በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች በተለየ ሁኔታ በ373 ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ፀሐይ ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያቀረበውን ጥያቄ ባለአክስዮኖች ተቀብለው በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ለመፈጸም ውሳኔ አሳለፉ፡፡
ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ካፒታል በተጨማሪ 2.1 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህም በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተክፍሎ እንዲጠናቀቅ የሚጠይቅ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ከተፈረመ የባንኩ 2.8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ ክፍያ ያልተፈጸመባቸው አክሲዮኖች በዚሁ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ እንዲከፈል ለባለአክሲዮኖቹ የውሳኔ ሐሳብ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ያለው የተከፈለ ካፒታል 865.97 ሚሊዮን ብር ሲሆን ፣ ካፒታሉን ለማሳደግና የተፈረውን ካፒታል ከዚህ ቀደም ከተቀመጠው የተራዘመ ጊዜ በፊት ከፍሎ ማጠናቀቅ እንደሚገባ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታዬ ዲበኩሉ ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ ይህንን ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ለባለአክሲዮኖቹ ያብራሩ ሲሆን፣ በተለይ ዓለም አቀፋዊ፣ አገራዊና በፋይናንስ ዘርፉ በታዩ ዓበይት ለውጦች ምክንያት የተፈረመ ካፒታል የክፍያ መርሐ ግብር ላይ ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጰያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ባንኮች ሊኖራቸው የሚገባው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ላይ ማሻሻያ በመደረጉና ይህንኑ ማሻሻያ በተገቢው መንገድ ለማሟላት በቅድሚያ የተፈረመው ካፒታል ባጠረ ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ማጠናቀቅ እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ ለባለአክሲዮኖች አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ የውጭ ባንኮች በባንክ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ፖሊሲ መውጣቱን በማስታወስ፣ እነዚህ የውጭ ባንኮች ወደ ዘርፉ በሚቀላቀሉበት ወቅት በሚፈጠረው ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የተሻለ የካፒታል ቁመና ላይ መገኘት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ያልተከፈለ ቀሪ አክሲዮንና ተጨማሪ ካፒታሉን በአጭር ጊዜ ማሟላት ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህ ሐሳብ ላይ የተወያዩት የባንኩ ባለአክሲዮኖችም ከቦርዱ የቀረበውን ሐሳብ ተቀብለው ቢያፀድቁም አንዳንዶች ግን የካፒታሉ ዕድገት ከዚህም በላይ ሊሆን ይገባል በማለት ሞግተው ነበር፡፡
ሆኖም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከዚህ በላይ ካፒታል ለመጨመር እንደሚከብድ ቦርዱ በማስረዳት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ እንዲጸድቅለት ጠይቋል። በዚህም መሠረት የቦርዱ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ የተፈረመው ቀሪ ካፒታል ለመከፈልና ካፒታሉን በ ተጨማሪ 2.1 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖቹ ተቀብለው በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውሰጥ ለመፈጸም ተሰማምተዋል።
የተፈረመውና ተጨማሪ ካፒታሉን ማሟላት ከቻለ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደሚገባቸው ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድሞ ማሟላት እንደሚያስችለው ታውቋል፡፡
የፀሐይ ባንክ ባለአክሲዮኖች በአብዛኛው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያንቀሳቅሱ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ያሉበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ፀሐይ ባንክ ወደ ሥራ ከገባ ገና አራተኛ ወሩ ሲሆን አሁን ላይ በዋናት የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ተግባር ላይ እየሠራ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ እስካሁን ብድር መስጠት ያልጀመረ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ አቅሙን ካጎለበተ በኋላ በቅርቡ የብድር አገልግሎቱን ይጀምራል ተብሏል፡፡ ባንኩ የከፈታቸውን ቅርንጫፎች ከ40 በላይ አድርሷል፡፡