Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ሁለት እስር ቤቶች ውስጥ አሥር ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውን አምነስቲ...

በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ሁለት እስር ቤቶች ውስጥ አሥር ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውን አምነስቲ አስታወቀ

ቀን:

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ በአል-ኻርጅ እና አል-ሹማይሲ ሁለት እስር ቤቶች አሥር ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ፡፡

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ታኅሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንደገለጸው፣ በእስር ቤት ሞተው ከተገኙት ውስጥ አንደኛው በድብደባ በደረሰ ጉዳት የሞተ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ሕክምና በመከልከላቸው ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቁሞ፣ በእስር ላይ የሞቱ አሥር ስደተኞችን ጉዳይ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት እንዲያጣሩ አምነስቲ ጥሪ አቅርቧል። 

አምነስቲ ይፋ ያደረገው ሪፖርት አል-ኻርጅ እና አል-ሹማይሲ በተባሉ ሁለት የሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች፣ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ያለፉበትን ስቃይ የሚገልጽ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተጨማሪም ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት በጎደለውና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ባለሥልጣናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን ስደተኞቸን ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ለአጭር ጊዜ በእስር ላይ እንዲቆዩ ካደረጉ በኋላ በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ እያሰረችና በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሰች እንደምትገኝ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሔባ ሞራዬፍ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ላልተወሰነ ጊዜ ታስረው የሚቆዩበትን ሁኔታ አስከፊና ኢሰብዓዊ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ በእስር ቤት ውስጥ ለስደተኞቹ የሚያደርጉት አያያዝ የረዥም ጊዜ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ በግዳጅ ወደ አገራቸው ሊመልሷቸው እንደሚችሉ ሥጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ሰነድ በሌላቸው ስደተኛ ሠራተኞች ላይ በጀመረችው ዘመቻ አማካይነት በኢትዮጵያውያኑ ላይ ዕርምጃ እየወሰደች ነው፡፡

‹‹ካፋላ›› ተብሎ በሚጠራው ሥርዓት፣ ሰነድ የሌላቸው ስደተኛ ሠራተኞች የመኖሪያ ፍቃዳቸውን ሕጋዊ የማድረግ ዕድል በአብዛኛው የላቸውም። ሰነድ ያላቸው ሠራተኞችም ቢሆኑ በደል ከሚፈጽሙባቸው ቀጣሪዎች ከተለያዩ፣ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን የማጣት ሥጋት እንዳለባቸው የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል።

ላልተወሰነ ጊዜ፣ በአስከፊ ሁኔታ በዘፈቀደ የመታሰር ዕጣ የገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ እስራታቸውን የሚሟገቱበት ዕድል እንደሌላቸው ሪፖርቱ ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ከመቀበል ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው እንደሚሰማቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ስደተኞቹ በመረጃ ላይ ተመሥርተው፣ በነጻነት ዕጣ ፈንታቸውን በፈቃደኝነት መወሰን ባለመቻላቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ በግድ እንዲመለሱ ያደርጋል ሲል አምነስቲ ገልጿል። 

አምነስቲ ለሪፖርቱ ዝግጅት ካነጋገራቸው ውስጥ በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የነበሩ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙበት ገልጿል። እነዚህ የቀድሞ ታሳሪዎች በሪያድ ከተማ የሚገኘው አል-ኻርጅ እስር ቤት የተጨናነቀ፣ ንጽህና የጎደለው እንደነበር ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከጅዳ አጠገብ የሚገኘውን አል-ሹማይሲ እስር ቤት ኢሰብዓዊ ሲሉ ገልጸውታል። 

ስደተኞቹ በእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት ስቃይና ድብደባ እንደገጠማቸው መናገራቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ስድስት የቀድሞ እስረኞች በብረት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ መደብደባቸውን፣ በጥፊና በቦክስ መመታታቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ሙቀት ባለበት ቆዳቸው እስኪቃጠል አስፓልት ላይ እንዲቆሙ መደረጋቸውን እንደተናገሩ አምነስቲ ገልጿል። ኢትዮጵያውያኑን ለስቃይ የዳረጋቸው፣ የእስር አያያዛቸውን በመቃወማቸው አሊያም የታመሙ ታሳሪዎች ሕክምና እንዲያገኙ በመጠየቃቸው መሆኑ በሪፖርቱ ሰፍሯል። 

በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች የቆዩት እነዚህ ኢትዮጵያውያን በቂ ምግብ፣ ውኃ፣ መኝታ አለመኖሩን ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋሙ አጋልጠዋል። በእስር ቤቶቹ ውስጥ ለልጆች፣ ለነፍሰ ጡሮች እንዲሁም በጠና ለታመሙ ሰዎች በቂ የሕክምና አገልግሎት እንደማይገኝም አክለዋል። 

ሁሉም የቀድሞ እስረኞች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት፣ እስር ቤቶቹ ተባይና የቆዳ በሽታ በሰፊው የተሰራጩባቸው ናቸው። የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት አማራጭ መከላከያ ባለማቅረባቸው፣ ስደተኞቹ የቅማል ሥርጭቱን ለመከላከል የቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ ገዝተው እንደ ብርድ ልብስ ለመጠቀምና የጭንቅላታቸውን ፀጉር ለማቃጠል መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ከሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ እስረኞች ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት፣ ሳንባ ነቀርሳን በመሳሰሉ የመተንፈሻ አካል ሕመምና ተላላፊ በሽታዎች የሚሰቃዩ እንደነበር አምነስቲ ሁለት የግብረ ሰናይ ሠራተኞችን ጠቅሶ በሪፖርቱ አስፍሯል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...