Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ከሕገ መንግሥቱ በማፈንገጥ የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀልና መዝሙር እንዲዘመር ማድረግ የሕግም ሆነ...

‹‹ከሕገ መንግሥቱ በማፈንገጥ የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀልና መዝሙር እንዲዘመር ማድረግ የሕግም ሆነ የሞራል ተቀባይነት የለውም›› የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የኦሮሚያ ክልል መገለጫ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀልና የክልሉ ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘመር የሚደረገው ጥረት፣ የሕግም ሆነ የሞራል ተቀባይነት የለውም ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ታኅሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሪፖተር በላከው መግለጫ፣ የኦሮሚያ ክልል ሊያገኛቸው የሚገቡ ልዩ ልዩ ጥቅሞችና የአፈጻጸም ሥርዓት በግልጽ በሕግ ባልተደነገገበት ሁኔታ፣ በትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘምሩ የማስገደድ ድርጊት፣ በግለሰብ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየተፈጸመ መሆኑንና የፌደራል ሥርዓቱን መሠረታዊ መርህ የሚጥስ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ድርጊቱ በሕዝቦች መካከል ፀንቶ የኖረውን የአንድነትና የእኩልነት መስተጋብር እሴት የሚበጣጥስና ለመልካም አስተዳደር ዕጦት መስንዔ በመሆኑ፣ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የክልል መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ የክልሉን ሕዝቦች የማንነት፣ ባህል፣ የወደፊት ተስፋ፣ ያለፈ ታሪክ ማንፀባረቂያ መሣሪያ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ዓይነት የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከትና ባህላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ እንዲሆኑ በሕግ መደንገጉን አስታውሷል፡፡

በመሆኑም በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሠረት የአማራን፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን፣ የሲዳማን ወይም የሌላ ክልልን ባንዲራ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ በትምህርት ቤት ማውለብለብና የክልል መዝሙር እንዲዘመር ‹‹ማስገደድ የሕግም ይሁን የሞራል መሠረት አለው ብሎ ተቋማችን አያምንም፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

‹‹የአንድን ማኅበረሰብ እሴት አዝሎ የሌላውን አንጠልጥሎ የሚገነባ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የእንቧይ ላይ ካብና ኢዴሞክራሲያዊ መሆኑን ተቋማችን ልብ ይለዋል፤›› ብሏል፡፡

በመሆኑም የክልል ሰንደቅ ዓላማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ይሰቀል የሚባልበት በቂ ምክንያት የሚኖር ከሆነም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ፈቃድና ይሁንታ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (የከተማ ነዋሪዎች) የሚወከሉበትና የፌደራሊዝም መርህ የሆነው የጋራ አስተዳደር ተግባራዊ የሚደረግበት የአስተዳደር እርከን መሆኑን ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ አስታውቋል፡፡ አክሎም በሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንደተቀመጠው የአዲስ አበባ ከተማ የአማራው ወይም የትግራዋይ፣ የወላይታ… ወዘተ ብቻ ሳትሆን የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች ከተማ መሆኗን በመግለጫው አትቷል፡፡

 ይህ በመሆኑም ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአንድን ክልል ሰንደቅ ዓላማ ለማውለብለብና የክልሉ መዝሙር በተማሪዎች እንዲዘመር በሚደረገው የማስገደድ ድርጊት ሳቢያ፣ በተማሪዎች ላይና በሕዝብ ንብረት ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂው የከተማ አስተዳደሩ እንጂ ሌላ ውጫዊ አካል ባለመሆኑ፣ ለችግሩ መንስዔ የሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡

ዕንባ ጠባቂ በመግለጫው በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚያዋስነውን ወሰን የማካለሉ ሥራ ተጠናቆ ለሕዝብ ይፋ መደረጉን በመጥቀስ፣ በዚህ ሒደት ከተማዋ የነዋሪዎቿ መሆኗን መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ ለማድረግና የክልሉን መዝሙር በግድ ለማዘመር የተደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ግጭትና ሁከት መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...