Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሕፃናት ማቆያ ሲባል ልጆችን ሲያጫውቱ መዋል ብቻ አይደለም›› ወ/ሮ ቤተልሔም ከልክላቸው፣ የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ባለሙያ

የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ከሚያግጥሟቸው አሳሳቢ ችግሮች ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ሥፍራ ማጣታቸው ነው፡፡ በርካታ እናቶች ከወሊድ በኋላ ልጆቻቸውን የሚያስቀምጡበት በማጣት ከሥራ ገበታቸው ቀርተው፣ ቤት ውስጥ ለማዋል ሲገደዱ ይስተዋላል፡፡ በቤት ውስጥ የቅርብ ቤተሰብ ወይም የቤት ሠራተኛ መቅጠር አማራጭ ቢሆንም ይህ የማይሳካለት አለ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚቀጠሩ የቤት ሠራተኞች ቤት ውስጥ ረግቶ አለመቀመጥና በሕፃናት ላይ እየደረሱ ባሉት በደሎች ምክንያት የልጆች ማቆያ ጉዳይ ወላጆችን የሚያስጨንቅ ሆኗል፡፡ በሠለጠኑ አገሮች የሕፃናት ማቆያዎች (ዴይ ኬር) ተለምደዋል፡፡ ሙያው በትምህርት ታግዞ የሚሰጥ ሲሆን፣ ሕፃናትን ቤት ከማዋል ይልቅ በማቆያዎች ውስጥ ማቆየት የተለያዩ ፋይዳዎች እንዳሉትም ይነገራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባም በትምህርቱ በሠለጠኑም ሆነ ባልሠለጠኑ የተከፈቱ የሕፃናት ማቆያዎች አሉ፡፡ አያት እና ሰሚት አካባቢ የሚገኘው ፋሲካ የልጆች ማቆያ ማዕከል ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ ማዕከሉ በሕፃናት ማቆያ ትምህርት ላይ ትኩረት ባደረገው የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት (Holistic Child Development) ዲፕሎማቸውን ከካናዳ ባገኙት ወ/ሮ ቤተልሔም ከልክላቸው ተመሥርቶ በ2009 .ም. ሥራውን ጀምሯል፡፡ በርካታ ሕፃናትን በማዕከሉ በማስተናገድ በትምህርትና ሥልጠና የታገዙ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ስለዘመናዊ ሕፃናት ማቆያና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ቶሎሳ የፋሲካ ሕፃናት ማቆያ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ቤተልሔም ከልክላቸውን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሕፃናት ማቆያው የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ትምህርትን እንዴት ጀመሩ?

ወ/ሮ ቤተልሔም፡- ባለቤቴ የትምህርት ዕድል አገኝቶ ወደ ካናዳ ባቀናበት ወቅት እኔም የመጓዝ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ካናዳ ልጆች ይዞ ሥራ ለመሥራት አስቸጋሪ በመሆኑ ልጆቼን በሕፃናት ማቆያ ማዋል ብቸኛው አማራጭ ነበር፡፡ ከዚያ ልጆቼን በሕፃናት ማቆያ ማዋል ጀመርኩ፡፡ በሕፃናት ማቆያው ለልጆቹ የሚያደርጉትን አያያዝ ስመለከት ሙያውን ለመማር ወሰንኩ፡፡ ከዚህ ቀደም በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ ስለነበረኝ፣ በሕፃናት ማቆያ ትምህርት የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት (Holistic Child Development) የዲፕሎማ ትምህርቴን ማጠናቀቅ ቻልኩ። ከዚያም በሕፃናት ማቆያ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በሕፃናት ማቆያው ሥራ ስጀምር፣ ዋናው የልጆች መሠረት ከታች እንደሆነና ለዚህም የሕፃናት ማቆያ ሥፍራዎች ኃላፊነት የጎላ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት ያለው የልጆች ዕድሜ መሠረት የሚጣልበትና ክትትል የሚደረግበት መሆኑንም ተረዳሁ፡፡ ማቆያውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመርም ወሰንኩ፡፡

ሪፖርተር፡- የሕፃናት ማቆያ አስፈላጊነትንና ጠቀሜታን እንዴት ይገልጹታል?

/ ቤተልሔም፡- እንደሚታወቀው የሕፃናት መሠረት የሚጣለው በለጋ ዕድሜያቸው ላይ እያሉ ነው። ሕፃናት በማቆያ ሲውሉ አስተዳደጋቸውን መሠረት የሚያሳይ የተጠኑ ክህሎቶች እንዲሰጣቸው ይደረጋል። የሚሰጡት አግልግሎቶች በማወቅም ይሆን ባለማወቅ በአብዛኞቻችን ዘንድ በቤት ውስጥ የሚዘነጉ ናቸው።  በአንፃሩ በማቆያዎች የእያንዳንዱ ሕፃናት እንቅስቃሴ፣ ከሚጫወቱት፣ ከሚነካኩት፣ ከሚያሳዩት ባህርይና ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የተጠኑ አግልግሎቶች ይቀርባሉ። ሕፃናት ማቆያን ለማቋቋም ልጆቹ እንደፍላጎታቸው እንዲጫወቱ የሚያስችላቸው ሥፍራ ያስፈልጋል። የሕፃናት ማቆያ ሲባል የልጆችን ገላ ማጠብና ማጫወት የሚመስላቸው አሉ፡፡ በሥነ ልቦና ልጆች ምን ላይ ነው የሚገኙት? በምን ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት? ባህርያቸውና ፍርኃታቸው ከምን የመጣ ነው? የሚለውን መረዳትን ያካተተ አገልግሎት ነው። ከዚያም በዘለለ ለሕፃናቱ መጫወቻ፣ ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ ቦታ፣ መፀዳጃ ሥፍራ፣ የሕፃናቱን ትኩረት የሚስብ ዕቃዎች፣ የሠለጠኑ ሞግዚቶች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ለሕፃናቱ የሚነበቡ መጻሕፍት መኖር አለባቸው።

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመዱት የሕፃናት ማቆያዎች በዘርፉ በትምህርት  ደረጃ ዕውቅና ባላቸው ባለሙያዎች የሚከወን እንደሆነ ይታወቃል። በኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ለማቋቋምና ባለሙያን ለማግኘት የተከተላችሁት መንገድ ምን ይመስላል?

/ ቤተልሔም፡- በኢትዮጵያ ከሕፃናት ማቆያ ጋር በተያያዘ በትምህርት ደረጃ መሰጠት አልተጀመረም። እኛ ሥራውን ስንጀምር፣ ከአሥረኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣ ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ነው የቀጠርነው፡፡ ሠራተኞቹን ከመቅጠራችን አስቀድመን ሥልጠና መስጠትን አማራጭ አደረግን። ሥልጠናውም በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን፣ ከወላጆች አያያዝ፣ ከጤና አንፃር፣ ከልጆች አያያዝና እንክብካቤ በቀዳሚነት ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በማቆያው ሕፃናትን እየጠበቁ ማዋል ብቻ ሳይሆን፣ የልጆችን ሁለንተናዊ ዕድገት መጠበቅ የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት ለሞግዚቶቹ በተሰጣቸው ሰዓት እያንዳንዱን የዕለት መርሐ ግብር ይተገብራሉ፡፡ ለምሳሌ በልጆች የጨዋታ ጊዜ በተለያዩ የጨዋታ ዓይነቶች እንዲያሳልፉ፣ ሰውነታቸው እንዲጠነክርና እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና እንዲጫወቱ፣ መጻሕፍት እንዲነበብላቸው፣ አዕምሯቸውን የሚያሰፉ የመጫወቻ ቁሳቁሶችን እንዲገጣጥሙና ምግባቸውን በሥነ ምግባር ቁጭ ብለው እንዲመገቡ ይደረጋል። ከሦስት ወር ጀምሮ እስከ አራት ዓመት ድረስ ያሉ ሕፃናት እንቀበላለን። ሁሉም በዕድሜያቸው መጠን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በሞግዚቶቹ አማካይነት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። በእያንዳንዱ የሕፃናት ዕድሜ ላይ የሚስተዋሉ ባህርይዎች እንዲሁም አዳዲስ ፀባዮች ሞግዚቶቹ ሳይደብቁ እንዲያቀርቡ ይደረጋል።

ሪፖርተር፡- የሕፃናት ማቆያ ሲነሳ አብዛኛው ወላጅ ፍራቻ የሚያድርበት ልጄ አንዳች ነገር ቢሆንብኝስ የሚለውና የሚዳኝበት መንገድ ነው። ከዚህ አንፃር የእናተ የሕፃናት ማቆያ የሕግ ማዕቀፉ ምን ይመስላል?

/ ቤተልሔም፡- ሞግዚቶችና ድርጅቱ የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ አለ። ለሞግዚቶቹ ከውጭ አገር በመጡ አሠልጣኞች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ በአገር ወስጥ ደግሞ በየሦስት ወሩ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ማንኛውም ወላጅ የሚሳሳለትን ልጁን እንድንጠብቅ አሳልፎ ነው የሚሰጠን። ሕፃናቱ ከሞግዚቶቹ ጋር ነው የሚውሉት። ሞግዚቶቹ ሥራውን ወደው እንዲሠሩት፣ ልጆቹን እንደ ልጆቻቸው እንዲመለከቱና በጥሩ ስሜትና ምቾት እንዲሠሩ ለማድረግ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን። ሁለም ሞግዚቶች ስለተረከቧቸው ልጆች ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይደረጋል። ከወላጆች ጋር በተያያዘ ልጆቹን ስንረከብ ማወቅ የሚገባቸውን ጉዳዮች ወይም መሥፈርቶች በየደረጃው በመጠየቅ እንዲሞሉ ይደረጋል። ስለምንሰጠው አገልግሎት የሚያስረዳና ሊያስጠይቁን ስለሚችሉ ጉዳዮች የሚያብራራ ቅጽ እንዲሁም ፖሊሲ አለን። በዚህም መሠረት ስለሚያስጠይቀን ጉዳይና ወላጆች ስለ ልጆቻቸው እውነተኛ የጤና ሆኔታና አጠቃላይ መረጃን በሚሰጡበት የሚሞላ መጠይቅ መሠረት ይስተናገዳሉ። ሕፃናት በማቆያ ወስጥ ስለዋሉ፣ አይወድቁም፣ አይታመሙም ማለት አይደለም። እያንዳንዱ የልጆቹ እንቅስቃሴ በካሜራ ተደግፎ ቤተሰብ እንዲመለከት ይደረጋል። እንዴት ወደቁ? ምን በሉ? ስንት ሰዓት በሉ? የሚሉና ሌሎች ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ያልተገነዘቧቸው ነገሮች ወይም አዲስ ባህርይዎች ከተስተዋሉ ቤተሰብ እንዲያውቀው ይደረጋል። የተለየ ባህሪ ያለቸው እንዲያሻሽሉ፣ መራመድ የማይችሉ ከሆነም እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና አፋቸውን እንዲፈቱ ይደረጋል። በማቆያው ካሉት የጤና ባለሙያዎች አቅም በላይ የሆነ የጤና እክልበልጆቹ ላይ ቢያጋጥም፣ አብረውን የሚሠሩ በርካታ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ስላሉን ችግሩ በእነሱም ይታያል።

ሪፖርተር፡- ወላጅ ልጁን አምኖ በማቆያ ጥሎ ከመሄድ አንፃር የሚያጋጥሙ ችግሮች ምንድናቸው?

/ ቤተልሔም፡- ሥራውን ስንጀምር በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ባለመኖሩ ፈታኝ ነበር። ለሕፃናት ማቆያ የነበረው ግንዛቤ እምብዛም ስለነበረ፣ ልጆቻቸውን ጥሎ መሄድ የሚከብዳቸው ወላጆች ነበሩ። አንድ ወላጅ ልጁን ከሰጠ በኋላ አጥር ሥር ተደብቆ ይመለከት ነበር። ደጋግመው ስልክ መደወል፣ ምግብ መመገቡን አለማመንና ሌሎች ችግሮች ነበሩ። አንድ አንድ ወላጅ ሞግዚቶች ልጆችን እንደሚቀጡ እንዲሁም እንደሚበድሉ ነው መረጃ ያላቸው፡፡ እኛ ግን እያንዳንዷን እንቅሰቃሴ በካሜራ ዕይታ ውስጥ ስለምናስቀር ለማስረዳት አይቸግረንም። የእኛ ሞግዚቶች ልጆቹን ሲያጫውቱ እንኳን የዓይን ዕይታ እንዲኖራቸው ጭምር እናስገድዳለን፡፡ በአንፃሩ ሰው ከሰው መረጃ እየተለዋወጠና የምንሰጠውን አገልግሎት እየተመለከተ ልጆቹን ይዞ እየመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናትን በሕፃናት ማቆያ ከማዋል ባሻገር ተመራጭ የሚያደርገው የተለየ ነገር ምን አለ?

/ ቤተልሔም፡- የሕፃናት ማቆያ በወላጆች እየተለመደና ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ከዚህም መካከል አሁን ላይ አብዛኞቹ ሕፃናት ቤት ውስጥ ሲውሉ፣ ምንም እንኳን ባይጎዱ በሕፃናት ማቆያ የሚያገኙትን የተለያዩ አገልግሎቶች አያገኙም። በተለይ በዚህ ዘመን አብዛኞቹ ሕፃናት ከስልክና ቴሌቪዥን ጋር መነጣጠል አልቻሉም። ይህ ደግሞ ለጤና እክል እየዳረጋቸው ይገኛል። ከዚያም ባሻገር በቤት ሠራተኞች አማካይነት እያጋጠሙ የሚገኙት ችግሮች ወላጆች ከልጆቻቸው ሕፃናት ማቆያን እንዲመርጡ አድርጓል።

ሪፖርተር፡- በርካታ ወላጆች በሥራ ጫና ምክንያት ልጆቻቸውን ለሠራተኛ ወይም ለቤተሰብ አባል ጥለው ለመሄድ ይገደዳሉ። የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡሕፃናት ማቆያ ማዕከሎችም ጥቂት ከመሆናቸው ባሻገር ክፍያቸው የአብዛኛውን ኅብረተሰብ አቅም ያማከለ አይደለም። ለዚህ መፍትሔው ምንድነው?

/ ቤተልሔም፡- ዛሬ ልጆችን በአግባቡ አንፆ ማሳደግ፣ ብቁ የሆኑ የነገ አገር ተረካቢ ልጆችን መፍጠር ነው። ልጆች ከአንደኛ ዓመታቸው ጀምሮ በአግባቡ ታንፀው ማደግ ካልቻሉ፣ ዕዳው ለአገር ይተርፋል፡፡ አብዛኛው በመንግሥት እንዲሁም በግለሰብ ድርጅት ላይ ተሰማርቶ የሚሠራው ሠራተኛ ወላጅ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ልጆች ይኖሩታል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ሥራቸውን ያለ ሐሳብ እንዲሠሩ ለልጆቻቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ኅብረተሰብ ተደራሽ የሚሆን እንዲሁም የሁሉንም አቅም ያገናዘብ የሕፃናት ማቆያ እንዲቋቋም መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ የሚሆን የኪራይ ቤቶችን ማቅረብ ይገባዋል። ለሕፃናት ማቆያ የሚያስፈልጉ የሕፃናት መጫወቻ ቁሳቁሶች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ ማድረግም አለበት፡፡ አብዛኛው የሕፃናት መጫወቻ ቁሳቁሶች ከውጭ የሚገቡ ከመሆናቸውም በላይ በጣም ውድ ናቸው። በሌላው ዓለም መንግሥት ለሕፃናት ማቆያ የመጫወቻ ቁሳቁሶችን ከታክስ ነፃ ከማድረግ ባሻግር፣ የምግብና የዳይፐር አቅርቦት ላይ ድጎማ ያደርጋል። መንግሥት ለሠራተኞች ሥልጠና ይሰጣል፣ ሰፊ ቦታ ያቀርባል፡፡ ለሕፃናት ማቆያ ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፎች ያሟላል። በኢትዮጵያም ይህ መለመድ ይኖርበታል።

ሪፖርተር፡- ፋሲካ የሕፃናት ማቆያ ወደፊት ዕቅዱ ምንድነው?

/ ቤተልሔም፡- በርካታ ወላጆች ከወሊድ በኋላ ወዲያው ወደ ሥራ ገበታቸው የመመለስ ፎላጎት ቢኖራቸውም፣ አማራጭ በማጣት ቤት ውስጥ ይቀራሉ። ለእነዚህ ወላጆች በአቅማቸው ልክ የሕፃናት ማቆያ ቦታን በማቅረብ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል። የፋሲካ የሕፃናት ማቆያ ማዕከልም እንዲሁም ማሠልጠኛ ተቋማትን በተለያዩ የክልል ከተሞች የማስፋፋት ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህ መሳካት ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ማግኘት ያስፈልጋል። እነዚህን ቁሳቁሶች እናምጣ ብንል ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም። ይህን ለማሳካት የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...