Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ስምንት ተፈናቃዮች በምግብና በሕክምና እጥረት መሞታቸው ተሰማ

በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ስምንት ተፈናቃዮች በምግብና በሕክምና እጥረት መሞታቸው ተሰማ

ቀን:

  • ክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የዕርዳታ እጥረት ገጥሞኛል አለ

በኢዮብ ትኩዬ

ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በጎንደር አዘዞ ክፍለ ከተማ ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ከሚገኙ ከ2,850 በላይ ተፈናቃዮች መካከል፣ ስምንት ሰዎች በምግብና በሕክምና እጥረት መሞታቸውን የተፈናቃዮች አስተባባሪ ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ መላኩ ገብሬ ሟቾቹ ጨቅላ ሕፃናትና አዋቂዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመጠለያው ምክትል አስተባባሪ አቶ መላሽ ታከለ በበኩላቸው፣ ‹‹እስካሁን ስምንት ሰዎች ሞተዋል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ተፈናቃዮቹ ወደ ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ከተጠለሉ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን፣ እስካሁን ስምንት ሰዎች በምግብና በሕክምና እጥረት ሕይወታቸው አልፏል፤›› ብለዋል፡፡

ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ጨቅላ ሕፃናት ሲሆኑ፣ ቀሪ አምስቱ ደግሞ አዋቂዎች ናቸው ተብሏል፡፡ ከአዋቂዎቹ መካከል አንዷ አረጋዊ እናት ነበሩ የተባለ ሲሆን፣ የሞቱትም በኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ዕጦት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተፈናቃዮቹ በጦርነትና በሌሎች ተፈጥሯዊ ችግሮች ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ (መተከል ዞን)፣ ከኦሮሚያ (በተለይም ምሥራቅ ወለጋ)፣ ከአማራ ክልልና ከሱዳን ድንበር አካባቢ ወደ መጠለያ ጣቢያው የተሰበሰቡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተፈናቃዮቹ በወር 15 ኪሎ ግራም የምግብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል ቢገባላቸውም፣ ድጋፉ የሚደርሳቸው እስከ አራት ወራት ድረስ ዘግይቶ ነው ተብሏል፡፡ በወቅቱ ድጋፍ የሚያደርጉት የማዕከላዊ ጎንደር ነዋሪዎችና በጎ አድራጊዎች ብቻ በመሆናቸው፣ ተፈናቃዮቹ ረሃብ ውስጥ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ሁለት የዊልቼር ተጠቃሚዎችና ከ100 በላይ የተለያዩ የአካል ጉዳቶች ያሉባቸው ሰዎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

‹‹2,100 የሚሆኑት ተፈናቃዮች ከትግራይ ክልል የመጡ ናቸው፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የጠየቃቸው አካል እንደሌለና መመለስ እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ መንግሥት ቋሚ መኖሪያ ቦታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተያያዘም በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን ዙሪያ ከኮረምና ከማይጨው ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች መካከል ከ250 ሺሕ በላይ ለሚሆኑት ድጋፍ ማድረግ እንዳልተቻለ፣ የዞኑ አደጋ ሥጋት መምርያ ከወራት በፊት ሲገልጽ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የድጋፍ እጥረቱ እንዳልተቀረፈና ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋና ከሌሎች አካባቢዎች ከአምስት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ሰሞኑን ወደ ዞኑ በመግባታቸው ምክንያት፣ የድጋፍ እጥረቱ መባባሱንና የከፋ ረሃብ መከሰቱን የዞኑ አደጋ መከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አቶ እያሱ መስፍን፣ በጎንደር አዘዞ ክፍለ ከተማ ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ሞቱ ስለተባሉት ተፈናቃዮች መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመው ነገር ግን በክልሉ የዕርዳታ እጥረት እንደተከሰተ ገልጸዋል፡፡

በጎንደር አዘዞ ክፍለ ከተማ ቀበሮ ሜዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ስድስት ዙር ድጋፍ ቢያስፈልጋቸውም፣ ድጋፍ የተደረገላቸው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ማኅበረሰቡ ለከፋ ረሃብ ተጋልጦ ስለነበር፣ 8.7 ሚሊዮን ሕዝብ ድጋፍ እንደሚሻ ለፌዴራል መንግሥት አሳውቀው፣ 5.4 ሚሊዮን ሕዝብ መርዳት ተችሏል ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ማለት ግን የሚቀርበው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፡፡ በትራንስፖርት ምክንያት ዙሩን ጠብቆ ለተፈናቃዮች እየደረሰ አይደለም፣ ፓኬጁም ሙሉ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ እያሱ፣ ሰሞኑን ለቀበሮ ሜዳ መጠለያ ከ400 በላይ ኩንታል መላኩን አክለዋል፡፡ በአማራ ክልል 34 የመጠለያ የጣቢያዎች እንዳሉና በውስጣቸው ከ68 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸው ታውቋል፡፡

ዓለም አቀፉ ሕይወት አድን ኮሚቴ (አይአርሲ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ውስጥ የሚገኙ 20 አገሮች ከምግብ አቅርቦት እጥረት ጋር በተገናኘ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 በእጅጉ አሳሳቢ ችግር እንደሚገጥማቸው ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ ሃያ ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በቂ ምግብ እያገኙ እንዳልሆኑም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...