Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንዱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየተዳደረ ሌላው በፖለቲካ ውሳኔ የሚተዳደርበት ሁኔታ መቅረት አለበት›› አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፣ የጉራጌ ማኅበራዊ አንቂ

ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ምሕንድስና ተመርቀዋል፡፡ በጉራጌ ዞን በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ውስጥ የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ቁጥጥር ባለሙያ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ጉራጌ የራሱ ክልል ሊኖረው ይገባል ብለው ይሞግታሉ፡፡ ብዙ በሚታወቁበት በማኅበራዊ አንቂነት ይህ የፖለቲካ ጥያቄ እንዲመለስ ይቀሰቅሳሉ፡፡ የዞኑን ወቅታዊ ሁኔታና ጥያቄው እያስነሳ ያለውን ውዝግብ በተመለከተ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የክልልነት ጥያቄ በአመፅና ተቃውሞ ነው የሚመለሰው?

አቶ ብርሃኑ፡- ምንም ዓይነት ጥያቄ ቢሆን ከአመፅና ተቃውሞ ይልቅ፣ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን አቅርቦ ምላሽ ማግኘት ሁሌም የተሻለው መንገድ ነው፡፡ ከጉራጌ ጥያቄ አኳያ ነገሩን ብናየው ምንም ዓይነት አመፅ ተካሄደ በሚያስብል ሁኔታ የቀረበ ጥያቄ የለም፡፡ ጉራጌ ዞን በተለይም በወልቂጤ ከተማ አንዳችም የአመፅ እንቅስቃሴ አልተካሄደም፡፡

ሪፖርተር፡- መንገድ አልተዘጋም? ጎማ አልተቃጠለም? የሥራ ማቆም አድማስ አልተደረገም?

አቶ ብርሃኑ፡- አንተ ለምሳሌ የአንድ ቤተሰብ አባል እንደ መሆንህ የመማር መብት አለህ፣ ለሌሎች ወንድሞችህ የሚደረግ እንክብካቤ ላንተም ሊደረግ ይገባል፡፡ እነዚያ መብቶችህን ስትከለከልና አንተ ላይ የተለየ በደል ሲደርስ ታኮርፋለህ፡፡ ስለዚህ የጉራጌ ሕዝብ ያደረገው ይህንን ነው፡፡ ማንም ወገን ከአካባቢዬ ይውጣ አላለም፣ የማንንም ቤት አላፈረሰም፣ የነካው ምንም ተቋም የለም፣ የትኛውንም ባንክ ቤት አልዘረፈም፣ የተዘጋም መንገድ የለም፡፡ የተዘጋ መንገድ አለ ከተባለም ለሦስተኛ ዙር በተጠራው አድማ የመጨረሻ ቀን፣ የፀጥታ ኃይሎች ቤቱን ዘግቶ የተቀመጠውን ሕዝብ ቤት ለቤት እየገቡ ወጣቶችን በማፈሳቸው ነበር አንዳንድ የተቆጡ ወጣቶች መንገድ ላይ ወጥተው ጎማ ያቃጠሉትና ለጥቂት ጊዜ መንገድ የተዘጋው፡፡ ይህም ቢሆን ማኅበረሰቡ በተለይም አዋቂዎች ተቆጥተውና መክረው ወዲያው ድርጊቱን አስቁመዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ነው ሰላማዊ የነበረው የቤት መቀመጥ አድማ ወደ አመፅ ሊያመራ የነበረው፡፡ ብዙ እናቶች፣ ሽማግሌዎችና ኃላፊነት የሚሰማቸው ወገኖች ችግሩን ፈተውታል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የጉራጌ ዞን በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው? መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሷል? የታሰሩ ወይም የተፈቱ ሰዎችስ አሉ?

