Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት በሌለበት የምርት መትረፍረፍ ዋጋ የለውም!

የአገራችን የግብይት ሥርዓት በችግር የተተበተበ ነው ብለን እንደ ምሳሌ ከምናነሳቸው ጉዳዮች አንዱ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ያለመዘርጋቱ ነው፡፡ በተለይ ከገበያ ትስስር ጋር የተያያዙ ችግሮች ለግብይት ሥርዓቱ መበላሸት አንድ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡

አንድን ምርት ወደ ገበያ ለማምጣትና በቀጥታ ከሸማቾች ጋር ለማገናኘት የሚያስችል አሠራር የለም፡፡ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን እንደምንሰማው አምራቾች ያመረቱትን ምርት ለገበያ ለማቅረብ የሚቸገሩ መሆኑ ነው፡፡ የገበያ ትስስር መፍጠር ስላልቻሉ ያመረቱትን ምርት ተገቢ በሆነ ዋጋ መሸጥ ያለመቻላቸውንም ሲናገሩ እንሰማለን፡፡

አንዳንድ ቦታዎች ላይም አምርቱ የገበያ ትስስር እንፈጥርላችኋለን የተባሉ አምራቾች ምርቱ ከደረሰ በኋላ የተገባላቸው ቃል መና መቅረቱን በቀጥታ ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ እንኳን የአቮካዶ አምራቾች አምርቱ ገበያውን እናመቻችላችኋለን ተብለን የተባለው ሳይሆን ቀረ በማለት የገጠማቸውን ችግር የደቡብ፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮች በመንግሥት ሚዲያ ሲናገሩ መስማታችን አንዱ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡

በተለይ በመንግሥት ደረጃ ቃል የሚገቡ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ሳይሆኑ ሲቀሩ ለቀጣይ በአምራችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከራቸው አይቀርም፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ ፍራፍሬ የሚያመርቱ አምራቾች በዘመናዊ መንገድ የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው የደላሎች ሲሳይ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል፡፡

ሰፊ ገበያ ባለበት አገር ምርቱን በአግባቡ ወደ ሸማች ለማድረስ የሚያስችል የተደራጀና የዘመነ አሠራር ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ ምርቶች ከዋጋ በላይ እንዲሸጡና ለዋጋ ንረት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ 

አምራቹም ቢሆን ተጠቃሚ የሚሆንበት ትክክለኛ የጉልበቱን ዋጋ እንዲያገኝ የሚሆነውም የግብይት ሰንሰለቱን የሚያሳጥር የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ 

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚመረቱ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች አምራቹ የሚሸጥበት ዋጋና ሸማቹ እጅ ሲደርስ የሚገባበት ዋጋ እጅግ የተራራቀ እንዲሆን የሚያደርገውም ይኸው በሕግና በሥርዓት የሚመራ የገበያ ትስስር ያለመኖር ነው፡፡

ትስስር በመስፋቱ በአምራቾች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይገበያዩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ይኸው ያልሠለጠነውና በደላሎች መዳፍ ሥር ያለው የገበያ ሥርዓት እንዳይያዝ በመደረጉ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌሎች ምርቶችም ቢሆን ከዚህ የተለየ የገበያ ታሪክ የለንም፡፡ ይህ ከታወቀ ደግሞ መፍትሔ መፈለግ የመንግሥት ድርሻ ቢሆንም በዚህ ረገድ እየሠራ ነው ብሎ ለመግለጽ አያስችልም፡፡ ምክንያቱም በየሚዲያው የገበያ ትስስር በማጣታችን ስንቸገር፣ ለፍተን የደላሎች መጫረቻ ሆንን የሚሉ ዘገባዎች አሁንም በተለያዩ ሚዲያዎች መሰማቱ ቀጥሏል፡፡

