Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባቫሪያ ኦቨርሲስ ሐበሻ ቢራን ለመጠቅለል ሐሳብ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በኢትዮጵያውያን የተያዘውን አክሲዮን ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ ውዝግብ ፈጥሯል

የሐበሻ ቢራ ፋብሪካን ከ71 በመቶ በላይ የባለቤትነት ድርሻ የያዘው ባቫሪያ ኦቨር ሲስ ብሬወሪስ የተባለው የሆላንድ ኩባንያ፣ የኩባንያውን አክሲዮኖች ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል ሐሳብ ያቀረበ ቢሆንም፣ ለባለአክሲዮኖች ያቀረበው የመግዣ ዋጋ ውዝግብ መፍጠሩ ተገለጸ፡፡   

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባቫሪያ አሁን ከያዘው የአክሲዮን ድርሻ ሌላ በኢትዮጵያውያኖች የተያዙ አክሲዮኖችን በግዥ ለመጠቅለል አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን በ2,500 ብር ለመግዛት ሰሞኑን ሐሳብ ቢያቀርብም፣ በቀረበው ዋጋ ላይ ስምምነት ላይ ሊደርስ አልቻለም፡፡

ባቫሪያ ከ30 በመቶ በታች የሆነውና በኢትዮጵያውያኖች የተያዙት አክሲዮኖች ለመግዛት ጥናት አድርጎ ያቀረበው የመግዣ ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ፣ ሰሞኑን በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አዎንታዊ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ኩባንያው ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት ወይም በባለአክሲዮኖች መካከል ለሚደረገው የአክሲዮን ግብይት፣ የኩባንያው ዋጋ ዓለም አቀፍ ገማች የተገመተ ቢሆንም፣ ይህ ግምት ትክክል አይደለም በሚል ልዩነት ተፈጥሯል፡፡

ኩባንያው አስጠናሁት ባለው ጥናት ግምቱ የተሠራው እ.ኤ.አ. መስረም 2022 ሲሆን፣ በዚህ ግምት አንዱን አክሲዮን 2,500 ብር መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ዋጋ ግብይት እንዲፈጸም የታሰበ ቢሆንም፣ በዳይሬከተሮች ቦርድና በባለአክሲዮኖች መካከል የተደረገው ውይይት መግባባት ላይ ሊደረስ አለመቻሉ ታውቋል፡፡

በዚህ የአክሲዮን ዙሪያ ያለመግባባቱ መንስዔ ደግሞ፣ ኩባንያው አክሲዮኖችን ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ በቂ አይደለም የሚል መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው ሰሞኑን ለባለአክሲዮኖች በላከው መልዕክትም ይህንን አረጋግጧል፡፡

በዚህም ምክንያት ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን ለመሸጥ ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ በቀረበውን ዋጋ ላይ ልዩነት አለን እያሉ ነው፡፡ በመሆኑም በኩባንያው ቦርድ በባለአክሲዮኖች ተወካዮች መካከል በተደረገው ውይይት ልዩነት የፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የኩባንያው ዋጋ እንደ አዲስ ተጠንቶ የመጀመርያው የአክሲዮን ግብይት እ.ኤ.አ. ከ2023 የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዲደረግ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡

በሰሞኑ ጠቅላላ ጉባዔ በተጠቀሰው ዋጋ አክሲዮኖችን ለማዘዋወር የሚያስችል ውሳኔ ማስተላለፍ ባይቻልም፣ ባቫሪያ ግን ከዚህ ስምምነት ውጪ አክሲዮኖችን ሊሸጡለት ለሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች በሩ ክፍት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን ለባለአክሲዮኖች ይድረስ ባለው መረጃም የሐበሻ ቢራ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የሆነው በቫሪያ ኦቨርሲስ ብሬወሪስ አክሲዮናቸውን ማስተላለፍ ለሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የአክሲዮን ግዥ ፍላጎት ያቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህ ጥሪ መሠረት መረጃ በመውሰድ ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን እንዲሸጡ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ግን እንዲህ ያለው ዕርምጃው ተገቢ አለመሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት እያቀረቡ ያሉት ከሐበሻ ቢራ ፋብሪካ በታች አቅም የነበራቸውና እምብዛም ገበያ ውስጥ ሳይገቡ በተመሳሳይ መንገድ የተሸጡት ራያ ቢራና ዘቢዳር ቢራ ፋብሪካዎችን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ሲሸጡ ራያ ቢራ ፋብሪካ 1,000 ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን በ7,000 ብር፣ ዛቢዳር ቢራ ፋብሪካ ደግሞ 1,000 ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን በ3,500 ብር መሸጣቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በመሆኑም አሁን ባቫሪያ ያቀረበው የሽያጭ ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በበኩላቸው አሁን ከሐበሻ ቢራ እያገኙት ያሉት ዓመታዊ ትርፍ ባንክ ከሚከፍለው የተቀማጭ ወለድ መጠን ጋር ብዙም ያልተራራቀ በመሆኑ መሸጡን እንደሚፈልጉ ያመለክታሉ፡፡

ሆኖም የቢራ ገበያ ከወቅታዊው ሁኔታ አንፃር እየቀነሰ በመሆኑ ትርፉም ምጣኔውም በታሰበው ደረጃ አለመሆኑን እንደ ምክንያት በማቅረብ፣ የአክሲዮኑን ዋጋ በ2,500 ብር ዋጋ እንዲወጣለት መደረጉ የኩባንያው መረጃ አመልክቷል፡፡ ባቫሪያ እንዲህ ያለ አመለካከት ቢኖረውም፣ አሁን ተቀዛቅዟል የተባለው የቢራ ገበያ ባለበት ስለማይቀጥል ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታንና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በማድረግ የኩባንያውንና የአክሲዮን ዋጋውን ማሳነስ ተገቢ እንደማይሆን ያመክታሉ፡፡ የሐበሻ ቢራ ባለአክሲዮኖች በቀረበው ዋጋም ሆነ ሊሻሻል ከቻለ በአዲሱ ዋጋ አክሲዮናቸውን የሚያስተላልፉ ከሆኑ በቢራ ጠመቃ ሥራ የኢትዮጵያውያን እጅ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ያደርጋቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዳይሬከተሮች ቦርድና በባለአክሲዮኖች መካከል ተደረሰ በተባለው ስምምነት መሠረት፣ የኩባንያው ዋጋ አንደ አዲስ ተጠንቶ ለቀጣዩ ዓመት የባለአክሲኖች ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ እንዲደረግ ተወስኗል እየተባለ ባቫሪያ አክሲዮኖች ለሚሸጡ ጥሪ ማቅረቡ ጉዳዩን አነጋጋሪ እንደሚያደርገውም ያነጋገርናቸው ባለአክሲዮኖች ያመለክታሉ፡፡  

የሐበሻ ቢራ ፋብሪካ ዋነኛ ባለድርሻ ውሳኔ የማሳለፍ አብላጫ ድምፅ ያለው በመሆኑ፣ ከ30 በመቶ ያነሰ ድርሻ ያለው ከስምንት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ጫና ሊፈጠርባቸው እንዲሚችል የሚጠቅሱ ደግሞ ውሳኔውን ለማስቀልበስ ከባድ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋታቸውን ሲገልጹ እየተሰማ ነው፡፡ ባቫሪያ ሐበሻ ቢራን ሲቀላቀል 49 በመቶ ድርሻ ለመያዝ የ17 ሚሊዮን ዶላር አክሲዮን በመግዛት እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች