Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ናይል ኢንሹራንስ የተሽከርካሪ ስርቆትን የተመለከቱ በርካታ የካሳ ጥያቄዎች እንደገጠሙት አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ናይል ኢንሹራስ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተሽከርካሪዎች ስርቆት ጋር በተያያዘ በርካታ የካሣ ክፍያ ጥያቄዎች እንደገጠሙት አስታወቀ። 

ኩባንያው የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ በሒሳብ ዓመቱ በሁሉም ረገድ ውጤታማ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከ227 ሚሊዮን ብር በላይ ቢያተርፍም ከሌሎች ዓመታት በተለየ ሁኔታ በርከት ያለ የካሳ ክፍያ ጥያቄ ገጥሞታል፡፡ 

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ የካሳ ክፍያው ጥያቄዎች በ46 በመቶ መጨመሩን አመልክቷል፡፡ ለካሳ ክፍያ ጥያቄዎቹ መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው ከተሽከርካሪዎች ስርቆት ጋር በተያያዘ በርካታ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች መቅረባቸው ነው፡፡ 

የናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሐሪ ዓለማየሁ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት ፣ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያቸው ለጠቅላላ ኢንሹራንስ 267.7 ሚሊዮን ብር ያተጣራ የካሳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡

የተፈጸሙ የካሳ ክፍያዎችንና ላልተከፈሉ የካሳ ጥያቄዎች የተያዘውን መጠባቂያ አካቶ ለኩባንያው የቀረበው የዓመቱ የተጣራ የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጠን የ46 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 291.2 ሚሊዮን ብር መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጠን ከፍተኛ የሚባል ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ የካሳ ጥያቄዎች ከፍ ማለቱ አንዱ ምክንያት ከተሽከርካሪዎች ስርቆት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ፤ ‹‹በገበያ ውስጥ የአዳዲስ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ ተደጋጋሚ የተሽከርካሪዎች ስርቆት ያስከተላቸው የበረከቱ የካሳ ጥያቄዎች የከባድ ተሽከርካሪ የጋቢና ቅያሪ ዋጋ መጨመርና የጋቢና ቅያሬ የካሳ ጥያቄዎች መበራት ለካሳ አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ጉልህ ድርሻ ነበራቸው›› ብለዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ በኩባንያው የተመዘገበው የካሳ ምጣኔ ባለፈው ዓመት ከነበረው 51.7 በመቶ ወደ 58.3 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡ 

በአንፃሩ ግን ኩባንያው ለሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የከፈለው የካሳ ክፍያ ከቀዳው ዓመት በ16 በመቶ ቀንሷል፡፡ በሕይወት መድን ዘርፍ በሒሳብ ዓመቱ የቀረበው የካሳ ክፍያ ጥያቄ 35.9 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ 

የተሽከርካሪዎች ስርቆት በካሳ ክፍያ ላይ እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የናይል ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሥ አንተነህ፣ በተለይ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተሽከርካሪ ስርቆት ጋር በተያያዘ በርካታ የካሳ ጥያቄዎች ለኩባንያው መቅረባቸውን ተናግረዋል። ይህ ክስተት በኢንዱስትሪው አልፎ አልፎ የሚያጋጥም የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በርከት ያሉ ጥቄያዎች እያቀረቡ መሆኑ የኢንሹራስ ኩባንያዎች ከመኪና ስርቆት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ካሳ እንዲከፍሉ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ሚኒ ባስን ጨምሮ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ተሰርቀው የካሳ ጥቄያ የቀረበባቸው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ሌላው ቀርቶ ‹‹ሃዩንዳይ ታክሰር›› የሚባል ተሽከርካሪ ሳይቀር ተስርቆ ከደንበኛቸው የካሳ ክፍያ መቅረቡን አቶ ንጉሥ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በ2014 ዓ.ም. በመበራከታቸውና ጉዳዩም ለኢንደስትሪው ስጋት በመሆኑ በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንዲካተት መደረጉን  አስረድተዋል፡፡ 

ኩባንያው በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አምስት ለሚደርሱ የተሰረቁ ተሽከርካሪዎች የካሳ ክፍያ መፈጸሙን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለዚህ የመድን ሽፋን የሚከፈለው የካሳ መጠን የመኪናው ሙሉ ዋጋ በመሆኑ በኩባንያዎች ላይ ጫና እንደሚያሰርፍ አስረድተዋል፡፡ አደጋ ላጋጠመው ወይም ለተጎዳ ተሽከርካሪ የሚከፈለው የካሳ ክፍያና ለተሰረቀ ተሽከርካሪ የሚከፈለው ክፍያ እጅግ የተለየ መሆኑንም ጠቁመዋል። እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ፣ ለተጎዳ ተሽከርካሪ ካሳ ቢከፈልም የተጎዳውን ተሽከርካሪ መልሶ በጨረታ በመሸጥ የተወሰነ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወጪ በተወሰነ ደረጃ ማካካስ ይችሉ ነበር። ለተሰረቀ መኪና ግን እንዲህ ያለው ዕድል የማገኝ በመሆኑ ከተሽከርካሪ ስርቆት ጋር የተያያዘ የካሳ ክፍያ ብዙ ወጪ የሚያስከትልና አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ሲኖ ትራክ የሚባል ተሽከርካሪ ተሰርቆ ካሳ የከፈለ ኩባንያ መኖሩን ያስታወሱት አቶ ንጉሥ፣ አሁን እየሰፋ ካለው የተሸከርካሪ ስርቆት ጋር በተያያዘ ኢንሹራንሶች ላይ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚችል ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ‹‹ ከዚህ ቀደም የመኪና ስርቆት እጅግ ጥቂት የሚባል ነበር፡፡ አሁን ግን ከወንጀል መብዛት ጋር ተያይዞ እየሰፋ መጥቷል። ተሽከርካሪን ሙሉ በሙሉ ከመስረቅ በተጨማሪ የተሽከርካሪውን አካል መስረቅም በዛው ልክ እየጨመረ ነው። እንዲህ ላሉ ስርቆቶች እየተከፈለ ያለው ካሳ ደግሞ የኩባንያችን የካሳ ክፍያ እንዲጨምር አድርታል›› ብለዋል፡፡ 

ከተሽከርካሪ ስርቆጽት ሌላ የመኪና አካላት ስርቆትም በተመሳሳይ የሚታይ ሲሆን፣ በተለይ ውድ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸም ስርቆት ከፍ ያለ ዋጋ እየተከፈለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በአብላጫው ከሞተር የኢንሹራንሽ ሽፋን ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚከፍሉት ዓመታዊ የጉዳት ካሳ ከ50 እስከ 60 የሚሆነው ለተሽከርካሪዎች ጉዳት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከተሽከርካሪ ስርቆት ጋር የተያዘው ድርጊት የሞተር የመድን ሽፋን ዘርፉን አሳሳቢ ሊያደርገው ይችላል፡፡ 

ናይል ኢንሹራንስ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ 59 በመቶ የሚሆነውን ከሞተር ኢንሹራንስ ያሰባሰበው ነው።

ናይል ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ከካሳ ክፍያ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ ነገር ቢገጥመውም፣ በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛ ትርፍና የዓረቦን ገቢ ያገኘበት ስለመሆኑም ተገልጻል፡፡ ኩባንያው በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 227 ሚሊዮን ብር ያረተፈ ሲሆን፣ ይህ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ43 በመቶ ብልጫ ይዟል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ በኢንዱትሪው ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ ክፍፍል ድርሻ (ደቪደንድ) ለመክፈል እንዳስቻለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሪፖርት ዓመቱ ናይል ኢንሹራንስ 1,000 ብር ዋጋ ላለው አክሲዮን የከፈለው የትርፍ ድርሻ (ደቪደንድ) 339 ብር ሲሆን፣ በቀዳሚው ዓመት ከከፈለው 279 ብር አንፃር ሲታይ የ22 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሆኗል፡፡  

በሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ምጣኔውን ከፍ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ፣ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ከፍ በማለቱ ነው፡፡ 

ከኢንቨስትመንት የተገኘ ገቢን አስመልክቶ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እንደተናገሩት ፣ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢ 164.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን ፣ይህም ባለፈው የሒሳብ ዓመት ከተገኘው ገቢ በ91.9 ሚሊዮን ብር ከፍ ያለ ነው። ከጠቅላላ የኢንቨስትመንት ገቢው ውስጥ ከአቢሲኒያ ባንክና ከኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ያገኘው የትርፍ ድርሻ 69.3 ሚሊዮን ብር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ኩባንያዎች የተገኘው ትርፍ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 29.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ132.9 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ በተመሳሳይ ተቀማጭ የባንክ ወለድ ገቢው ደግሞ በ26.1 በመቶ ዕድገት በማሳየት 58.3 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ የኩባንያው ሪፖርት አመልክቷል፡፡ 

ይህም ኩባንያው ከኢንቨስትመንት ያገኘው ገቢ ከፍተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ ዕድገት ማሳየቱ፣ አጠቃላይ የኩባያውን ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔን ከፍ ለማድረግ አንዱ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ እስከ ተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱን 1.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ30.1 በመቶ ብልጫ ያለው ነው ተብሏል፡፡ 

ከጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ ውስጥ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ያለው የአክሲዮን ኢንቨስትመንት 54.5 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም ከመድን ሥራ ዘርፍ ያስመዘገበው ውጤትም ከፍተኛ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበውን የዓረቦን መጠን በ33 በመቶ በማሳደግ 714.9 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉ ተነግሯል፡፡ ይህ በኢንዱስትሪው ከግል የኢንሹራንስ በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው አራተኛው ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ ነው፡፡ ከሕይወት መድን ዘርፍ ያሰባሰበው ዓረቦን ደግሞ 66.7 ሚሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ ከሕይወት ዘርፍ ያገኘው ገቢም ከቀዳሚው ዓመት የ15 በመቶ አድጓል፡፡ ኩባንያው አዳዲስ የመድን ሽፋኖችን ከመስጠት አኳያ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ለኢንዱስትሪው አዲስ እንደሚሆን የተነገረለትን የሳይበር ደኅንነት መድን ለመስጠት የሚያስችለውን ቅድመ ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 

የወለድ አልባ የመድን አገልግሎት በመስኮት ደረጃ ለመሸጥ የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱንም አመልክቷል፡፡ 

ናይል ኢንሹራንስ ጠቅላላ የሀብት መጠኑን በ30 በመቶ በማሳደግ 2.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉንም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 646.4 ሚሊየን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ኩባንያው ባለፈው ዓመት ባካሄደው ጠቅላለ ጉባዔ የኩባንያውን ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡ 

ናይል ኢንሹራንስ 413 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ 58 ቅርንጫፎችና ሁለት አገናኝ ቢሮዎች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች