Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማዮኒዝ በሚጥሚጣ!

ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ ቃሊቲ ልንጓዝ ነው። ዛሬ ባቡር ላይ ነን። ‹‹ይቅርታ አንዴ ላስቸግርህ?›› ይላል አንዱ መንገደኛ ዘመናዊ ሞባይሉን እጁ ላይ ዘርግቶ። ‹‹ውሰደው ልትለኝ ባልሆነ? የኢኮኖሚ ዕድገታችን ሞባይል መንታፊውን ድራሹን አጥፍቶ እዚህ አደረሰን እንዴ?›› ይላል ተቀበለኝ የተባለው ቀልቃላ። ‹‹ኧረ ፎቶ እንድታነሳኝ ነው ተረጋጋ እንጂ…›› ይላል ደንግጦ። ‹‹ታዲያ እንደ እሱ አትልም? ምን የሰው ልብ ታቆማላችሁ እንቁልልጭ እየተጫወታችሁ?›› አለ ሞባይሉን ተቀብሎ ብርሃንና ጥላ እያስተካከለ። ‹‹እንቆቅልሽ ነው ያለው እንቁልልጭ?›› ትለዋለች የከንፈር ወዳጇ ትከሻ ላይ ተለጥፋ ባይተዋሮችን ከንፈር የምታስመጥጥ ቆንጆ። ‹‹ምንስ ቢል ምን አገባሽ? አርፈሽ አትቀመጪም?›› ይላታል የከንፈር ወዳጅ። ‹‹አሁን አብራው አድራ እስኪ ምን እንደ ደመኛ ያሳጣታል? ይኼኔ ብቻቸውን ሲሆኑ እኮ ልምምጡ አይጣል ይሆናል…›› ሲለው አብሮት ላለው ወዳጁ፣ ‹‹አዳራቸውን በምን ታውቃለህ?›› ብሎ ያፋጥጠዋል። ‹‹ልምምጥ ነው ያለው? ምንድን ነበር ልምምጥ? አስታውሰኝ እስኪ?›› ይላል አንዱ ተራቢ። ወይ ይህ የቋንቋ ነገር!

ፎቶ አንሺው አንስቶ ተነሺው ደግሞ ፎቶውን እያየ፣ ‹‹ቴንኪዩ!›› ይላል። ‹‹አይገባም፣ አይገባም፣ በገዛ ‘ስማርት ፎንህ’ ደግሞ የምን ምሥጋና ነው? ባይሆን ‘ባክግራውንዱን’ ያሳመረልህን አመሥግን…›› ብሎት ሳይጨርስ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹ገጽታውን ሳያስተካክል በስንት መከራ የተገነባ የአገር ገጽታ ሊያበላሽ ነው? ምናለበት በቫዝሊን እንኳ አመዱን ቢያብሰው…›› ብሎ ያጉረመርማል። ‹‹ምን ታውቃለህ ስንት ብልቃጥ ቫዝሊን እንደ ጨረሰ? በመቀባባት ቢሆን የእስካሁኑ የሥልጣኔ ቅብ ብቻ እንቧይ ያስመስለን አልነበር?›› ይለዋል በዕድሜ የሚስተካከለው ካጠገቡ። ‹‹ዋት ኢዝ እንቧይ?›› ብትላት ደግሞ አንድ ኢርፎን ነጥለው ለሁለት ሙዚቃ እያዳመጡ ከፊት ከቆሙት ታዳጊዎች አንደኛዋ፣ ‹‹ኢግኖር ሂም…›› ብላ ያችኛዋ ሙዚቃውን ‘ኔክስት’ አለችው። እንደ አዲሱ ትውልድ ወደፊት ብቻ ሽምጥ መጋለብን ምነው ሌሎቻችንም ብንችልበት ያስብላል አንዳንዴ፡፡ ‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ እያሉ ማዛጋት ሰለቸን›› የሚሉም አሉ እኮ፡፡ አንዳንዴ ያሰኛል!

ባቡራችን በጣም ዘግይቶም ቢሆን ሲደርስ እየተነባበርን ገባንበት። አገባባችን ያላማራቸው አንድ አዛውንት፣ ‹‹የመግቢያና የመውጫው ነገር በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ ነው…›› ብለው ሲናገሩ ቀልብ ሳቡ። ለእንከን ያሰፈሰፈ ደግሞ ቆመው መጓዛቸው ሳያሳዝነው ሊያስለፈልፋቸው አሰፈሰፈ። ‹‹እንዴት?›› አላቸው አንዱ ነገር ጠማኝ። ‹‹በዚህ በከፋ ዘመን ወንዱም ሴቱም አንድ ላይ እንዲህ ተጠባብቆ ገብቶ እየወጣ? እንዴ… እንዴት ነው ነገሩ?›› ብለው ነገር ሲያሳጥሩ፣ ‹‹እርስዎ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? እንዴት እንዲህ ይላሉ?›› ብሎ የቅድሙ ጎልማሳ ተበሳጨ። ‹‹ምን አልኩ ልጄ?›› አዛውንቱ ደነገጡ። ‹‹ደግሞ ብለን ብለን በፆታ ፉርጎ እንከፋፈል?›› ቢላቸው፣ ‹‹እኔ ያወራሁት ስለበሩ ነው፣ ስለእልፍኙ አትፈትፍትብኝ ወዲያ…›› ብለው ንዴቱ በእሳቸው ባሰ። ‹‹ኧረ በገላጋይ፣ በቅጡ አገልግሎት ያልሰጠውን የባቡራችንን መስኮት ልታረግፉት ነው እንዴ?›› ሲል ያ ተናግሮ ያናገራቸው ሲሳለቅ፣ ‹‹’የቤትዎን አመል እዚያው’ ሲሉን የኖሩት ወያሎች ስንቱን ችለዋል…›› ብላ ፍጥጫው ያሳሰባት ወይዘሮ ነገር ጣል ታደርጋለች። ነገረኛ ሁሉ ያለች ይመስላል፡፡ ምን ታድርግ!

‹‹ቆይ እኛ የሕዝብ መገልገያዎችን ከመስበርና መንገድ ከማቆሸሽ ሌላ አናውቅም ያላችሁ ማን ነው? እኛ እኮ ኩሩ፣ የኩሩ ዘር፣ ጥንቁቅ እንደ ቆቅ…››  እያለ ሊቀጥል ሲል አንዱ ማዶ ብረት ይዞ የሚወዛወዘው፣ ‹‹ኧረ እባክህ አዲሷ ወዳጃችን አሜሪካ እንዳትሰማህና በሳቅ እንዳትሞት…›› ትለዋለች ከጎኑ። ከእሷ ጀርባ ዓይን ዓይኗን ሲያያት ያረፈደ ወጣት ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ከ120 ምናምን ዓመታት በላይ ወዳጅ የነበረችው አሜሪካ አዲስ ተባለች እንዴ?›› ብሎ ጠጋ ሲላት፣ ‹‹አሜሪካማ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት የለም ብላ አይደለም እንዴ ቁም ስቅላችንን ስታሳየን ሰንብታ ሰሞኑን ጠቅላያችንን እንደ አዲስ ዘመድ በቀይ ምንጣፍ ተቀብላ ስትገማሸር የሰነበተችው…›› ስትል፣ ‹‹ዛሬስ መንገደኛው ሁሉ እንደ ባቡሩ በኤሌክትሪክ ኃይል ነው መሰል የሚንቀሳቀሰው…›› የሚለው አንድ ታዳጊ ነው፡፡ ያሰኛል!

ጥቂት እንደተጓዝን ደግሞ ሜክሲኮ አካባቢ የተሳፈረ ወጣት የተሳፋሪዎችን ቀልብ ሳበ። ‹‹ነገርኩህ እኮ፣ ለምን እሺ አትልም… አምጣ የያዝከውን…›› ትላለች አስተናባሪዋ። ‹‹ምን ይዞ ነው? ምንድነው እሱ?›› ድንጉጧ ወይዘሮ ቀወጠችው። ‹‹ነገርኩሽ እኮ ቆሎ ስበላ ነው ያየሽኝ። ለምን ትጨቀጭቂኛለሽ?›› ብሎ ከኪሱ እፍኝ ዘግኖ አውጥቶ፣ ‹‹ዝገኝ ከፈለግሽ…›› ይላል የትርምሱ መሪ ተዋናይ። ‹‹ባቡር ውስጥ ምግብ መብላት ክልክል ነው…›› አለችው ተቆጣጣሪዋ በትህትና። ‹‹ከባቡር ውጪስ መቼ በላን ብለሽ ነው? ኑሮ እንደ እቶን እሳት ነደደ እኮ እናንተ፡፡ ዘንድሮማ የእህል ዋጋ አልቀመስ ማለቱን እያስታወስኩኝ እንዴት እንደሚከረም እንጃ?›› ይላሉ አዛውንቱ ለፊተኞቹ ጀርባቸውን ሰጥተው ፊት ወደ ሰጡዋቸው ዞረው። ይኼኔ ነበር ደህና ደጋፊ አፍርቶ የነበረው ባለቆሎ ወጣት ነገሩን ያበላሸው። ‹‹ቆይ ከመቼ ወዲህ ነው ቆሎ ምግብ የሆነው?›› ሲል፣ ‘እንዴት ቆሎ ምግብ አይደለም ይላል?’ እያሉ ከጥግ እስከ ጥግ ተሳፋሪዎች አጉረመረሙ። ‹‹ቆሎ ባሳደገን ደመኛ ያድርገው?›› ሲል አንዱ፣ ስካርፍ በአንገቷ ዙሪያ ጠምጥማ ወንበር ይዛ የተቀመጠች የቀይ ዳማ ደግሞ፣ ‹‹ኧረ ድምፃችሁን ቀንሱ፡፡ ቻይና ተምሮ የመጣው ሾፌራችን ሰምቶ በንዴት ባቡሩን አቁሞ እንዳይወርድ…›› ማለት ጀመረች። ነገር ሊጀመር ነው!

እንደተፈራው አልቀረም ነገር ተገለበጠና ወደ እሷ ዞረ። ‹‹ምን ያናድደዋል ደግሞ በእኛ ነገር? ደግሞስ እንኳን የባቡር ሾፌር የቱ ባለሥልጣን ወይም መሪ ነው በንዴት ሥራውን ሲያቆም የታየው….›› ሲላት አጠገቧ የተሰየመ ጎልማሳ ንዴት የኬላ ገደብ እንዳለበት ሁሉ ቆንጅት መልሳ፣ ‹‹በክፉ ቀን በልቶ ያደገውን ቆሎ ምግብ አይደለም ብሎ ይኼ ሲከራከር፣ እንኳን የባቡሩ ሾፌር ጠቅላዩ ቢሰሙ ዝም የሚሉ ይመስልሃል?›› አለችው። ጎልማሳው፣ ‹‹ምነው ታዲያ ሠለጠንን ባዮች ባቡር ውስጥ አትብሉ የሚሉን?›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ባቡሩን ከማቆሸሻችን በተጨማሪ እርስ በርስ እንዳንባላ ይሆናላ…›› አንዱ ወጣት፣ ‹‹እርስ በርስ እንድንበላላማ ባለሥልጣናቱም ሆኑ ተገዳዳሪዎቻችን ተራውን ነገር ሁሉ እየቆሰቆሱ ሰላም ይነሱናል…›› የሚሉት አዛውንቱ ናቸው፡፡ የመረራቸው ይመስላሉ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሜክሲኮን እያለፍን ነው። ተጓዥ ይሸኛል ሌላ ተጓዥ ይቀላቀላል። ‹‹ይገርምሃል ውጭ አገር ብዙ ሰዎች ሲደክማቸው ‘ሜትሮ’ ውስጥ ለመተኛት ይሳፈራሉ…›› ይላል ከአዲስ ገቢዎች አንዱ ለወዳጁ። ‹‹ብዙ? ብዙ? አውቀዋለሁ እኔ?›› የወዳጁ ሰዋስው አጠቃቀም ሁለቱም ስለሚያውቁት ሰው የሚያጫውተው መስሎታል ይሄ። ‹‹ኖ! አልገባህም የማወራህ (እንዴት ይግባው ግራ እያጋባኸው ወንድሜ?) በብዛት የቤት ችግር ያለበት፣ ኑሮ ሩጫ የሆነበት የባህር ማዶ ሰው እንዲህ ባቡር ይሳፈርና አልጋ ያደርገዋል ነው የምልህ…›› ብሎ አብራራለት። ‘ሎካሉ’ የእኛ ብጤ ደነገጠ። ‹‹እንዲህ ያለውን ነገር ታዲያ እንዴት ጮክ ብለህ ታወራለህ እዚህ? ስንት አለ ገና ካሁኑ ፌርማታዎቹን ታኮ የጨረቃ ቤት ሊቀልስ ያሰበ። ምን ነካህ?›› አለው ተገላምጦ እያየ። ‹‹ምንድነው ደግሞ የጨረቃ ቤት? ‘አይ ዶንት ጌት ኢት…’›› ዳያስፖራው እንደ ማላገጥ ቃጣው። ‘ሎካሉ’ የጨረቃ ቤትን ማስረዳት አቃተው። ‹‹ጨረቃ ድንቡል ቦቃ አፄ ቤት ገባች አውቃ፣ አፄ ቤት ያሉ ሰዎች…›› ወዲያ ለሥራ ሳይሆን ለጉብኝት ባቡሩን የተሳፈሩ ጎረምሶች ማውካካት ያዙ። የቀልድ ዘመን!

‹‹ዝም አትልም አንተ ውሪ ሁላ! እዚያ ሠፈራችሁ የለመዳችሁትን እዚህ ዘመናዊ ባቡር ውስጥ…›› ወዲያ ኮፍያ ደፍቶ የተቀመጠ ጎልማሳ ተቆጣ። ‹‹ጋሼ ሠፈር ምንድነው?›› ሲል ከጎረምሶቹ አንዱ ጓደኛው በመቀጠል፣ ‹‹ያልዘመነ ባቡርስ እንዴት ያለ ነው?›› አለው። ጎልማሳው ተናዶ፣ ‹‹ሂድ ሰባራ ባቡር…›› ከማለቱ አጠገቡ የተቀመጠች የቀይ ብስል ቆንጆ ልጅ፣ ‹‹ባቡር ሲሰበር እንደ ሰው በክራንች ነው የሚሄደው?›› ብላ ትጠይቀዋለች። ፀሐይ እያሞቀው ጨረቃ የምታበርደው ጥያቄና መልስ ብዛት፡፡ ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወዲያ ጥግ የተሰየሙ መንገደኞች ባቡሩ በእንግሊዝኛ ምን እንደሚባል ጭቅጭቅ ላይ ናቸው። ‹‹ትሬን ነው ለምን ትከራከራለህ?›› ሲል አንደኛው፣ ‹‹የለም ‘ሜትሮ’ ነው የሚሉት ፈረንጆች…›› ይላል ሌላው። ‹‹ምንስ ቢባል ባቡር ብለውናል ባቡር ነው ብለን ተቀብለናል፣ አለቀ…›› ትላለች ወይዘሮዋ በዚህ በኩል። ‹‹ታዲያስ፣ ‘ባሉን’ ብለውት ቢሆንስ ኖሮ አዳሜ ምን ይውጥሽ ነበር?›› ሲል ጎልማሳው በዚያ በኩል ‹‹እነማን ናቸው ግን ባዮቹና አባባዮቹ?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ደግሞ እንደ ፈረደባችሁ በቻይናዎቹ አሳቡና እረፉታ…›› ይላል ከወጣቶቹ መሀል። ‹‹እነሱ የ‘ኦርጂናል’ ዕቃዎች ፀር ናቸው እንጂ የኦርጂናል ቋንቋ ጠላት ናቸው እንዴ?›› ትለዋለች አጠገቡ የቆመች ለግላጋ። ‹‹ዘለዓለም ሽሙጥ፣ ቅር ካላችሁ ቅሬታችሁን በደብዳቤ ጽፋችሁ ለቅሬታ ሰሚ አካላት ማስገባት ነው፤›› አለ አንዱ። ምን ይበል ታዲያ! ‹‹ቅር ብሎናል እንዴ ጎበዝ?›› ደግሞ ሌላ ሽሙጥ ተጀመረ። ‹‹እኔስ አልከፋም ምንድነው ቅሬታ’ የሚለውን ውብ ሙዚቃ ጋብዤሃለሁ…›› ይላል ከወዲያ። ‹‹ለመሆኑ ቅሬታችንን ጽፈን በደብዳቤ እናስገባስ ብንል በምንድነው የምንጽፈው?›› ብሎ ደግሞ አንዱ ሲጠይቅ ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ነዋ። እስከ ዛሬ ታሪካችንም ሆነ ፖለቲካችን ስርዝ ድልዝ የበዛው የጋራ ማንነታችን ተክዶ እኮ ነው…›› ይለው ጀመር። አንዱ ደግሞ ‹‹አደራ እዚያው ራሳችሁን ቻሉ። ይኼ የከንቱዎች ፉክክር ባቡሩን እንዳይገለብጠው ደግሞ…›› ይላል። ‹‹አቤት ዕድገትና ሥልጣኔ፣ እንዲህ ‘ማዮኒዝ በሚጥሚጣ’ እያጣቀሱ መላስ ከሆነስ…›› ብላ ሳትጨርሰው አንዷ ወዝ የደፋባት፣ ‹‹‘ማዮኒዝ’ በሚጥሚጣ ይበላል እንዴ?›› ብሎ አንዱ ያፈጣል። ይኼን የሰማ ሌላ ተሳፋሪ፣ ‹‹ወንድሜ ለፕሮቶኮል መጨነቅ ድሮ ቀረ። እንዲያማ ባይሆን ክብር፣ ማንነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ጨዋነት በጥያቄ ምልክት ሳጥን ውስጥ አሽገን ከየልቦናችን መጋዘን ቆልፈንባቸው አንቀመጥም ነበር…›› አለው። ባቡሩ ዞሮ መመለሱ ነው። ዙሩ እየከረረ ሲሄድ የአኗኗሩ፣ የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ የኑሮው፣ የዴሞክራሲው፣ የመልካም አስተዳደሩ ጥያቄ ሌላ ጥያቄ እየወለደ ይቀጥል ይሆን? ለማንኛውም የዘመኑ ነገር ማዮኒዝ በሚጥሚጣ ማጣጣም አይመስልም ግን… መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት