Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ለመገንባት በሁለቱ አገሮች የተያዘውን የጋራ ዕቅድ ወደ ተግባር ለማስገባት ያግዛል የተባለው የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ።

መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ሲፒሲኤስ ትራንስኮም (CPCS Transcom) የአዋጭነት ጥናቱን እንዲያከናውን ኔፓድ (NEPAD) እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በጋራ በለገሡት 3.4 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተቀጥሮ ሥራውን ለዓመታት ሲያከናውን ከቆየ በኃላ፣ የደረሰበትን የመጨረሻ ውጤት ለሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች በሱዳን ከተማ አቅርቧል። 

የባቡር መስመሩ 1522 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን የተመለከተ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚዘረጋው የባቡር መስመር መነሻውን የሚያደርገው አዋሽ ኮምቦሎቻ ወልዲያን ከሚያገናኘው የባቡር መስመር ይሆናል። በዚህም መሠረት የባቡር መስመሩ ከወልዲያ ተነስቶ በወረታ ወደ ጎንደር በመቀጠልም መዳረሻውን በመተማ ከተማ ያደርጋል። በሱዳን በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያ ድንበር ተነስቶ በጋላባት፣ ጋዳሪፍ፣ ከሰላ እና ሄያ አድርጎ መዳረሻውን ሱዳን ወደብ ላይ እንደሚያደርግ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

የአዋጭት ጥናቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዋና የትንታኔ ክፍሎች መካከል የባቡር ፕሮጀክቱ የአጭርና ረዥም ጊዜ የትራፊክ ፍሰት ትንታና ትንበያ፣ የፕሮጀክቱ ምህንድስና ዲዛይንና ልማት አንዲሁም የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖዎችን መተንተን ይገኙበታል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው የግንባታ ወጪና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን ያገናዘበ የአዋጭነት ትንነተና፣ ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድሩ የሁለቱ አገሮች ተቋማዊ አደረጃጀቶች ግምገማ፣ ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ የሚጠይቀውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችሉ አማራጮችን (የፕሮጀክት ፋይናንስ ስትራቴጂዎች) የመለየትና የፕሮጀክቱን ግንባታ በመንግሥትና የግል አጋርነት ለመፈጸም አመቺ መሆኑን መለየት የሚሉት ይገኙበታል።

የአዋጪነት ጥናቱን የሚገመግም የሁለቱ አገሮች ባለሙያዎችንና የአማካሪ ድርጅቱን ተወካዮች ያሳተፈ ውይይት ትናንት ታኅሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሱዳን ካርቱም ከተማ እንደተጀመረ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በጥናቱ ላይ ለሁለት ቀናት ውይይት ከተደረገ በኋላ ሁለቱ አገሮች የጥናት ግኝቱን በማጽደቅ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ተግባራት እንደሚሸጋገሩም መረጃው ያመለክታል።

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ አዲስ የባህር ወደብ ከመፍጠሩ በተጨማሪ በመሠረተ ልማቱ አቅራቢያና በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ አካባቢዎች፣ የኢኖሚ ዞኖችን ለመገንባት በሁለቱ መንግሥታት መካከል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ይህ ፕሮጀክት የአፍሪካ አገሮችን በትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ለማስተሳሰር ከተነደፈው የኔፓድ ማስተር ፕላን ጋር የሚጣጣም ሲሆን በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኡጋንዳ ካምፓላ ደቡብ ሱዳን ከሚያገናኘው የትራንስፖርት ኮሪደር ጋር ሊገናኝ እንደሚችል በመቀጠልም ወደ ቻድና መካከለኛው አፍሪካ ሊገናኝ እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል።

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች