Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስና ዓባይ ኢንሹራንስ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማግኘታቸውን አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያና ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማግኘታቸውን አስታውቁ። 

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከታክስ በፊት 239.8 ሚሊዮን ብር ትርፍ ሲያገኝ፣ ዓባይ ኢንሹራንስ በበኩሉ ከታክስ በፊት 120.5 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን ከተቋማቱ የተናጥል የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለመረዳት ትችሏል።

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያው የ2014 ሒሳብ ዓመት ሪፖርትርን ባለፈው ቅዳሜ ታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ለተካሄደው የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ ያቀረበ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ 925.2 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ መሰብሰቡንና ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ38 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክቷል፡፡ 

ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍም 19.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ ማግኘት መቻሉን የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ከሕይወት ኢንሹራንስ ያሰባሰበው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት 13.3 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ45 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

ኩባንያው የ2014 የሒሳብ ዓመትን ሥራ ሲጀምር በዕቅድ ይዞት የነበረው ከሕይወት ኢንሹራንስ 28.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ደግሞ 1.08 ቢሊዮን ብር እንደነበር በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

የኦሮሚያ ኢንሹራስ በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ 312.6 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የካሳ ክፍያ ጥያቄ የቀረበለትና ከቀረበው የካሳ ክፍያ ጥያቄ ውስጥ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 251.5 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ገልጿል፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ31 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ኩባንያው በ2013 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን 192.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያስታውሷል፡፡ በሒደት ላይ ያሉ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎችም 660.6 ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ መያዙን የሚያመለክተው ሪፖርሩ በቀዳሚው ዓመት ለመጠባበቂያ ተይዞ የነበረው 553.5 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

በተመሳሳይ በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በሒሳብ ዓመት 13.8 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ጥያቄ ቀርቦ ከዚህ ውስጥ 10.2 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ በሒደት ላይ ላሉ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች 1.35 ሚሊዮን ብር ለመጠባበቂያ ተይዟል፡፡ ማይክሮ ኢንሹራንስ ጨምሮ የኩባንያው ሕይወት ነክ ያልሆኑ ኢንሹራንስ የካሳ ክፍያ ምጣኔ 57 በመቶ ሲሆን፣ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት 60 በመቶ ነበር፡፡

ኩባንያው በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ያለው የአክሲዮን ድርሻና በራሱ የሚያደርጋቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎች አጠቃላይ ዋጋው 1.38 ቢሊዮን ብር እንደደረሰለት ገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ በጊዜ የተገደበ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ (Fixed Time Deposit) የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ 785 ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ከዓምናው የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መሪም ጨብሳ እንዳመለከቱት ኩባንያቸው ያመለከተው የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2014 የሒሳብ ዓመት 239.8 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ አግኝቷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት አስመዝግቦት ከነበረው 141 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ2014 የሒሳብ ዓመት ትርፍ የ131 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ 1,000 ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 350 ብር ትርፍ ማስገኘቱንም ጠቅሰዋል፡፡ 

ኦሮሚያ  ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የተከፈለ ካፒታሉን በ36 በመቶ በማሳደግ 680.7 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ጠቅላላ የሀብት መጠኑን በ34 በመቶ በማሳደግ 2.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመላክቷል፡፡ ኩባንያው የቅርንጫፎች ቁጥር 56 የደረሱ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ 454 ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ከተመሠረተ አሥረኛ ዓመቱን የያዘው ዓባይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ያቀረበው የ2014 የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ደግሞ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከ424.2 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን በመሰብሰብ ከታክስ በፊት 120.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይጠቁማል፡፡ 

ዓባይ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻለው 424.2 ሚሊዮን ብር የተጣራ ዓረቦን ከቀዳሚው ዓመት በ26.6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ሪፖርቱ ይጠቁማል። 

ኩባንያው ካሰባሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 412.8 ሚሊዮን ብር ከጠቅላላ የመድን ሽፋን ቀሪው 11.3 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ካሰባሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 43.4 በመቶ የሚሆነው ከመድን ሽፋን የተገኘ ነው፡፡ በኩባንያው ሪፖርት መሠረት ባለፉት አሥር ዓመታት የዓረቦን ገቢው በአማካይ 27 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 

ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ የተሰበሰበው ዓረቦን ከቀዳሚው ዓመት የአምስት በመቶ ቅናሽ የታየበት መሆኑን የሚያመለክተው የኩባንያው ሪፖርት ለቅናሹ የሕይወት መድን ዋስትና ገበያ ውስን ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል እምብዛም በመሆኑ እንዲሁም በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ለታየው ቅናሽ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክቷል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ የተጠራ የካሳ ክፍያው 134.3 ሚሊዮን መድረሱንና ይህም በ18.7 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑንም ያመለከተው ዓባይ ኢንሹራንስ ለካሳ ክፍያ ከዋለው ገንዘብ ውስጥ 73.6 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የመድን ሽፋን ለሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት የተከፈለ ነው፡፡ 

ለሕይወት የመድን ዘርፍ ለካሳ የዋለው የገንዘብ መጠን ግን የቀነሰ ሲሆን በሒሳብ ዓመቱ ለዚህ ዘርፍ የተጣራ የሕይወት መድን ሽፋን 4.2 ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ በቀዳሚው ዓመት ከተከፈለው 8.88 ሚሊዮን ብር አንፃር ሲታይ የ51.8 በመቶ ቅናሽ ያለው ነው፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 120.5 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ41.6 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ 

ኩባንያው ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢ ደግሞ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢ 50.2 በመቶ ያደገ ሲሆን በቀዳሚው ዓመት አግኝቶ የነበረው 46.6 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውቋል፡፡ ከፍተኛ ገቢ ያገኘውም ከባንክ ተቀማጭ ወለድ ነው፡፡ 

ዓባይ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለ ካፒታሉ በ28.8 በመቶ በማሳደግ 361.2 ሚሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ የከፈታቸው ቅርንጫፎች ብዛትም 34 ደርሷል፡፡

 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች