Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየልጆችን ባህርይ የማነፅ ትልም

የልጆችን ባህርይ የማነፅ ትልም

ቀን:

‹‹ሰው የዘራውን ያጭዳል›› እንዲሉ፣ መልኩ ብዙ የሆነው የሰው ልጅ ጠባይ ከልጅነት አስተዳደግ ጋር እንደሚያያዝ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የሰውን ልጅ ጠባይ የሚወስነው ተፈጥሮ? ወይስ አካባቢ? የሚለው ሐሳብ እስካሁን መቋጫ ያልተገኘለት የክርክር ነጥብ ነው፡፡ ሆኖም አካባቢ ወይም ማኅበረሰብ የሰውን ልጅ ጠባይ በመወሰን ረገድ የራሱ የሆነ ሚና አለው የሚሉም አሉ፡፡

የሰው ልጅ ሲወለድ ከየትኛውም አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮች ነፃ ቢሆንም፣ በዕድገት ወይም በዕለት ተዕለት ኑሮ በሚቀስመው ባህርይው ይወሰናል የሚሉም አይጠፉም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባህርይ የሚቀሰም ስለመሆኑም የሚመላክቱ፣ ‹‹ከአህያ የዋለች ጊደር…››፣ ‹‹ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ›› እና የመሳሰሉ አባባሎች አሉ፡፡ ባህርይ በአብዛኛው ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመዱ በመሆናቸውም ወላጆችና አሳዳጊዎች የልጆቻቸውን ባህርይ ለማነፅ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያያሉ፡፡

በኢትዮጵያ እንደ አካባቢና የቤተሰብ የግንዛቤ ሁኔታ ልጆች ሲያጠፉና ያልተገባ ባህርይ ሲያሳዩ ወላጆች ልጆቻቸውን ከተግባራቸው ለመመለስ ይመክራሉ፣ ይቆነጥጣሉ፣ ይገርፋሉ፣ ሲያልፍም በርበሬ ያጥናሉ፡፡  

ጨዋታ በመከልከል፣ አንድ ክፍል ውስጥ በመቆለፍ፣ አለፍ ሲልም በመለስተኛ ግርፊያ የሚቀጡም ይስተዋላሉ፡፡

የልጆችን ባህርይ ለማስተካከል ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ከመምከር እስከ መቅጣት ያሉ ባህርይን የመግራት ዘዴ ቢጠቀሙም፣ የልጆቻቸው ጠባይ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ የሆነባቸው ሲማረሩ ይታያል፡፡

‹‹አፍሪ ዘር ኢቨንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የልጆች አስተዳደግ ምን መምሰል አለበት? በሚል ታኅሣሥ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአቤል ሲኒማ ባዘጋጀው መድረክም በርካታ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

መድረኩ ወላጆችና ትውልድን በማነፅ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ከወላጆች ጋር የመከሩበት ነበር፡፡ በወላጆች ከተነሱት ጥያቀዎች መካከል፣ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ከልጆቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ግልጽነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለው በመድረኩ ከተነሱ ጥያቄዎች ይገኝበታል፡፡

የየኔታ አካዴሚ መሥራችና ባለቤት ወ/ሮ ጥሩወርቅ አየለ እንዳሉት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ብዙ ነገሮችን ይደብቃሉ፡፡ ልጆቻቸው ከሌሎች ሰዎች ወይም ከአቻዎቻቸው ጋር በአንድ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ሲያዩም ይደነግጣሉ፡፡ ልጆች ግልጽ ከሆኑላቸው ሰዎች ጋር መጠጋት ሲጀምሩ፣ ወላጆች ደግሞ የተጠጓቸውን ሰዎች መጠራጠር ሲጀምሩ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም ከወላጆች የሚጠበቀው ከልጆቻቸው ጋር ያላቸው ተግባቦት በእውነት ላይ የተመሠረተ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር እውነቱን ከሚነግሯቸው ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ለመወያየት ይገደዳሉ፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ግልጽ ሲሆኑ በዕድሜያቸው ልክና የሚመለከታቸው ሐሳብ ላይ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡

ለልጆች ጊዜ ሰጥቶ ማየትና መስማት በአስተዳደጋቸው ወይም በሥነ ባህርይ ግንባታ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በተለይም ከዕድሜ እኩዮቻቸው ፈጥነው የሚያውቁ ልጆች ላይ ወላጆች ቶሎ መድረስ አለባቸው፡፡

በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ፣ ወላጆች የሚያስቡትን ዓይነት ልጅ ለማሳደግ የሚፈልጉ ከሆነ፣ ከፋብሪካ የወጣ ምርት እንደሚሆኑ ወይም ራሳቸውን መድገም እንደሚሆንም ይጠቁማሉ፡፡

ልጆች ሲያድጉ፣ ሲማሩና ሲበሉ ለራሳቸው እንደሆነ እየተነገራቸው ቢሆን፣ ይህም ከእነርሱም በኩል ያለውን ፍላጎት (ተሰጥዖ) እና ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ በመሆኑ ይደግፉታል ይላሉ፡፡

ወላጆች ልጆቸው ግልጽ እንዲሆኑ የሚፈልጉት እንዳይሳሳቱና የተሻለ ዜጋ እንዲሆኑ ቢሆንም፣ ከአሳዳጊዎች በተጨማሪ ቴሌቪዥን፣ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ፣ ጎረቤትና ትምህርት ቤት ሥነ ባህርያቸው ላይ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ወላጆች ቆም ብለው ማጤን አለባቸው፡፡

ግልጽነትን ለልጆች ማስተማር የሚያስፈልገውም ከአሳዳጊዎች በተጨማሪ፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የማኅበረሰብ ክፍሎች በአስተዳደግ ላይ አስተዋጽኦ ስላላቸው ነው፡፡

ልጆች ያዩትን፣ የሰሙትንና የተገበሩትን ለአሳዳጊዎቻቸው እንዲነግሩ ከተፈለገ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ግልጽነትን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

በመድረኩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የአንዲት እናት ገጠመኝ ይገኝበታል፡፡  የስምንትና የሦስት ዓመት ልጆች አሏቸው፡፡ የስምንት ዓመት ልጃቸው ግልጽ ብትሆንም፣  የምትጠይቀውን ጥያቄ መመለስ አቅቷቸዋል፡፡ ከጥያቄዎቿ መካከል ‹‹በትምህርት ቤት ቲክቶክ የማልጠቀመው እኔ ብቻ ነኝ›› የሚል ይገኝበታል፡፡ ጥያቄያቸውም ማኅበራዊ ድረ ገጾችን እንዴት ከልጆች መነጠልና እንዳያገኙ ማድረግ ይቻላል? የሚል ነበር፡፡

ወ/ሮ ጥሩወርቅ እንደተናገሩት፣ ወላጅነት ወይም ልጅ አሳዳጊነት ሙያ ነው፡፡ በመሆኑም ክህሎት ያስፈልጋል፡፡ ልጆችን ለማሳደግ ዘመን የሚያመጣቸውን አዳዲስ ትምህርቶችና ቴክኖሎጂዎች ማወቅ እንዲሁም፣ ራስን ማዘመንና ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡

ልጆች ከአራት ዓመታቸው ጀምሮ የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንደሚያስፈልጋቸው፣ ለዚህም በልጆቻቸው ዕድሜ ልክ በሰዓት የተገደበና በወላጆች ክትትል የሚደረግበት የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ያስፈልጋል፡፡  

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሕፃናት መግባት የለባቸውም፡፡ ለትምህርታቸው ከሆነ ደግሞ በወላጆች ዕገዛ እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከመድረክ የተነሳው ሌላው ጥያቄ በሥነ ሥርዓትና ወላጆች ባወጡት ሕግ መሠረት የሚመራ ልጅ ለማሳደግ ምን ያስፈልጋል? የሚል ነው፡፡ በማይንድ ሞርኒንግ የባህርይ ሥልጠና ማማከር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የባህርይ ጥናት ባለሙያ አቶ አድሚዓለም ግዛ እንዳሉት፣ የአንድ ሕፃን ወይም ልጅ ሥነ ባህርይ በተመሳሳይ ቦታ፣ ማንነትና ሰዓት ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ብዙ መሥራትና ከጎናቸው መሆን አለባቸው፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው የሚመኙትን ማወቅ፣ በመጀመርያ የነገሯቸውን ቅርፅ (ሒደት) አዕምሯቸው እንዲያውቅ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው መንገርና ማሳየት ያለባቸውም የመጨረሻቸውን [መሆን ያለበትን] መሆኑን አቶ አድሚዓለም አስረድተዋል፡፡

‹‹በሥነ ሥርዓት፣ በግልጸኝነትና በሌሎች ነገሮች ከልጆች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር የመጨረሻውን መጀመርያ ማሳየት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ልጅን ሲመክሩ፣ ሲቀጡም የመጨረሻውንና የማያዳግመውን መጀመርያ እያሳዩ መሆን እንዳለበትም ካላቸው ልምድ አካፍለዋል፡፡ ‹‹አንዲት እናት ልጇን እኔ ጋ ጥላ ሄደች፡፡ እናም አላሠራ አለቺኝ፡፡ እኔም የምትወደውን ጨዋታ አምጪ አልኳት፡፡ ገመድ መዝለል አለችኝ፡፡ ገመድ ለመዝለል ምን ያስፈልጋል? አልኩ፡፡ ገመድና ቦታ አለችኝ፡፡ እኔ ገመድና ቦታውን አዘጋጀሁ፡፡ የምትዘይው ምን ያህል ደቂቃ እንደሆነ ጠየቅኳት፡፡ 30 ደቂቃ አለችኝ፡፡ ይህንን መዘገብኩ፡፡ ስትጨርሺ ሪፖርት አድርጊ አልኳት፡፡ ከ30 ደቂቃ በፊት መምጣት እንደማይቻል ነገርኳትና ሄደች፡፡ በአሥረኛው ደቂቃ መጣች፡፡ ለምን በአሥር ደቂቃ መጣሽ አልኳት፡፡ አይ ተሳስቻለሁ አለችኝ፡፡››

ገጠመኙን ተንተርሰው ማብራሪያ የሰጡት አቶ አድሚዓለም፣ የዚህች ሕፃን መልስ ‹‹ተሳስቻለሁ›› እንጂ፣ ‹‹ሰለቸኝ›› አይደለም ይላሉ፡፡ ልጆች ራሳቸው በሚያወጡት ሕግ ቢዳኙ ጥሩ ሥነ ባህርይ ለመገንባት ያግዛል ይላሉ፡፡

ይህንን ለእናቷ በመንገርና በምግብ ሰዓት፣ በጨዋታ፣ በጥናትና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ከልጇ ጋር ስኬታማ ግንኙነት መመሥረት እንደቻሉም ጠቁመዋል፡፡

አንድ እናት የአራተኛ ክፍል ልጃቸውን ይዘው በመምጣት፣ የሚያውቀው ነገር መብዛቱንና የሚያውቀውን ነገር በልኩ ማድረግ ይቻል እንደሆነ የጠየቋቸውም ሌላው የአቶ አድሚ ዓለም ገጠመኛቸው ነው፡፡

አቶ አድሚዓለም እንደሚናገሩት፣ አንድ ሰው ከነቃ በኋላ ወደኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ልጆች ማወቃቸው ለክፉ እንዳይሰጥ የወላጆች ክትትልና ዕገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡  

‹‹የታዳጊ ወላጆች ትርታ›› የሚል መድረክ የሚያዘጋጀው አፍሪ ዘር ኢቨንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኢትዮጵያም ተስፋና አለኝታ የሆኑ ሕፃናት በጥሩ ሥነ ምግባርና በመልካም ሰብዕና ታንፀው የሚያድጉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከወላጆች ጋር በየወሩ እየተገናኘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ያደርጋል፡፡

በዚህ ውይይትም የሥነ ባህርይ ጥናት ባለሙያዎች፣ የትምህርት ቤት ባለቤቶችና ሌሎችም ከሕፃናት ጋር የሚገናኙ ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝ ከወላጆች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...