Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነፃነትና የአንድነት ትዕምርት እንጂ የድህነትና የጉስቁልና ምክንያት...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነፃነትና የአንድነት ትዕምርት እንጂ የድህነትና የጉስቁልና ምክንያት አይደለችም!

ቀን:

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ማሳሰቢያ ይህ ጽሑፍ የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን እምነትን አስተምህሮ ለማውገዝ ወይም ለመተቸት፣ አሊያም ደግሞ የእምነቱ ተከታይ የሆኑትን አማኞችንም ለመንቀፍ የተጻፈ አይደለም፡፡ ‹‹ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው›› እንደሚባለው የሁላችንም እናት፣ የጋራ በሆነች አገራችን ኢትዮጵያ ሁላችንም ተከባብረንና ተዋደን ለመኖር የሚያስችሉንን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ትውፊታዊ ዕሴቶቻችን ከፍ በማድረግ በሰላምና በወንድማማችነት የአንድነት መንፈስ የጋራ በሆነች ኢትዮጵያችን በሰላምና በፍቅር መኖር እንዳለብን የምረዳ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ ለተግባራዊነቱም በፅናት የምቆም፣ የምታገልም ሰው ነኝ፡፡

ስለሆነም ይህ ጽሑፍ ከሃይማኖቶች አስተምህሮ፣ ከሥነ ምግባርና አገሪቱ ከምትመራበት ሕገ መንግሥት ባፈነገጠ መንገድ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ እየተደረጉ ያሉ ሕገወጥ የሆኑ አካሄዶች ሊታረሙ፣ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የሚል መልዕክትን ያዘለ ብቻ መሆኑን አንባብያን ከወዲሁ እንዲረዱልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ!!)፡፡

  1. እንደ መንደርደሪያ

በዚህ ሰሞን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ዮናታን አክሊሉ የተባለ ‘‘አገልጋይ’’፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ምዕመኖቿን ለማፅናት፣ ለምክርና ለተግሳፅ የምትጠቀምባቸውን እንደ ተዓምረ ማርያምና ገድለ ተክለ ሃይማኖት የመሳሰሉ አዋልድ መጻሕፍትን እያጣቀሰ፣ ‹‹…ይህ በቅዱስ ወንጌል ላይ የተደረገ ክህደት፣ ምንፍቅና ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ተዓምረ ማርያምና ገድለ ተክለ ሃይማኖት የመሳሰሉ መጻሕፍት ‘‘ወንጀለኞች’’ ናቸውና ሊወገዙ ይገባቸዋል!›› የሚል መልዕክትን አስተላልፏል፡፡

ዮናታን አክሊሉ ያለበትን የእምነት ተቋም አስተምህሮ ለተከታዮቹ ከማስተማር ባለፈ፣ በምን ምክንያት ወደሌላ የእምነት ተቋም ተሻግሮ እንዲህ ዓይነቱን ፍፁም ድፍረት የተሞላበት ዘለፋና የውግዘት ቃል ለማስተላለፍ እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ ይህን በጊዜው ግለሰቡ መልስ ይሰጥበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት በምትጠቀምባቸው መጻሕፍት ዙሪያ አገልጋይ ዮናታንና ተከታዮቹ ላለባቸው ጥያቄና ላስተላለፉት የውግዘት ቃል፣ እንደየደረጃው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ (ዶግማዋንና ቀኖናዋን) በተመለከተ ምላሽ የሚሰጥ ዝግጁ የሆነ ‘የሊቃውንት ጉባዔ’ ስላላት በእነሱ በኩል ተገቢውን ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አስገራሚው ነገር ዮናታን በውግዘትና በወንጀለኛነት ከጠቀሳቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት መጻሕፍት ባሻገርም፣ ‹‹’የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የድህነትና የጉስቁልና ምክንያት መሆኗን’›› ጭምር በአደባባይ ለማወጅ ደፍሯል፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የድህነትና የጉስቁልና ተምሳሌት አድርጎ መግለጽ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ይህን ዕሳቤ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ፓስተር ቶሎሳ ጉዲና (ዶ/ር) የተባሉ የፕሮቴስታንት እምነት አገልጋይና መሪ የሆኑ ሰው፣ ‹‹…የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምዕመኖቿና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድህነትን፣ የጉስቁልናንና የመከራ ቀንበር የጫነች ተቋም ናት…›› በሚል በአደባባይ ተናግረው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ይህ የፓስተር ቶሎሳ ንግግርም በወቅቱ በአባቶችና በምዕመናን ዘንድ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር፡፡ በዚያው ሰሞንም የአሜሪካ ሬዲዮ ድምፅ መምህር ዘበነ ለማን (ዶ/ር) እና ፓስተር ቶሎሳ ጉዲናን ጋብዞ ፓስተሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን በወቀሱበት ሐሳብ/ትችት ላይ በመመርኮዝ አከራክሯቸው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እንደገና ከዓመታት በኋላም ‘‘አገልጋይ’’ ዮናታን ተመሳሳይ የሆነ ክስና ዘለፋ በአደባባይ አቅርቧል፡፡

በመሠረቱ ‘የብልፅግና ወንጌል ‘The Prosperity Gospel’ ሐሳብ አቀንቃኞች ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቦቿ ላይ የጉስቁልና፣ የመከራ ቀንበርን የጫነች ተቋም ብቻ ሳይሆን የዕድገትና የብልፅግና እንቅፋት መሆኗን…›› ጭምር በግልጽ መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ይህንን የተሳሳተ ዕሳቤ ማረም ያስፈልጋልና በዚህ በዛሬው ጽሑፌ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነፃነትና የአንድነት፣ የሰላምና የልማት ትዕምርት (Symbol) እንጂ፣ የድህነትና የጉስቁልና ምንጭ ወይም ምክንያት አለመሆኗን›› ከታሪክ መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገር ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ሕዝብና በአጠቃላይም የሰው ልጆች ሁሉ የነፃነትና የአንድነት ትዕምርት/ሲምቦል መሆኗ፤›› ከመግለጽ ለመጀመር እወዳለሁ፣

  1. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ‘የነነትና የአንድነት ትምህርትነት’

ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰማያዊ፣ ከመንፈሳዊና ከሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ ጥበብ፣ ኪነ ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ወዘተ. ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ናት፡፡

በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለአገር ክብር፣ ስለእውነት፣ ስለፍትሕ፣ ስለነፃነትና ስለአንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህችን ጥንታዊትና ጠንካራ ሃይማኖታዊ ተቋም መምታት ለብዙዎቹ የኢትዮጵያንን የነፃነትና የአንድነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡

በኢጣሊያ ፋሽስት የዓድዋውን አሳፋሪ ሽንፈት ለመበቀል ለሁለተኛ ወረራ በመጣበት ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓድዋው ዘመቻ እንዳደረገችው ሁሉ ሕዝቡ ከፈጣሪው ዘንድ ለተቸረው ለነፃነቱ፣ ለክብሩና ለሃይማኖቱ ቀናዒ እንዲሆን በማስተማር ረገድ የምታደርገውን ሃይማኖታዊና አገራዊ ተልዕኮዋን አስቀድሞ ለማጨናገፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና ውድመት አካሂዷል፡፡ ይህንን እውነታ የሚዘክሩ ከታሪክ መዛግብቶቻችን ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ ለማንሳት ልሞክር፡፡

ፋሽስት በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ዳግመኛ ወረራው በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶና የዓድዋውን ሽንፈት በሚገባ ለመበቀል የመርዝ ጋስ ጭስ ሳይቀር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡ በተጨማሪም ፋሽስት ሕዝቡን በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል በአንድነቱ እንዳይቆም፣ እንዲሁም ስለአንድነቱና ነፃነቱ የሚያስተምሩና በፅናት እንዲቆሙ የሚመክሩ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት ለማዳከምና ለማፍረስ፣ ከተቻለም በሮም ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግም ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ ከፍቶ ነበር፡፡

ስለሆነም ፋሽስት በዚህ ዘመቻው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዋነኛ ዒላማው አድርጓት ነበር፡፡ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም፣ እንዲሁም ደግሞ የበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የሆኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናንያን፣ ዲያቆናትና ምዕመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የኢጣሊያ ፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው የከፋና እኩይ አቋሙ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሊኒ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ንቀትና ጥላቻ ያሳየበት፣ ቢቻለውም ቤተ ክርስቲያኒቱን በፋሽስት ወይም በሮማ አስተዳደር ሥር እንድትሆን የነበረውን ሕልም የሚያጋልጠው እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 16 ቀን 1935 በአስመራ ለሚገኘው ለጦር አዝማቹ ለማርሻል ባዶሊዮ ያስተላለፈው ጥብቅ ሚስጥራዊ ቴሌግራም እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹በቁጥር 421M እና በቁጥር 426 ዳግም ያስተላለፍክልኝን የሚስጥር ቴሌግራም ደርሶኝ በሚገባ አይቼዋለሁ፡፡ የአክሱም ገዳም ተቀደሰ ሥፍራ እንደ መሆኑና ካለውም ጥንታዊ ታሪክና ቅርስ አኳያ በጦር መሣሪያም ሆነ በማናቸውም ዓይነት ወረራ እንዳይነካ፣ የኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ መቆየት አለበት የሚለውን የውጭ መንግሥታት ሐሳብ ከምንም አልቆጥረውም ማለትህና ወደፊትም ይህን ሐሳብ የምቀበል ሰው አይደለሁኝም ማለትህ ትክክለኛ ነህ፣ ጥሩም አድርገሃል፡፡ አሁን የቀረህ ደግሞ የአክሱምን ገዳም ካህናትና መነኮሳት ብዛታቸውንና ማዕረጋቸውን ጠይቀህ ካወቅህ በኋላ፣ በገናናዋ በሮምና በሞሶሎኒ ዙፋን ሥር እንተዳደራለን የሚሉ እንደሆነም በውል አጽፈህና እያንዳንዳቸውን አስፈርመህ ቃል የገቡበትን ሰነድ ወደ እኔ እንድትልክልኝ ነው፡፡››    

የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ፣ በወቅቱ ለምሥራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚኒስትሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ሚስጥራዊ የቴሌግራም መልዕክት ‹Ethiopia and Eritrea› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፣

‹‹… The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favorable attitude. A telegram of March 1, 1937.››

ትርጉም፡- ‹‹በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ ለኢጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሳሱና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል…›› በተመሳሳይም የፋሽስት ጦር በደብረ ሊባኖስ ገዳም ባሉ መነኮሳት አባቶችና አገልጋዮች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ያስተላለፉት ትዕዛዝ በተመለከተ በወቅቱ የፋሽስት አዛዦች የተለዋወጡት ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል፡፡

‹‹ለኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ጠቅላይ ግዛት

የፕሮቶኮል መዝገብ ቁጥር 9325

አዲስ አበባ ግንቦት 24 ቀን 1937 ዓ.ም.

ጥብቅ ሚስጥር ለጄኔራል ማሌቲ ደብረ ብርሃን፣

ለክቡር ምክትል ገዥ ኤታማጆር አዲስ አበባ፣

ለፖለቲካ ጉዳይ ዋና አዛዥ አዲስ አበባ፣

ለጦር ፍርድ ቤት አዲስ አበባ፣

ለካራቢኜራዎች ዋና አዛዥ አዲስ አበባ፡፡

ቁጥር 26609 የደብረ ሊባኖስ ጉዳይ ሙሉ ኃላፊነቱ የእርስዎ እንደሆነ አረጋግጬያለሁ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት ሁሉም አንድ ሳይቀር በጥይት እንድትፈጇቸው አዝዣለሁ፡፡ ትዕዛዝህን በአስቸኳይ አስፈጽሜያለሁ በሚል ቃል እንድታረጋግጥልኝ ይሁን›› ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፡፡

በወቅቱ በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የግድያ ዕርምጃ፣ ኢጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ (Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience) በሚለው መጽሐፋቸው፣

‹‹… የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገብረ ማርያም ወልደ ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ዓ.ም. ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጓዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ…›› በማለት ገልጸውታል፡፡

እንግዲህ እነዚህ በጥቂቱ ለማሳያነት ያነሳኋቸው ታሪካዊ ሰነዶች የሚነግሩን ሀቅ ቢኖር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት ያላትን ፅኑ አቋም በደም ማኅተም የመሰከረች ጥንታዊት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት ተቋም መሆኗን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን የውጭ አገሮች ወረራና ጥቃት በማውገዝ ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነፃነቱና ሰብዓዊ ክብሩ ቀናዒ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች ተቋም መሆኗ የታሪክ ድርሳናት ይመስክሩልናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና አንድነት የነበራት ልዩ ሥፍራና የከፈለችው ይህ ዋጋ ከአገራችን ምድር ተሻግሮም፣ በመላው ጥቁር ሕዝብ ልብ ውስጥ የሰረፀ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም የነፃነት ተምሳሌት ሆነው ተደርገው እንዲሳሉ አድርጓል፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን እ.ኤ.አ. በ1884 በተካሄደው የበርሊኑ ኮንፈረንስ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ በተቀራመቱበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን አኩሪ ነፃነታቸውን፣ ታሪካቸውንና ሥልጣኔያቸውን በመጠበቅና በማስከበር በዓድዋ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የለኮሰውን የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ ለመላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ ታላቅ ታሪክን በደማቸው ጽፈዋል፡፡ ይህንን የታሪክ ሀቅ በተመለከተ አንዳንድ የውጭ የታሪክ መዛግብትን በጥቂቱ ለማየት እንሞክር፡፡ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ የፈረንሣይ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. በ1963  ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል ጋዜጣ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቋታላችሁን?!›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሀተታ፣

‹‹…ኢትዮጵያን ወራሪዎች ምድሯን በግፍ ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉባት አገር መሆኗን ታሪክ ያወሳል፡፡ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴዋ መሣሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነፃነቷን አስከብራ ቆይታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆኗል እየተባለ ስለኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍፁም ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባህሪ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች፣ የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባህር ዓሳም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ሥፍራዋን ይዛ ቆይታለች…›› በማለት ምስክርነቱን አሥፍሯል፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁርና በኢትዮጵያ ዙሪያ ሰፊ ምርምር ያደረጉት ዶናልድ ሌቪን፣ በተለይ ደግሞ በብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ‘‘Wax and Gold’’ በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው የሚታወቁት እኚህ ምሁር፣ ኢትዮጵያውያን በዓድዋው ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንድ፣ ሴት፣ ቄስ፣ መነኩሴ ሳይባል ተባብረው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበትን ጦርነት በጸሎት ተጋድሎና በማስተባበር ያደረገችው ተሳትፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም ልዩ ሥፍራና ክብር ሊያሰጣት እንደቻለ (The Battle of Adowa as Historic Event) በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹‹For a number of colonized African countries, the Ethiopian victory at Adowa symbolized and signaled the possibility of the future emancipation. Hence the Black South African of the Ethiopian Church came to identify with the Christian kingdom in the Horn, a connection that leads South African leaders to write Menelik for help in caring for the Christian communities of Egypt and the Sudan.››

በዚህ በዓድዋ ጦርነት በወራሪው የኢጣሊያ ጦር ላይ ኢትዮጵያውያን የተጎናፀፉት ድል በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ፣ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ትልቅ የሆነ ብሔራዊ ኩራትንና ፅናትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም አፍሪካውያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ ለነፃነት ትግላቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የነፃነት ትግላቸው ዓርማቸውና ሰንደቃቸው አድርገው ተቀበሏት፡፡ በተለይ ለደቡብ አፍሪካውያን የፀረ አፓርታይድና የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ቤተ ክርስቲያኒቱ በትልቁ ትነሳለች፡፡

ለአብነትም አፍሪካዊው የነፃነት አርበኛ፣ የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ስለዓድዋ ድል፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በኋላም በአገራቸው በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃይቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስምና ጥላ ሥር የተቀጣጠሉ የፀረ ቅኝ ግዛትና የፀረ አፓርታይድ የነፃነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት ከእስር በተፈቱ ማግሥት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው፣

‹‹Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.››

(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa፣ 1991)    

በተጨማሪም ይህንን የታሪክ ሀቅ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2002 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ትልቅ ኩራትና መነቃቃት የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር፣

‘’…The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church…’’

የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታምቦ ኢምቤኪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ስለኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነፃነት የተጋድሎ ታሪክና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ አስተዋጽኦን በተመለከተ ያደረጉት ንግግራቸውን የአማርኛ ትርጉም በጥቂቱ ቀንጭቤ ላስነብባችሁ፡፡

‹‹ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፡፡ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መሥራቾች የአገራችን የመጀመርያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያን ልሂቃን ናቸው፡፡ የተነሱትም ከአብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመርያዎቹ አፍሪካውያን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚሲዮኖች ራሳቸውን አላቀው በቤተ ክርስቲያናቱ ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እንደ መነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፰ ላይ ይገኛል፣ ይህም፣

‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው ነው፡፡ እንደ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቀድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፣ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ሥነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡

ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አፍሪካያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ሉዓላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብዓዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ሕልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታና ታሪካዊ ሀቅ ላይ ተመሥርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት ራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡ በአኅጉራችን ላይ የመጀመርያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ANC) የተወለደውም ከእዚሁ ከአገራችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ (ይቀጥላል…)

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብና በደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነትና በታሪክ ጥናትና ቅርስ ጥበቃ ምርምር ሥራ ያገለገሉ፣ በአሁን ወቅትም በጥናትና ምርምር ሥራ ላይ እየሠሩ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...