Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በባትሪና በሶላር የሚሠራ የመኪና ፈጠራዋን ዕውን ለማድረግ ድጋፍ የምትሻው መምህርት 

ትውልድና ዕድገቷ ደቡብ ክልል ምዕራብ ዓባያ ብርብር ከተማ ነው፡፡ የልጅነት ህልሟ የሕክምና ባለሙያነት ቢሆንም፣ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪዋን ያገኘችው በሲቪል ምሕንድስና ነው፡፡ ሰሞኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የኢንተርፕሩነር ሳምንትም ፈጠራ ሥራዋን ለማቅረብ ከወረዳዋ ጀምሮ በርካታ ውድድሮችን አልፋለች፡፡ የብዙዎችን ቀልብ የገዛውን የፈጠራ ሥራዋንም አቅርባለች፡፡ መምህርት ጽዮን መንግሥቱ ከዓለም አቀፍ፣ በአኅጉርና እንደ አገር ያለውን የነዳጅ ውድነትና ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሥራ መሥራቷን ትገልጻለች፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ በገጠራማና በከተማ አካባቢዎች ያለውን የትራንስፖርት እጥረትና ውድነት በተወሰነ ደረጃ ያቃልላል ብላ በማሰቧ የሠራችው እንደሆነም ታክላለች፡፡ መምህርት ጽዮን ስለ ፈጠራ ሥራዋና ዕቅዶቿ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትሽን ካጠናቀቅሽ በኋላ ሥራ እንዴት አገኘሽ?

ጽዮን፡- ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ እንደ አብዛኛው የምሕንድስና ተማሪ ሥራ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ዓይቻለሁ፡፡ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ወጣ ባለችው ሐመር ወረዳ በሚገኘው ቱርሚ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ማስታወቂያ በመውጣቱ ዕድሉን ለማግኘት ወደ አካባቢው አቀናሁ፡፡ በሐመር ወረዳ የሚገኘው ቱርሚ ኮንስትራክሽንና ኢንዱትሪ ኮሌጅ መምህር ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ እኔን ጨምሮ ሃያ ሥራ ፈላጊዎች አመለከትን፡፡ ከተወዳደሩት ውስጥ እኔና አንድ ሥራ ፈላጊ ለመምህርነት አለፍን፡፡ ኮሌጁ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ፣ እኔና የሥራ ባልደረባዎቼ ከምንኖርበት መንደር እስከ ኮሌጁ ድረስ ሦስት ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ ስድስት ኪሎ ሜትር ተጉዘን እናስተምራለን፡፡ አካባቢው በጣም ሞቃታማ በመሆኑ ብዙ ሥራ ፈላጊዎች አይመርጡትም፡፡ በኮሌጁ እኔን ጨምሮ ሦስት የሴት መምህራን ብቻ ነው ያለነው፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም ሴቶች ውኃ ለመቅዳትና እንጨት ለመልቀም በባዶ እግራቸው ረዥም ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ማየቴ በኤሌክትሪክና በፀሐይ ብርሃን የሚሠራ መኪና ለመሥራት  አንድ ምክንያት ሆኖኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ፈጠራሽ ብታብራሪልን?

ጽዮን፡- የሠራሁት ሰው መያዝ የሚችል በሶላርና በኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚሠራ መኪና ነው፡፡ በሥራ ፈጠራ በተዘጋጀው መድረክም ብቸኛዋ ሴት እኔ ነበርኩ፡፡ ገጠራማ የሐመር ወረዳ ነዋሪዎች በውኃ እጥረት፣ በኤሌክትሪክ ዝርጋታና የትራንስፖርት ችግሮች ምክንያት ኑሮዋቸው አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ አንዱ ምክንያቴ ሲሆን ሌላው በኮሌጃችን ያሉ መምህራን በየዓመቱ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች የመሠራት ልምድ እንዳላቸው ማየቴ ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ማበልፀግ በኮሌጅ የሥራ ዕድገትና ዝውውር ለማግኘት ያግዘናል፡፡ እኔም መኪናውን ለመሥራት ችያለሁ፡፡ ምንም እንኳን በኮሌጁ መሥራት ከጀመርኩ አንድ ዓመት ብቻ ቢሆነኝም፣ የፈጠራ ሥራዬን ለመሥራት በቂ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂዎችን የምንሠራው የአካባቢውን ችግሮች መነሻ በማድረግና ማኅበረሰቡን ለማገዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት የተማርሽው ትምህርት ወይም ሙያ አግዞሻል?

