Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአዲስ አበባ ማናት? 

አዲስ አበባ ማናት? 

ቀን:

በይርጋ ዓለም ማኅተመ (ዶ/ር)

ከአራት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች አላስፈላጊ ወደ ሆነ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ ከሚል ሥጋት የተነሳ፣ ‹‹አዲስ አበባ ከአቡጃና ከብራሰልስ ልትማር የሚገባት ተሞክሮ›› በሚል ርዕስ ሙያዊ አስተያየት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አስነብቤ ነበር። የጽሑፉ ዓላማ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች አካባቢ እየተስተዋለ ያለው ዓይነት ጭቅጭቅና አምባጓሮ እንዳይነሳ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ‹‹አዲስ አበባ የማናት?›› በሚል ጥያቄ መነሻነት የመፍትሔ አቅጣጫ ለመጠቆም ነበር።

አሁንም ባለኝ የግል አቋም አዲስ አበባን የግል ለማድረግ የሚያስብ ማኅበረሰብ ወይም ብሔረሰብ አለ ብዬ አላምንም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች የሉም ብሎ መደምደም አይቻልም። ከዚህም ባለፈ የአዲስ አበባን ጉዳይ በማራገብ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት የሚሞክሩ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ የሚያስብሉ ብዙ አመልካች ሁኔታዎች ይታያሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አዲስ አበባ ማናት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣ የአዲስ አበባ ብዙና ውስብስብ ማንነቶችን ለመረዳትና ከተማዋን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚኖራቸውን ፋይዳ ለመጠቆም ነው። ለመሆኑ አዲስ አባባ ማናት?

የሰው ልጅ ብዙ የማንነት መገለጫዎች አሉት። የፆታ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የሙያና የስም ማንነቶች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ ማንነቶች የማንነት መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ አብረውት ይዘው የሚመጡት ተግባርና ኃላፊነቶችም አሉ። ለምሳሌ ወንድና ሴት የማንነት መገለጫዎች ሲሆኑ፣ ይህንን ማንነት የያዙ ሰዎች በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ሥርዓቶች ማዕቀፍ ውስጥ የሚያከናውኑት ተግባርና ኃላፊነቶች አሉ።

በተመሳሳይ በዓለማችን የሚገኙ አገሮች ርዕሰ መዲናዎችም ብዙ ውስብስብ የማንነት መገለጫዎች አሏቸው። ከእነዚህ ማንነቶች የተነሳ ርዕሰ ከተሞች የሚያከናውኑት ኃላፊነትና ተግባራት አሏቸው። አዲስ አበባ እንደ ማናቸውም የዓለም ዋና ከተሞች ቢያንስ አምስት ውስብስብ ማንነቶች አሏት። እነዚህም ታሪካዊ ማንነት፣ መልክዓ ምድራዊ ማንነት፣ ክልላዊ ማንነት፣ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ ማንነቶች ናቸው።

  1. ታሪካዊ ማንነት

መላው የአፍሪካ አገሮች ለረዥም ዓመታት በቅኝ ግዛት በነበሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ግን ብቸኛዋ ነፃነቷን በመስዋዕትነት ያስከበረች አገር ናት። አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ብትላቀቅም፣ የቅኝ ግዛት ቅሪቶችን በርዕሰ መዲናዎቿ ታቅፋ ነው የምትኖረው። የአፍሪካ አገሮች ርዕሰ መዲናዎች አዲስ አበባን ሳይጨምር የተመሠረቱትና ያደጉት፣ በቅኝ ገዥዎች የዘረኝነትና የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ ላይ ነው። ስለዚህ ከተሞቹ በዋናነት የነጭና የጥቁር መኖሪያ ሠፈር በሚል መሥፈርት ነበር መሪ ዕቅዳቸው የተዘጋጀውና ተግባራዊ ሲደረግ የኖረው። ከነፃነት በኋላም ከተሞቹ እነዚህን መሬት ላይ የሚታዩ የቅኝ ገዥዎችን ቅሪቶች እንደ ታሪካዊ ማንነት ይዘው ይገኛሉ።

ማናቸውንም የአፍሪካ አገሮችን ርዕሰ መዲና የማየት ዕድል ያገኘ ሰው፣ በግልጽ መሬት ላይ ሊያይ የሚችለው በቅኝ የመገዛት ታሪካዊ ማንነትን ነው። በተቃራኒው ደግሞ አዲስ አበባ የተቆረቆረችው በራሷ ሕዝብ ከመሆኑ የተነሳ፣ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ርዕሰ መዲና የሚጋሩትን ታሪካዊ ማንነት አትጋራም። የአዲስ አበባ ታሪካዊ ማንነት ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ነፃ የነበረች ብቸኛ አፍሪካዊ ርዕሰ መዲና መሆኗን ያሳያል። ስለዚህ ከተማዋ በታሪካዊ ማንነቷ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካ ከተሞች ቅርስ ጭምር ናት። ይህ ግዙፍ ማንነት አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነትን ሚና እንድትጫወት ታሪካዊ ኃላፊነትን አጎናጽፏታል። ይህንን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና የአዲስ አበባ ታሪካዊ ማንነቷን አስጠብቆ መኖር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።

መልክዓ ምድራዊ ማንነት

ይህ ማንነት በዋናነት የሚያተኩረው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመሆኗ በሚኖራት ማንነት ላይ ነው። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ መልክዓ ምድር ጋር የተሳሰረች ብትሆንም፣ ከዚህ መልክዓ ምድራዊ ማንነት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ተግባር፣ ኃላፊነትና ተግዳሮት አለባት። ዛሬ አዲስ አበባን ከማስተዳደር አኳያ የሚስተዋለው ችግር የተፈጠረው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በመገኘቷ ሳይሆን፣ ከከተሞች ተፈጥሮዓዊ ባህሪና ማንነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። የአዲስ አበባ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከተማዋ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ለሚኖራት ሥነ ምኅዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

አዲስ አበባ ለዕድገቷና ለመስፋፋቷ የሚያስፈልጋትን መሬት፣ የግንባታና ሌሎች ግብዓቷን በብዛት የምታገኘው ከኦሮሚያ ክልል ነው። እንዲሁም ከተማዋ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የሚያስፈልጋትን መሬት የምታገኘው ከዚሁ ክልል ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ካላት መልክዓ ምድራዊ ማንነት አኳያ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ መስተዳድሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሯ የማይካድ ሀቅ ነው። ይህንን አሉታዊ ተፅዕኖ አዲስ አበባ ለጎረቤቷ በምትፈጥረው መልካም አጋጣሚ ማለትም (በመሠረተ ልማት ተጠቃሚነትና የግብር ገቢን በመጋራት) ማካካስ ስለሚቻል፣ የኦሮሚያን ክልልን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስም ሆነ የአዲስ አበባን ነዋሪዎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሟላት የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በቅርበትና በአገራዊ የትብብር መንፈስ እንዲሠሩ ግድ ይላል።

አዲስ አበባ የመልክዓ ምድር ማንነት ሚናዋን በአግባቡ ለመጫወት ከኦሮሚያ ክልል ጋር ለሚኖራት የሥነ ምኅዳር፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ግንኙነት የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ሊኖራት ይገባል። ይህንን የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ለመቅረፅ የአዲስ አበባ መስተዳድር፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የፌደራል መንግሥት በጋራ በመወያየትና በመደራደር የሚቀርፁት ሲሆን፣ ሌሎቹን የአዲስ አበባ ማንነቶች በማይደፈጥጥ መንገድ መደረግ ይኖርበታል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ሰጥቶ የመቀበልን መርህ ከተከተለ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ደግሞ አገራዊ ጥቅምንና ፋይዳን ካስቀደመ፣ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት የአዲስ አበባን ታሪካዊ፣ ብሔራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ማንነቶችን በማያደበዝዝ መንገድ መደራደር ከቻለ የሁሉንም ፍላጎቶች በማጣጣም አዲስ አባባን ለዜጎቿም ለዓለምም ተመራጭ ከተማ ማድረግ ይቻላል።

  1. ብሔራዊ ማንነት

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ከመሆኗ አንፃር ብሔራዊ ማንነት፣ ተግባርና ኃላፊነት አላት። ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ የስበት ማዕከል ከመሆኗም በላይ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ከተማም ነች። ይህ ብሔራዊ ማንነቷ አዲስ አበባን የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ዋና ከተማ አድርጓታል። ምንም እንኳ አዲስ አበባ ራስ ገዝ ከተማ ብትሆንም፣ ካላት ብሔራዊ ማንነት የተነሳ የፌደራል መንግሥቱ በአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ስለሚገባ እንደ ሌሎቹ የክልል ከተሞች ብዙ ነፃነት የላትም።

ይህ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ሲታይ፣ ጤናማና በሁሉም አገሮች የተለመደ አሠራር ነው። ከዚህ የተነሳ አዲስ አበባ ከክልላዊ ጥቅም ይልቅ አገራዊ ጥቅምን ለማስቀደም የምትገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ይህ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ሕግንና መርህን የተከተለ መሆን ይኖርበታል።

  1. ዓለም አቀፋዊ ማንነት

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ከመሆኗ የተነሳ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ባህል ማዕከል ናት። ይህ ማንነቷ አዲስ አበባ የዓለም ዲፕሎማቶች መኖሪያ፣ የዓለም አቀፍ በረራዎች መሸጋገሪያ ማዕከል፣ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሥሪያ ቤቶች መቀመጫ ከተማ እንድትሆን አድርጓታል። የአዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊ ማንነት ለኢትዮጵያ ይዞት የሚመጣው ብዙ የብሔራዊ፣ የፖለቲካዊ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ ተግዳሮቶችም አሉት።

የፌደራሉ መንግሥት ደግሞ ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ለማሳደግና ከአሉታዊ ተፅዕኖ ከተማዋንም ሆነ አገርን የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ ስላለበት፣ በአዲስ አባባ አስተዳደር ውስጥ የላቀ ሚና አለው። ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊ ማንነት የተነሳ ሌሎች የክልል ከተሞች የሚኖራቸውን ያህል ከተማዋ ነፃነት እንዳይኖራት ያደርጋል። ይህንን እውነት በቅጡ መገንዘብ የአዲስ አበባን ብዙ ማንነቶች አጣጥሞ ለማስተዳደርና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብሎም ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው።

  1. ክልላዊ ማንነት

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ብቸኛ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው። አዲስ አበባ እንደ ራስ ገዝ ከተማ የምታስተዳድረው ሕዝብ አላት። አዲስ አበባ በክልላዊ ማንነቷ ለምታስተዳድረው ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግልጋሎት የማቅረብ ኃላፊነት አለባት። እንደ ማንኛውም ከተማ አዲስ አበባ የማደግ፣ የመስፋፋትና የመብዛት ተፈጥሮአዊ ባህሪ አላት። ይሁን እንጂ ይህ ክልላዊ ተግባርና ማንነት አዲስ አበባ በፌደራል መንግሥትና በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጥላ ሥር እንድትሆን ያደርጋታል።

ስለሆነም በሦስቱ ባለድርሻ አካላት መካከል የጥቅምና የፍላጎት ግጭት መኖሩ የማይቀር ነው። በሌሎች አገሮች እንደተለመደው ሁሉ እንዲህ ዓይነት የጥቅምና የፍላጎት ግጭት ሲፈጠር የሚፈታው ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ነው። የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ክልል አስተዳደር በከተማዋ ላይ የሚኖራቸው ሚና፣ ከብሔራዊ ጥቅም በላይ ሊሆን አይገባም። አዲስ አበባ በብሔራዊ ማንነቷ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ቤት ስለሆነች ሁሉንም በእኩል ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት የፌደራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው።

ማጠቃለያ

  • የአዲስ አበባ ከተማ እንደ ማንኛውም ርዕሰ መዲና የብዙ ውስብስብ ማንነቶች ውጤት ናት። ከዚህ ማንነት የተነሳ አዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊ፣ ብሔራዊ፣ ክልላዊና ታሪካዊ ተግባርና ኃላፊነት አለባት።
  • አዲስ አበባን የሁላችንም የጋራ ቤት ለማድረግ የፌደራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባን ማንነቶችና ያላቸውን አገራዊ ፋይዳ በቅጡ ሊገነዘቡና ተገቢውን ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባል።
  • አዲስ አበባ የርዕሰ መዲናነት ሚናዋን በብቃት መወጣት የምትችለው ሁሉንም ማንነቶች በማጣጣም ከተማዋን መምራት ሲቻል ነው።
  • በአዲስ አባባ አሁን እየታየ ያለው ችግር ከብዙ የተወሳሰበ ማንነት የሚመነጭ ስለሆነ፣ የከተማዋ የመልክ ዓምድር ማንነት (በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ውስጥ መገኘቷ) እና በክልል ማንነቷ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ምክንያት የመጣ ስለሆነ፣ ሊያስፈራንና ስሜታዊ ሊያደርገን አይገባም። ምክንያቱም ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ችግሩን መፍታት በመቻላቸው እኛም ይህን ለማድረግ አቅሙም ዕድሉም አለን። የሚያስፈልገን ቅንነትና አገራዊ አስተሳሰብ ብቻ ነው።
  • የክልል ዓርማና የክልል መዝሙር የአፍሪካ የቅርስ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ የሚያጣላን ጉዳይ ሳይሆን፣ በአንድ ላይ ተቀምጠን ለችግሩ አገራዊ መፍትሔ እንድናበጅለት የተፈጠረ መልካም አጋጣሚ ጭምር መሆኑንም መገንዘብ አለብን።
  • አዲስ አበባ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ርዕሰ መዲና የቅኝ ገዢዎች አሻራ ስላላረፈባት የዓድዋና የአዲስ አበባ ታሪካዊ ማንነት የማይነጣጠሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ናቸው።
  • በታሪካዊ ማንነቷ አፍሪካን አንድ ያደረገች አዲስ አበባ ለእኛ የመከፋፈል ምክንያት ከሆነች፣ ይህ የምንኮራበት ታሪክ ሳይሆን የምናፍርበትና በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዘንድ ራሳችንን የምናዋርድበት ተግባር ይሆናል።
  • በዓለም ዘንድ ያዋረደንን የረሃብና የድህነት ታሪክ ለመቀየር በጋራ የምንጥረውን ያህል፣ ነፃነት ያጎናፀፈንን ዓለም አቀፍ ክብር በጋራ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል።
  • ለዚህ አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችለው አዲስ አበባ ላይ እየታየ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ ነው። ችግሩን በሰከነና በአገራዊ ኃላፊነት በጋራ መፍታት ብሔራዊ ከብርና ኩራት ይሰጠናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው Yirgalemm2001@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...