Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ የተጣራ 1.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ወደ8 በመቶ ወርዷል

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት ታክስ ከፍሎ የተጣራ 1.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና አጠቃላይ ሀብቱም 61.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩ ዳይሬክተር ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደ ተንሳይ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ከታክስ በፊት 1.76 ቢሊዮን ብር አትርፏል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ139.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ8.6 በመቶ ዕድገት እንዳለው አመልክተዋል፡፡ ከግብር በኋላ የተገኘው የተጣራ ትርፍ ደግሞ 1.34 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ112.04 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 39.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው አዲስ የብድር መጠን ደግሞ 4.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነም አመልክቷል፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 14.2 በመቶ ዕድገት ያሳየና የተበዳሪዎቹን ቁጥርም 18,234 ማድረሱን ገልጿል፡፡ ባንኩ የአጠራጣሪና የተበላሸ ብድሮች ምጣኔውን በ2013 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 3.6 በመቶ፣ በ2014 መጨረሻ ላይ ወደ 2.8 በመቶ መቀነሱንም አቶ ወልደ ተንሳይ አመልክተዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ14.3 በመቶ አድጎ 49.8 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ፣ ይህም በሒሳብ ዓመቱ 6.2 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ በመቻሉ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ባንኩ የገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር በ445,981 ማሳደግ መቻሉን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ26.6 በመቶ ብልጫ ያለውና አጠቃላይ የአስቀማጮችን ቁጥር ወደ 2.12 ሚሊዮን ከፍ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው አጠቃላይ ገቢ ሰባት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ1.2 ቢሊዮን ብር ወይም የ20.3 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ ለሚሉ ደግሞ የ24.9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 5.2 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ በበኩላቸው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 4.82 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው፣ ይህም በቀደመው ዓመት ከነበረው 4.3 ቢሊዮን ብር አንፃር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ያሳየ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደሌሎች ባንኮች ካፒታሉን የማሳደግ አጀንዳ አለማቅረቡን በተመለከተ ተጠየቁት አቶ ገነነ፣ ‹‹ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እዲያድግ ውሳኔ በመስጠቱ በዘንድሮው ስብሰባ ካፒታል ማሳደጉ በአጀንዳነት አልቀረበም፤›› ብለዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔ ላይ ግን ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ ባንኮች ካፒታላቸውን እያሳደጉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ንብ ባንክ ካፒታሉን ያለማሳደጉ ለምን? የሚል ጥያቄ በባለአክሲዮኖች ተነስቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ውድድር ለመቋቋም ምን እንደታሰበም እንዲገልጹላቸው የጠየቁም ነበሩ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደ ተንሳይ ጨምረው እንደገለጹት፣ በዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔ ካፒታል ለማሳደግ አጀንዳ ያልተያዘበት አንዱ ምክንያት ባንኩ ባለ 2013 የሒሳብ ዓመት ካፒታሉን ከአምስት ቢሊዮን ወደ አሥር ቢሊዮን ብር እንዲያድግ የፀዳ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን የውጭ ባንኮች ይገባሉ በሚል ብዙ ባንኮች ካፒታል ማሳደግ አለባች የሚለው ላይ የተለየ ምልከታቸውን ለጠቅላላ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡  

የቦርድ ሰብሳቢው ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ የውጭ ባንኮች ሲገቡ አንዱ መወዳደሪያ ወይም እነሱን ለመሳብ ካፒታልን ማሳደግ አንድ መሥፈርት ይሆናል እንጂ፣ ዋነኛ መሥፈርት ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ የውጭ ባንኮችን ለመሳብ ወይም ከእነሱ ጋር ለመሥራት ብዙ የሚያቀርቧቸው መሥፈርቶች ያሏቸው መሆኑን በመጥቀስ እነሱ የማይፈልጉት ዋና ነገር ካፒታሉ በጥሬ ገንዘብ ነው ያለው ወይስ ወደ አሴት ተቀይሯል? የሚለው ላይ ነው፡፡

ጥሬ ገንዘብ ወይም ካፒታሉ እንደ ሕንፃ ያሉ ሀብቶች ላይ ቴክኖሎጂና የመሳሰሉት ሀብቶች ላይ የዋለ ከሆነ የሚሳበቡት ስለሆነ፣ ካፒታል ማሳደግን ብቸኛ አማራጭ አደርጎ ማየት ተገቢ አይሆንም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ እንደ ሕንፃ ያሉ ሀብቶች ዋጋቸው በየጊዜው የሚጨመር በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ የሚል ምልከታ አላቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ካፒታሉ በጥሬ ገንዘብ የተቀመጠ ከሆነ ግን በኢንፍሌሽን እየተባለ የሚሄድ በመሆኑ ይቀንሳል ስለዚህ ይህ የውጭ ባንኮችን አይማርካቸውም ይበላሉ ስለዚህ ቁልፉ ነገር ካፒታሉ ምን ላይ ዋለ የሚለው በመሆኑ ካፒታል ማሳደጉ ብቻ የውጭ ባንኮችን ለመሳብ ይችላል በሚለው ላይ ብዙም የማይስማሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ካፒታልን ሀብት ላይ በማዋል ረገድ ደግሞ ባንካቸው የተሻለ አቋም ያለው መሆኑን የጠቀሱት ቦርድ ሰብሳቢው ከውጭ ባንኮች ጋር ለመሥራት ሌሎችም መሥፈርቶች ያሉና ይህንን በመድረኩ ላይ መግለጹ እንደማይጠቅም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ከውጭ ባንኮች ጋር አብሮ ለመሥራትም ሆነ ለመወዳደር በራሻችን መንገድ በቂ ዝግጅት አድርገናል፤›› ይላሉ፡፡ በቂ ሥራም እየሠራን ነው በማለት የባንካቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ 

ንብ ባንክ አጠቃላይ የሒሳብ መጠኑን 61.5 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም የ13.5 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 29 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎችን ቁጥር 410 ማድረስ ችሏል፡፡ 23 ዓመታትን የተሻገረው ንብ ባንክ 7,578 ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች