Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዛሬም ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን››

ዛሬም ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን››

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ለውጡ፣ የለውጥ ጅምሩ መጋቢት ሲመጣ አምስት ዓመት ይሞላዋል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ትዕግሥት እያጣንና ቅደም ተከትል እየጠፋን የጥበብ ሁሉ መጀመርያ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬ›› መሆኑ አልጨበጥልን ብሎ፣ በየጊዜው የምንደርስበትና የተያያዝነው ጊዜ ማለትም የወቅቱ ዋና ተግባር የሚከፋፍሉ ተግባራትን መሸሽ፣ የለውጡን የራሱን ቅድሚያ መጠናከር የሚሹ ጥያቄዎችን ማሳደር መሆኑ ‹‹አልከሰትላችሁ›› ብሎ እነሆ የለየለት ጦርነት ውስጥ መግባታችንን ከመነሻው ፉርሽ የሚያደርግ፣ ወይም የሚከለክል አማራጭ ተስቶን ጦርነቱን ራሱን የማቆም ስምምነት ያደረግነው ገና ሙሉ ሁለት ወራት ባልሆነው ቅርብ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በቀናት ሲቆጠር ገና ሃምሳዎቹ ውስጥ ነን፡፡

‹‹ግጭትን በቋሚነት በመግታት አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት››ን የመሰለ ነገር እንደምን ነው? እንደምንስ ይዞታል? ብሎ ለመጠየቅ፣ ገድ ነው? መንገድ? ብሎ ጠይቆ ምላሽ ለማግኘት ከጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ያለውና የየዕለቱን ዜና እየሰማን ያሳለፍነው፣ ገና ሁለት ወራት ያልሞላው ጊዜ በየአቅጣጫው በቂ ምልክት በመስጠት ረገድ በጭራሽ ንፉግ አልነበረም፡፡ እስካሁን ቢያንስ ቢንያስ አሜሪካ ዋሽንግተን የተካሄደው የአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅ ድረስ፣ ከዚያም በላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ያዘጋጁት የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ፍትሕን ዝግጅት ለማበልፀግ ያወጡት ሰነድ ይፋ እስከሆነበት ታኅሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ፣ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ክፉ ነገር ገጠመው ሲባል አልተሰማም፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹No News›› ወይም ወሬው ጠፋ ማለት፣ ‹‹Good News›› ወይም ጥሩ ዜና ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት ክፋ ቢያጋጥመው ይሰማ ነበር ለማለት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይኼው ጊዜ ግን የሰላሙን ስምምነት፣ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኘውን የሰላም ሁኔታ ሁሉ ሊገዛና ሊወስን የሚችለውን ‹‹የስምምነቶች›› ሁሉ አናትና እናት የሆነውን ይህንን ስምምነት መፈታተን፣ ማጨናገፍ፣ መቅጨትና መቀልበስ የሚችሉ እንቅፋቶች ያንዣበቡት ጊዜ ነበር፡፡ ያንዣበበው አደጋ አሁንም ጥቁር ደመናውን እንደሠራ አለ፡፡ ገና መበተን ያልቻለ፣ ያላወቅንበት፣ በዚህ ብቻ ሳይወሰን እስካሁን ገድ ነው መንገዱ ያልነውን የስምምነቱን አፈጻጸም የቅን ልቦና ድንጋጌ መሸወድ፣ ወይም ዞሮ ማለፍ የሚያስችል ማመካኛ እያደፋፈረ ነው፡፡ ኦሮሚያ በአጠቃላይ በተለይም ወለጋ ውስጥ የሚካሄደውና አላባራ ያለው ጭፍጨፋና ነውጠኛ ትግል ራሱም፣ በዚህ ላይ መንግሥት የሚወስደው ፀጥታና የሕዝብ ደኅንነት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ዕርምጃ በቂ አይደለም፣ ወይም የለም መባል ያስከተለው ተቃውሞ ንጭንጭ መንግሥት ላይ የተሰባሰበውን ድጋፍና ርብርብ በእጅጉ እየጎዳ ነው፡፡ በዚህ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢያንስ ቢያንስ ‹‹አላዋቂ ሳሚ›› ሆኖ የፈጠረው አዲስ የጦር ግንባርና በመካሄድ ላይ ያለ ‹‹ጦርነት›› አለ፡፡ በአፍ ቋንቋ የመማር መብትና ነፃነት ውስጥ ድንገትና በአጋጣሚ ‹‹ገብቶብኝ›› ነው ያለው የክልል ባንዲራና መዝሙር ጉዳይ ‹‹ሰበብ›› ሆኖ ያስከተለው ተቃውሞ፣ ይህም ቀስ እያለ ፍጭጭ እያደረገ የሚያሳየው ‹‹ነውጥ›› መሰል የትምህርት ቤቶች ምላሽ፣ በዚህ ላይ የሚወሰደው የመንግሥትና የፖሊስ ሕግ የማስከበር አያያዝ ከእነ ፕሮፓጋንዳው ጭምር ያለ ማጋነን ስምምነቱ ላይ ለመድረስ ስንቅም ትጥቅም ሆኖ ያገለገለውን የመንግሥትና የሕዝብ ካፒታል እየሸረሸረ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር በገዛ ራሱ እምነት ሆን ብሎ ሳይሆን ‹‹አላዋቂ ሳሚ›› ሆኖ የቀሰቀሰው ተቃውሞ መመለሻ ቀርቶ ማብራሪያ እንኳን ባጣበት ወቅት፣ የፌዴራል መንግሥት (የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፌዴራሉ መንግሥት አካል ነው፣ ተጠሪነቱም ለፌዴራሉ መንግሥት ነው) ዝምታም ‹‹የዝምታ ሴራ››፣ ‹‹የሥራ ማቆም አድማ›› እስከ መባል ስም ወጥቶለታል፣ በአራዳ ሹክሹክታ፡፡

ባንዲራ ማውለብለ በአጠቃላይ፣ አሁን ጉዳዩ አዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥያቄው በቀረበበት መልኩ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በፖለቲካችንና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን ውስጥ የአገርንና የሕዝብን የጋራ መግባባት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሕጎቻችንን ከማቃናት፣ ከማረም፣ ከመንቀስና አጠናቅሮ ከማሰናዳት ጀምሮ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው ከክልሎች፣ ከክፍለ ክልሎች ባንዲራ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በሕግ መደንባት አለበን፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አስቀድሞ የሕዝብን ልብ የረታ የጋራ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መኖር ስለሚገባው የጋራ መግባባት፣ ይህ መግባባት የአገር አጀንዳ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ስለሚቀርብበት ጊዜና ሁኔታ ከመነጋገራችን በፊት፣ መጀመርያ ጉዳዩ ዝም ብሎ የ‹‹ጨርቅ›› ጉዳይ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የ‹‹ጨርቁ›› ስም ራሱ ባንዲራ ነው ሰንደቅ ዓላማ፣ በየጎራው ንግግር እንኳን የሚፈቅድ አይደለም፡፡ የዚህ ‹‹የአገር ምልክት›› ስም ‹‹ባንዲራ›› አይደለም ሰንደቅ ዓላማ ነው ብለን ብንረታ (በነገራችን ላይ ባንዲራ በጣሊያንኛ ብቻ አይደለም ፖርቹጊዝም፣ ስፓኒሽም፣ ስዋሂሊም፣ ማልቲዝም፣ ማለይም፣ ኢንዴኔዥያም፣ ወዘተ ነው) እንኳን ክልል ወይም ጠቅላይ ግዛት ወይም ከብሔራዊው መንግሥት በታች ያለ በየትኛውም ደረጃ ያለ መንግሥት ምልክት ሰንደቅ ዓላማ ይባላል ማለት እንደ ጦር የሚፈራ ርዕስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን በአንቀጽ 3 (3) የፌዴራል አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፣ ዝርዝሩን  በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ ይላል፡፡

እንዲህ ያለ ነገር በሚገባ ከተደነባ፣ ሥርዓትና አሠራር ከተበጀለት የግድና ሁልጊዜም የፀብ መዳረሻ ጉዳይ አይደለም፡፡ በአሜሪካና በጀርመን የማዕከላዊ ወይም የፌዴራል መንግሥትም የክልሎችም ወይም ላንደሮች በጀርመን፣ ስቴቶች በአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ማለት ‹‹ተፈጥሯዊ›› ነው፡፡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ህንድ ውስጥ ለየት ያለ ገጸታ አለው፡፡ እስካሁን ድረስ (ጃሙና ካሽሚር ከሚባለው የተለየ ጉዳይ ካለበት ስቴት በስተቀር) አንድም የህንድ ስቴት ወይም ዩኒየን ቴሪተሪ ዕውቅና ያገኘ ሰንደቅ ዓላማ የለውም፡፡ የህንድ የፌዴሬሽኑ አባላት ሰንደቅ ዓላማ ይኖራቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ያገኘው በ1994 ዓ.ም. የአገሪቱ ‹‹ክፍለ አገሮች›› የገዛ ራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከማቋቋም የሚከለክል ሕግ የለም ተብሎ ሲወሰን ነው፡፡ ከዚህ ፍርድ ጋር የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰነው የየትኛውም ክልል ወይም ስቴት ወይም ዩኒየን ቴሪተሪ ሰንደቅ ዓላማ ግን፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን ክበር የሚቀንስ/የሚያዋርድ መሆን የለበትም በማለት ጭምር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በጥሞና የሚደረስበት ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው የክልል፣ የአገር ሰንደቅ ዓላማ ከሚል ጉዳይ አኳያ ብቻ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ራሱ በተደጋጋሚ ጊዜና አጋጣሚው ‹‹ባመቸ›› ወይም ‹‹የተመቸ›› አጋጣሚ በተገኘ ቁጥር የሚፈነዳ አለመግባባት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ይህ ጉዳይ አለ፣ እስኪ ተነስቼ ይህንንም ጉዳይ ልፍታው ብላ ዛሬ/አሁን ለውይይት የምታቀርበው ጉዳይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መነጋገሪያ ሊያደርጋቸውና ብሔራዊ መግባባት ሊደርስበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ ግን አንድና ሁለት የለውም፡፡ ይህ ሁሉ ንግግር፣ ከሁሉም ላይ ደግሞ የንግግራችን መቅደም የሆነው የትኛውም ጥያቄ ግን አገር የያዘችውን የወቅቱን ዋና ተግባር፣ በእሱ ላይም ያለውን አገራዊ ርብርብ የሚከፋፍል መሆን የለበትም፡፡ የለውጡንና የዴሞክራሲን የራሱን መጠናከር በቅድሚያነት የሚፈልጉ ጥያቄዎችን እየሰነቀርንና አለ‹‹ቦታቸው›› እያስገባ የሚበትን መሆን አይገባውም፡፡

የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ከተነሳ መነጋገሪያ መሆን ካለበት ጉዳይ መካከል አንዱ አብሮ መኖራችንን፣ የመፈቃቀድ ነገር የሚያደርገው የዓርማው ትርጉም ነው፡፡ ልብ ይደረግልኝ ዓርማውን እያልኩ አይደለም፡፡ እሱ ራሱን የቻለ ክርክርና የፍልሚያ ጎራ ያለው ነው፡፡ ልሙጡ ነው ወይስ ባለ ዓርማው? ወይስ ሰንደቅ ዓላማችን ሌላ ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡ ንግግርን እንደ ጦር የሚፈራ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ አሁን እዚህ እኔ የማነሳው በሰንደቅ ዓላማ ሕጋችን የዓርማውን ትርጉም የሚመለከተው ‹‹የመፈቃቀድ›› አንድነታችን ነው፡፡ አሁን እንጀምረው ማለቴ ሳይሆን ብሔራዊ መግባባት ልንይዝበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ዕውን መፈቃቀድ ምርጫ ነው ወይ?

በዕድገት ኋላቀር ነን፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ሥርጭትና በሕዝቦች ስብጥር፣ በባህልና በታሪክ ያለን ቁርኝት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያለን ሥፍራና የጥቅም ግንኙነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላማቸውን አስጠብቀው፣ በዕድገት የመጓዝ ዕድላቸውን አብሮ በመኖራቸው ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ራሱ ጦርነት፣ አለመረጋጋት፣ አክራሪነትና ሽብርተኝነት ሁሉም ያለበት ከመሆኑም በላይ፣ አገራችን ኢትዮጵያ በቀንዱ ውስጥ የበረሃማነት ግፊት የታከለበት የውኃ፣ የግዛትና የወሰን ውዝግብ፣ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥ የጎረቤት ጠላትነት አለባት፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖቶች በተለይም የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች አገር ብትሆንም፣ በጎረቤቶቿ ሙስሊም አገሮች ዘንድ የክርስቲያን ደሴት ወይም አገረ መንግሥት ተደርጋ መቆጠር ገና አልቀረላትም፡፡ ለአሜሪካና ለእስራኤል ያጋደለች ተደርጋ የምትታይ የመሆኑ ክስና ስሞታ ገና አልተዘጋም፡፡ በዚህ ላይ በእስራኤል፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን እጅ እየተነካካ እንደ የመን የመሰለ የትርምስ እሳት በሚንቀለቀልበት ቀጣና ውስጥ የፖለቲከ ሰላም አለመፍጠር ሁሉንም በሚበላ አደጋ ውስጥ ማንቀላፋት ነው፡፡

ይህንን የመሰለውን አደጋ ማስተዋልና አደጋውንም ለማምከን የአገሪቱ ሕዝቦች በብሔርም ሆነ በሃይማኖት የመሸካከር ስንጥቃት ሳያቆዩ፣ እንዲሁም ለውጡ ላይ በደረሰው ጥቃት (አገረ መንግሥቱን ገለልተኛ አድርጎ፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት አፅድቶ የማዋቀርና በዚህ ላይ ዴሞክራሲን የማደላደል አደራ ላይ የተከፈተው ጦርነት) ሳይታመሱ በአገራዊ የጋራ ደኅንነታቸው ላይ አንድ ልብ ሆነው እንዲቆሙ ማስቻል፣ በተለይም አሁን እዚህ ላይ ያለውንና መንግሥት ላይ የተሰባሰበውን ርብርብ ጠብቆ ማቆየት እንቅልፍ የማያስወስድ ተግባር ሆኖ እያለ ፖለቲከኞቻች ድኅረ 2010 ዓ.ም.፣ እንዲያውም ቅድመ 2011 ዓ.ም. ታይቶም ተሞክሮም የማያውቅ ሌላ ዓለም ውስጥ ሲገቡ ዓይተናል፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው አዲስ በተፈጠረው የለውጥ ጅምር ውስጥ ገና ጉዞ ሲጀመር አንስቶ ትዕግሥት እየታጣ፣ ቅደም ተከተል እየጠፋ፣ የሕገ መንግሥትን መሻሻል፣ የክልል እንሁን ጥያቄን በአጣዳፊው የሕግና የሰላም ማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ የአገርን ህልውና ከመከላከል ግዳጅ ላይ መጫንና ማካለብ ትግል ሆኖ መጥቷል፡፡ ዞኖችና ሌሎች የአስተዳደር ዕርከኖች ክልል እንሁን፣ የኢፌዴሪ አባል እንሁን ብለው የሚከራከሩትና የሚታገሉት፣ መጀመርያ ክልል መሆን በቅድመ ሁኔታነት የሚጠይቀውን የዴሞክራሲ ግንባታ እየገዘገዙ፣ ይልቁንም ዴሞክራሲ ስላቋቋምን ሳይሆን አፈናና ጥርነፋ ከላያችን ላይ ቀለልና ገፈፍ በማለቱ ምክንያት ትንሽ የተለቀቀቸውን ሐሳብን የመግለጽና ፍላጎትን ጥያቄ አድርጎ የማቅረብ ለጋ ነፃነት በገዛ ራሳቸው እያጡና እየገበሩ፣ ለውጡ ላይ ጦርነት የከፈተውን ጎራ አወቁትም አላወቁትም እያገዙ ነው፡፡

በለውጡና ባሳለፍነው አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደመሰከርነው ሌሎች ደግሞ ለውጡ ውስጥ የተፈጠረውን የሐሳብ ልዩነት፣ የአሠላለፍ መገለባበጥ ምክንያት አድርገውና አጋጣሚ ተጠቅመው የብሔረሰቦችን መፈቃቀድና፣ የመገንጠልንም መብት ካርታ እያወዛወዙ ማስፈራሪያ ብቻ ሳይሆን መሣሪያ ያደረጉም አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ተከባብሮ ያለመኖር አማራጭ ተበታተን ነው ባዮች ናቸው፡፡ ጥያቄውም አገር ሊነጋገርበት የጋራ መግባባት ሊፈጥርበት የሚገባው ጉዳይም ይኼው ነው፡፡ ዕውን የመፈቃቀድ አመለካከት እውነት ነው? ከመፈቃቀድ በላይ የሆነ የህልውና ግድ የለብንም ወይ? እያንዳንዱ ብሔረሰብ ትንሽም ትልቁም ሰላምና ዕድገት ያለው ሉዓላዊ አገር መሆን የመቻሉ ነገር ተጨባጭ ዕድል ሳይሆን ተምኔት ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ከዓለም የትስስር ጉዞና ከአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ጋር የሚጋጭና ማለቂያ ወደ ሌለው መጠፋፋት የሚወስድ መሆኑን ማየት ለሚፈልግ መሪ የማይሻ፣ አስተርጓሚ የማይፈልግ፣ ወለል ብሎ የሚታይ ገሃድ እውነት ነው፡፡

ሰላማችንና ወደ ልማትና ብልፅግና የመግባት ዕድላችን ግድ የሚለው አማራጭ በመላ አገሪቱ ያለውን የማቴሪያል፣ የዕውቀትና የችሎታ ሀብት በፍትሐዊነት ተጠቅሞ እኩል ተያይዞ ማደግ እንጂ ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናቸው፣ የማይታጠፍ፣ የማይነጠልና የማይገነጠል የመገንጠል መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመፈቃቀድ ኢትዮጵን ፈጥረዋል፣ ቅር ያለው ተበደልኩ የሚል በሕጋዊ አግባብ መለየት ይችላል በሚል አስተሳሰብ ውስጥ መሽከርከር ዛሬ ያለውን አከላለል ከአስተዳደራዊ ይዞታነት ባሻገር፣ የአገር መለያና የባለሀብትነት ማረጋገገጫ አድርጎ መውሰድ ሀብቴ/ሀብትህ እያሉ መናቆር ተጨፍኖ በእሳት መጫወት መሆኑ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 የተደነገገው የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ የመነጠል ጉዳይ የራስን ብሔረሰብ ዕድል የመወሰን ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ በሌሎችም ብሔረሰቦች ዕድልና ህልውና ላይ የመወሰን ጉዳይ ነው፣ የሌሎችን አብሮ የመኖር ፍላጎት ያሳጣል፣ በቅንጣትነት ቆርጦ ያስቀራል፣ ትልቅ ሆኖ የማደግና ደኅንነትና ሰላምን የማስጠበቅ አቅም ያሳጣል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህንን የህልውና ጥቅም ላለማጣትም ተቃውሞ የሚነሳበት ጉዳይ ነው ብሎ ሌሎች ጉዳዮችን መዘርዝር ይቻላል፡፡ ይህንን እዚህ የተነሳውንም ሆነ የሌላውን የግራ ቀኙን ክርክር ግን ሕገ መንግሥቱን እናሻሽል፣ አናሻሽል ስንል እንደርስበታለን፡፡ አብሮ መኖር የ‹‹መብት›› ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ግን ሌሎችም ምክንያቶች አሉ፡፡

ቀጣናችን ወጀባም ነው፡፡ እሱን እንኳን ብንተወው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወጀብ ራሱ ተበታትኖ ከመጨራረስ ይልቅ፣ ሲከፋ እየተረገጡም መትረፍን እስከ መመከት ድረስ አስፈሪ ነው፡፡ ዛሬ በምንገኝበት ሁኔታና እውነታ ውስጥ ያለን ዕድል እንደ ምንም ችግሮችን አቃልሎ መከባበር የሰፈነበት ቤት ከማደራጀት በቀር፣ አብሮ መኖር አማራጭ የለሽ መሆኑን ማስታወስ እንቆቅልሽ አይደለም፡፡ ሶማሊያ ከፈራረሰች በኋላ ሶማሌላንድና ፑንትላንድ ተፈጥረዋል፡፡ እኛም አገርን ባጥለቀለቀ ቀውስ ተለይተን የየራሳችንን መንግሥት በየአካባቢያችን ማደራጀት እንችላለን ብሎ ቅዠታም ዕብደትን ማወጅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በትርምስ ማዕበል ስትመታና ተመትታ ሌሎች የተወሰኑ ክፍሎች ከኢትዮጵያ ወጥተውና ተለይተው ሰላምም መንግሥትም የሚያገኙበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ የዚህ ምክንያት ሌላው ቢቀር የግዛት ድርሻን መተሳሰብና መከፋፈል ቀላል ያለመሆኑ እንኳንስ ተገነጣጥሎ አንድ አገርም ነን ተብሎ እያናጨ መሆኑ፣ ከኢትዮጵያ የበለጠ አስረጂ አገር የለም፡፡ ከተለያዩ በኋላ የግዛት ድርሻን መተሳሰብና መከፋፈል ደግሞ ያጨፋጭፋል፡፡ አሁን በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሎች መካከል ያሉ ውዝግቦች የዚህ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው፡፡ አብሮ መኖርን የጋራ ዕጣችን ያደረገው ከአብሮ መኖር ውጪ ያለ የትርምስ አዘቅት ብቻ አይደለም፡፡ የጋራ ዕጣ ያጎናፀፈን ብዙ የረዥም ታሪክ ሰበዞችም አሉን፡፡

ኢትዮጵያን ቀናንሶና በጣጥሶ ትንንሽ አገር የመፍጠር ‹ነፃነት›ና ፍላጎት፣ ከዘመኑ የጉዞ አቅጣጫና ሕይወትን በዕድገት ከማቃናት ጋር የሚጋጭ አደጋ ያጋጥመዋል፡፡ ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ከድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጋር የተያያዘ እውነታ ከተባለው የተለየ ፈተና አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ክፍለ አኅጉራዊ ትስስር ብትፈጥር እንኳ፣ የኢትዮጵያ የልማት ግስጋሴ ሁልጊዜ በዓይነ ቁራኛ መታየቱና የአየር ንብረትና ፀባይ ለውጥ መጠርጠርያ መሆኗ የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ንዶ እንደገና አካባቢ አቀፍ ስብስብ መፍጠርም የሚታሰብ አይደለም፡፡ መቀናነስ፣ ለየብቻ መሆን ‹‹ነፃነት›› አይደለም፡፡ እየተጨፋጨፉ መርገፍን፣ እየተጨራረሱ በስደት ጎርፍ መፍጠርን፣ ፍርስራሽ በፍርስራሽ መሆንን ያመጣል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትና በዕድገት ጎዳና ላይ መጓዝ ከክፍልፋይነት ይልቅ አያያዥና ትስስር እንደሚሻ ኑሮ ራሱ በመከራ እየመከረን ነው፡፡

አብሮ መኖር፣ በአንድነት ውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲንና ልማትን መፈለግና ለዚህም መታገል የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ አማራጭም የለውም የሚባለው አንድነትና ወይም አብሮ መኖር ራሱ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ መበታተን ወደ ግጭትና መጨራረስ ስለሚያመራ ብቻ አይደለም፡፡ አንዴ ከተለያዩና ከተበታተኑ በኋላ እንደገናና መልሶ በ‹‹አዲስ መልክ››ና ጥንካሬ መሰባሰብ አዳጋችና ምናልባትም የማይቻል ስለሚሆን ነው፡፡ የዚህም ምክንያት አለው፡፡ ኢትዮጵያን አፍርሰው፣ ነፃነት ነው ብለው፣ የየብቻ የሆኑት ቁርጥራጮችን የእርስ በርስ ቅራኔ ከሚያናጫቸው ባሻገር የጎረቤት አገር ግዛት አለን ባይነት በየአቅጣጫው የወረራና የምንተፋ እጁን የሚሰድበት፣ በሌላ ገጽም ከ‹‹ቀድሞዋ›› ኢትዮጵያ ከሚወጡ ወንዞች ጋር ህልውናቸው የተያያዘ ወገኖችም (የኢትዮጵያን በውኃ ሀብቷ መጠቀም መብት የአገራቸው የደኅንት ሥጋት አደርገው ያወጁ፣ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ሲወጉና ሲያስወጉ የኖሩ ወገኖችም) ከትርምስና ከድቀት አዙሪት እንዳይወጡ ለማድረግ የሚያስችላቸው ጥሬና ጥሩ ዕድል የቀውስ ጊዜን ጠብቆ ስለሚመጣ ጭምር ነው፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያዘጋጀው መድረክ አጀንዳና ርዕስ ጉዳይ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል መካተት ያለበት ይኼው የመፈቃቀድ ጉዳይ ነው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ታኅሳስ 20 ቀን ድፍን አንድ ዓመት የሚሞላው በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መወያያ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች፣ ‹‹…የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች፣ እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት…›› የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ እንደተመለከተው አብሮ መኖርን የህልውና ሳይሆን የመፈቃቀድ ነው የሚለው ጉዳይ፣ የአገራዊው ኮሚሽንና የአገር የራሷ አጀንዳ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ተከባብሮ መኖር ላለመቻል መበታተን አማራጭ ነው ወይ? ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍና ከዚሁ የመፈቃቀዱ ጉዳይ ጋር የተነሱ የሰንደቅ ዓላማም ጉዳይ፣ የፌዴሬሽኑ አባላት ክፍፍልና የአሸናሸን መርህም የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት የተጠናወተው ነውና ጭብጡ ሳይሸፋፈንና ሳያጌጥ በሚገባ ተዋቅሮ መነጋገሪያ መሆን አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 52 የክልልን ሥልጣንና ተግባር ሲደነግግ፣ ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል›› ይላል፡፡ ራስን በራስ ለማስተዳር፣ እንዲሁም ለብሔረሰቦች መብት መረጋገጥ የየብቻ መሬት መለየት ቅድመ ሁኔታና ዋስትና ነው ወይ? መሬት የብሔረሰብ ማንነት ገጽታ አካል ነው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ከግራ ቀኝ መከራከሪያዎቻቸው ጋር መታየት አለባቸው፡፡ እዚሁ ውስጥም እያለን የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ ስለሚደራጁትና ስለሚወዳደሩት ፓርቲዎች የአደረጃጀት መርህ መነጋገር አለብን፡፡ የብሔር ፓርቲ መፍቀድ አለብን ወይ? የብሔር ፓርቲ በአደረጃጀቱና በዓላማው አንድ ዓይነተኛ ማኅበረሰብን የእኔ ብሎ፣ ሌላውን ደግሞ ስለሚያገል፣ ማብለጥ፣ ማድላት ውስጣዊ (ኢንኸረንት) ባህርው በመሆኑ፣ እንዲህ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀትን መፍቀድ አለብን ወይ የሚለው መነጋገሪያችን መሆን ያለበት ይመስኛል፡፡

ይህን የመሳሰሉ ጉዳዮች ሕገ መንግሥቱን ወደ ማሻሻል ጉዳይ ይወስዱናል፡፡ በየትኛውም ጎራ ሕገ መንግሥቱን የሁሉም ነገር ምንጭ አድርጎ ከመወዛገብ በፊት፣ መጀመርያ ሕገ መንግሥቱ አመጣቸው የምንላቸውን እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች እንለይ፡፡ ‹‹የሐሳብ ልዩነትና አለመግባባት›› ዝርዝሮችን እንዘርዝር፡፡ ከዚህ ጋር የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ አድርጎ ከማነፅ ጋር ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጉዳይ ይመጣል፡፡

ይህ ሁሉ ግን ቅደም ተከተልን ማወቅ፣ አጣዳፊውን የአገር አጀንዳ ከማያጣድፈው ብቻ ሳይሆን፣ መጀመርያ የሌላውን አጀንዳ መከናወን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ከሚጠይቀው፣ ወዘተ እየለየን መረማመድ አለብን፡፡ ለውጡን ከክሽፈትና ከአደጋ ማዳን የዛሬ አምስት ዓመት አጀንዳችን ነበር፡፡ ይህንን የጋራ አደጋ መሸከም አልችል ብለን፣ የለውጡን አካሄድ ከለውጡ ጠንቀኞች መጠበቅ አቅቶን ዴሞክራሲ የማደላደሉ የሪፎርም ሥራ የአገርን ህልውና ከመጠበቅ የጦርነት ትግል ጋር እስኪቀላቀል ድረስ ከባድና ውስብስብ አደረግነው፡፡ ዛሬ ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ የሰላም ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ አፈጻጸሙም እስካሁን አደጋ አላጋጠመውም፡፡ እዚህ አፈጻጸም ላይ የሚያንዣብብ አደጋ መጣሁ ቀረሁ ማለቱን በራሱ ማሳየት ግን ድርድር ማድረግ፣ ስምምነት ላይ መድረስ ያበቃንን ካፒታል የሚሸረሽር መሆኑን ከ‹‹ጠላት›› ካምፕ ይልቅ የ‹‹ወዳጅ›› ካምፕ የገባው አይመስልም፡፡ አዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመጣውን አደጋ የደገሠው ይህ ድንቁርና፣ ‹‹አላዋቂ ሳሚነት› ነው፡፡ የሰላም ስምምነቱን ፈጣሪ በችሎታው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግሉ ከአዲስ አበባ የለውጡ ‹‹ወዳጆች›› ይጠብቀልን ፀሎት የገባነውም በዚህ ስሜት ውስጥ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...