ጽዮን፡- ትምህርቴ ከፈጠራ ሥራዬ ጋር ተዛማችነት የለውም፡፡ ከትምህርቴ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ብቻ ብዙ ማንበብ፣ ጥናት ማድረግና መልፋት ነበረብኝ፡፡ የተማርኩት ሙያ ለፈጠርኩት ወይም ላበለፀኩት ቴክኖሎጂ ምንም ዕገዛ ባያደርግልኝም መረጃዎች ለማግኘትና ለመፈለግ ረድቶኛል፡፡ በኮሌጁ መኪና ለመሥራት ሐሳቤን ሳቀርብ አለቃዎቼ አልተቃወሙኝም፡፡ ይህም ለእኔ ጥሩ አጋጣሚና ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ ከፈጠራ ሥራዬ በፊት ስለ መኪና ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን በማንበብና ጥናት በማድረግና ባለሙያዎችን በመጠየቅና በመሞከር ለውጤት በቅቻለሁ፡፡ በደቡብ ክልል በአጠቃላይ ከሚገኙ የፈጠራ ሥራዎች ተወዳድሮ አንደኛ የሆነው የእኔ ሥራ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባዘጋጀው መድረክ  ክልሌን ወክዬ ሥራዬን አቅርቤአለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወጪውን ማን ሸፈነልሽ? መኪናውን ለመገጣጠም የጉልበት ሥራውን ማን ረዳሽ?

ጽዮን፡- የመኪና ወጪውን የሸፈነው ኮሌጁ ነው፡፡ መኪናው በፀሐይ ብርሃን በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር በኤሌክትሪክ ከሆነ ደግሞ 120 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡ መኪናውን ለመሥራት ከምኖርበት ሐመር ወደ ጂንካ ከተማ በአንድ የግለሰብ ጋራዥ ተከራይቼ ነበር፡፡  የጋራዥ ባለቤቱ አቶ ብሩክ ታደለ ይባላል፡፡ በወር የተወሰነ ክፍያ እየከፈልኩት የመኪና ቦዲውን ለመሥራት ብዙውን ሥራዎች አግዞኛል፡፡ የመኪና አካሉን ለመገጣጠም እኔን ጨምሮ ሦስት የጋራዥ ባለሙያዎች አግዘውኛል፡፡ ነገር ግን በዋናነት ከአቶ ብሩክ ጋር ብዙ የመኪናውን ክፍል በጋራ ገጥመናል፡፡

ሪፖርተር፡- መኪናውን የሠራሽበትን ጥሬ ዕቃ ከየት አገኘሽ?

ጽዮን፡- አብዛኛውን ነገሮች ኮሌጁ ውስጥ ከነበሩ የተበላሹና ጥቅም ከማይሰጡ መኪናዎች ወስጄ ነው የተጠቀምኩት፡፡ መሪውንና ሌሎችም ነገሮች ከተበላሹ መኪናዎች ወስጃለሁ፡፡ የተቀረውን የመኪና ባትሪ፣ ሶላር፣ ላሜራና ሌሎችም ነገሮች በግዥ ነው፡፡ የትራንስፖርት ወጪ፣ የተገዙ ዕቃዎች፣ የሰው ኃይል፣ የመብራት፣ የጋራዥ ኪራይን ጨምሮ መኪናውን ለመሥራው 400,000 ብር ጨርሶብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- መኪናውን ሠራሽ ከዚያ በኋላ ለገበያ ለማቅረብ የተመቻቸ ሁኔታ አግኝተሻል? ያጋጠሙ ችግሮችስ አሉ?

ጽዮን፡- አሁን ላይ አቅም ካለቸውና ሐሳቤን በተሻለ ሁኔታ ወደ ቢዝነስ መቀየር ከሚችሉ ሰዎች ጋር መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ መኪናውንም አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ወይም ለማዘመን ጥናቴን አጠናቅቄያለሁ፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ ከሚፈልጉ ባለሀብቶች ጋር መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ከገጠሙኝ ችግሮች በዋናነት የነበርኩበት አካባቢ ገጠራማና መኪና የሌለበት በመሆኑ ጂንካ ከተማ ድረስ በመጓዝ ሥራዎቼን መሥራቴ ይጠቀሳል፡፡ በአካባቢው መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ቢሟሉ ብዙ ወጪዎችን ማዳን ያቻል ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢንተፕሩነር ሳምንት ምን ጠብቀሽ ነበር?

ጽዮን፡- በኢንተርፕሩነር ሳምንት በርካቶች የፈጠራ ሥራዬን ዓይተውታል፡፡ የፈጠራ ሥራዎች የውድድር ውጤት ላይ ግን ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡ ኅዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የፈጠራ ሥራዎች በተሸለሙበት ቀን፣ ከዘጠኝ የሥራ ፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ስድስተኛ መውጣቴ አሳዝኖኛል፡፡ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን፣ የሽመና ማሽን፣ የጣውላ መሰንጠቂያ ማሽንና ሌሎችም የፈጠራ ሥራዎች የመጀመርያ ሆነው ተሸልመዋል፡፡ የተናደድኩት ቅሬታዬ ለምን ተሸለሙ? የሚለው ሳይሆን ‹‹መብራት፣ ትራንስፖርትና ሌሎች መሠረተ ልማት ከሌለበት ከተማ ለመጣ ፈጠራ ሥራ ቦታ ባለመሰጠቱ ነው፡፡ የወድድሩ መሥፈርትም ስለፈጠራ ሥራው ማብራሪያ የሚሰጥ ሰፊ ዶክመንት፣ ዲዛይንና ቴክኖሎጂው፣ ፋሲሊቲው፣ የውጭ ምንዛሪን የሚያድን፣ ችግር ፈቺና ሌሎች መሥፈርቶች አሉት፡፡ የፈጠራ ሥራዬ የተጠቀሱት መሥፈርቶችን ያሟላ ነው፡፡  የተሰጠኝ ደረጃ ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንም ከመጨረሻዎቹ ተርታ በመሠለፌ ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም፡፡ በወቅቱ የነበረኝ ስሜት ጥሩ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት የፈጠራ ሥራዬን የተሻለ ለማድረግ እልህ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ፈጠራ ሲታሰብ ብዙ የፈጠራ ሥራዎች፣ ውድድር፣ ሥራን ወደ መሬት ማውረድና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖሩን አውቄያለሁ፡፡ ሌሎች ወጣቶችም በቅድሚያ ሥነ ልቦናቸውን አዘጋጅተው ወደፊት መጓዝ አለባቸው፡፡ በሐመር ወረዳ የሚገኘው የቱርሚ ኮሌጅ አመራሮች በተቻላቸው አቅም አግዘውኛል፡፡ ነገር ግን ፌዴራል ላይ ነገሮች ውስብስብ ናቸው፡፡ የፈጠራ ባለሙያዎችን እንዲሠሩ ከማበረታታት በዘለለ ሥራቸውን ለገበያና ለማኅበረሰቡ የሚያቀርቡበት መንገድ የለም፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችን ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኖ አግኝቼዋሁ፡፡ ሌሎችም ሥራዎችን ለመሥራት መንገድ ላይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ በሶላር የሚሠሩ ለግብርና ሥራ የሚያግዙ አዳዲስና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎቿን ለመሥራት በሒደት ላይ እገኛለሁ፡፡  ለአሁኑ ግን  ከእኔ ዕውቀቱን በገንዘብ የሚገዛኝና አብሮኝ የሚሠራ ሰው እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ከውጭ መግባቱን የምታበረታታ አገር ናት፡፡ የእኔ ፈጠራ በደንብ ቢታገዝ ብዙ የውጭ ምንዛሪን ወጪ ማዳን ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...