እሑድ ታኅሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ አንዲት ዘመዴን ከማስታምምበት ቤተዛታ ሆስፒታል አድሬ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ ነው፡፡ በእንቅልፍ ዕጦት ዓይኖቼ ገርበብ ቢሉም፣ የባለቤቴ ወንድም ከሚያሽከረክረው መኪና ሬዲዮ ውስጥ ለጆሮዎቼ የሚደርሰው ዕድሜ ጠገብ በክራር የተቃኘ ሙዚቃ ግን መሳጭ ነበር፡፡ ‹‹አላውቅም ነበረ ትናንትና ሲያልፍ፣ ለካስ ዛሬ ኖሯል የሚያስለፈልፍ…›› እያለ ነፍሱን ይማረውና ካሳ ተሰማ በዚያ ቤዝ ቅኝት ድምፁ ሲያንጎራጉር እንቅልፌ ጭልጥ ብሎ ጠፋ፡፡ ከአምባሳደር ቴአትር በአሮጌው ቄራ ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት የሚያቀናውን ጎዳና ስንያያዝ ደግሞ፣ ‹‹… ምንም ወደር የለው የዛሬው ይብሳል…›› የሚለውን ሲጨምርበት ብዙ ዓመታት ወደኋላ ተሳብኩ፡፡
‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› ሲባል እንደ ቀልድ የሚታለፍ ሳይሆን፣ በውስጡ በርካታ ቁምነገሮች ያጨቀ መሆኑን የምረዳ ሰው ነኝ፡፡ ትናንት ሲባል እንዲህ እንደ ዋዛ የታለፈ ሳይሆን፣ በርካታ ሁነቶች የተስተናገዱበት እንደሆነ ከመጻሕፍትና ከመዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡ አንድም ከበፊት ጀምሮ እስካሁን እየታተሙ ከሚቀርቡልን መጻሕፍት፣ ሌላም በርካታ ታሪካዊ ሰነዶችን አጭቆ ከያዘው ወመዘክር ማግኘት ይቻላል፡፡ በዚህ ዘመን ንባብ ለብዙዎች የዳገት ጉዞ እንደሆነባቸው ቢታወቅም፣ አለማንበብና ታሪክን በቅጡ አለመረዳት የማንም መጫወቻ ያደርጋል፡፡
በነገራችን ላይ በቅርቡ አንድ ከጥቅሶች በላይ የረባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀት የሌለው መናፍቅ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱሳን ላይ የሰነዘረው ምንፍቅና እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ እኔ ስለሰውየውም ሆነ ስለሚሳተፍበት የእምነት ዘውግ ሳይሆን፣ ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ከሰው ልጅ ጋር ጠላት የሆነው ዕባብ መሰሪ ተልዕኮ ነው ማውሳት የምፈልገው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አበው መምህራን እንደሚነግሩን ከሆነ፣ ዕባቡ የሚወክለው ከጥንት ጀምሮ የእመቤታችን ጠላት የሆነውን ዲያብሎስ ነው፡፡ በዚህ ዘመንም ዕውቀት ሳይኖራቸው የሚዘባርቁትም የዲያብሎስ ወኪል መሆናቸውን ለመረዳት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የተገነባችበትን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ መረዳት በቂ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሚገባ እያነበቡና እየተወያዩ ዲያቢሎስን ማሳፈር ያስፈልጋል፡፡
የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በአርምሞ ስንቃኝ ለሥጋችንም ሆነ ለነፍሳችን ጠንቅ የሆኑ በርካታ ብልሽቶች ይስተዋላሉ፡፡ በቀደም ዕለት አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል በረንዳ ላይ ከአንድ ወዳጄ ጋር ማኪያቶ ስንጠጣ፣ በግምት 30 ዓመት የሚሞላው ወጣት ሙሉ ልብስ በከረቫት ሽክ ብሎ መጥቶ ፊት ለፊታችን ቆመ፡፡ ቀላ ብሎ ረዥም ሲሆን፣ ፀጉሩ ገባ ገባ ማለት ጀምሯል፡፡ እጁ ላይ የዘመናዊ መኪና አንዳች የሚያህል ቁልፍ አንጠልጥሏል፡፡ ምን ሊለን ነው ብለን ቀና ብለን ስንጠባበቀው፣ ‹‹የመዳን ጊዜው አሁን ነው…›› እያለን ስልኩ ድንገት ጮኸ፡፡ ከኮቱ የውስጥ ኪሱ ውስጥ የመዘዘው አይፎን ፕሮማክስ ስልክ ወርቃማ ሆኖ ዓይን ያጥበረብራል፡፡
‹‹ሃሎ ጀለስካ… አሁን ያለሁት አራት ኪሎ ሲሆን፣ ስድስት ሰዓት ላይ ሜሬጅ ካውንስሊንግ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ እሄዳለሁ፡፡ ከዚያም ከእነ… ጋር ላፍቶ ሞል ውስጥ ያለው ስቴክ ሃውስ ላንች ቀጠሮ ሲኖረኝ፣ በመቀጠል ደግሞ ሴሚናሪ ከእነ… ጋር ስለአክሲዮን ማኅበሩ….›› እያለ ካወራ በኋላ ወንበር ሳብ አድርጎ፣ ‹‹ድሮ ጎተራ ሙሉ ወንጌል እንተዋወቃለን አይደል…›› ብሎ ወደ እኔ እያየ ተናገረ፡፡ አብሮኝ ያለው የጥንት ወዳጄ ይህንን ቀልድ አይሉት ግራ መጋባት ለማቋረጥ፣ ‹‹ወንድም በጣም ተሳስተሃል ፕሮቴስታንት አካባቢ አታውቀውም…›› ሲለው፣ ‹‹አየህ እኔ እዚያ የምትለው ሠፈርም ሆነ የእምነት ተቋም ውስጥ አልታወቅም…›› አልኩት፡፡ ‹‹ኦው ቬሪ ሶሪ… የጌታን መንገድ አልያዛችሁማ…›› እያለ መመፃደቅ ሲጀምር፣ ‹‹ስለማታውቀው ሰውና እምነት ከመዘላበድህ በፊት ምግባር ይኑርህ…›› ብለን ከአጠገባችን ስናሰናብተው፣ ‹‹ኢትስ ኦኬይ… ዩ ዊል ሪግሬት ዩር አክሽን ዋን ዴይ…›› እያለ እንደ ማይክል ጃክሰን እየነጠረ ሄደ፡፡
እኔና ወዳጄ በገጠመን ድንገተኛ ነገር መነሾ ሌሎች አጋጣሚዎችን እያነሳን ስንጨዋወት የመኪና ጥሩምባ ድምፅ ተሰማን፡፡ እኛ ከተቀመጥንበት በረንዳ ፊት ለፊት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ፊቱን አዙሮ ቆም ሄድ ከሚል ሃዩንዳይ ታክሰን መኪና ውስጥ፣ ወደ እኛ እያየ ጥሩምባ የሚነፋው የቅድሙ ጎረምሳ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ምን ፈልጎ ነው በጥሩምባ የሚያደነቁረን እየተባባልን ስንመለከተው፣ ‹‹በአረጀችና በአፈጀች የተረት እምነታችሁ ውስጥ እንደ ተደበቃችሁ አትቀሯትም…›› ብሎ ሲፈተለክ፣ ‹‹አባት ሆይ አቤቱ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው…›› ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ ልመና ነበር የታወሰኝ፡፡ ጎበዝ አንዳች የሚያህል አዳራሽ ውስጥ ምስኪኖችን ሰብስበው ወዛቸውን የጠረጉበትን ሶፍት የሚያስበሉ፣ በትዕቢት የሚታበዩና በማቴዎስ ወንጌል ቁጥር 24 ውስጥ ትንቢት የተነገረላቸውን ሐሰተኞች ይቅር ይበላቸው ከማለት ውጪ ምን ይባል ይሆን፡፡
ወደ ተነሳሁበት ገጠመኝ ልመልሳችሁና ከቤተዛታ ሆስፒታል ወደ ቤት ስንሄድ እንቅልፌ ጠፍቶ የባጥ የቆጡን እያሰብኩኝ የበፊቱን ሁኔታችንን ሳስታውስ፣ በሥራም ሆነ በጉርብትና አብረን ከኖርናቸው የተለያዩ የእምነት ተከታዮች ጋር የነበረን መከባበር ፊቴ ድቅን እያለ ነበር፡፡ እንደ ዛሬው የብሔርና የእምነት ዘውገኝነት አናታችን ላይ ሳይወጣ ‹‹አገር የጋራ ሃይማኖት የግል›› በሚለው ብሄል አብረን ኖረናል፡፡ ዛሬ ግን ወፍ ዘራሾችና ጥራዝ ነጠቆች በዝተው፣ አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በእምነት እየከፋፈሉ ሲተነኩስን የእኛ ምላሽ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ አንድ ታዋቂ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መምህር እንዳሉት፣ በሥጋዊ ስሜት ለዱላና ላልተፈለገ ድርጊት መነሳሳት ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀት ሰይጣንን ማሳፈር ተገቢ ነው፡፡ ዲያቢሎስ ቀንዱ የሚሰበረውና አገር ሰላም የምታገኘው ፈጣሪ የሚወደውን ነገር ብቻ ስናደርግ ነው፡፡
ስለዚህም በማያውቁት እምነት ላይ በግብዝነት ተነሳስተው የሚዘባበቱትን ማቆም የሚቻለው፣ በጉልበት ሳይሆን በጠለቀ ዕውቀት መሆኑን እንገንዘብ፡፡ ከጥቅስ በላይ የረባ ዕውቀት ሳይኖራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርታ ዕፁብ ድንቅ ዕውቀት አጭቃ የያዘችውን ቤተ ክርስቲያን የሚያመናጭቁትን፣ ጥራዝ ነጠቅነታቸውን እየነቀሱ እያወጡ ከዲያብሎስ ባሪያነት ነፃ እንዲወጡ ማገዝ አስፈላጊ ኃዋርያዊ ተልዕኮ ነው፡፡ አገር በአላዋቂ ፖለቲከኞች እንዳትጠፋ ከተፈለገም፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፋና ወጊነት እንጂ፣ ከንቱ መተናነቅ ፋይዳ ቢስ መሆኑን በዚሁ እንገንዘብ፡፡
(ሰይፈ ሚካኤል ጌዲዮን፣ ከስድስት ኪሎ)