እንደው ለማሳያ ይሆን ዘንድ በዚህ ጉዳይ የተለያዩ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችን በማነጋገር ከሠሩዋቸው ዘገባዎች የአንዳንድ አምራቾችን ቃል በጨረፍታ እንመልከት፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች አርሶ አደር ከተናገሩት ልጀምር ‹‹አርሶ አደሩ ይለፋል በደላሎች ይታለላል፡፡ በአብዛኛው ተጠቃሚዎች ደላሎች የሆነው፡፡ በደንብ እናመርታለን ደላሎችን እንዲወጡ ቢደረግ የበለጠ እንጠቀማለን፤›› ግን ይህ ባለመሆኑ አምራቹ በሞተ ዋጋ ምርቱን እየሸጠ ነው ይላሉ፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ዥሩ ወረዳ ይመረብ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች እንደ ሽንኩርትና መሰል ምርቶችን በማምረት ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ችግራቸው የገበያ ትስስር ብቻ ሳይሆን መሠረተ ልማት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ምርታቸው እየተበላሸ ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡

በዚህ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች አንድ ኪሎ ሽንኩርት አሥር ብር ድረስ እየሸጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የገበያ ትስስሩ ቢኖር ግን ይህንን ምርት በብዛት በማቅረብ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበርና ገበያንም ለማረጋጋት ይችሉ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

የጋሞ ዞን ሙዝ አምራች ደግሞ ‹‹ብዙ ገንዘብ አውጥተንና ለፍተን ያመረትነው ሙዝ ሲሸጥ ተጠቃሚ እኛ አይደለንም፤›› ይላሉ አያይዘውም ‹‹ዋጋ የሚተምነው ደላላ ነው፡፡ አርሶ አደሩ እየተኮረኮመ ነው፤›› በማለት የገበያ ትስስር ያለመኖር የደላሎች ሲሳይ መሆናቸው በምሬት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

በዚሁ አካባቢ ያሉ ሌላ ሙዝ አምራች ደግሞ የደላላች ተፅዕኖ ምን ያህል እንደሆነ ጭምር ሲገልጹ ‹‹ማሳ ላይ ያለ ምርትን እንገዛለን ብለው ከተቆረጠ በኋላ አዲስ አበባ ላይ ዋጋ ስለቀነሰ በተነጋገርነው ዋጋ አንገዛም እንባባላለን፡፡ እኛ ደግሞ ምርቱን ቆርጠናልና መቆየት ስለማንችል ባነሳ ዋጋ ለምነን እንሸጣለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ዘገባ በተሠራበት ወቅት ከአርሶ አደሩ በስምንት ብር የተገዛ ኪሎ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ አንድ ኪሎው ሙዝ በ29 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡

ይህ የሚያሳየው የገበያ ትስስር ለመፍጠር ምንም ያለመሠራቱ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ይህንን ችግር እንዲቀርፍ የተሰጣቸውን ኃላፊነት አይወጡም፡፡ እነዚህ ደላሎች በሚፈጥሩት ሸፍጥ የገበያ ትስስሩ ሊፈጠር አለመቻሉንም በአካባቢው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ጭምር ሲናገሩ ከመሰማቱ ደግሞ የችግሩን ጥልቀት ያሳያል፡፡

በአፕል አምራችነት በምትታወቀው ጨንቻ ወረዳ አምራቾችም በተመሳሳይ የገበያ ትስስር ያለመፈጠሩ የአፕል ዋጋ እንዲወደድ አድርጓል፡፡ በአካባቢው አሁን ላይ አንድ ነጠላ አፕል ከአንድ ብር ያልበለጠ ዋጋ ቢሸጥም በከተሞች አካባቢ ዋጋው እስከ 50 ብርና ከዚያም በላይ የመድረሱ አንዱ ምክንያት ይኸው የገበያ ትስስር ዕጦት ነው፡፡ አርሶ አደሮችን ዋጋን የመተን ጉልበት ማሳጣት ነው፡፡ 

በአማራ ክልል የአቮካዶና መሰል ምርት አምራቾችም በአማረ ሁኔታ ያደረሱት አቮካዶ በገበያ እጦት ስለመበላሹ ሲገልጹ ተሰምቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ችግሮች በየቦታው ይሰማሉ፡፡ መረጃዎቹ በግልጽ የሚነግሩን ነገር የገበያ ትስስር በመጥፋቱ በአምራቾች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይገበያዩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ይኸው ያልሠለጠነውና በደላሎች መንደር ሥር ያለው ገበያ ሥርዓት እንዳይዝ በመደረጉ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌሎች ምርቶችም ቢሆን ከዚህ የተለየ የገበያ ታሪክ የለንም፡፡ ይህ ከታወቀ ደግሞ መፍትሔ መፈለግ የመንግሥት ድርሻ ቢሆንም በዚህ ረገድ እየሠራ ነው ብሎ ለመግለጽ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በየሜዳው የገበያ ትስስስር ማጣታችን ተቸገርን፣ ለፍተን የደላሎች መጫወቻ ሆንን የሚሉ ዘገባዎች አሁንም በተለያዩ ሚዲያዎች መሰማቱ ቀጥሏል፡፡

ሙዝ ከሚመረትባቸው የአገሪቱ ክፍሎች አንድ ኪሎ ሙዝ ከአሥር ብር ባላነሰ ዋጋ እየተሸጠ ከምርት መገኛው በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት የችርቻሮ ዋጋው ሦስትና አራት እጅ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ሲደርስ ደግሞ በአምስትና ስድስት እጅ ልቆ 50 እና 60 ብር የመሸጡ ምክንያት እንግዲህ ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ ባለው የግብይት ሰንሰለት በመካከል ያለው ዋጋ ልዩነት ሲሠራ የዚህ አገር የዋጋ ንረት ሰው ሠራሽ መሆኑን ጭምር በደንብ የሚያሳብቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 

በተመሳሳይ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የችርቻሮ አትክልት መሸጫዎች አምስት ፍሬ አፕል የመሸጫ ዋጋው 220 ብር ገብቷል፡፡ ይህ የዋጋ ለውጥ የመጣው በጥቂት ወራት ልዩነት ነው፡፡ ከወራት በፊት አምስት ፍሬ አፕል የሚሸጥበት ዋጋ 120 ብር ነበር፡፡ ምርቱ ከሚመረትበት ቦታ ግን አምራቾች የሚያስረክቡበት ዋጋ ቢበዛ 80 ብር ነው፡፡ በመካከል ያለውን ልዩነት ሲታይ የዘመነ የገበያ ትስስር ቢኖር ወይም የግብይት ሰንሰለቱን ለመቁረጥ የሚያስችል አሠራር ቢዘረጋ እንዲህ ያሉ ምርቶችን ሸማቹ አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ ባነሰ ባገኘ ነበር፡፡

የግብይት ሰንሰለቱን ከመፍጠር አንፃር መንግሥት ትልቅ ሚና አለው፡፡ የግብይት ትስስሩን በተመለከተ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር እንደገለጹት ‹‹አምራችና ተጠቃሚውን በቀጥታ በማገናኘት የግብይት ሰንሰለቱን ማጠናከርና የገሕወጥ ደላሎችን ተፅዕኖ ማስተካከል የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡

ይኸው እንደሚታየው ሙዝ፣ ፓፓዬና አቮካዶ ተመርቷል ይባላል፡፡ ገበያ ላይ ግን እየታየ አይደለም ይህም የሆነው በደላላ ምክንያት ነው፡፡ ቲማቲም እየተበላሸ መሆኑን ጭምር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት እንዳረጉበት ማሳ ውስጥ ሆነው እዚህ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 11 ብር እየተሸጠ  አዲስ አበባ 60 ብር መሸጡ አግባቡ አለመሆኑን ገልጸው ነበር፡፡ የአስተያየታቸው ማሳረጊያም አምራቹንና ሸማቹን የሚያገናኝ ሥራ መሥራት ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡ ይህንን ማገናኘት ደግሞ የመንግሥት ዋነኛ ድርሻ ነው፡፡

ስለዚህ የገበያ ትስስሩን መፍጠር የመንግሥት ከሆነ ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ማለት ነው፡፡

ቢያንስ እንዲህ ያሉ በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን በኃላፊነት መሥራት ሳይቻል የፈለገውን ያህል ትርፍ ምርት ቢመረት ገበያን ሊያረጋጋ አይችልም፡፡ ውጤታማ ሥራው የሚመዘነው ደግሞ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ምን ያህል ጠቀመ? ገበያውስ እንዴት ተሳለጠ? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ሳያገኝ መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡

   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት