Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበግጭትና በውዝግብ የታወከው አገራዊ ፖለቲካ ይታረም

በግጭትና በውዝግብ የታወከው አገራዊ ፖለቲካ ይታረም

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረች ሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ ዕድሜ ብታስቆጥርም፣ ተስፋና ሥጋት የተሞላበት ጉዞ ነው ስታሳልፍ የቆየችው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት እንደ አገር ሥር ሰዶ ከቆየው አሀዳዊ ሥርዓት በመላቀቅ የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር መጀመሩና ብዝኃነት ያላቸው ሕዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ታሪካቸው እየጎለበተ መምጣቱ የዚህ ዘመን መልካም ተግባር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ መለስ ቀለስ የሚል የትርክት መዛባት፣ ፍጥጫና መካረር፣ የፖለቲከኞች መፈላቀቅ፣ ግጭትና አልፎ ተርፎም የእርስ በርስ ጦርነት ከማስቀጠል አላሳረፈንም፡፡ በሒደት በተወሰነ ደረጃ የፍትሐዊነትና የሙስና ተግዳሮት ቢታይበትም፣ ከቀደሙት ሥርዓቶች በተሻለ ልማትና ያልተማከለ ዕድገት መምዝገቡም አይካድም፡፡ ሥርዓቱ አስተማማኝ ሰላምና ዴሞክራሲ ለመገንባት አለማስቻሉ ግን፣ አሁን ለደረስንበት ሥጋትና የተባባሰ ፍጥጫ ዳርጎናል የሚሉ ድምፆች እንዲበረክቱ ምክንያት ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገራችን አዲስ ዓይነት የሥራ አጥ ለውጥ መምጣቱ ያጫረውን ተስፋ፣ የሚያደፈርስ የግጭትና ያለመግባባት ፖለቲካ አገሩን አውኮት ያለውም ለዚሁ ነው፡፡ በምንገኝበት ጊዜ የፖለቲካ አኩራፊዎች (በተለይ አክራሪ ብሔርተኞች) እና የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብና ሕዝብም፣ ወደ ግጭትና ጦርነት የገቡበት ጊዜ እንደመሆኑ አደገኛና የሚያስፈራ ወቅት ነው ሊባል ይቻላል፡፡ እንዲህ ያለ አለመተማመንና ሥጋትን በሰከነ የፖለቲካ ትግል ለማስተካከል አለመሞከር ነው የመጪው ጊዜ ሥጋት፡፡

ትርምሱ ባረበበትና የንፁኃን ሞትና ስደት እየጨመረ በሄደበት፣ ዕገታ፣ ዘረፋና ውድመት ጋብ ባላለበት ሁኔታ ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ (ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ከ11 ዓመታት በኋላ መከበር መጀመሩን ልብ ይሏል) የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ ተከብሯል፡፡ በዚህ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ብዙዎቹ የመንግሥት ሹማምንት ስለአንድነትና ኅብረ ብሔራዊ አብሮነት መናገር ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ትፈተናለች እንጂ ልትወድቅ አትችልም ከማለት አልቦዘኑም፡፡ የመንግሥት ሚዲያውም ሲያስተጋባ የሰነበተው ይህንኑ ነው፡፡

በተቃራኒው የሰሜኑ ጦርነት በጊዜያዊነትም ቢሆን ጋብ ብሎ አገር ዕፎይ ያለች ቢመስልም፣ በመሀል አገርና በምዕራብ ኢትዮጵያ ዜጎች እየሞቱ፣ እየታገቱና የመንቀሳቀስ ዋስትና እያጡ መሆናቸው የተሰወረ ሀቅ አይደለም፡፡ የእርስ በርስ ግጭቱም በዋናነት በማንነት ላይ ስለማተኮሩ የውጭ ሚዲያዎችና ኢሰመኮን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አረጋግጠውታል፡፡

ሐሳባቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ አማርኛ መርሐ ግብር የሰነዘሩ የበዓሉ ታዳሚዎችም፣ አሁን በአገሪቱ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ሥጋት እንደገባቸውና  መንግሥት ለምን የንፁኃን ጉዳትና የአገር ሰላም መታወክ እንዲቆም ተግቶ አይሠራም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የአገራችን ሕዝቦች አንድነት ይበልጥ የሚጠናከርበትና መቻቻል የሚስፋፋት ሥርዓት በአግባቡ የማዘይረጋውስ በምን ምክንያት ነው? ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ እንደ ኢዜማ፣ አብንና እናት ፓርቲ የመሳሰሉትም ስለራሳቸው ድርሻ ብዙ ባይሉም መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ለነገሩ ባለፉት አምስት ዓመታትም በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ምንም ያህል ስለመደመር፣ ዕርቅና አንድነት እየተሰበከ ቢሆንም አክለው የዘውግ ፖለቲካችን በጥላቻ ትርክት እየተለወሰ ከዕለት ወደ ዕለት አገርን ወደ ከፋ አቅጣጫ እየጎተታት ነው፡፡ ምንም ያህል ለውይይትና ለድርድር ብሎም ለዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት የተከፈተ ጅምር ቢኖርም፣ ፅንፍ የረገጠው ትርክትና ተከታዩ አዲሱ ትውልድ ባለመገራቱ፣ ነጣጣይ የሕገ መንግሥት አናቅጽቱም መታረም ባለመጀመራችው የፖለቲካ ባህሉም ድክመት ተጨምሮበት ንፁኃንን ለዕልቂት እየዳረገ ከፍተኛ የአገር ሀብት እያወደመ እየሄደ ነው፡፡

የተለያዩ ምሁራንና አስተያየት ሰጪዎችም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደ አገር ከሚያግባቡን የማያግባቡ ጭብቶች ለመብዛታቸው የሕገ መንግሥቱን አለመስተካከል በዋናነት ይጠቅሳሉ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ምክክር የተዘራው የጥላቻና የውዝግብ ትርክትም አለመታረሙን እያነሱ ነው፡፡ በሚያሳዝን ደረጃ የመንግሥት ሆደ ሰፊነትና የዴሞክራሲ ምኅዳር የማስፋት ጥረት በፍረኃትና በአቅመ ደካማነት እየታየ ያለውም በፖለቲካ ሴራው መባባስ እንደሆነ በመጠቆም ጭምር ነው፡፡

በእርግጥ ከትናንት የተሻለ ዛሬ እየመጣ መሆኑ ላይ ተስፋ ያደረጉ ሰዎች ቢኖሩም፣ በመንግሥትና ፖለቲከኞች ዳተኝነት ላይ የነፃነትና የሐሳብ ብዝኃነት ምልክት የሆኑት ማኅበራዊ ድረ ገጾች አሉታዊ ሚናቸውን እያባባሱ ችግሩን አክፍተውታል፡፡ ትልልቁ ሚዲያም ቢሆን የሐሳብ ክርክርና የጋራ እሴት ግንባታ ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ሁሉም በየራሱ የማይበጅ ትርክት ውስጥ ተጠምዶ በመጠዛጠዝ ላይ መሆኑ  የፖለቲካው አንድ ጋሬጣ ሆኖ ይገኛል፡፡

በአገር ሰላምና አንድነት ግንባታ ረገድ ትንሽም ቢሆን ተስፋ የሚጣልባቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች (የጋሞ አባቶች ዓይነቶቹ) እና አባ ገዳዎች  ቢሆኑም በፖለቲካው ተፅዕኖ ውስጥ ከመውደቅ ሊድኑ አልችሉም፡፡ በዝምታ ውስጥ ተቀብረው የጎላ የአስታራቂነት ሚናቸውን አለመወጣታቸውም ብዙዎችን እያሳዘነ ይገኛል፡፡ የአገራችን ምሁራን ሚናም ከራስ ወዳድነትና አካባቢያዊነት ተላቆ አገራዊና ዓለም አቀፋዊነትን አለመላበሱ በተደራጀና በጎላ መልክ ተፅዕኖ መፍጠር አልቻለም፡፡ ለምን ብሎ መነሳት ያሻል፡፡

በመሠረቱ በአገሪቱ ለውጥ ከተጀማመረ በኋላ እንደ ሥልት ኦሮማራን የመሰሉ ታክቲካዊ ጥምረቶች ቢታዩም፣ እምብዛም አመርቂ ውጤት አልታየባቸውም፡፡ እንዲያውም ብዙ ተቀናቃኝ ነው ያተረፉት፡፡ እነዚህ መርህና ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ያላጀባቸውና በግለሰቦች ግንኙነት ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ የሚመስሉ ጥምረቶች ለምን ውጤት አላመጡም ብለው መታየት አለባቸው፡፡ መላው የአገሪቱ ሕዝቦች ተቻችለውና ተሳስበው የሚኖሩበትን ዕድል ማምጣትም የሚችሉ ሥልቶችም መቀየስ አለባቸው፡፡

በምንገኝበት ሁኔታ እምብዛም የሕዝብ ምክክር ሳይደረግ፣ በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ብቻ ሊተገበሩ የሚሞከሩ ማሻሻያዎች (በተለይ በአዲስ አባባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ መሰቀል፣ የከተማዋ አከላል መቀየር፣ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር መቀያየር…) በርከት ያለው የከተሜ ሕዝብና በተለይ የተማረው ኃይል፣ ‹‹በአገሪቱ በአንድም በሌላም፣ የሚጋጩ ህልሞችን አስታርቆ አገርን ሊመራና ቢያንስ አቀራርቦ ሊያስቀጥል የሚችል ወገን የለም›› የሚል የተምታታ ስሜት ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ነው፡፡ ያለመግባባትና የግጭት መንስዔዎችም ሆኗል፡፡ የዚህች አገር ጣጣ ፈንጣጣ ገና ያልወጣና መጪው ጊዜም አስፈሪ እንደሆነ እየተነገረ የሚገኘውም ከዚሁ አኳያ ነው፡፡

በዚህ አካሄድ ዛሬም ሆነ ወደፊት እንደ አገር ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሳይመጣ፣ በብሔር ባርኔጣ ብቻ እያሰሉ ማሻሻያ ለማድረግ መሞከር የሚያዋጣ አይመስልም፡፡ ለነገሩ ይህንኑ አስመልክተው ዓብይ (ዶ/ር)ም አጠቃላይ የአገሪቱ ችግር ሳይፈታ የየትኛውም መንደርና ማንነት ችግር አይፈታም ሲሉ ነበር የተናገሩት በሰሞኑ ሕገ መንግሥታ በዓል ላይ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ቀደም ትክክል ያልነበረና ኢፍትሐዊ አካሄድ ሆኖ የቆየን አሠራር ማስተካከል ቢያስፍልግ እንኳን፣ ሕዝብን ሳያሳምኑ በትርምስና በኃይል ለማረም መሞከር ለምን አስፈለገ የሚል ሒስ እየቀረበ ነው፡፡

እውነት ለመናገር እንደ አገር ሕዝቡ ተደማምጦና ተግባብቶ የመኖር ችግር የለበትም፡፡ ለዘመናትም ኖሮበታል፡፡ ትልቁ ችግር ቆስቋሽ ግን የፖለቲካ ልሂቁ ነው፡፡ በተለይ በማይታረቁ ህልሞች የሚባዝን የቡድን ፍላጎት ከአገር ጥቅም የበለጠባቸው ግለሰቦች፣  አገራዊ መንግሥቱን ክፉኛ እየፈተኑት መሆኑን መጠራጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ  በዚያም በዚህም ያለ ኃይል አገርና ሕዝብን ወደ መቀመቅ ይዞ ሳይወርድ ከወዲሁ መገሰጽ ነው ያለበት የሚሉ ሚዘናዊና መሀል ላይ ያሉ ዜጎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡

የአገር ብልፅግናንም ሆነ ዴሞክራሲውን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ሰላምና ደኅንነትን በጋራ ማረጋጋጥ ያስፈልጋል፡፡ የተረጋጋ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ብሎም አገራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚቻልበትም ሁኔታ የሚፈጠረው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ቀስ እያለ ወደ ትርምስና አገራዊ ቀውስ የሚገፋውን መካረር ለማስቆም ነው መረባረብ ያለባቸው፡፡

በሰከነ መንገድና በሠለጠነ ሁኔታ መነጋገርና ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የለውጥ ዕርምጃም የወሰደውን ጊዜ ያህል ቢወስድም በሕዝብ ይሁንታ መፈጸም ይበጃል፡፡ በሒደት ዴሞክራሲንም እየገነቡ በኃይል ሳይሆን በሠለጠነ ምርጫ ሥልጣን ለሚረከብ ወገን ዕድል ማመቻቻትም ይኖርባቸዋል፡፡ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውም ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው የመንጋ አካሄድም ሆነ ሥርዓተ አልበኝነት ከወዲሁ በሕግ ሊዳኝ ነው የሚገባው፡፡

እስካሁን በመጣንበት መንገድ እንደ አገር የረዥም ታሪክ ባለቤቶች ብንሆንም፣ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ረገድ ትርጉም ያለው ምዕራፍ አልነበረንም፡፡ ለአብነት ያህል ከ1983 ዓ.ም. በፊት በአገራችን ለሥልጣን የሚወዳደር ፓርቲ ማቋቋም በራሱ ከባድ ወንጀል እንደነበር ይታወቃል። በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ለነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባዳ ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ የተደራጀና ተቋማዊ ተቃውሞን ማስተናገድ ለቅድመ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልሂቃን (ያ ሁሉ መስዋትነት ተከፍሎም) የማይታሰብ ነበር መባሉም ለዚሁ ነው፡፡

ያለፈውን የሩቁ ዘመን የፖለቲካ ትግል አቆይተን  ባለፉት 33 ዓመታት በአገሪቱ ሰማይ ሥር በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ሕዝብ የከፈለውን መከራና እንግልት መዘንጋት አይገባም፡፡ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ አገሩን ለመቀየርና ለሌላ አዲስ ምዕራፍ ነበር ዋጋ መክፈል ያለበት፡፡ አደራን ቸል እያሉ ግን በታለፈው የኪሳራ አካሄድና  የተበላሸ መንገድ ለመቀጠል በመሞከር አትራፊ ሳንሆን፣ ሁላችንንም ወዳቂ ነው የሚያደርገው፡፡ አገር እንደ አገር እንዳትቀጥል የሚያስከተለው ዳፋም የከፋ ነው የሚያደርገው፡፡

እንግዲህ ከከፋው ችግርና ወደ አደጋ ከሚወስደው መንገድ እንዴት እንውጣ ነው ብሎ ማሰላሰል የሚያስፈልገው፡፡ በቀዳሚነት በአክራሪና ፅንፈኛ ጦማሪያን፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አማካይነት እዚያና እዚህ የተወጠረ የፖለቲካ ንትርክትን ከምኅዳሩ ማውጣት፣ አለመቀበልና አለመከተል የዜግነት የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ነጋዴዎችንና የቀውስ አዙሪት ተመላላሾችን አንጓሎ ለመጣልም እርስ በርስ መተማመንና የአገርን ጥቅም ማስቀደም ይበጃል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ‹‹ያገባኛል!››  የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችና አካላት ከታሪክ ተምረው፣ በሥራ ላይ ያለውን  ሕገ መንግሥት ጨምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተረጋገጡላቸውን መብቶችና ግዴታዎች ብቻ እንዲጠቀሙ፣ መንግሥት  አስፈላጊውን ጫና ማሳደርና ማስቆም ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡም የተጣለበት ታሪካዊ ኃላፊነት ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝቦ አገሩን ከፅንፈኞች ለመታደግ በአንድ ላይ መነሳት አለበት፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት ገዥውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን ፓርቲዎች በማሳተፍ ሚዲያዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ አክቲቪስቶችና የዴሞክራሲ ተቋማት የተካተቱበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራና ሕግ የማክበርና የማስከበር ተግባር ይጠበቅበታል፡፡ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ወገኖች (በትጥቅም በሰላምም ጎራ ካሉት ጋር) ድርድር የማድረጉ ሒደትም፣ ካለፉት ጊዜያት በተሻለና ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰ መንገድ አጠናክሮ መጀመር አለበት፡፡ አሁናዊ ግዴታም ነው፡፡

የሚካሄዱ  ውይይቶችና ድርድሮችም ዋነኛ ማጠንጠኛቸው አገርና ሕዝብ መሆን አለበት፡፡ አንዱ በሌላው ጫማ ላይ እየቆመ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ መነሳትም የሁሉም አገራዊ አደራቸው ነው፡፡ በዚሁ ሥር ሁሉም ሒደቶች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን የተከተሉ፣ የሕግ የበላይነትንም ያረጋገጡ መሆን እንዳለባቸውም ነጋሪ አያስፈልገውም፡፡ ሀብት፣ ሥልጣንም ሆነ ታዋቂነት ጊዜያዊ እንደ መሆናቸው ዘላቂዎቹን አገርና ሕዝብ ማትረፍ ነው ለማንም የሚበጀው፡፡

በምንገኝበት ሁኔታ አየሩን የሞላውን የጥላቻ ፖለቲካና የተዛባ ትርክት በማስወገድ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩንና ባህሉን ይበልጥ ለማስፋት መነሳትም በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ሳይሆን፣  በውይይትና በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችንና አማራጮችን በዕውቀትና በእውነት ሚዛን እየለኩ እንደ ግብዓት በመጠቀም፣ ለቀጣይ መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል መነሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህም በአገር ግንባታ ሒደት ውስጥ መቼም ቢሆን የማይቋረጥና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

ከመንግሥት ውጭ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃንም ይኽው ጉዳይ ይመለከታቸዋል፡፡ በመሠረቱ እኮ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር የፓርቲዎችን ዴሞክራሲያዊ ባህልና  የእርስ በርስ ግንኙነት ብቻ አይደለም የሚያጠናክረው፡፡ ይልቁንም አዲሱ ትውልድ ከተካረረ ጥላቻና የንቁሪያ ፖለቲካ እየወጣ፣ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግም ያስችላል፡፡ አገር ለማረጋጋትና ለማዘመን ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖራቸውን የማይነጣጠል አስተዋጽኦ በተግባር ለማየትም ይረዳል፡፡

እውነት ለመናገር እስካአሁን በአገራችን ተጀምረው በከሸፉትም ሆነ ዴሞክራሲያዊነትን አሟልተው ባለመያዛቸው በተወለካከፉት የለውጥ ሒደቶች፣ ወይም በሒደቱ በባከነው የአገር ሀብት ብክነት ተወቃሾቹ መንግሥታት ብቻ አይደሉም፡፡  መጠኑ ይለያይ እንደሆነ እንጂ ሕዝቡ ራሱ (በጋራም በተናጠልም)፣ እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተወቃሽ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ግን እስከ መቼ አንዱ አንዱን እየወቀሰ ይቀጥላል ነው ጥያቄው መሆን ያለበት፡፡

አሁን ጭምር እየተፈጠሩላት መቆራቆሶች የተዛባው ታሪካችንና ራሱ ያለፍንበት የፖለቲካ ትግል ታሪካችን የሚያሳደረው አፍራሽ ተፅዕኖም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ይህን እውነት ተገንዝቦና አንዱ የሌላውን ስሜትና ነባራዊ ሁኔታ እየመዘነ ችግሮቻችን መፍታትስ እንዴት ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ለኖርን ሕዝቦች (በተለይ ለምሁራን) ከባድ ሆነ ብሎ መቆጨት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም እየታያ ያለውን የሁከትና የፉክክር አልባሌ ድርጊት አቁሞ፣ ካልሰመረው ታሪካዊ ዳራ በመውጣት በአገራችን የዴሞክራሲ ጅማሮ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ሁሉም ሊተጋ ይገባል ነው ማለት የሚቻለው፡፡

ለሁሉም ወገኖች ቢሆን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ትግል የፖለቲካ ፍላጎትን በሕዝብ ላይ ለመጨን መሞከርም ተያይዞ ከመጠፋፋት የተሻለ ዕድል ሊፈጥር እንደማይችል ማስተዋል ይገባል፡፡ መብትን ለማስከበር በሚል በፀጥታ ኃይል ላይ ጫና እያሳደሩ፣ በሰላም ውሎ ማደር የሚሻውን እያወኩና አገር እያደናቀፉ መኖር ፈጽሞ የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ ያውም አሁን፡፡

ጥገኞች ከለውጡ ማዕበልና የሕዝብ ትግሉ ለመትረፍ ብለው ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት ዓይነት የአመፅ ጥሪ እያስተጋቡ የደሃ ልጅን ከመማገድ መቆጠብም አለባቸው፡፡ የትኛውንም የፖለቲካ ትግል ሰላማዊና ሕጋዊ ወደ አልሆነ አቅጣጫ መግፋት እንደ አገር ተጨማሪ ዕድልም እንዳያሳጣን መሥጋት ይገባል፡፡ ዳፋው ለውጭ ጠላቶችና ለውስጥ አድፋጭ ሽብርተኞች ሰፊ በር እየከፈተ ውርደት እንዳያስከትልብን እንጠንቀቅ (ይህ ነገር አሁንም አልተጀማመረም ለማለት ስለሚከበድ ቆም ብሎ መመርመር ግድ ይለናል)፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሕገወጥ አካሄድ ደግሞ ዋነኛው ተጎጂ ሕዝቡ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በግጭቱ አራማጆችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ያለ ጥርጥር የንፁኃን ደም ይፈሳል፣ ሕይወት ያልፋል፡፡ የታሰቡና ያልታሰቡ፣ የሚጠበቁና በፍፁም ያልተጠበቁ በርካታና ከፍተኛ ጉዳቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ አብዮት ማስነሳት ቀላል ባይሆንም ማቆሙ ግን ይበልጥ የከበደ ነው፡፡ ይህን ባለመረዳት ወይም በድፍረት በተለይ አዲሱ ትውልድ አገርን ወደ ቀውስ እንዳይገፋ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...