በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ መጀመሩን የከተማው ኃላፊዎችን አስታወቁ፡፡
ክልሉ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ስድስት ከተሞችን በአንድ ከተማ አስተዳደርና በአንድ ከንቲባ እንዲመሩ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሱሉልታ፣ ገላንና መናገሻ በሥሩ የሚገኙ ከተሞች መሆናቸውን የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የሸገር ከተማ በ12 ክፍላተ ከተሞች፣ በ36 ወረዳዎች፣ እንዲሁም 40 የገጠር ቀበሌዎች የተደራጀ (የተዋቀረ) መሆኑን አቶ ጉግሳ ተናግረዋል፡፡
የከተሞች ዕድገት ወደኋላ የቀረ በመሆኑና በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ አርሶ አደሮች ከመኖሪያ ቀዬአቸው በመፈናቀላቸው የሸገር ከተማ መመሥረቱን ጠቁመው፣ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የሚያስችል እንዲሆን ታስቦ ምሥረታ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ከተሞቹ ተበጣጥሰው የተመሠረቱ በመሆናቸውና የጋራ የሆነ የዕድገት ማዕከል መፍጠር ባለመቻላቸው፣ በተመሳሳይ ራዕይና የዕድገት ሒደት እንዲጓዙ በአንድ አስተዳደርና ከንቲባ እንዲመሩ መደረጉን አቶ ጉግሳ ገልጸዋል፡፡
ከተሞቹ በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ቢተሳሰሩም፣ አስተዳደራቸው የተለያየ በመሆኑ ዕድገታቸውን ወጥ ማድረግ እንዳልተቻለ ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል፡፡
ስድስቱ ከተሞች በጋራ የሚያከናውኑት ሥራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል የሚሉት ምክትል ከንቲባው፣ ዋና ጽሕፈት ቤታቸው አዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
‹‹ዋና ጽሕፈት ቤቱን ለመምረጥ የራሱ የሆነ መነሻ ተቀምጦለታል፡፡ ይህም ለሁሉም ከተሞች አማካይ መሆን የሚያስችል ቦታ ታሳቢ በማድረግ አዲስ አበባ ሆኗል፤›› ሲሉ አቶ ጉግሳ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስድስት ወረዳዎችና ዘጠኝ ከተሞች ስለሚገኙ ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር የወሰን ማካለል ሥራ መከናወኑን ያስታውሱት አቶ ጉግሳ፣ ወሰኑ ግልጽ የሆነ መለያ የለውም በሚል አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውን አክለዋል፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከረዥም ጊዜ ጥናት በኋላ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. የወሰን ማካለል ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ የወሰን ማካለሉ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ጉግሳ አስተያየት በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች ጋር የወሰን ማካለል ሥራ ባለማከናወኑ በርካታ አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፡፡ የከተሞች አስተዳደግ ሌሎችን የሚገፋ በመሆኑ ይህን አካሄድ ለመቀየር የሚያስችል ውጥን ግብ በማድረግ፣ ስድስቱን ከተሞች አንድ ላይ እንዲዋቀሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ሸገር ከተማ ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲሆን፣ እንደማንኛውም መንግሥታዊ አስተዳደር ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነቱ ሥርዓትን የሚመሩ አካላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡
ሸገር ከተማን የመሠረቱት የከተማ አስተዳደሮችና ክፍላተ ከተሞች በዋነኛነት ተጠሪነታቸው ለከተማ አስተዳደሩ ሆኖ፣ የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ወይም የክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ የሚል መጠሪያ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት የክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ በከንቲባው የሚሾም መሆኑን፣ ከንቲባው ደግሞ ዕጩ ተመራጩን ለከተማ ምክር ቤት እንዲያፀድቅለት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
በተዋረድ ክፍለ ከተማ ወረዳን ሲያዋቅር፣ የወረዳው አስተዳዳሪ በወረዳው ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀድቅለት የወረዳው አስተዳዳሪ እንደሚያሾም ታውቋል፡፡
ለአዲሱ የሸገር ከተማ በቅርቡ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ከንቲባ ሆነው መሾማቸው ተገልጿል፡፡