በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ከአራት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ልዩ ሥፍራው ኤጄሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን አደጋ በበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ችግር መከሰቱ ይፋ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ተከስክሶ የ157 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ የደረሰው አደጋ የመጨረሻ ሪፖርት በሁለት ዓመት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ሲገለጽ ቢቆይም፣ በኮቪድና የአደጋውን መንስዔ በጥልቅት ለመመርምር አስቸጋሪ በመሆኑ የመጨረሻው ሪፖርት በአስገዳጅ ሁኔታ መዘግየቱ ተገልጿል፡፡
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሥር ያለው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቬሺን ድርጅት (ICAO) የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ደንብ፣ በአውሮፕላን አደጋ ምርመራ አዋጅ መሠረት የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት በማድረግ የምርመራ ሒደቱ የደረሰበትን ደረጃ፣ ከቅድመ አደጋ ምርመራ መረጃ አንስቶ ቀጣይ ሒደቶችንና በመጨረሻም የተጠቃለለ ሪፖርት ይፋ ማድረጉን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ አስታውቀዋል፡፡
ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስና ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አምዳዬ አያሌው ታኅሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 አደጋ ሊከሰት የቻለው በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሯ አውሮፕላኑ ከመብረሩ በፊት አብራሪዎቹ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የአብራሪነት ፍቃድ ያላቸውና የተመሰከረ ብቃት ያላቸው መሆኑን፣ አውሮፕላኑ ከባለሥልጣኑ የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ያለውና በአግባቡ የተጠገነ መሆኑን ገልጸው፣ አዋሮፕላኑን ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ዉጪ ያደረገው ‹‹ኤምካስ›› በመባል የሚታወቀዉ የአዉሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ችግር እንደሆነ በምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት፣ የአውሮፕላን አምራች ከሆነው ቦይንግ ኩባንያ ጋር የጥቅም ግጭት ቢኖርም፣ ለተጠቃለለው ሪፖርት የአሜሪካው ፌደራል አቪየሽን አድሚኒስትሬሽን፣ ከናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ፣ ከፈረንሣዩ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ (ቢኢኤ) ጋር በመተበበር የምርመራ ሥራው መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን የጥቅም ግጭት ቢኖርም ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ከፍተኛ የመረጃ ልውውጥ አድርገናል፡፡ መረጃ በመስጠት ተባብረውናል፤›› ሲሉ ኮሎኔል አምዳዬ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ በዓለም ላይ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ካለባቸው የደኅንነት መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ በረራ እንዲያቆሙ ተደርገው መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ በጥር 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ሰዓት የፈጀ የአገር ውስጥ የሙከራ በረራ አድርጎ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ዳግም አውሮፕላኑን ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ስድስት ደቂቃ እንደበረረ አደጋ የደረሰበት ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን፣ አደጋው የደረሰበት በሶፍትዌር ችግር መሆኑን የአውሮፕላኑ አምራች ኩባያ ቦይንግ ማመኑ ይታወሳል፡፡
የአደጋው መንስዔ የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የመርማሪ ቡድኑ ካስታወቀ በኋላ፣ የቦይንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው “ኤምካስ” የተባለው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ለአደጋው መንስዔ መሆኑን መግለጻቸውን ሪፖርተር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