አቶ ብርሃኑ፡- ዞኑ የተመለሰለት ጥያቄ የለም፡፡ ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ እኔ የሕግ ባለሙያ አይደለሁም፣ ነገር ግን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው ያቀረበው፡፡ እነዚህ ሕጋዊ መብቶች እንዲከበሩለት ሕዝቡ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ የሚመለከተው አካል ድምፄን እየሰማ አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ ይህ በመሆኑ ጥያቄው እየሰፋ ነው የሚገኘው፡፡ ከዚህ ቀደም ቀዝቀዝ ብለው የነበሩና ሒደቱን በአርምሞ ሲከታተሉ የቆዩ አካባቢዎች ጭምር ጥያቄውን እየተቀላቀሉት ነው፡፡ ቡታጅራ ከተማ የክልልነት ጥያቄያችን ይመለስልን፣ እንዲሁም ሪፈረንደም እየጠበቅን ነው የሚሉ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች ከሰሞኑ ሲበተኑ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡ ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ግፊቱን ማጠናከሩ በተለያዩ ቦታዎች እየታየ ይገኛል፡፡ በዞኑ የታወጀውን ኮማንድ ፖስት በተመለከተ፣ በጉራጌ ዞን ሕግን በተከተለ መንገድ አይደለም ኮማንድ ፖስት የታወጀው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይም የኮማንድ ፖስት አስተዳደር የሚበጀው በምክር ቤት አስፈላጊነቱ ታምኖበት ሲፀድቅ ነው፡፡ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት አንድ አገር የገጠመውን ችግር መወጣት አልችልም ብሎ ሲያምንና አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ነው እንዲህ ያለው አሠራር በምክር ቤት የሚፀድቀው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ወይም ሥራ አስፈጻሚው አካል ይህን ሊያደርግ አይችልም?

አቶ ብርሃኑ፡- ሥራ አስፈጻሚው ቢያደርገው እንኳ ወደ ምክር ቤት መሄድ መቻል አለበት፡፡ መንግሥት የወሰነው በምክር ቤት የሚወድቅበት ዕድል ያነሰ ቢሆንም፣ ሕጋዊ አሠራሩ በቀናት ውስጥ ቀርቦ በምክር ቤት መፅደቅ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ እኛ ጋ የትኛው ሥራ አስፈጻሚ፣ የትኛው መንግሥትና የትኛው ምክር ቤት እንዳፀደቀ በማይታወቅበ ሁኔታ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ በኮማንድ ፖስት ሥር ነው ዞኑ የሚገኘው፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ ኮማንድ ፖስት ነው ያለው፡፡ ሌላውን ትተን ለኮማንድ ፖስቱ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛነት ያሳሰባቸው የሥራ ኃላፊዎች አቤት ቢሉም አልተሰሙም፡፡ የዞኑ የፋይናንስ መምርያ ኃላፊ ይህን የወጪ አሳሳቢነት በማንሳታቸው መታሰራቸውን አውቃለሁ፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ስድስት የዞን አመራሮች ተቃውሞ በማንሳታቸው ታስረዋል፡፡ ፓርቲ ሕግ ጣሰ ብለን እኛ ሕጋዊ የመንግሥት አሠራርን አንጥስም ያሉ የራሱ የብልፅግና አመራሮች ታስረዋል፡፡ የርዕዮተ ዓለምና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፣ የጤና መምርያ ኃላፊውና የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ሳይቀሩ ታስረዋል፡፡

ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የዞኑ ምክር ቤት የክላስተር ክልል አደረጃጀትን ዕቅድ ውድቅ ያደረገበትን ውሳኔ የተመለከተ ዜና አሠራጭተሃል ተብለው ነው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው የታሰሩት፡፡ እስራት በዞኑ አለ፡፡ የደቡብ ልዩ ኃይልና ኮማንድ ፖስቱን የሚመሩት ኃላፊዎች ናቸው ይህን የሚመሩት፡፡ እኔ እስከማውቀው በአንድ ማቆያ ወልቂጤ ከተማ አይሪሽ አዳራሽ ተቃወማችሁ በሚል 37 ወጣቶች ታስረዋል፡፡ ወልቂጤ ፖሊስ ጣቢያ ሦስት ሰዎች አሉ፡፡ ሐዋሳ ደግሞ ሁለት ሰዎች ታስረዋል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከዚህ ከአዲስ አበባ ተይዘው ሐዋሳ የታሰሩ ናቸው፡፡ አንደኛው የጉራጌ ዞን እዣ ወረዳን ወክለው የዞንና የክልል ምክር ቤት ተወካይ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ናቸው፡፡ በ2013 ዓ.ም. በሕዝብ የተመረጡት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳና በእጅ ከፍንጅ ወንጀል ሳይያዙ ነው የታሰሩት፡፡ አዲስ አበባ ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው፣ ሁለት ቀን የት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ግፊቱ ሲበዛ ክፉኛ ተደብድበው ሐዋሳ መታሰራቸው ይፋ የሆነው፡፡ በአንድ የሕዝብ እንደራሴ ላይ ይህ ከደረሰ ሌሎቹ ላይ ደግሞ ምን ሊፈጸም እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ብዙ የተገረፉ ልጆች በእስር ላይ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጉራጌ ዞን ከሦስት ብሔረሰቦች አስተዳደሮች የተዋቀረ ዞን ነው፡፡ በጉራጌ  በክላስተር አንደራጅም የሚለው ሐሳብ ቢደገፍም፣ ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች ድጋፍ እንዳገኘ ነው የሚነገረው፡፡ ስለዚህ የጉራጌ  ዞን በሙሉ የክላስተር አደረጃጀቱን እንዴት ተቃውሞታል ተብሎ ለመደምደም ይቻላል?

አቶ ብርሃኑ፡- ጉራጌ ዞን ሦስት ብሔረሰቦችን ጉራጌ፣ ማረቆና ቀቤና ይዞ የተዋቀረ ነው፡፡ በአጠቃላይ 21 ወረዳዎች ያሉት ነው፡፡ ከእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ አምስት በሚሆኑት ማለትም በቡታጅራና አካባቢው ባሉ ወረዳዎች ክላስተሩን መንግሥት ደግፈውታል ይላል፡፡ የዞኑ ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የክላስተር አደረጃጀትን ኢሕገ መንግሥታዊ አሠራር ነው ብሎ ውድቅ አደረገ፡፡ ነገር ግን ይህ በሆነ በሁለት ቀናት ልዩነት ነሐሴ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በእነዚያ አምስት ወረዳዎች የዞኑን ምክር ቤት ውሳኔ አንቀበልም፣ የክላስተር አደረጃጀቱን ነው የምንፈልገው የሚል ውሳኔ አስወሰኑ፡፡ የክላስተር አደረጃጀት ተብሎ አማራጩ ወርዶ ሕዝቡ በተወካዮቹ በአብላጫ ድምፅ አልፈልገውም ብሎ በዞን ምክር ቤት ተቃውሞታል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ይደግፋል ተብሎ ሌላ ውሳኔ ይዞ ለመምጣት ተሞክሯል፡፡

ክላስተር አደረጃጀት ራሱ ምንድነው? የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ክልልነት ጥያቄን በፍፁም አብላጫ ድምፅ አፅድቆ አቅርቧል፡፡ አጠቃላይ ማኅበረሰቡም የእሱን ጥያቄ ምላሽና ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድበትን ቀን እየጠበቀ ነው፡፡ ክላስተር ሲባል ሕዝቡ ግራ ነው የተጋባው፡፡ ምክረ ሐሳቡን ለማወያየት ለተላከው አካልም ሕዝቡ በግልጽ አቋሙን ነግሮታል፡፡ ሐሳቡን አደናግረው ድጋሚ በዞን ምክር ቤት ሊያስወስኑ ሲያቀርቡትም በሚያስገርም ሁኔታ ውድቅ አድርጎታል፡፡ በኢትዮጵያ በግሌ የሕዝብን ፍላጎት እንጂ መንግሥት ያለውን አላስፈጽምም ሲል ያየሁት ጠንካራ ምክር ቤት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ነው፡፡ ክላስተር የተባለውን አደረጃጀት ከተገኙ 92 የምክር ቤት አባላት 52 የሚሆኑት አንፈልግም ብለው ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሐሳቡን ያልተረዱና ለተሳሳተ ውሳኔ የተጋለጡ እንደሚኖሩበት ቢታመንም ወደ 40 የሚሆኑ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ፣ ጥቅም ይቀርብናል ብለው ያመኑና ምቾታቸው እንዳይጎድል የፈለጉ ሰዎች ክላስተርን እንደግፋለን ብለው መርጠዋል፡፡ ነገር ግን በክላስተር ክልል ሁኑ የሚለው ሐሳብ በድምፅ ብልጫ ውድቅ ሆኗል፡፡ ይህ ውሳኔ ባለበት ነው በማግሥቱ በአራት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ መስተዳድር ላይ ውሳኔውን የሚቀለብስ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት አደረጉ፡፡

በነገራችን ላይ በጉራጌ ዞን ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ምርጫ ተደርጎባቸው የማያውቁ አካባቢዎች አሉ፡፡ በፀጥታ ችግርና በሌላም ተብሎ በ2013 ዓ.ም. የታለፉ አካባቢዎች አሉ፡፡ ክላስተሩን እንደግፋለን ካሉ ወረዳዎች አንዳንዶቹ ምርጫ የተራዘመባቸው ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ ወረዳዎች ምርጫ ያደረጉ እንኳን ቢሆን ከዞኑ ምክር ቤት በላይ ድምፃቸው ሆኖ፣ የጉራጌ ሕዝብን ይወክላሉ ሊያስብል የሚችል አይደለም፡፡ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያፀደቀውን ውሳኔ የወረዳ ምክር ቤት ሊሽረው አይችልም፡፡ የወረዳ ምክር ቤት ያፀደቀውን የቀበሌ ምክር ቤት፣ የቀበሌ ምክር ቤት ያፀደቀውን ደግሞ የመንደር ሸንጎ ሊሽረው አይችልም፡፡ ይህ የሕግ ጥሰት መፈጸሙ ሳያንስ፣ የመንግሥት ሚዲያዎች የዞኑን ምክር ቤት ውሳኔ ትተው እሱን ውድቅ የሚያደርግ በማስመሰል የወረዳዎቹን ውሳኔ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀባበሉ ሲዘግቡት ከርመዋል፡፡

በጉራጌ ዞን ያሉ ሦስቱ ብሔሮች ቀቤና፣ ማረቆና ጉራጌ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ ባላቸው ድምፅ ደግሞ ዞናቸውን በጋራ እያስተዳደሩ ተቻችለው በሰላም የሚኖሩ ናቸው፡፡ ጉራጌ ዞን ተሰባስቦ በመኖር ለሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ጉራጌ ክልል ሲጠይቅ ለብቻው ልውጣ ብሎ ሳይሆን፣ በዞኑ በጋራ አብረው የሚኖሩ ሕዝቦች በሙሉ ናቸው አንድ ሆነን ክልል እንሁን እያሉ ያሉት፡፡ ለመልማት፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና በጎ እሴቶቹን ለማበልፀግ እንዲያመቸው ነው የዞኑ ሕዝብ የራሱን ክልልነት ጥያቄ ያቀረበው፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስቱም ብሔሮች ደግፈውታል ማለት እንችላለን?

አቶ ብርሃኑ፡- ማኅበረሰቡ በወኪሎቹ በኩል አብላጫ ድጋፉን ክልል ልሁን ለሚለው ውሳኔ ሰጥቷል ብለን እንውሰደው፡፡ ከሁሉም የዞኑ ብሔሮች ሐሳቡን ያልደገፈ መኖሩ አይካድም፡፡ ይህ በዞን ምክር ቤት ላይም ድምፅ ባልሰጡ ሰዎች መገለጽ የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የጉራጌ ዞን ማኅበረሰብ የክልልነት ጥያቄው እንዲመለስለት እንደሚፈልግ ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ ዞኑ ድምፅ የሚሰማው በዞኑ ምክር ቤት ነው፡፡ በዞኑ ምክር ቤት ደግሞ ክላስተር አደረጃጀቱ ውድቅ ሆኗል፡፡ የእያንዳንዱ የጉራጌ ዞን ሕዝብ ስሜት ምንድነው? የሚለው የሚረጋገጠው ግን ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጉራጌ ዞን ከሌሎች ዞኖች ጋር ተሰባስቦ በክላስተር ክልልነት ቢደራጅ ምን ያጣል? ክላስተሩን ለምን ይቃወማል?

