን ጭምር፡፡ የተመረጠ ፓርቲ ደግሞ የራሱን መንግሥት የሚመሠርትበት ሕጋዊ  የሆነ መሠረት አለው፡፡ ከዚያ መሠረት የወጣ አሠራር ካለ ግን አጠያያቂ ይሆናል፡፡ የተቋማትን ገለልተኝነትና ራሳቸውን የቻሉ ሆነው መቆምን ስትመለከት ግን፣ አንዳንዴ ገለልተኛ ሆነው መቋቋም አለባቸው የሚባሉ ተቋማትን በተመለከተ በዋናነት መታሰብ ያለበት የተቋማት ኃላፊዎችን ብቻ ሳይሆኑ፣ በተቋማቱ ያሉትን አሠራሮችና ሠራተኞች ሊመራ የሚችል ሲስተም መኖርና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ የአሠራር ሥርዓት በተዋረድ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡  

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ብልሹ አሠራርን ለመግራት የእናንተን ዓይነት ተቋም ምን ዓይነት ሚና ይጫወታል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ  የዳበረ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ የሲቪል ማኅበራት ከአገልግሎት አቅርቦትና ከዕርዳታ ጋር የተገናኘ ነው ተግባራቸው፡፡ በተለይም የዕርዳታ ሥራዎችና መንግሥት ሊደርስባቸው ያልቻሉ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ሲሯሯጡ ነው የሚታዩት፡፡ በሌላ መስኮች በተለይ ከመብት ጋር ተያይዞ ሲሠሩ የነበሩ ተቋማት በቀደመው ጊዜ በነበረው አሠራር እንዲከስሙ ተደርገዋል፡፡ አዲሱ የሲቪል ማኅበራት ሕግ እንደ አዲስ እስኪወጣ ድረስ ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ አዲሱ አዋጅ ከወጣ ወዲህ ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች እየተመለሱ ነው፡፡ በአንድ በኩል አንዳንድ ወገኖች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ባለው ሕግ መሠረት፣ መንግሥት የሚሠራቸውን የልማት ሥራዎች ማገዝ፣ መደገፍና ማስፋፋት የሚገባቸው ናቸው ይላሉ፡፡ በተለይም ከፖለቲካ ፀድተው መንቀሳቀስ አለባቸው የሚሉ አካላት አሉ፡፡ ሁለተኛው ዕሳቤ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትልቁ ሥራቸው ሕዝቡ ነው፣ በመሆኑም የሕዝቡ አፈቀላጤ ሆነው እሮሮና ስሜት የሚያንፀባርቁ መሆን አለባቸው ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ስትመለከት ለምሳሌ በጎረቤት ሱዳን የሚካሄደው የፖለቲካ ትግል ውስን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሰፊ ነው፡፡ በግንባር ቀደምትነትም እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እንደ አገሩ ሁኔታ አመለካከቱ ትንሽ ዘርዘር ያለ ነው፡፡ ለእኛ አገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቁጥር ትንሽ በልምድ ብዙም ያልተራመዱ፣ በፋይናንስም ያልተደራጁ፣ በውጭ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሆኑ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ እንቅስቃሴያቸው እንደምናስበው ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

አሁን ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የእኛ የመጀመሪያ ሥራችን ዕውቀት ማመንጨት ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ውይይትም ይሁን ክርክር በዕውቀት ላይ መመሥረትና መመርኮዝ አለበት፡፡ ዛሬ በአብዛኛው ችግራችን በቂ ዕውቀት አለመኖሩ ነው፡፡ ያለውም ዕውቀት በሚገባ ተደራጅቶ በሚፈለገው ጊዜና ቦታ የሚገኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በተለይ የገለልተኛ ምሁራዊ ተቋማት ዋነኛ ሚና ዕውቀትን ማበልፀግ ነው፡፡ ለምሳሌ የታችኛው የመንግሥት እርከን ችግር አለው ካልን ተሰባስበን ብንንጫጫ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ የሚሻለው የሚነሳው ችግር የት እንዳለ፣ ምን ዓይነት እንደሆነና ለምን እንደተፈጠረ ሊታይ በሚችልና ሊረጋገጥ በሚችል መንገድ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚያ በመቀጠል ዕውቀትን ማሠራጨት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲከኞችን እንወቅሳለን፡፡ ይህን አላደረጉም፣ ያን አላደረጉም እያልን እንወቅሳለን፡፡ እንግዲህ ይህ ሊሆን የሚችለው በመረጃ እጥረት ነው፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የሚፈለጉት ዕውቀቶች ውስን ናቸው፡፡ ኃላፊነታቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ መደረግና መሆን ያለበት ከገለልተኛ አካላት የተገኙ ዕውቀቶችን ማድረስ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በመረጃ ደተደገፈ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ አካል ሲከራከርና ሲነጋገር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ተቀምጦ መሆን አለበት፡፡ መገደብ የለብንም፣ እንቀመጥና በቅንነት እንነጋገር ማለት አለብን፡፡ ውይይቶች መከበር አለባቸው፡፡ ካለመነጋገር አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ የሲቪክ ማኅራት በማወያየትና በማስተባበር ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገዳቢው ሕግ ተነስቶላቸዋል፣ የአቅም ውስንነት ካልሆነ በስተቀር በስፋት ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት ከመልካም አስተዳደር ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– ይህ ከዴሞክራሲ ባህላችን ጋር ይገናኛል፡፡ አገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከጀመረች ምን ያህል ጊዜ ነው? በትክክለኛው መንገድ መተግበር የጀመረውስ መቼ ነው? የሚለው መታየት አበለት፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራም አቀራረፅ ላይ ምን ያህል ዕውቀት አለን? ከባህላችን ተነስተህ የፖለቲካ የውይይት ባህላችንን ስታይ ገና ነጥረን አልወጣንም፡፡ አንዱ የሚከብደን እኛ ውይይት ለማካሄደ ስናስብ የትኛውን ፓርቲ ጠርተን የትኛውን እንተው የሚል ግርታ ውስጥ እንገባለን፡፡ እንዳንዴ አድልኦ እንዳይመስልብን እንፈራለን፡፡ በምን መሥፈርት መጥራት እንዳለብን አናውቅም፡፡ ሁሉንም ፓርቲዎች ለመጥራት አቅማችን አይፈቅድም፡፡ አንዳንዶች በጣም ውስን የሆነ አባላትን የያዙ ፓርቲዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለምን እንደተቋቋሙም ግራ ይገባኛል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ የፖለቲካ ሒደቱ አክሳሪ የሚሆንባቸው ፓርቲዎች ወደ አንድ ፓርቲ መጥተው የተሻለ አቅም ይፈጥራሉ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ተስፋ የማደርገው አሁን ካለው የፖለቲካ ፓርቲ ቁጥር ያነሱ፣ ነገር ግን በአቅም የጠነከሩ ፓርቲዎች ይፈጠራሉ የሚል ነው፡፡ እኛም እንደ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት እንሠራበታለን፡፡

ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ምሁራን ችግር ፈቺ ናቸው? ወይስ ችግር ፈጣሪዎች?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– እንግዲህ ምሁር ስንል የመጀመሪያው አጨቃጫቂ ጉዳይ ማነው ምሁር የሚለው ነው፡፡ ምሁር በፒኤችዲ ወይስ በማስተርስ? ወይስ በሌላ? የሚለው ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ እንኳ ብንስማማ በትምህርት ደረጃ ከማስቀመጥ ውጪ ሌላ ብዙ የሚለያይባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የፖለቲካ አመለካከት በሳልነት ደረጃና የግል ፍላጎት እያልክ የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት ነው እንጂ፣ በአንድ ቅርጫት ሁሉንም ከተህ ምሁር ብለህ አታስባቸውም፡፡ በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ ብዙ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ ያለው ችግር አፍሪካ በብዙ ጎሳ የተከፈፋለች መሆኗ ነው ብለው የሚያነሱ አሉ፡፡ ይህን ደግሞ በተቃራኒው የሚተረጉሙት አሉ፡፡ ከቅኝ ግዛት ጋር አገናኝተው የሚተረጉሙትም አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ወስደን ግን በትልቁ የሚታዩ የአፍሪካ ችግሮች ግን ከምሁራን የሚመነጩ ናቸው የሚለው ነው፡፡ ምሁራኑ ሥልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ሩጫ፣ በተለይ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ አሉ፡፡ እንደ እምነትና ብሔርን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ከውስጥ መዞ በማውጣት፣ የተበዳይነትን ስሜት ኅብረተሰቡ ውስጥ በመክተትና በመኮርኮር ከጀርባው በኩልም ለራሳቸው የፖለቲካ ግብ እንሚጠቀሙበት የሚገልጹ ሳይንሳዊ ጽሑፎች እናያለን፡፡ ያ እንግዲህ እንደ ቦታው ይለያያል፡፡ በቦታው ያሉትና የሚታዩት ግጭቶች ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን የማንስተው ነገር የማኅበራዊ ሚዲያ መበልፀግ የእነዚህን አካላት አቅም በመጨመር ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለማየት ጥሩ መሠረት አለው በተባለው የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፖለቲከኖች በማኅበራዊ ሚዲያ ምን ያህል እንደተናነቁ በቅርቡ ዓይተናል፡፡ ይሁን እንጂ የምሁራንን ሚና መናቅ አንችልም፡፡ በጣም ጠቃሚ ሚና አላቸው፡፡ በዚያ ልክ ደግሞ ያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ያለው ቦታው ሲቀመጥ ሊያመጣ የሚችለው ቀውስ ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ የክልሎች አመሠራረትና አሁንም የቀጠለውን የክልልነት ጥያቄ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– እስከ 1983 ዓ.ም. አሀዳዊ ሥርዓት ለረዥም ጊዜ ቆይቶ የኢትዮጵያ ችግር አልፈታም፣ የኢትዮጵያ ዋናው ችግር የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔር ብሔረሰቦችን ራሳቸውን አስችለው በፌደራል ሲስተም መዋቀር አለብን በሚል መርህ ነው ሕገ መንግሥቱ የወጣው፡፡ ክልሎችም ይህንን መሠረት አድርገው ነው የተዋቀሩት፡፡ እነዚህ ክልሎች ቋንቋን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ጉዳዩ አጨቃጫቂ ነው፡፡ ዛሬ አይደለም ከድሮ ጀምሮ ሲወርድ ሊወራረድ የመጣ ነው፡፡ አንዳንዶች ብሔርተኝነቱ ተፈጥሯዊ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ብሔርተኝነት እንደ ፍላጎትና እንደ ሁኔታው ይቀየራል ይላሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስትመለከት በመርህ ደረጃ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ መሬት ስታወርደው የአተገባበሩ ጉዳይ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ማለት የብሔር ግንኙነት ወይስ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ነው የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ቦታ ስንሄድ ሁለቱንም ማንነቶች የያዙ አሉ፡፡ ለምሳሌ በአርሲና በሲዳማ ወሰን አብሮ በመኖር፣ በመጋባትና በመዋለድ ባህል በመወራረሳቸው የተነሳ የብሔር ማንነቱ ደብዝዟል፡፡ ግንኙነቱ ልክ ቀስተ ደመና ላይ ቀለማትን መለየት እንደሚያዳግተው ሁሉ፣ ቁርጥ ያለ መስመር የለውም፡፡ መሬት ያለው ወሰን ደግሞ ቁርጥ ያለ ነገር ይፈልጋል፡፡ ይህንን ግልጽ ያልሆነ የብሔር ማንነት ወስደህ፣ ቁርጥ ያለ የጂኦግራፊ ድንበር ላይ ላውል ስትል ችግር ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ ምን ይጀመራል? እኔ እዚህ ነኝ፣ እኔ እዚያ ነኝ፣ ማለት ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰው ሁለቱንም ማንነት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ይህ ሊፈጠር የቻለው ከምንድነው? ከጅምሩ የመጣንበት አንድን ብሔር ብቻ መሠረቱ ያደረገው አወቃቀር ነው፡፡ ይህ ማለት ወይ ኦሮሞ ነህ፡፡ ወይ ሲዳማ ነህ ለምሳሌ ድሮ በነበረው የመታወቂያ አሠራር ሲዳማና ኦሮሞ ብለህ ማጻፍ አትችልም፡፡ መምረጥ አለብህ ተብለህ ትገደዳለህ፡፡ ነገር ግን ሰዎች እንደዚያ አይደሉም፡፡ በተለይም ድንበር ላይ ያሉ ዜጎች ሁለት ቋንቋ ይናገራሉ፣ ሁለቱንም ባህል ያውቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ችግር አይደለም፡፡ ችግር የፈጠረው ግን ጉዳዩን ወደ ፖለቲካው ስናስገባው ነው፡፡ አዳዲስ የሚፈጠሩ የክልል ጥያቄዎች መነሻ በቅርቡ በአንድ ጥናት ላይ እንዳየነው አንዱ የተሻለ ጥቅም ታገኛለህ የሚል ነው፡፡ አካባቢው የዞን ወይም የክልል አስተዳዳር ይሆንና የበለጠ እናድጋለንና የተሻለ ማኅበራዊ ግልጋሎቶችን እናገኛለን በሚል ነው፡፡  ከፖለቲከኞች አንፃር ደግሞ የተሻለ የሥልጣን ደረጃ እናገኛለን በሚል በተለይ የዞን አስተዳዳሪ ከመሆን፣ የክልል ፕሬዚዳንት መሆን ይሻላል የሚሉ ነገሮች በመኖራቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሎች ውስጥ የእኔ ብቻ የሚል ዕሳቤን እንዴት ማስቀረት ይቻላል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡- በብሔራዊ ውይይቱ እንዲመጣ የምንፈልገው ይኼንን ነው፡፡ ባለፉት ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በነበሩት ጊዜያት ብሔራዊ ማንነት ኮስሶ የብሔር ማንነት የነገሠበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው አንድ ከምንሆንበት ይልቅ የምንለያይበትን የማጉላት ሁኔታ አብዝቶ ያሳየ ነበር፡፡ ያ ደግሞ ለአገራዊ ዕድገት፣ ለማንነትም ሆነ ለኢኮኖሚ የሚበጅ እንዳልሆነ ዓይተነዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ያለፍንባቸውን ሁኔታዎች እንደገና ማየት አለብን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአንዳንድ ክልሎች አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የሚመስል አመለካከት እየተንፀባረቀ ይታያል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተገለጸው በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራትና ንብረት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት መከበር ስላለበት ይህንን ጉዳይ ተመልሶ መመርመርና መገምገም ይኖርብናል፡፡ ብሔራዊ ምክክሩም ይህንን ይፈታዋል ብለን እናስባለን፡፡ ከሕዝቡ በሚመጣው ጥያቄ መሠረት መልሰን ማዋቀርም የሚያስፈልገን ከሆነ መልሰን ማየት የሚገባን ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ሙስና ነው፡፡ ከሰሞኑ መንግሥት የጀመረውን የፀረ ሙስና ዘመቻ በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– እንግዲህ በዘመቻ መደረጉ የአጭር ጊዜ ችግርን በአጭር ጊዜ ትፈታለህ፡፡ አሁን በኮሚቴ ደረጃ ሲቋቋም መጀመርያ ደረጃ መደረግ ያለበት ሙስናን በቋሚነት እንዲከታተል የተቋቋመ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፓርላማው ተጠሪ ሆኖ እያለ፣ አስፈጻሚው ይህን ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ማቋቋም ለምን አስፈለገ ሲባል ያኛው ኮሚሽን የጎደለው ነገር ካለ ማሟላት ያስፈልግ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የምርመራ ሥራ አይሠራም፣ እንደዚህ ዓይነት ሥልጣኖች ተወስደውበት በሥነ ምግባር አስተምህሮ ላይ መሠማራት የአንድ ኮሚሽን ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ ሥነ ምግባር ከታች ከቤተሰብ ጀምሮ ተኮትኩቶ በትምህርት ቤት በመማር የሚመጣ እንጂ፣ ከታች ያላደግነውን በመንገድ የምንቀይረው ነገር የለም፡፡ አሁን የተቋቋመው ኮሚቴ ጅማሮ ጥሩ ነው፡፡ በመጀመርያ ሙስና እንደ ችግር ታይቶ በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ አገር ሊያፈርስ የሚችል ነው ተብሎ ዕውቅና መሰጠቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ግን ይህ ኮሚቴ ዘላቂ ውጤት ሊጠበቅበት አይገባም፡፡ አንደኛ በኮሚቴ ውስጥ እንዲሠሩ የገቡ አካላት ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩ ትልቅ የሥራ ጫና ያለባቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛ አንዳንዶቹ የሚመሯቸው መሥሪያ ቤቶች  በሙስና ቅሌት የሚታሙ ናቸው፡፡ ተጠያቂነት ሲጀመር እኔ የምመራው መሥሪያ ቤት ውስጥ ያለ ሰው ችግር ካለበት የመጀመርያ ተጠያቂ እኔ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ከእኔ ሥልጣን ላይ ነው ቆርሼ ለእሱ የሰጠሁት፡፡

ስለዚህ ኮሚቴው በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በሕዝቡ ዕይታ ተዓማኒነቱን ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማስተካከል ምን ማድረግ ይቻል ነበር? አንዱ አሁን በሙስና እየታማ ያለው አስፈጻሚው አካል በመሆኑ፣ በየትኛውም ደረጃ መንግሥት በሙስና እየታማ ራሱ አስፈጻሚው ይህን ልታገል ብሎ ኮሚቴ ሲያቋቁም ትንሽ በተመልካቹ ዓይን ቀልብ ላይገዛ ይችላል፡፡ ስለዚህ መሆን የነበረበት ገለልተኛ የሆነ አካል ከምሁራን፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብና ከመሳሰሉት አውጣጥቶ ነገሮችን እንዲመረምር ቢያደርግ ፓርላማውም በበላይነት ቢመራው የተሻለ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አሁን እየተነሳ ያለው የሲሚንቶ እጥረትን በተመለከተ መንግሥት አሻጥር ነው፣ እጥረት የለም ይላል፡፡ ግን ይህን ጉዳይ እየተቆጣጠረ ያለው ራሱ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ለእንዲህ ዓይነት ችግር ገለልተኛ የሆነ አካል በፓርላማው ቢቋቋም፣ በተለይ ጡረታ የወጡ የፖሊሲ ኮሚሽነሮች፣ ጄኔራሎች፣ ትልልቅ ስም ያላቸው ዜጎች እንዲመረምሩት ሙሉ ድጋፍ በመስጠት ቢሠራ ያኔ ጉዳዩ ተዓማኒነት ይኖረዋል፡፡ የተሻለ መፍትሔ ይዞ ይመጣል፡፡ ነገር ግን ሙስናን ለመዋጋት የተቋማትን አወቃቀር በሚገባ በመፈተሽና ኃላፊነትን ዘርዝሮ በመስጠት፣ አድርግ የተባልከውን ባታደርግና አታድርግ የተባልከውን ብታደርግ ምን ሊከተልህ ይችላል የሚል አሠራር በመዘርጋት ነው መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው፡፡

ሪፖርተር፡– ተቋማችሁ በመልካም አስተዳደር ላይ እንደ መሥራቱ ከመንግሥት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ዘሪሁን፡– የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ያን ያህል ጠንካራ የሥራ ግንኙነት አለን ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ይህ ከሁሉም ወገን ያለ የአቅም ውስንነት ነው፡፡ እኛ ፓርላማውን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ ነገር ግን እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የምንሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ መሆን አለበት፡፡ ልናሳምናቸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል እነሱም ወደ እኛ ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እንደ እኛ ተቋም ከፓርላማው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት፣ ቤትና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ተቋማት ግለሰባዊ በመሆናቸው ግለሰቦች ሲቀያየሩ ግንኙነቶችም ይፈርሳሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ያለን እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ሥራ ከጀመረ አራተኛ ወሩን የያዘው ፀሐይ ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች በተለየ ሁኔታ በ373 ባለአክሲዮኖች...

ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...