Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊግብረ ሠናይ ድርጅቶች ለትምህርት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እስከ ምን ድረስ ነው?

ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ለትምህርት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እስከ ምን ድረስ ነው?

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በየጊዜው በሚከሰቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሳቢያ አሉታዊ ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት ዋናውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ድርቅንና ጦርነትን ተከትሎ የሚመጣው ረሃብም ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡

ረሃብን ተቋቁመው ለመማር ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችም ውጤታቸው እያሽቆለቆለ እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለአብነት በሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ክልል ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ እንደሆኑ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ በእናቶችና በሕፃናት ላይ የከፋ እንደሚሆን ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይህንን በብዙ ችግሮች የተከበበውን የትምህርት ዘርፍ ለማከም የመንግሥት ጥረት ብቻ በቂ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው፡፡

በመሆኑም የተለያዩ አገር በቀልና የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ በሥራቸውም ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እንዲማሩ አድርገዋል፡፡

ለሴቶችና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚሠሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ አንዱ ነው፡፡

በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ 2.7 ሚሊዮን ሕፃናትና ተማሪዎች ተጨማሪ ምግቦችንና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ዳይሬከተር ሊሊ ኦሞዲ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ታኅሣሥ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሚያተኩርባቸው ሥራዎች ላይ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ እስካሁን በየዓመቱ 2.7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች፣ እንዲሁም በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወላጆች የዕለት ደራሽ ምግቦችን ጨምሮ፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችንና አልባሳትን ሲደግፍ መቆየቱን ተናግሯል፡፡

ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሕፃናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሠራ የቆየው ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ እንደገለጸው፣ በአገሪቱ በየጊዜው በሚከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶችና በድርቅ ምክንያት በርካታ ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን እንዲሁም አካል ጉዳተኞች፣ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ላሉ ሕፃናት፣ ለሚያጠቡና ለነፍሰ ጡሮች ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርና በቀጣይም በስፋት እንደሚሠራም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ13 አገር በቀል ድርጅቶች ጋር በጥምረት እንደሚሠራ የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሊሊ ኦሞዲ ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ ሦስት ክልሎች ላይ በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በተለይም ሕፃናት ተማሪዎችን ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ከማድረግ አንፃር ውጤታማ ሥራን እንደሠሩ ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ላይ፣ በተለይም በድርቅና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በመለየት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡

በእናቶችና በጨቅላ ሕፃናት ጤና አገልግሎት፣ በሥነ ምግብ፣ በሕፃናት ጥበቃ ላይ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወላጆች ጊዜያዊና ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ፣ እንዲሁም ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የቤተ መጻሕፍት ግንባታና አጠቃላይ ምቹ የትምህርት ሥነ ምኅዳር በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

ድርጅቱ በየዓመቱ በቀጥታ ድጋፍ ከሚያደርግላቸው 2.7 ሚሊዮን ሕፃናት በተጨማሪ፣ ለአጋር ድርጅቶቹ ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን ብር በመመደብ በአጋሮቹ በኩል 4.7 ሚሊዮን ሕፃናት ተደራሽ እንደሚሆኑ የተናገሩት ደግሞ የቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ የፕሮግራምና ስፖንሰርሽፕ ኃላፊ የሆኑት አቶ አባዲ ዐምዱ ናቸው፡፡

ከሰሜን ወሎና ከደቡብ ወሎ በጦርነት ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ ለነበሩ ወገኖች ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ፣ የዕለት ደራሽ ምግቦችንና አልባሳትን እንዲሁም በነፍስ ወከፍ 1,500 ብር ጥሬ ገንዘብ ሲረዳ እንደቆየ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

‹‹በየጊዜው በሰሜን ሲገድቡት በሌላው እየፈነዳ ያስቸገረው የእርስ በርስ ግጭት፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ድርቅ በየዓመቱ የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ እያደረገው ይገኛል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም ተረጂዎች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ ድርጅታቸውም ተደራሽነቱን ከፍ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡  

በቀጣዮቹም አምስት ዓመታትም ተጨማሪ አራት ክልሎችን ድርጅታቸው ለማቀፍ እንዳሰበ አብራርተዋል፡፡

የትግራይ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በዚህም ሰባት ሚሊዮን ሕፃናት ተጠቃሚ ለማድረግ 3.5 ቢሊዮን ብር በመበጀት እየተንቀሳቀሰ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ከሚሠሩ አሥራ ሦስት አጋር ድርጅቶች መካከል ‹‹የነገ ተስፋ የተቀናጀ የልማት ድርጅት›› አንዱ ነው፡፡ ‹‹ከቻይልድ ፈንድ በሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በማሟላት፣ ብቁና አገር ወዳድ ዜጎችን ለማፍራት ከወዲሁ እየሠራን ነው፤›› ያሉት የነገ ተስፋ የተቀናጀ የልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ተስፋ ናቸው፡፡

ከሕፃናት በተጨማሪ ሴቶችና ወጣቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የመነሻ ገንዘብ፣ እንደ አልባሳት፣ የልብስ መተኮሻና ማጠቢያዎችን የመሳሰሉ ማሽኖች በመስጠት ልጆቻቸውንና  ቤተሰባቸውን እንዲረዱ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ የሚረዳን በገንዘብ ብቻ አይደለም፤›› ያሉት አቶ አንዱዓለም፣ የሪፖርት ቁጥሮችን ከማንበብ ይልቅ ቦታው ድረስ በመውረድ የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም ሰንሰለቱን የጠበቀ አሠራር እንዲኖር፣ የተደራጀና ውጤት ተኮር ሥራ እንዲሠሩ የሚያስችል አቅም ከመፍጠር አንስቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ከጎናቸው እንደቆመ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በቻይልድ ፈንድ ድጋፍ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንደሆኑ ለሪፖርተር የተናገረችው የዕውቀት ለኅብረት ተማሪ የሆነችው ተማሪ ዓይን አዲስ ዓለሙ ናት፡፡

ተማሪ ዓይን አዲስ በትምህርት ቤቷ የተሟላ ቤተ መጻሕፍት በመገንባትና በውስጡም የተለያዩ አጋዥ የመማሪያ መጻሕፍት በመሟላታቸው እሷና መሰሎቿ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግራለች፡፡

ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ‹‹ፍቅር ለሕፃናት›› የተሰኘ ክበብ በማቋቋም፣ ዕውቀታቸውን እንዳዳበሩና በሥነ ተዋልዶ ጤና፣ በኤችአይቪ፣ ኤድስና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ለተማሪዎችና ለወላጆች ትምህርት አዘል መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ተማሪ ዓይን አዲስ ተናግራለች፡፡

በሌላ በኩል ለተማሪዎች ደብተርና እስኪርቢቶ እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጀ ላይ ላሉ ወላጆች በቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ድጋፍ ሲደረግላቸው ለማየት እንደቻለች ተናግራለች፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...