በተሾመ ብርሃኑ ከማል
ሔለን መለስ ‹‹ከመይ ዲና/መን ዲና›› (እኮ እኛ እነማን ነን?) የሚል ዘፈን አውጥታለች፡፡ ስለነሱ ከመግለጼ በፊት ስለሷ ጥቂት ልበል፡፡
ሔለን መለስ በ1966 (1959) የተወለደች ኤርትራዊት ድምፃዊትና ተዋናይት ሐትሆን የድምፃዊነት ሙያዋን የጀመረችው ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለች ነው፡፡ ቀጥሎም ሱዳን ውስጥ በተለይም ከሰላ በኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ኢፒኤልኤፍ) በተቋቋመው ‹‹የቀይ አበቦች የኪነት ቡድን›› አባል ሆነች፡፡ በ15 ዓመት ዕድሜዋም የኢፒኤልኤፍ አባል ሆነች፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ድምፃዊት ናት፡፡ ብዙ ዘፈኖችንም በአልበምና በነጠላ ዜማ ለቃለች፡፡ በድምፃዊነቷም ብዙ ተሸላሚ ናት፡፡ በዚህ ዓመት የለቀቀችው ‹‹ከመይ ዲና/መን ዲና?›› ማለትም እኮ እኛ ማን ነን? የሚል ዘፈን አላት፡፡
ሔለን በመልኳ ያደረች ስለሆነች እዚህ ላይ ስለውበቷ ሳደንቅ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ሔለን መለስ የ56 ዓመት ሴት ብትሆን በዚህ ዘፈን ከ30 ዓመት የምትበልጥ አትመስልም፡፡ አምራለች። ተውባለች። “ሲሠራት የዋለና ሲሠራት ያደረ” ትመስላለች። የኤርትራ ባንዲራን የሚወክል በዶቃ ጥንግ አሠርታ የግንባርና የአንገት ጌጥ አድርጋዋለች፡፡ በጣም ያምራል። በዚያ ላይ የኤርትራ ባንዲራ የሆነ ጉፍታ (ሻርፕ፣ አደሬ) ደርባለች። የለበሰችው ቀሚስም የኤርትራ ባንዲራ ጥልፍ ያለው ነው። ሔለን መለስ ድምፀ መረዋ ናት፡፡ የጀግንነት ዘፈን አቀንቃኝ ናት። በተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በታላላቅ ባለሥልጣኖችም ትወደዳለች። መቼም አሉባልታ ሊሆን ቢችልም በማኅበራዊ ሕይወቷ ብዙ ይባልላታል።
“መን ዲና” የሚለው በፊልም የተደገፈውን ዘፈኗ ባለሙያዎች እንደደከሙበት ያስታውቃል። የምትዘፍነው ምናልባት ምፅዋዕ/ዳህላክ ዳር ሊሆን ይችላል። በመሠረቱ የእኔን ትኩረት የሳበው መልዕክቱ እንጂ የዜማው ውበት አይደለም። እስከ መጨረሻው በትዕግሥት ታነቡት ዘንድም ግጥሟን ተቀራራቢ በሆነ ትርጉም ለመተርጎም ሞክሬያለሁ። የማይሰማኝም ነበር። የያዝኩትን ስተረጉመው እንዲህ ይላል።
ማነው? ማነው ይህ ሕዝብ?
ብሎ የሚጠይቅ ምላሰኛ ቢገጥምሽ
ነፍሴ ከቶ ምን በሆነ ምላሽሽ?
ደጋግማ ትላለች፡፡ ቀጥሎ ሦስት በወንጭፍ የሚወረውሩ ሽማግሌ፣ አሮጊትና ልጅ እግር ይታያሉ፡፡ በወንጭፍ የሚወረውሩት ወንዝ ዳር ላይ ሆነው ነው፡፡ በተለይም ትልቋ ሴት የሚወነጭፉት ማማ ላይ ሆነው ነው፡፡ ወንጭፉ፣ ማማውና ወንዙ ምን እንደሚወክል በዚህ በኩል ዕውቀቱ ያላቸው ቢተረጉሙት መልካም ነው። “ከመረብ ምላሽ ያለውን ግዛታችን ማማ ላይ ሆነን እንጠብቃለን” ማለት ይሆን? አላውቅም። ብቻ ግን ከወንጭፉ በኋላ አልፎ አልፎም በባህር ዳርቻ የተዘፈነው ይገባል፡፡ ያኔ በሚከተለው ግጥም ይዘፈናል፡፡
ብልህስ በሰፊው እጆቹን የጨበጠ፣
እያመመው ውስጡ እያበጠ፡፡
ብርቱ ችግሮች እንደላባ የቀለሉት፣
ትልሞቹ በራሱ እጅ የተነደፉት፡፡
ያ ሁሉ የጅራፍ ድምፅ እየጮኸበት
ፍንክች ያላለ ካመነበት፡፡
ባልኩት ነበር እኔ፣
ባልኩት ነበር እኔ
በባህሩ ዳርቻና ቦታው ተለይቶ ቦታ በሰው እየታጀበች ዘፈኗን ትቀጥላለች፡፡ ሰዎቹ የኤርትራን ብሔሮች ሁሉንም ዕድሜና ጾታ የሚወክሉና ቀዳዳ በማያስገባ ሁኔታ እጅብ ያሉ ናቸው። ፕሮዳክሽኑ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ሲታይ ደህና የሚባል ነው፡፡ ግጥሟ እንዲህ ይቀጥላል።
‹‹አፈነው፣ ልሳኑም ተለጎመ››
‹‹ጣልነው እንግዲህ ተዳከመ፣››
‹‹አለቀለት ወደቀ›› ሲሉት
ሰንክሎ ደፋቸውና አረፉት፡፡
በሐዲዱ ፍፁም የሌለ፣ ምክራቸውን ያልሻተ (ያልፈለገ)
የሚያብርለትን ፍለጋ ተዟዙሮ ያልተመለከተ፡፡ (አጋዥ የማይፈለግ፡፡ የማያስፈልገው)
እያለች የ”እሱን ምናልባት የኢሱን” ጀግንነቱን፣ አርቆ አሳቢነቱን ብልህነቱን በስሜት ትገልጻለች፡፡ የተጠቀሰው ትዕይንት ከታየ በኋላ አሣ አጥማጆች ይታያሉ፡፡ መጠነኛ ማዕበል የሚደፍቀው ባለ ጀልባም አለ፡፡ ሆኖም ከአሣ አጥማጆቹ አንዱ በውበቱ የታወቀውን የቀይ ባህር ዓሣ ከጀልባው በማውጣት ያራግፋል፡፡ በዚህ ትዕይንት ግጥሙና ዜማው ይንቆረቆራል።
የማይናገር ግን ደግሞ ያገኘ ተሰሚነትን፣
የማይፎክር ግን ደግሞ የሚያሳምን፣
መጥፎ ሲያልሙለት የሚያድሩትን፣
ቀድሞ ነቅቶ ያደረጋቸው ብትንትን፡፡
ይህን አልኩ እኔ፣
ይህን አልኩ እኔ።
እያለች በወሸኔ ድምጿ እየዘፈነች በብዙ ሰዎች መካከል ሆና ትታያለች፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰዎቹ በኤርትራ ውስጥ ያሉ ብሔሮችን ጾታን፣ ዕድሜንና ማኅበራዊ ሕይወትን የሚወክሉ ይመስላሉ፡፡ ድምፀ መረዋዋ ሔለን ትቀጥላለች ፤
ይህን ሕዝብ የደፈረ፣
ተናግሮ ያናገረ፡፡
ማን መልካም ሌሊት አደረ
አተርፍ ብሎ የከሰረ፣ ማን አያችሁ የከበረ፡፡
ደፍሬ ባልኩት ነበረ፣
አተርፍ ብሎ የከሰረ፣ ማን አያችሁ የከበረ፡፡
ደፍሬ ባልኩት ነበረ፡፡
ቀጥሎም ሦስት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ልብስ የለበሱ ወጣቶች ይመጣሉ፡፡ ወጣቶቹ ወጠምሻዎች ናቸው። ከፊት ለፊታቸው እግራቸው በረዥም ገመድ የታሰረ ሁለት ቡላ አህዮች አሉ፡፡ እነሱን ያልፏቸዋል፡፡ አህዮቹና አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የለበሱ ሰዎች የተገናኙት በአጋጣሚ አይመስልም፡፡ የአህዮቹ ቀለም ቡላ መሆኑም ጭምር የሚገልጸው ነገር ሊኖር ይችል ይሆን? ምናልባት የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለባሾቹ አርማ ይሆኑ? ምናልባት ምናልባት እነቡላ የአረንጓዴ ብጫ ቀይ ለባሾቹ መገለጫዎች ይሆኑ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ይህን በሚመለከት የድሮው የኢትዮጵያ ወታደሮች ሐሳብ ይኖራቸዋል ብዬ እገምታለሁ።
ድምፀ ጣፋጯና መልከ ሸጋዋ ሔለን መለሰ ግን እንዲህ ትለናለች፣
አያውቁም እንዴ፣ እኛ ለሀራችን
አያውቁም እንዴ፣ እኛ ለሀራችን
እንዴት እንደሆንን ብንጠየቅ በመሰከርንላት ሁላችን
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ለባሾቹ ወጠምሾች ሁለቱን ቡላ አህዮች አልፈው ወደ አንድ ሜዳ ሲሄዱ አንድ በጣም ግዙፍ ሰው ተንጋሎ ተኝቶ ያገኛሉ፡፡ ይህንንም ሰው አንዱ በእግሩ ረግጦ ያስነሳዋል፡፡ ግዙፉ ሰውም ተጀንኖ ይነሳል፡፡ ሦስቱ ተባብረው ዘርጥጠው ሊጥሉት ሲሉ እንደ አቧራ ከላዩ ያራግፋቸዋል፡፡ ሊይዛቸው ሲል ይበተናሉ፡፡
ሰማዩ በጥቁር ደመና ተሞልቷል፡፡
የአገራችን ሰማይ ከበደ
ነፋሱ እስኪሰክን
የአገራቸውን ሕመም ሊያስታግሱ፣
በሕይወታቸው የሚፈውሱ
ሀገሬ ባልኳቸው
ትላለች፡፡ ምን ማለቷ እንደሆነ አልገባኝም፡፡
ሆነም ቀረ በጀግንነት ዘፈን አቀንቃኝነቷ የምትታወቀው ሔለን መለስ በአጠቃላይ መልዕክቱ “ኧረ ጉድ! እንዴት አሳምራ ገልጣዋለች እባካችሁ!” የምል አድናቂ እንድሆን አላደረገችኝም። ይልቅስ በኦፊሺያል ሚዩዚክ ቪዲዮዋ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የለበሱና ቡላ አህዮችን ምልክት ያደረጉ ሦስት ወጣቶች አንድን የማይደፈር ሰው ደፍረው እንደጉም ሲበትናቸው ሳይ ደነገጥኩ። በአሁኑ ጊዜም እንዲህ ይባላል እንዴ? “አንተ የአቅማዳ ዳጉሳ፣ ስማ ጉድህን ስማ ንሳ” የሚል የቆየ ተረት አስታወሰኝ።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