Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕፃናት መብት ሕግ አፈጻጸም ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት ተነገረ

የሕፃናት መብት ሕግ አፈጻጸም ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት ተነገረ

ቀን:

በኢዮብ ትኩዬ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገው ኢትዮጵያ የተቀበለችው የሕፃናት መብትን ማስጠበቅ የሚያስችለው የሕግ አፈጻጸም፣ በኢትዮጵያ ክፍተት እየገጠመው መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሕፃናት መብትን ከማስጠበቅ አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገውን ሕግ የማስፈጸም ክፍተት መኖሩን፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ የሚኒስትሯ ማኅበራዊ ዋስትና አማካሪ ደበበ ባሩድ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ደበበ (ዶ/ር) ይህን ያሉት ጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ አጋር አካላት በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2 ቀን 2015 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን (Univocal Health Coverage Day) ማክሰኞ ታኅሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባከበሩበት ወቅት ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው በ2073 ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ቢሆንም፣ ዕቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ተግዳሮቶች በመኖራቸው፣ የሚፈለገውን የጤና አገልግሎት በጥራትና አነስተኛ ዋጋ ለማስፋፋት ለጋሽ ድርጅቶችና ዳያስፖራው ዕገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ደበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሕፃናት መብት አፈጻጸምን በተመለከተ ለሪፖርተር ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገውን የሕፃናት መብት ተቀብላለች፣ ሕጉ አለ፣ ከማስፈጸም አንፃር ግን ክፍተት አለ፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሕጉን ለማስፈጸም መሥሪያ ቤቶችን የማጠናከር ትምህርት የመስጠትና ሌሎች መሰል ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፉ የአፈጻጸም ችግር መኖሩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁን በስፋት መኖሩን ስላስተዋለ፣ አፈጻጸሙን ለማሻሻል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶች ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች ለተለያዩ ነገሮች ተጋላጭ ናቸው ያሉት ደበበ (ዶ/ር)፣ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያና በተለያዩ ክፍሎች በተካሄዱ ግጭቶች ሴቶችና ሕፃናት በእጅጉ ተጠቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ሕፃናት፣ አዛውንቶችና የአካል ጉዳተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጣም የተጠቁ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፖሊሲ ለእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በተለይም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ክንውኑ በቂ ነው ብሎ ስለማያምን ገና በርካታ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ተገደው የተደፈሩ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወንዶችን በተመለከተ በሚኒስቴሩ በኩል ሰፊ ጥናት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

በጦርነቱ ከ800 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሞቱ የሚነገር መሆኑን፣ ለጊዜው የተደፈሩ ሰዎችን በተመለከተ በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች ጥናት እየተደረገ መሆኑንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ነው ደበበ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ያስረዱት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ፣ የፍርድ አሰጣጥ ጠንካራ እንዳልሆነ ከዚህ በፊት ሲገልጽ ነበር፡፡ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገው የሕፃናት መብት አፈጻጸም ክፍተት እንዳለበትና ጉዳዩን በተመለከተ በቅርቡ መሻሻል እንደሚኖር ጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሌላ እንደ ክፍተት ሆኖ የሚስተዋለው፣ ከተቋሙ እስከ ታችኛው (ቀበሌ) ድረስ መዋቅር አለመኖሩ መሆኑን ደበበ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ከማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከሴቶችና ከወጣቶች ጋር በተያያዘ የሚወጡ ፖሊሲዎችን የሚያስተዳድር ተቋም በቀበሌ ደረጃ አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ነው ያሉት ደበበ (ዶ/ር)፣ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚኖር ተስፋ አለ ብለዋል፡፡

በተለየ ሁኔታ የጤና ችግር የሚገጥማቸው ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን፣ ችግሩን ለመፍታት የመንግሥትን ሀብት በትክክል መመደብና የተመደበውን በጀት በትክክል የመጠቀም አሠራርን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የጤና ሽፋን ለሁሉም የሚለው መርሐ ግብር ለችግሩ መቀረፍ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ፆታዊ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሴቶችና ሕፃናት መካከል ችግር እንደገጠማቸው ለሚመለከተው አካል የሚያሳውቁት 20 በመቶ ብቻ እንደሆኑ፣ 80 በመቶዎቹ የደረሰባቸውን ጥቃት እንደማያሳውቁ ወይም እንደሚደብቁ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...