የዋጋ ንረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁንም የሸማቾች መሠረታዊ ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍላጎትን ያገናዘበ በቂ ምርት ኖረም አልኖረም በዘፈቀደ ምርትና የሸቀጦች ላይ የሚጫን ዋጋ ገበያው እንዳይረጋጋ አድርጎታል፡፡ ገበያን አገናዝቦ ዋጋ ለመስጠት የሚሻ የለም፡፡ የተትረፈረፈ ምርት ቢኖር እንኳን ከነበረው ዋጋ ቀንሶ ለመሸጥ ያልተለመደ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል፡፡
የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲህ ያለውን ብልሹ አሠራር ማከም እስካልተቻለ ድረስ ችግሩ መባሱ አይቀርም። ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ኖሮዋቸው የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አምራችና አስመጪዎች እንደሚኖሩ ቢታመንም፣ ባልተገባውና ምንም ግንኙነት በሌላው ምርት ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን እያመካኙ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶችን እየደረደሩ የሸቀጦችን ዋጋ ማናር ተባብሷል፡፡ በቀናት ሳይሆን በሰዓታት ልዩነት ዋጋቸው ወደ ላይ የሚንር ምርቶች እየበዙ መሆኑ መነገር የጀመረው ዛሬ ባይሆንም አሁን ላይ በተደጋጋሚ በብዙ ምርቶች ላይ የመሆኑ ነገር አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች በይበልጥ ለዚህ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በቂ ምርት በተመረበት ወቅት እንኳን የአገር ውስጥ ምርቶች ዋጋ እያሻቀበ ነው። አንድ ዕቃ ወደ አገር ከገባ በኋላ ወጪው ተሰልቶና ትርፍ ተቀምጦ ቁርጥ ዋጋ ወጥቶለት ይሸጣል ተብሎ ቢታሰብም በተመጠነ የትርፍ ህዳግ የሚሸጥ እየጠፋ መጥቷል፡፡
በአንድ ወቅት የሚፈጠሩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የምርትና ሸቀጦች የዘፈቀደ ዋጋ እየተሰጣቸው ኅብረተሰቡን እያማረሩ ነው፡፡ ዕለት በዕለት ያለከልካይ ዋጋ ሲጨመር ምክንያቱ ምንድነው? ብሎ የሚጠይቅ በሌለበት አገር ደግሞ ሁሉም በዚህ ዓይነት አጉል ልምድ ቢዋጅ የሚገርም አይሆንም፡፡
የዓለም ዋጋ ይህንን ያህል ነው፣ ወደ አገር ሲገባ ወጪ ይህንን ያህል ነው፡፡ ይህንን ያህል ትርፍ ተይዞበት በዚህን ያህል ዋጋ ሊሸጥ ይገባል ብሎ የዋጋ ግነትን የሚከላከል አካል የለም፡፡ ይህ ምርት ከውጭ ሲገባ ይህንን ያህል ዋጋ ያለው በመሆኑ እዚህ የሚሸጥበት ዋጋ ለምን ይህንን ያህል ተጋነነ ብሎ የሚሞግት የሸማቾች ተሟጋች መጥፋቱ በዘፈቀደ ዋጋ ሸማች እየተበዘበዘ ነው፡፡
ችግሩ በሸማቾች ላይ በሚፈጠረው ጫና ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ለአጠቃላይ የኑሮ ውድነትና ላልተቋረጠ የዋጋ ንረት ሰበብ እየሆነም ነው፡፡ ልቅ የሆነው የዋጋ ትመናና ያልተቋረጠ የዋጋ ጭማሪ ሄዶ ሄዶ በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡ እየፈጠረም ነው፡፡ የአገራችን ሸማች በተለያየ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ አቅም የሚባለው የኅብረተሰቡ ክፍል የቱንም ያህል ዋጋ ቢኖር ሊሸምት ይችል ይሆናል፡፡ ብዙኃኑ ግን ይህንን ማድረግ የማይችል በመሆኑ ታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ያላገናዘበ ልቅ የዋጋ አተማመንን መከላከል ካልተቻለ ሊፈጥር የሚችለው ቀውስ ቀላል አይሆንም፡፡
የአገራችን ገበያ በተለይ በዚህ ወቅት የዋጋ ቁጥጥር የሌለበት የመሆኑ ጉዳይ መላ የማይበጅለት ከሆነ የአገር አገራዊ ጉዳቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ሰሞኑን የተሽከርካሪ ዋጋ በየቀኑ 50 እና 100 ሺሕ ብር እየጨመረ በወራት ልዩነት የአንድ መኪና ዋጋ በመቶ ሺሕ ብሮችና በሚሊዮኖች ሲጨምር እየታየ እንዲህ ያለው አካሄድ ጤናማ ያለመሆኑን በማሳወቅ ድርጊቱን ለምን መከላከል እንደማይቻል ያስገርማል፡፡ በዚህ አገር ንግድ አጋጣሚን ተጠቅሞ መዝረፍ ሆኗል ለሚለው አመለካከት ይህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡
በእርግጥ መኪናው የቅንጦት ቁስ ስለሆነ እንደፈለገው ዋጋ ቢጨምር እዚህ ላይ የሚራኮቱት እጅግ ጥቂት ሊሆኑ ስለሚችሉ ነገሩን ጉዳዬ ላንለው እንችላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ምርት ምን ያህል ትርፍ ተይዞለት መሸጥ እንዳለበት የጠራ ሥርዓት እንደሌለንና አጠቃላይ የግብይት ሥር ሥርዓታችን ብልሽት በሚገባ የሚያሳይ አንድ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን ግን ይችላል፡፡ የመኪና ተጋኖ ወጣ እንጂ ሌሎች ምርቶችና ሸቀጦችም በዚሁ ዓይነት መንገድ ዋጋ እየተቆለለባቸው የሚሸጡ መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡
እንዲህ ያሉ ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪዎች አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ከመበረዝ ባለፈ ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠሩ መሆኑን በግልጽ እያየን ነው፡፡ በስመ ነፃ ገበያ ሸማች እየተማረበት ያለው ይህ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ መክተቱ አይቀርም፡፡ አንድ ኪሎ ስኳር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለትና ሦስት እጥፍ ጨምሮ 120 ብር ሲሸጥ ለምን ይህ ሆነ? ብሎ የጠየቀ ጠይቆም መፍትሔ ያመጣ አካል እስከሌለ ድረስ ችግሩ እየሰፋ መሄዱ አይቀርም፡፡ የሲሚንቶ ጉዳይም እንዲሁ ነው፡፡ 90 በመቶ ግብዓቱ በቀላሉ በሚገኝ አፈር የሚመሩት መሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ ከየፋብሪካዎቹ ቢበዛ 700 ብር እየተሸጠ ገበያ ላይ ግን ከ1,800 ብር በላይ የሚሸጡበት ምክንያት ምንድነው?
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው ምርቶችን በመቀጠም የሚመረቱና ለሸማች የሚቀርቡ ምርቶችም በዚያው ልክ ዋጋቸው እየጨመረ በመሆኑ ችግሩን ማስፋቱንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለንበት ገበያ ሁኔታ እንደተፈለገ እንዲተረፍበት ወይም እንዲዘረፍበት የተፈቀደ አስመስሎታል፡፡ መነገድ ያለአግባብ የሚተረፍበት ዘርፍ ወደ መሆን እየተቀየረ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ንግድ የተመጠነ ትርፍ የሚገኝበት ነው፡፡ ይህ እንዲሆንም ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ በሕግም የሚመራ ነው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን እየሆነ ያለው ይህ ባለመሆኑ ትንሹም ትልቁም ነጋዴ ከተመጠነ ትርፍ ጋር በተቃርኖ ቆመው ገበያው ሥርዓት እያጣ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ውስጥ የደላሎች ሚና ቀላል ያለመሆኑን ብንረዳው ቅጥ እያጣ ያለው የዋጋ ንረት ግን ከምንሸከመው በላይ እየሆነ ለመምጣቱ ዋነኛ ምክንያት ንግድ በሕግና በሥርዓት እንዲመራ አለመደረጉ ነው፡፡ አገሪቱ ዶላር የላትም እየተባለ የሚገባው ዕቃ አሁንም ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ተከፍቶ ወደ አገር የሚገባው ዓመታዊ ዕቃ ግምት 18 ቢሊዮን ዶላር ተሻግሯል፡፡
ስለዚህ በብዙ ድካም በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣ ዕቃ በስንጥቅ ትርፍ እንዲቸበቸብ የሚፈቀድበት ምክንያት መኖር እንደሌለበት እንድናስብ ያደርገናል፡፡
በብዙ ድጋሚ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣ ዕቃ በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለማዋሉ ልናረጋግጥ ከምንችልባቸው ማሳያዎች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ተፈቅዶላቸው የሚመጡ ምርቶች ለገበያ ሲቀርቡ በተመጣጠነ ዋጋ ለኅብረተሰቡ መቅረብ ሲችሉ ጭምር ነው፡፡ ስለመዋሉና በተመጠነ የትርፍ ህዳግ ለሕዝብ ስለመቅረቡ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ቢያንስ አሁን ካለንበት ችግር እስከምንወጣ ድረስ በተመጠነ የትርፍ ህዳግ ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ እካልተቻለ ድረስ ገበያው በዘፈቀደ የዋጋ ትመና መጫወቻ መሆኑ ይቀጥላል፡፡ አንድ ከውጭ የሚገባ ምርት ከሚመጣበት አገር የመሸጫ ዋጋው ይታወቃልና ይህንን መረጃ በመያዝ ሊከፋፈል የሚችልበትን ከዚያም የችርቻሮ ዋጋው ከዚህ መብለጥ የለበትም የሚለውን ሥሌት ለመሥራት ከባድ ስለማይሆን የንግድ ሥርዓታችን በተመጠነ የትርፍ ህዳግ እንዲጓዝ መሠራት አለበት፡፡
የተመጠነ የትርፍ ህዳግ አስገዳጅ መሆን ዋጋንም ከማረጋጋቱ በላይ የግብይት ሥርዓቱ ለማዘመንና ጨዋ የንግድ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ያግዛል ስለዚህ የትርፍ ህዳግ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ያስፈልጋል ተብሎ አንዳንድ ሥራዎች ተጀማምረው እንደነበር ይታወቃልና ይህን ጉዳይ መልሶ በማንቀሳቀስ መተግበር የግድ ሊሆን አይገባም፡፡