አቶ ብርሃኑ፡- አንደኛ ክላስተር ክልል ማለት በራሱ ምንድነው? ከአሠራር አንፃር አዲስ ነገር ስለሆነ ዘው ብሎ ለመግባት ሊያሠጋ ይችላል፡፡ ክላስተር አደረጃጀትን እንፈልጋለን ብለው ያፀደቁ ዞኖች አሉ፡፡ እነሱ መብታቸው ነው፡፡ ጉራጌ ዞን ግን ክላስተርን አልፈልግም ብሏል፡፡ የማይፈልግባቸው ምክንያቶች ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡ አንደኛው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር ሆኖ ያጣቸው ብዙ ነገሮች በመኖራቸው ነው፡፡ የልማት ተጠቃሚነት እንደ አንዱ መነሳት ይችላል፡፡ ጉራጌ ዞን የረባ ልማት የለውም፡፡ የሚመደብለት ውስን በጀትም ቢሆን በአስተዳደር ነው የሚባክነው፡፡ በዋና ከተማዋ ወልቂጤ እኔ የምኖርበት ደህና የሚባል ሠፈር እንኳ በወርና በሃያ ቀናት ነው ውኃ የሚመጣው፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት በወልቂጤ ውኃ በጀሪካን ሸክም ነው የሚገኘው፡፡ ከተማ እንዲህ ከሆነ ገጠሩማ ከከብት ጋር እየተጋፋ የጎርፍ ውኃ ነው የሚጠጣው፡፡ ይህን ሁሉ ዓመት ጉራጌ የተበደለው ለምንድነው? ቢባል ማኅበረሰቡ አገራዊ ዕይታ ስላለው ነው፡፡ ጉራጌ አካባቢዬ ምን ይመስላል? ብሎ ለማየት ዕድሉን አላገኘም፡፡ ምን ጥሩ ነገር ምንስ መጥፎ ነገር እየተሠራ ነው? ብሎ ለማየት ዕድሉን አላገኘም፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦት በጉራጌ አለ፡፡ ዞኑ የራሱን ቋንቋ፣ ባህልና በጎ እሴቶች ማሳደግ ይፈልጋል፡፡ ለሌሎችም ማጋራት ይፈልጋል፡፡ የሥራ ባህሉ ከዚህ በላይ ማደግ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ በአካባቢው ልማት ማየት ይፈልጋል፡፡ ጉራጌ ዞን ሄዶ አንድ ሰው ለማልማት ቢፈልግ አመቺ አይደለም፡፡ ዞኑ ከ100 ሔክታር መሬት በላይ ለኢንቨስትመንት መፍቀድ ስለማይችል፣ ክልል መቀመጫ ሐዋሳ ወይም ደግሞ አሁን የክላስተር መቀመጫዎች ይሁኑ ወደሚባሉ ከተሞች ሄዶ ለኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመጠየቅ ብዙ እንግልት ያያል፡፡ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ማለትም የአበባ ልማት፣ የኮከብ ሆቴሎች ግንባታም ሆነ ሌላ ኢንቨስትመንት ዞኑ ያመልጠዋል፡፡ እንግልቱ ስለሚሰለቸው እዚያው ሐዋሳ ያለማል፣ ወይም ደግሞ ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ይቀራል፡፡ ጉራጌ በዚህ የተነሳ የልማት ዕድሎችን ያጣል፡፡ በዚህ መንገድ ነው ዞኑ አካባቢውን እንዳያለማ አሻጥር ሲሠራበት የቆየው፡፡

ሪፖርተር፡- ጉራጌ ዞን በራሱ ክልል ሆኖ ለመውጣት የክልልነት መሥፈርቶችን ያሟላል?

አቶ ብርሃኑ፡- የክልልነት መሥፈርቶችን በተመለከተ እኔ የፖለቲካ ሰው ባልሆንም ብዙ የምረዳው ነገር አለ፡፡ ከሐረሪ ክልል አንፃር ብታየው ጉራጌ እጅግ ሰፊ ነው፣ በቂ የቆዳ ስፋት አለው፡፡ ከሌሎች ክልሎችም በዚህ ረገድ የሚተናነስ አይደለም፡፡ በቂ የሕዝብ ቁጥር አለው፡፡ ክልሉን ለመምራት የሚያስችል በቂ የተማረ የሰው ኃይል ጉራጌ አለው፡፡ ለመሥራትና ለመልማት የሚችል ሰውም አለው፡፡ ጉራጌ ዞን በተፈጥሮው ሥራ ወዳድ ማኅበረሰብ ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕጋዊ ጥያቄ መቅረቡና ፌዴሬሽን ምክር ቤት መድረሱ ይነገራል፡፡ ጥያቄው አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው? ምን ምላሽስ አገኘ?

አቶ ብርሃኑ፡- ክልል እንሁን የሚለውን ጥያቄ የዞኑ ምክር ቤት አፅድቆ ለክልል ምክር ቤት ነው የሚልከው፡፡ ይህን ጥያቄ የክልል ምክር ቤቱ በአንድ ዓመት ውስጥ ምላሽ መስጠት የማይችል ከሆነ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይልካል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ለዚህ ጥያቄ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ልኮ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያስፈጽም ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ምርጫ ቦርድም በጀት መድቦና ቀጠሮ ይዞ ማስፈጸም አለበት፡፡ የጉራጌ ጥያቄ እነዚህን ሕጋዊ ምላሾች አግኝቷል ወይ? ቢባል አይደለም ነው መልሱ፡፡ የዞኑ ምክር ቤት ክልልነት ጥያቄውን አፀድቆ ዶክመንቶችን አሟልቶ ለክልል ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ የክልል ምክር ቤቱ ግን የት እንዳደረሰው አይታወቅም፡፡ ከዚያ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዘግይቶ መሄዱ ተሰማ፡፡ በመጨረሻ ደግሞ ክላስተር ክልል ሁኑ የሚል ምክረ ሐሳብ መምጣቱ ተነገረ፡፡ ሕጋዊ ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ ከመመለስ ይልቅ፣ ከጥያቄው ጋር የማይገናኝ ክላስተር ክልል እንካችሁ የሚል ምላሽ ነው የተገኘው፡፡ ነገ ደግሞ እነዚህ ክላስተር ያፀደቁ ሰዎችን ማንም ቢከሳቸው ጥፋተኛ ነው የሚባሉት፡፡ ሕጋዊ ጥያቄው ክልል እንሁን የሚል ነው፡፡ የክላስተር ክልል አስፈጽሙልን የሚል ጥያቄ አልቀረበም፡፡

ሪፖርተር፡- በደቡብ ክልል  ቀሪ  ዞኖችን በሁለት ክላስተር ክልሎች ለማደራጀት ዕቅድ ወጥቷል፡፡ ደቡብ  ኢትዮጵያ  የሚባል ክላስተር ክልል ለመፍጠር ለጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡ የጉራጌ ዕጣ ፈንታስ ከዚህ የተለየ ይሆናል?

አቶ ብርሃኑ፡- ደቡብ ኢትዮጵያ የሚል ክልል ለመፍጠር ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ በጀት ተመድቦ ቀጠሮ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ጉራጌ ያለበት ክላስተር ማለትም ከምባታና ጠምባሮ፣ ሐዲያ፣ ስልጤ፣ ሀላባና የም ልዩ ወረዳ የተካተተበት በአጠቃላይ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ተሰባስበው የሸዋ ክላስተር ክልል ካልፈጠሩ እየተባለ ነው፡፡ ጉራጌ ዞን ይህን ቢቃወምም ሌሎቹ ደግፈውታል፣ መብታቸውም ነው፡፡ ጉራጌ ይህንን የተቃወመውን አደረጃጀት በግድ ተቀበል እየተባለ ነው፡፡ ጉልበት ያለውና ጉልበተኛ ነኝ ያለ አካል አሁን በጉልበት እንዲያስፈጽም ማስገደድ ይችላል፡፡ ሕዝቡ በዚህ የተነሳ ሊታፈን፣ ሊታሰርና ሊገደል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊው አሠራር የሚወሰነው በምክር ቤት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የጉራጌን ምክር ቤት ሊጠሩና ሊያስወስኑ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የጉራጌ ምክር ቤት መልሶ ውድቅ ነው እንደሚያደርገው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወይም ሸዋ ክላስተር በሚሉት አደረጃጀት ውስጥ ጉራጌ አለ እያሉ ነው፡፡ ክልሉ ያለ ጉራጌ ይሁንታ ቢደራጅ እንኳ ክልሉ አዲስ ሕገ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሲካሄድ ደግሞ በየዞኑ ምክር ቤቶች ተገምግሞና ፀድቆ ነው የሚተገበረው፡፡ የጉራጌ ክልል ምክር ቤት ባላፀደቀው መዋቅር ገብቶ ድጋሚ ሕገ መንግሥት ለማፅደቅ ሊገደድ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ የፈለጉት በመሆኑ ያን ሥራ በፈቃዳቸው ሊያካሂዱት ይችላሉ፡፡ ጉራጌ በግድ በክላስተር መዋቅሩ ግባ ቢባልም ዞሮ ዞሮ ግን ለብቻው ክልል ወደ መሆን መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ የጉራጌ ዕጣ ፈንታ በመጨረሻ ክልል መሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካልሆነስ? ጥያቄያችሁ ገፍቶ ሄዶ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት ካልቻለስ  አማራጫችሁ ምንድነው?

አቶ ብርሃኑ፡- ሕግማ ይከበራል፡፡ ሕግ የሚያከብረው አካል ዛሬ ላይኖር ቢችልም፣ ነገር ግን በመጨረሻ ሕግ መከበሩ የማይቀር ነገር ነው፡፡ ካልሆነና ክልል አልሰጥም የሚል አካል በክልልነት መደራጀት የሚፈቅደውን ሕገ መንግሥት መቀየር ነው ያለበት፡፡ በአንቀጽ 39 ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ተብሎ ለሁሉም ብሔሮች የተሰጠውን መብት መሻር ነው ያለበት፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን መብት ጉራጌ ማግኘቱ የማይቀር ነው፡፡ እንዴት ላያገኝስ ይችላል? እኔ በግሌ በብሔር ፖለቲካ የማምን ሰው አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ እስከቀጠለና ብዙኃኑ ሕዝብ ይህን ፖለቲካ እስከፈለገው ድረስ፣ እኔ አልፈልግም ብል ምንም ትርጉም የለውም፡፡ እኔ ይህን ፖለቲካ አልፈልግም ብል ምንም ላልሆን እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙኃኑ የጉራጌ ማኅበረሰብ በዚህ ፖለቲካ ጦስ መጎዳቱ የማይቀር ነው፡፡ አንዱ በፈለገው መዋቅር የሚደራጅበት ሌላው ደግሞ የሚከለከልበት ሁኔታ ይቀራል፡፡ አንዱ የእንጀራ ልጅ ሌላው ደግሞ ልጅ እየተባለ ሊኖር አይችልም፡፡ አንዱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየተዳደረ ሌላው በፖለቲካ ውሳኔ የሚተዳደርበት ሁኔታ መቅረት አለበት፡፡ በመጨረሻ ማለት የምፈልገው የጉራጌ ሕዝብ አገር ወዳድ ሕዝብ ነው፡፡ የትኛውም ቦታ ሄዶ የሚሠራ፣ ሀብት አፍርቶ የሠራበትን አካባቢ የሚያለማና ግብር እየከፈለ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ ጉራጌ አካባቢዬ ብሎ ለራሱ የሚሳሳ ሕዝብ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕዝብን መናቅ አያስፈልግም፡፡ ማክበርና ሕጋዊ ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ጉራጌ፣ አማራና ኦሮሚያም ሆነ የትም ቢኖር ብዙ በጎ እሴቶችን እንዲለመድ ያደረገ ነው፡፡ መሥራትና መለወጥ ነው የሚፈልገው፡፡ ለአገሩ ያለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሚዲያው ለጉራጌ ሕዝብ ድምፅ ሊሆነው ይገባል፡፡ መንግሥትም በአግባቡ ጥያቄውን መመለስ ይገባዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች