Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀሐይ ኢንሹራንስ በአመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት በሰጠው ዋስትና ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፀሐይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት፣ በፖለቲካ አመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት በሰጠው የመድን ሽፋን 58.1 ሚሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰቡን አስታወቀ። 

ከዚህ የመድን ሽፋን የተገኘው የዓረቦን መጠን ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከሁሉም ዘርፎች ለሰበሰበው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ፣ የአሥር በመቶ ድርሻ ማበርከቱም ተገልጿል።

ከሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለየ ለፖለቲካ አመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት የሰጠው የመድን ሸፋን በሒሳብ ዓመቱ ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ቀጥሎ ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ የተመዘገበበት ሊሆን መቻሉን፣ ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለፖለቲካ አመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት የመድን ሽፋን የሚሰጡ ኩባንያዎች ጥቂት ሲሆኑ፣ ኩባንያዎቹ በጥቅል ከሚሰበስቡት ዓረቦን ከዚህ ዘርፍ የሚሰበስቡት ከአንድ በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ነው፡፡ 

የፀሐይ ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ማኅደር ክብር ባቀረቡት ሪፖርት በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ማሰባሰብ የቻለው አጠቃላይ የዓረቦን መጠን 584.9 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጸው፣ ይህ የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ37 በመቶ፣ በዕቅድ ከያዘው ደግሞ የ17 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ከተሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ የተሽከርካሪ መድን ሽፋን 62.5 በመቶ ወይም 365.5 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ የተሰባሰበበት በመሆኑ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል ብለዋል፡፡ 

ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ቀጥሎ ኩባንያው የመድን ሽፋን የሰጠበት ዘርፍ በፖለቲካ አመፅና ሽብር ለሚደርስ ጉዳት የተሰጠው የመድን ሽፋን መሆኑን፣ ከዚህ የመድን ሽፋን 58.1 ሚሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰቡን አመልክተዋል፡፡ ይህም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ካሰባሰበው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ውስጥ ለፖለቲካ አመፅና ለሽብር ለሚደርስ ጉዳት የተሰጠው የመድን ሽፋን አሥር በመቶ ድርሻ ከማድረጉም በላይ፣ በዚህ የመድን ሽፋን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር መጨመሩንም ገልጸዋል፡፡  

ፀሐይ ኢንሹራንስ ኩባንያም ሆነ ሌሎች የኢንሹራስ ኩባንያዎች ብልጫ ያለውን የዓረቦን መጠን የሚያሰባስቡት ከተሽከርካሪ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል በአብዛኛው ከማሪን፣ ከሕጋዊ ኃላፊነት፣ ከገንዘብ ነክ ዋስትናዎች፣ ከእሳት አደጋና ከመሳሰሉት ሲሆን፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ ግን ዘንድሮ በተለየ በፖለቲካ አመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት የሰጠው የመድን ሽፋን ሁለተኛው ትልቁ መሆኑ ታውቋል፡፡  

በቦርድ ዳይሬክተሯ ሪፖርት መሠረት በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው ዓረቦን በዋስትና ዓይነቶች ሲታይ የሕጋዊ ኃላፊነት፣ የጉዞ ጤና መድን፣ የምሕንድስና፣ የተሽከርካሪ መድን፣ የእሳትና ተያያዥ አደጋዎች መድን፣ የገንዘብ ነክ ዋስትናና የፖለቲካ አመፅ ሽብር ለሚደርስ ጉዳት የዋስትና ዓይነቶች ከዕቅዳቸው ከ102 በመቶ እስከ 317 በመቶ ያለውን ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡

ሠራተኞች በሥራ ላይ ለሚደርስባቸው አደጋና በባህር በየብስና በአየር ለሚጓጓዙ ዕቃዎች የሚሰጥ ዋስትና ዓይነቶች የተሰበሰበው ዓረቦን መጠን ግን ከታቀደው በታች ክንውን ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በሁሉም የዋስትና ዓይነቶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ የዓረቦን ምርት አፈጻጸም የተመዘገበበት ዓመት ነበር፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሯ፣ በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለው የካሳ መጠንም በ36 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው የተከፈለው ጠቅላላ የጉዳት ካሳ ክፍያ መጠን 279.1 ሚሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም ካለፈው ዓመት አፈጻጸም 205.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ36 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል ለኩባንያው ቀርበው   በእንጥልጥል ላይ ያሉ የካሳ ጥያቄዎች 361.04 ሚሊዮን ብር መድረሳቸውን፣ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ከነበረው የካሳ ጥያቄ 325.7 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡ ለዚህ የካሳ ክፍያ መጨመር ዋና ምክንያቶች ተደርገው በሪፖርቱ የተጠቀሱት የተሽከርካሪ አደጋ መጨመር፣ የዋስትና (ቦንድ) ካሳ ጥያቄ ማደግ፣ የሕጋዊ ኃላፊነት ሽፋንና የፖለቲካ አመፅና በሽብር ለሚደርስ ጉዳት የቀረበ የካሳ ጥያቄ መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ ከተጋነነው የመለዋወጫና የጥገና የእጅ ዋጋ ጋር ተደምሮ ያስከተለው ጭማሪ ነው ተብሏል፡፡ ይህም ሆኖ የኩባንያው ጠቅላላ የአደጋ ምጣኔ (Loss Ratio) ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ69 በመቶ ምጣኔ ወደ 67 በመቶ ምጣኔ ዝቅ ያለ ሆኖ መመዝገቡን፣ የቦርድ ሊቀመንበሯ በሪፖርታቸው አካተዋል፡፡ ይህም የሆነው የተከፈሉና በእንጥልጥል ያሉ የካሳ ጥያቄዎች በዚህ ዓመት  የተመዘገቡ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከቀደሙት የሒሳብ ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የካሳ ጥያቄዎችን የሚጨምሩ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ለካሳ ክፍያ ካዋለው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የካሳ ክፍያ የፈጸመው ለተሽከርካሪዎች ለተሰጠ ዋስትና ሽፋን መሆኑን፣ የክፍያ ምጣኔውም በኢንዱስትሪው ለሞተር ኢንሹራንስ የተከፈለ ከፍተኛ መጠን ያለው መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡

ለተሽከርካሪ ዋስትና ዓይነት የተከፈለው የካሳ መጠን በአጠቃላይ ከተከፈለው ካሳ ውስጥ 225.3 ሚሊዮን ብር ወይም 81 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ ለተሽከርካሪ ዋስትና ከተከፈለው ካሳ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የሚይዘው የሕጋዊ ኃላፊነትና የገንዘብ ነክ ዋስትና ዓይነት መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ለሕጋዊ ኃላፊነት 27.5 በመቶ፣ ለገንዘብ ዋስትና 27.5 ሚሊዮን ብር መከፈሉን፣ ቀሪዎቹ የዋስትና ዓይነቶች በድምሩ 18.3 ሚሊዮን ድርሻ እንደነበራቸው ተጠቅሷል፡፡ 

ፀሐይ ኢንሹራንስ እንዲህ ካለው የሥራ አፈጻጸሙ በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በኋላ 52.5 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን፣ ይህም የትርፍ ምጣኔ ከቀዳሚው ዓመት በ23 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 180 ብር ትርፍ ማስገኘቱ ታውቋል፡፡

ፀሐይ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች 56.7 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንም ተገልጿል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን 1.3 ቢሊዮን ብር ማድረሱን፣ ከቀዳሚው ዓመት የ26 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉ 291.4 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅት 317 ሠራተኞች እንዳሉት፣ የቅርጫፎቹን ቁጥር 33 ደግሞ ማድረሱ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች