Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ የከተማ አስተዳደሩንና ትምህርት ቢሮን ሊከስ መሆኑን አስታወቀ

ኢዜማ የከተማ አስተዳደሩንና ትምህርት ቢሮን ሊከስ መሆኑን አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀልና ተማሪዎች የኦሮሚያ ክልላዊ መዝሙር እንዲዘምሩ የተደረገውን እንቅስቃቀሴ እንደሚቃወም ገልፆ፣ የከተማ አስተዳደሩንና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን እንደሚከስ አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ማክሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ የተፈጸመው ድርጊት ሕጋዊ ማዕቀፍ የሌለው፣ በጽሑፍ ምንም ዓይነት መመርያ ያልተቀመጠለት፣ የኦሮሚያ ክልል ዓርማና መዝሙር አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ካልተሰቀለና ካልተዘመረ የሚል ግብግብ ነው ሲል ገልጾታል፡፡

ኢዜማ ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠው የከተማ አስተዳደሩንና የትምህርት ቢሮውን በደብዳቤ የጠየቀ ቢሆንም፣ እስከ ታኅሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ለሁለተኛ ጊዜ ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዱን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የተፈጠረውን ክስተት ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የከተማው ምክር ቤት ይህን ተግባር ለመከወን ያወጣውን የጽሑፍ መመርያ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ የሌላ ክልል ሥርዓተ ትምህርት ሲሰጥ በምን መልኩና እንዴት ሊሆን እንደሚገባ ግልጽ የሆነ የሕግ አግባብ ካለና መመርያም የተዘጋጀለት ከሆነ፣ በግልጽ ነዋሪው እንዲያውቀው እንዲደረግ ኢዜማ አሳስቧል፡፡

‹‹ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የከተማዋ ከንቲባም ቢሆኑ ለችግሩ ምንጭ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ ችግሩን ወደ ደኅንነት ሥጋትና ከሙስና ትግል ጋር የተገናኘ እንደሆነና በሌላ አካል እንደተቀነባበረ አድርገው ማቅረባቸው፣ መሬት ላይ ከሚታየው እውነት የራቀ ነው፤›› ብሏል፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሰጡኝ ባለው መረጃ ጉዳዩን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከመማርና የኦሮሚኛ ቋንቋ ከመማር ጋር ለማገናኘት የሞከሩበት መንገድ፣ ‹‹ፍፁም ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝቦች መካከል መቃቃርን የሚጋብዝ የተዛነፈ መግለጫ›› በማለት በመግለጫው አትቷል፡፡

‹‹በመሠረቱ ይህ የኦሮሚያ ክልል ዓርማ እንሰቅላለን መዝሙሩም መዘመር አለበት የሚለው አቋም ያስነሳውን ግጭት፣ አቅጣጫ ለማስለወጥና ከደኅንነት ሥጋት ወይም ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ከመማር መብት ጋር ለማገናኘት የተሞከረበት መንገድ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት ያለው አይሆንም፤›› ብሏል፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ውክልና ባላቸው የከተማዋ ምክር ቤት ተመራጮች የምትተዳደር ራሷን የቻለች ከተማ ለመሆኗ በግልጽ በተደነገገበት ሁኔታ፣ ይህንን መብት መጋፋት ‹‹ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር በገሃድ መጋጨት›› እንደሆነም አስረድቷል፡

በመሆኑም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተፈጠረው ብጥብጥ የተነሳው ሕጋዊ መሠረት የሌለው ውሳኔን ለማስተግበር በተደረገ ግብግብ መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹ከሕግ አግባብ ውጪ በማናለብኝነት ፍላጎትን በኃይል ለመጫን በተደረገ ሙከራ እስካሁን የደረሰው ኪሳራ የሚያሳዝን ሆኖ፣ ከዚህ በኋላ የከፋ ችግር እንዳይፈጠር የከተማ አስተዳደሩ በሕግና በሥርዓት የማስተዳደር ግዴታ አለበት፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

የኦሮሚያን ክልል ዓርማ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መስቀልን የአፍ መፍቻ ቋንቋን ከመማር መብት ጋር ለማያያዝ መሞከሩ ተገቢነት የሌለው መሆኑን፣ በከተማዋ በየመዋቅሮቹ የተሾሙ ባለሥልጣናት ራሳቸው የፈጠሩትን የግጭት አጀንዳ በሌሎች ለማሳበብ የሚደረገው ፕሮፓጋንዳ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ከሰሞናዊው ውዝግብ ጋር በተያያዘ ከየትምህርት ቤቱ እየተለቀሙ በግፍ የታሰሩ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱና ከኦሮሚያ ክልል ዓርማ መሰቀል ጋር ተያይዞ በተነሳ ግርግር ትምህርት የተስተጓጎለባቸው አንዳንድ ትምህርት ቤቶች፣ በአስቸኳይ ወደ መደበኛ መማር ማስተማር ተግባራቸው እንዲመለሱ ፓርተው ጠይቋል፡፡

በየትምህርት ቤቱ መግቢያ በሮች ላይ የሚመደቡ የፀጥታ ኃይሎች በተማሪዎች ላይ አንዳችም አደጋ እንዳይፈጠር የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ እንዲተገብሩ፣ ሕጋዊና ከመብት ማክበር ጋር የተያያዘውን የቋንቋ ጥያቄ ሕጋዊ ባልሆነ፣ ማናለብኝነትን በሚያንፀባርቅና ፍላጎትን በጉልበት ለመጫን መሞከር ከትርፉ ኪሳራው እንደሚበዛ ኢዜማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...