Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግብዓቶች ዋጋ መወደድ ምክንያት የኅትመት ዘርፉ ተዋንያን ሥራ እያቆሙ መሆናቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከትልልቅ እስከ ትንንሽ የኅትመት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማት፣ በግብዓት ዋጋ መወደድ ምክንያት ችግር ውስጥ መውደቃቸውንና ከሥራቸው እየወጡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ፕራና ኤቨንትስ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት፣ ከታኅሳስ 11 እስከ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው አፍሪ ፕሪንትና ፓኬጂንግ ዓውደ ርዕይ ላይ ነው፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርምርና ልማት ማዕከል  ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ አራጌ እንደገለጹት፣ በኅትመት ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማት የወረቀት ውጤቶችን በሚፈለገው መጠን ባለማግኘታቸው ከሥራቸው እየወጡ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኅትመት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት፣ በግብዓት እጥረት ምክንያት ከሥራ ገበታቸው እየወጡ መሆኑንና በዚህም ሳቢያ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአብዛኛው የመገናኛና የኢንፎርሜሽን መለዋወጫ ዘዴዎች መካከል የኅትመት ውጤቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በመጨመራቸው ሳቢያ በኅትመት ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ሥጋት ውስጥ ሊወድቁ መቻላቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

ለኅትመት የሚያገለግሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ግብዓቶችን ለማቅረብ ተቋሙ የአሥር ዓመት ዕቀድ ውስጥ አካትቶ እየሠራ መሆኑን፣ ይህንንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የጎላ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የፕራና ኤቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ በበኩላቸው፣ የኅትመት ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ዓውደ ርዕይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኅትመት ኢንዱስትሪው ላይ የሚሰማሩ ተቋሞች እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት ዓውደ ርዕይ መሆኑን ገልጸው፣ በዓውደ ርዕዩም ከ40 በላይ የዘርፉ ተዋናዮች ምርቶቻቸውን እንደሚያስተዋውቁ አብራርተዋል፡፡

‹‹በተለይም ለዘርፉ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠውና የኅትመትና የማሸጊያ ኢንዱስትሪ ፈጣን ዕድገት እንዲኖረው፣ እንዲህ ዓይነት ዓውደ ርዕይ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለሰባተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ከ3,000 በላይ ጎብኚዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የኅትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ የተሰማሩ ተቋማት መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች