Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየክላስተር እርሻን ‹‹ይቃወማል›› ትርክት! (ክፍል አንድ)

የክላስተር እርሻን ‹‹ይቃወማል›› ትርክት! (ክፍል አንድ)

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

መንደርደሪያና የቃላት አጠቃቀም

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የፕላን ልማት ኮሚሽን የተሠራጨው የአሥር ዓመት (2013 እስከ 2022) የልማት ዕቅድ ስለግብርና ልማት በክፍል 3.1 የ‹‹ኩታ ገጠም›› አሠራር በእንግሊዝኛው (Land Consolidation) እንደሆነ አመላክቷል፡፡ ፍኖተ ብልፅግና የሚል ተቀፅላ ባለው በዚህ ሰነድ በግብርናው ዘርፍ ዕቅድ ውስጥ ‹‹ክላስተር›› የሚባል ቃል ያልተገለጸ ሲሆን፣ በክፍል 3.2 የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማትን አስመልክቶ ግን እንደ ትኩረት አቅጣጫ ቀርቧል፡፡ በርካታ የብልፅግና መንግሥት ሠራተኞች፣ በተለይ ደግሞ በፌዴራልም ይሁን በክልል የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ የተለያዩ የሚደያ አካለት ጭምር ኩታ ገጠም የሚለውን አገላለጽ ክላስተር ከሚለው ጋር እየቀያየሩ ‹‹የክላስተር እርሻ ወይም ማሳ›› የሚለውን አገላለጽ ሲጠቀሙም ይደመጣል፡፡ ታዲያ ይህን ሐረግ ከየትኛው ሰነድ ላይ አግኝተው ነው አገላለጹን  የሚጠቀሙበት? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በ2012 ዓ.ም. ባሳተምኩት ‹‹ኢኮኖሚው፣ 3ቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚል ርዕስ በተጻፈው መጽሐፌ በምዕራፍ ስምንት ንዑስ ክፍል 8.3.3 ስለኩታ ገጠም አሠራር የሰጠሁትን አጭር ምክረ ሐሳባዊ ማብራሪያ ‹‹የችብቻቦ ግብርና (Agricultural Clusters)›› ብዬ ሰይሜዋለሁ፡፡ ለእንግሊዝኛው ‹‹Cluster›› የአማርኛ አቻው ‹‹ችብቻቦ›› ነው ማለቴ ሲሆን፣ ይህን ያልኩት ደግሞ ከሜሪት እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለውን ትርጓሜ ተጠቅሜ ነው፡፡ በዚሁ መጽሐፍ በምዕራፍ 6 ንዑስ ክፍል 6.4 ‹‹የመሬት ፖሊሲ፣ ሜካናይዜሽንና የማሳ ሽግሽግ›› በሚል ርዕስ የመሬት ፖሊሲው ተከልሶና ተሻሻሎ፣ የገበሬው ነፃ ኢኮኖሚ ተዋንያንነት ተጠብቆ፣  የግል እርሻ ባለቤትነትን ወደ ሚያስተናግድ ኢኮኖሚ ሥርዓት እስከሚቀየር ድረስ፣ አሁን ካለው የገበሬዎች አነስተኛ የማሳ ስፋት ጋር ተያይዞ ሚሊየነር እየሆኑ ያሉ አነስተኛ ገበሬዎች ሰፋፊ መሬት በሚሹ የሰብልም ሆነ እንስሳት ምርቶች ልማት ላይ በተግባር፣ ዘመናዊና ንግድ ተኮር ሥራዎችን እንዲሠሩና በዘርፉ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲያስችሉ፣ በተለይም በእርሻው ንዑስ ዘርፍ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ይችሉ ዘንድ ‹‹የማሳ ሽግሽግ፣ የእርሻዎች ልውውጥ፣ ኩታ ገጠም (Land Consolidation)›› ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ኢንስቲትዩሽን (ፖስፕኢ) ተቀርፆ መተግበር አለበት ብዬ ምክረ ሐሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ ኩታ ገጠምን  ከእንግሊዝኛው ‹‹Land Consolidation›› ከሚለው ስትራቴጂካዊ ዕሳቤ ጋር አቆራኝቼ ሙያዊ ማብራሪያ በምዕራፍ 8 ንዑስ ክፍል 8.3.3  በፍላጎት መር (Demand Driven) እና በአቅርቦት መር (Supply Driven) የግብርና/እርሻ ችብቻቦ (Agricultural Clusters) አደረጃጀት ላይ ትችትና ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡

 እኔ ስለክላስተር አደረጃጀት መተቸት የጀመርኩት ብልፅግና ፓርቲም ሆነ እሱ የሚመራው መንግሥት ኢሕአዴግን አስወግዶ ይከሰታል ተብሎ በማይገመትበት ጊዜ ሆኖ ሳለ፣ ሳያውቁም ሆነ አውቀው ወይም ከፖለቲካዊ ጨዋታ ጋር በማዛመድ ውዥንብር  ፈጥረው፣ ‹‹ደምስ (ዶ/ር) የክላስተር እርሻን ይቃወማል›› የሚል ትርክት በመተረክ የሚንቀሳቀሱ ሙያተኞችና ፖለቲከኞች ብቅ ብለዋል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2017 (2009 ዓ.ም.) በእንግሊዝኛ ባሳተመኩት መጽሐፍ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አሁን ኢንስቲትዩት (Agriculturale Transformation Agency/Institute) ከአሁን በኋላ በምህፃረ ቃል (ATA-ኤትኤ ወይም ATI-ኤትአይ) እየተባለ የሚጠራው ፕሮጀክት ‹‹Agricultural Commercialization Clusters›› (የግብርና ንግድ ተኮር ክላስተር) ብሎ የጀመረውን እንቅስቃሴ በመተቸት፣ አካሄዱ የሚስተካከልበትን ሙያዊ ምክር አቅርቤያለሁ፡፡ ያኔ ብልፅግና ፓርቲም ሆነ በመደመር ዕሳቤ ክላስተር እርሻ ተሰብኮ አያውቅም፡፡ ይህ የቅርቡ የ‹‹ይቃወማል›› ትርክት ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ አንደኛው ገፊ ምክንያት (Push Factor) ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጣይ አጭር ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡ በማብራሪያዎቼ ቀደም ሲል የጻፍኳቸውን ጽሑፎች፣ መጻሕፍትን ጨምሮ ማጣቀስ ግድ ብሏል፡፡ ቢቻል አንባቢያን የተጠቀሱትን ጽሑፎችና መጻሕፍት ተውሰውም ሆነ ገዝተው ቢያነቧቸው እመክራለሁ፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትም በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ የተመለከተውን የኢሜይል አድራሻ መጠቀም ይቻላል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍሎች ውስጥ የማሳ ሽግሽግ፣ የእርሻዎች ልውውጥ፣ ኩታ ገጠም፣ ክላስተር፣ ችብቻቦ የሚባሉት አገላለጾች ተመሳጥረው ጥቅም ላይ ስለዋሉ እንደ አገባባቸው አንባቢያን ይረዷቸዋል፣ ወይም በቀጣይ በሚያደርጓቸው ውይይቶች ላይ ይጠቀሙባቸዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ አንድ ነገር ግን ከመነሻው ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በአጠራር ልዩነት ይኑረው እንጂ ዛሬ ላይ የሚነገርለት የክላስተር እርሻ አሠራር መተግበር የተጀመረው በንጉሡ ዘመን ሲሆን፣ በቅርበኛው የኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ በ1990ዎቹ መባቻ ነበር፡፡

ከላይ ባቀረብኩት መንደርደሪያና የቃላት አጠቃቀም መግለጫ ላይ ተንተርሼ፣ በቀጣይ በክፍል አንድ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሱኝን ገፊ ምክንያቶችና የግብርናውን አዎንታዊ ለውጥ አቀርባለሁ፡፡ ተከትሎም የክላስተር እርሻ አጀማመር ታሪካዊ ዳራ፣ የይቃወማል ብዥታ በፈጠሩ መድረኮች ስለክላስተር  እርሻ አሠራር ሙያዊ ፍተሻ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ዕሳቤዎችና መርህዎች ላይ ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡ በክፍል ሁለት ደግሞ፣ የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ የአጭርና ረዥም ጊዜ ውጤታማነት፣ የቅርብ ጊዜው የክላስተር እርሻ አሠራር ዕሳቤ ችግርና ትብታቦሽና የእኔን ምልከታዎች፣ በመጨረሻም በስብሻቦሽ፣ መደምደሚያና ጥቂት ምክረ ሐሳብ ጽሑፉን አጠናቅቃለሁ፡፡

ገፊ ምክንያቶችና የግብርና አዎንታዊ ለውጥ

ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ካነሳሱኝ በርካታ ገፊ ምክንያቶች አንዱ ‹‹ደምስ (ዶ/ር) የክላስተር እርሻን ይቀወማል›› የሚልና ተያያዥ አባባሎች እንደሆኑ በመንደርደሪያው አመላክቻለሁ፡፡ ለዚህ መነሻ ሆነዋል ብዬ የምገምታቸው በተለያየ ጊዜ የጻፍኳቸው ጥናታዊ ጽሑፎችና መጻሕፍት፣ በተለያዩ ሚዲያዎች (የኅትመትም ሆነ ኤሌክትሮኒክስ)፣ በተለያዩ የሙያ ማኅበራት ኮንፈረንሶችና ጥናታዊ የውይይት መድረኮች ላይ የምሰጣቸው አስተያየቶች፣  የማነሳቸው የመከራከሪያ ነጥቦችና ምክረ ሐሳቦች ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ አንዳንዴ ግን የእኔን ሙያዊ ግንዛቤና መከራከሪያ ነጥቦች አንዳንዶች (በተለይም ፖለቲከኞች) በግብርናው ዘርፍ ያለውን አዎንታዊ ለውጥ አሉታዊ አድርገው ለመግለጽ ሲጠቀሙበትም አስተውያለሁ፡፡ ይህም ተገቢ ስላልመሰለኝ ለጽሑፌ መዘጋጀት ሌላኛው ገፊ ምክንያት ሆኗል፡፡

እኔ ዛሬ ሳይሆን ከአሥር ዓመት በፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ አዎንታዊ ለውጥ እየተመዘገበ ነው በማለት፣ በጥናት በተደገፈና በአኃዛዊ መረጃ በታገዘ በቀዳሚነት ከሞገቱና ዛሬም ቢሆን ከሚሞግቱ ጥቂት ሙያተኞች መሀል አንዱ ነኝ፡፡ አዎንታዊ ለውጡን ከፖሊሲና ስትራቴጂ ጋር በማዛመድ ለማቅረብና ለማብራራት ስጥር በዚያው ልክ ግን የተገኘው አዎንታዊ ለውጥ መገኘት ነበረበት ብዬ ከምገምተው ያነሰ እንደሆነ በማመላከት፣ ለበለጠ ውጤት መሠራት ያለባቸውን የፖስፕኢ ይዘቶችና አፈጻጸሞችን፣ የማሻሻያና የክላስተር አቅጣጫዎችን በመጠቆም ምክረ ሐሳቦችን በጽሑፍ ሰንጄ በማቅረብም ነው፡፡ ለዚህ አንባቢያን እ.ኤ.አ. በ2004 (በእኛ 1996 ዓ.ም.) በእንግሊዝኛ ‹‹Agricultural Policy and Farm Price Support in Ethiopia) እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2015 (በ2007 ዓ.ም.) ‹‹Ethiopia’s Indigenous Policy and Growth: Agriculture, Pastoral and Rural Development›› በሚሉ ርዕሶች፣ በማከታተል ደግሞ በ2009፣ 2012፣ 2013 ዓ.ም. በእንግሊዝኛና በአማርኛ ያሳተምኳቸውን መጻሕፍት ቢመለከቱ በአኃዛዊ መረጃዎች ጭምር ያቀረብኳቸውን ማብራሪያዎችና ምክረ ሐሳቦች ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ቀደም ያሉት ማለትም በ1996 እና በ2007 ዓ.ም. የታተሙት መጻሕፍት ገበያ ውስጥ ባይኖሩም፣ ሌሎቹ አሁንም ስለሚገኙ ገዝቶ ማንበብ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት በተጨማሪ ከማማከር ሥራዬ ጥናት ሰነዶች፣ በተለያዩ የሙያ መድረኮችና ወርክሾፖች ላይ ያቀረብኩዋቸው በድኅረ ኮንፈረንስ ኅትመት ታትመው የሚገኙ ጽሑፎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መጣጥፎች ጋር በተጓዳኝ በክላስተር እርሻ አደረጃጃት ላይ በተለያዩ መድረኮች የእኔ ማብራሪያና አቋም በተለያዩ ሰዎች የመቃወም ዓይነት መረዳትና ብዥታን የፈጠሩ ይመስለኛል፡፡ ስለመድረኮቹ ከሚከተለው ክፍል ቀጥዬ ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡

የክላስተር እርሻ አጀማመር ታሪካዊ ዳራ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ውስጥ የስም አጠራሩ ይለያይ እንጂ፣ የክላስተር አሠራር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ታውቆ ተግባር ላይ የዋለው ከበርካታ ዓመታት በፊት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ከወቅቱ ፖለቲከኞች ትርክት ወጣ አድርጎ ማጥናትና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ በአጠራር (Nomenclature) ላይ ያለን ልዩነት እንደ አግባቡ የምንመረምረው ሆኖ፣ በይዘትና በታቀደ መንገድ የክላስተር እርሻ አሠራር የተጀመረው ቢያንስ በንጉሡ ዘመን እንደሆነ ማስገንዘብ እሻለሁ፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት የወላይታ አውራጃ አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ በአውራጃው ውስጥ የልማት አቅጣጫውን ለመቀየር ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች መሀል አንዱ፣ በግል የመሬት ባለቤትነት ሥርዓት ውስጥ ያሉ አነስተኛ ገበሬዎች ለቴክኖሎጂ ቅርበት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ በሙያተኞች ታግዘው በአንድ አካባቢ አንድ ዓይነት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አምርተው ኤክስፖርት አስከሚያደርጉበት ደረጃ አድርሰዋቸው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ አነስተኛ ገበሬዎችን ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጋር በማቆራኘት፣ በውል ሰነድ አስተሳስረው፣ ኢንዱስትሪው የምክርና ቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረገ (የትምባሆ ተክል ምርጥ ዝርያን ጨምሮ)፣ ለገበሬዎች ሥልጠና እየሰጠ፣ የክላስተር እርሻ አደረጃጀት ያለው  የማምረት ሥርዓት ዘርግተው ነበር፡፡ ዝርዝሩን ከደጃዝማች ‹‹ሕይወቴ ለአገሬ ኢትዮጵያና ለወገኖቼ ኢትዮጵውያን  ዕድገት የነበረኝ የሥራ ጥማት›› በሚል ርዕስ በ2012 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፋቸው ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ በእሳቸው ጅማሮ ላይ ተመሥርቶ የጭላሎና የወላይታ ልማት ድርጅቶች እንቅስቃሴም መሰል ስትራቴጂካዊ የልማት አቅጣጫ ይዘው ነበር፡፡ ይህ እንቀስቃሴ በደርግ በሚመራው አብዮት ምክንያት ሳይቀጥል ቀረ፡፡

በደርግ ጊዜ የግል መሬት ባለቤትነት ቀረ፡፡ በሶሻሊስት ሥርዓት እመራለሁ ያለው የደርግ መንግሥት ለአነስተኛ ገበሬዎች የልማት ሥራ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ አድርጎ ያወጀውና ያስፈጸመው ገበሬዎችን በገበሬ ማኅበራት (Peasant Associations) አደራጅቶ የአምራቾች የኅብረት ሥራ (Producers Cooperatives) በማደራጀት ነው፡፡ የእነዚህና መሰል ማኅበራት የማደራጀት ምክንያቶቹ ከዛሬው የብልፅግና ፓርቲ መር መንግሥት የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አካሄድ ጋር ተመሳሳይና በይዘቱም አቅርቦት መር (Supply Driven) ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደኋላ እመለስበታለሁ፡፡

በኢሕአዴግ መንግሥት የክላስተር እርሻ አሠራር በ1990ዎቹ መጀመርያ አካባቢ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ድርጅት አነሳሽነት መተግበር ተጀምሮ ነበር፡፡ የምርምር ድርጅቱ በተመረጡ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነትና ለኤክስፖርት ሊውሉ በሚችሉ ሰብሎችና የእንስሳት ምርቶች ላይ በአንድ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን በማደራጀትና ከፋብሪካዎችና ከኤክስፖርተሮች ጋር በማቆራኘት፣ በሕግ በታሰረ የኮንትራት ሥርዓት የክላስተር እርሻን ማስፋፋት ጀምሮ ነበር፡፡ በይዘቱ ፍላጎት መር (Demand Driven) ነበር፡፡ የፓስታ/ማካሮኒ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ሽንብራ፣ የማር ምርት የመሳሳሉት በእንቅስቃሴው ታቅፈው ነበር፡፡ ይህ ሥራ ከግብርና ሚኒስቴር የኤክስቴንሽን መምርያ ጋር በቅንጅት የሚሠራ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያየ ጊዜ በምርምር ድርጅቱም ሆነ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ በሚደረጉ የመዋቅርና የአመራር ለውጦች ምክንያት፣ ከእነዚህም ጋር ተያይዘው በሚመጡ የፖለቲካ ሽኩቻዎችና  የስትራቴጂ ለውጦች ምክንያት ተቋርጦ እስከ መጀመርያው የኢሕአዴግ ዕድገትና ልማት ዕቅድ (ዕልዕ) መተግበሪያ ጊዜ ድረስ ደብዛው ጠፍቶ ነበር፡፡

በመጀመርያው ዕልዕ መተግበሪያ ጊዜ በውጭ አገር መሠረቱን ያደረገ፣ ሲነርጎዝ (Synergoes) የሚባል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በፍላጎት ላይ የተመሠረተን የክላስተር እርሻ አሠራርን በተለያዩ ክልሎች ውስጥ እንደገና ለማንቀሳቀስና ለማስፋፋት ጀመረ፡፡ የሲነርጎዝ እንቀስቃሴ ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ኤትኤ) በፕሮጀክት አወቃቀሩ ሳቢያ ከውጭ በሚያገኘው ረብጣ ዶላርና የፕሮጀክቱ መሪዎች ለኢሕአዴግ መንግሥት የበላይ አመራር ከነበራቸው ቀረቤታ የተነሳ፣ በግልጽ በማይታወቅ ምክንያት ሲነርጎዝ የሚሠራውን ሥራ ወስዶ የግብርና ምርት/ሸቀጥ ክላስተር (Agricultural Commodities Cluster (ACC) ከዚህ በኋላ በአማርኛ ምኅፃረ ቃል ኤሲሲ ተብሎ የሚጠቀሰውን መተግበር ጀመረ፡፡ ትግበራው በአገሪቱ በአራት ክልሎች (ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) በተመረጡ ወረዳዎች ውስጥ እንዲሁም ከሰብሉም ሆነ ከእንስሳቱ እርሻ  በተመረጡ ሸቀጦች/ሥርዓቶች ላይ ነበር፡፡ ኤትኤ እንደ ግብርና ምርምር በኋላም እንደ ሲነርጎዝ ሥራውን ፍላጎት መር አድርጌ እቀጥልበታለሁ ብሎ ነበር የጀመረው፡፡  ኤሲሲን በዕውቀቱ አራምደዋለሁ ብሎ ከቀረፀው ‹‹የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ›› ጋር አዳብሎ በፍላጎት መር መርህ ለመተግበር እየተንቀሳቀሰ ባለበት ጊዜ ግን፣ የወቅቱ የግብርና ሚኒስቴር የኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ደግሞ የግብርና ክላስተር አሠራርን በአቅርቦት መር መርህ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋጋጥ እንዲያስችል በኮማንድ ዕዝ በሚመራ የዘመቻ እንቅስቃሴ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቀድ ሁለት መባቻ ላይ ጀመረ፡፡ በዚህን ወቅት ነበር የክላስተር አካሄድ (የኤሲሲን) ክፍተቶችና የአደረጃጀት ህፀፆች ማስተዋልና በተለያዩ መድረኮች በጽሑፍም፣ በንግግርም የዕርምትና ማስተካካያ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱበት ማሳሰብና መምከር የጀመርኩት፡፡

በተለይ በ2017 (በ2009 ዓ.ም.) በእንግሊዝኛ ‹‹The Quest for Change…›› በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፌ፣ በንዑስ ክፍል 8.3.5 ‹‹ACC Institutionalization››   በሚል ርዕስ የሰጠሁትን ማብራሪያ ቢያነቡት ዛሬ በኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አሠራር ላይ የማነሳቸውን ጉዳዮችና የምሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች ምንጫቸውን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ወቅቱ ኢሕአዴግ ለሁለት ይሰነጠቃል ብዬ የማልገምትበት ወይም ብልፅግና ፓርቲ በኢሕአዴግ ውስጥ ተረግዞ እንደነበር የማላውቅበት ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ ላይ ያሉት አመራር አካለት የክላስተር እርሻ አሠራርን  የብልፅግና መንግሥት ያመጣው አዲስ የአደረጃጀት አቅጣጫ አድርገው ለማቅረብ ከመሞከር ባሻገርም፣ ደምስን ዛሬ ላይ እንደተከሰተ የክላስተር እርሻ ተቃዋሚ አድርገው ለማቅረብ ይንተፋተፋሉ፡፡ እኔ ግን ቀደም ሲል ጀምሮ በ2009 ዓ.ም. መጽሐፌም ሆነ በኋላ በ2012 እና በ2013 ዓ.ም. በአማርኛ ባሳተምኳቸው መጻሕፍቶቼ ውስጥ የ‹‹ችብቻቦ›› (Agricultural Cluster) የእርሻ ሥራ አካሄድና ተጓዳኝ የዕሳቤና መርህ ጭብጦች ላይ መወሰድ ስላለባቸው ማስተካከያዎች ምክሮች አቅርቤያለሁ፡፡ ሙያዊ አስተያየትና ምክር እንጂ ተቃውሞ አይደለም፡፡ ተቃውሞ የሚለው ቃል ራሱ የፖለቲከኛ እንጂ የሙያተኛም ሊሆን አይችልም፡፡

የይቃወማል ብዥታ የፈጠሩ መድረኮች

በ2009 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ ባሳተምኩት መጽሐፌ፣ ስለግብርና ንግድ ተኮር ክላስተር አደረጃጃት ይዘትና ትችት የለውጡ መንግሥት ከመምጣቱ በፊት ሳቀርብ እንደነበር አመላክቻለሁ፡፡ ታዲያ ይህ እንቀስቃሴዬ ትናንት የተጀመረ ይመስል ‹‹ይቃወማል›› የሚለው አገላለጽ ጎልቶ መሰማት ጀምሯል፡፡ በእኔ ግምት ይህን ጳጉሜን  3 ቀን በ2013 ዓ.ም. በተዘጋጀ፣ ከሦስት ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋር እኔም ተጋብዤ በተደረገ ፓናል ውይይትና በፋና ቴሌቪዥን በተላላፈው ላይ የክላስተር አደረጃጃት፣ የኢትዮጵያን አነስተኛ ገበሬዎች በአክሲዮን በማደራጀት በኢንቨስተርነት በኮርፖሬት አወቃቃር ሰፋፊ እርሻዎችን እንዲያርሱ ለማድረግ እንደታሰበ በተሰጠው መረጃ ላይ የሰነዘርኩት ትችት ያስጀመረው ይመስለኛል፡፡ ትችቱን ያቀረብኩት፣ የመሬት ፖሊሲው በግል ባለቤትነት ላይ ለውጥ ሳያመጣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በደርግ ጊዜ ከተቋቋሙት የአምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆንም ቅፅበታዊ ግንዛቤ ስለሰረፀብኝ ነው፡፡ በከፊልም ይህ ቀደም ሲል ካአካሄድኳቸው ጥናቶች የመነጨ ነው፡፡ 

ከ15 ዓመታት በፊት በመሬት አስተዳደርና አጠቃቃም ዙሪያ እኔ ከመራሁት ጥናት በመነሳት እ.ኤ.አ. በ2015 (2007 ዓ.ም.) በእንግሊዝኛ በጻፍኩት መጽሐፍ በንዑስ ክፍል 8.3.2 አነስተኛ ገበሬዎች ኢንቨስተር መሆን እንደሚችሉ፣ ለዚህም የሚያስፈልጉ የፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያዎችን በምክረ ሐሳብ ደረጃ አቅርቤ ነበር፡፡ ታዲያ ከዚህ ምክረ ሐሳብ ላይ ተነስቶም ሆነ ከሌላ፣ ክላስተር አደረጃጀትን የኮርፖሬት አደረጃጀት ያለው ዘመናዊና ንግድ ተኮር እርሻ ለመፍጠር ማሰብ በደፈናው የአንድን ታታሪ፣ ጥሮ ግሮ በራሱ ሥራ የከፍተኛ እርሻ ባለቤት ለመሆን የሚፈልግን ኢትዮጵያዊ ገበሬ ራዕይ መግደል እደሆነ ተሰማኝ፡፡ በጥልቀት ከታየ በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ በግል ኢኮኖሚ ተዋንያን መሪነት ሊመጣ የሚችልና ባደጉት አገሮች የግል የቤተሰብ (Family)፣ የጥምረት (Joint Venture) እና የአክሲዮን (Corporate) እርሻን መፈጠርና መስፋፋት ለመግታት የታሰበ ሴራም አድርጌ ቆጠርኩት፡፡

ከጳጉሜን ፓናል ውይይት ቀጥሎ በክላስተር አሠራር ላይ ይሻሻል የምለው እንደ መቃወም ተደርጎ ጎልቶ እንዲገለጽ ካደረጉ ኩነቶች አንዱ፣ በ2014 ዓ.ም. በፋና ቴሌቪዥ፣ ፋና መድረክ እኔና በመንግሥት ከፍተኛ አመራር ላይ ባለ፣ ግን እንደ ኢኮኖሚሰትነቱ ከሙያ አንፃር ብቻ ተጋብዞ ያደረግነው ክርክር ነው፡፡ ከዚህ በኋላም በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ለቃለ መጠይቅ ተጋብዤ የሰጠኋቸው ማብራሪያዎች ለጉዳዩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይ በኢቢሲ መድረክ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ፕሮግራም በእኔና በግብርና ሚኒስቴር የኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄኔራል መሀል የምግብ ዋስትናን አስመልክቶ ተቀርፆ በተላለፈው ክርክራችን ላይ፣ አነስተኛ ገበሬዎች ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተገደው የክላስተር እርሻን አደረጃጀት እንዲቀበሉ እንደሚደረጉ ያቀረብኩት የመከራከሪያ ጭብጥ አንዱ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሙያተኞች ማኅበር (ኢግሙማ) በግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ዓመታዊ ጉባዔ (ኮንፈረንስ) ላይ ‹‹በኢትዮጵያ የግብርና መዘመንና ንግድ ተኮር ሒደት የክላስተር እርሻ ሚና›› በሚል በእንግሊዝኛ የተጻፈ ጽሑፍ ጽፌ እንዳቀርብ ጋበዘኝ፡፡ በዚህ መድረክ ላይና በማስከተልም የሪፖርተር ጋዜጣ ከእኔ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በእሑድ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕትሙ ‹‹ኩታ ገጠም እርሻ በተዛባ አረዳድና መንገድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ›› በሚል በዘገበው ላይ በመንተራስ፣ በኤትአይ ውስጥ ያሉ አመራር አካላት ቅሬታቸውን በኢሜይል ለሙያ ማኅበሩ አመራር አካላት አቀረቡ፡፡ ይህ ኩነት ‹‹ደምስ የክላስተር እርሻን ይቃወማል›› የሚለውን አገላለጽ መስመር እንዲለቅ እያደረገው መጣ፡፡ በመቀጠልም መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዴሚ፣ የግብርና ትግበራ ቡድን ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ተቀናጅቶ ባዘጋጀው መድረክ፣ በዕለቱ የመነሻ ጽሑፍ የአቀረበው የኤትአይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስለክላስተር እርሻ ያቀረበውን ጽሑፍ ሲያብራራ (እኔም ነበርኩ)፣ ደምስ (ዶ/ር) እነ እሱ የሚከተሉትን የክላስተር አካሄድ እንደማልቀበለው ገለጸ፡፡ በእርግጥ በዕለቱ ስሜ የተነሳው በዚህ ብቻ ሳይሆን፣ ተቋቁሞ የነበረውን የግብርና ሴክተር አማካሪ ካውንስል/ቡድን የመምራት ሥራዬን እንዳቆምኩም ለታዳሚው አሳውቋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ አላቀርብም፡፡ ስለክላስተር እርሻ በወቅቱ የሰጠሁት ምላሽ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን በጉዳዩ ላይ እንድንከራከርበት፣ እንድንመክርበት ቢያንስ ግማሽ ቀን የሚፈጅ መድረክ ቢዘጋጅ የሚል ነበር፡፡ በዕለቱ ሁለት የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታዎች ስለነበሩ ይህ መድረክ እንደሚዘጋጅ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ የተባለው መድረክ ይህን ጽሑፍ እስካዘጋጀሁበት ጊዜ ድረስ ስለዘገየ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የ‹‹ይቃወማል›› ትርክቱ እየበዛ ስለሄደ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ወሰንኩ፡፡

በክላስተር  እርሻ  አሠራር ላይ ሙያዊ ፍተሻ ለማድረግ የሚያስፈልጉ መርህዎችና ዕሳቤዎች

የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዘላቂነት ያለው፣ ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ ገቢና ኑሮ መሻሻል፣ የምርታማነትና ምርት ጭማሪ የሚያበቃ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ፣ በእኔ ትምህርታዊ መሠረት፣ ዕውቀትና ተሞክሮ በዘርፉ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውም የፖስፕኢ ቀረፃዎችና ትግበራዎች በሚከተሉት መርህዎችና ዕሳቤዎች ዙሪያ የሚያተኩሩ መሆን አለባቸው፡፡

  • የኢትዮጵያ አነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች (ገበሬዎች) የግሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ አውነተኛ ነፃ ኢኮኖሚ ተዋንያን መሆናቸውን ማወቅ፣ ይህንም በሚተገበር (Pragmatic) ፓስፕኢ መደገፍ፣
  • ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች በእርሻውም ሆነ በግብርናው ኢኮኖሚ የእሴት ጭመራ፣ ማኑፋክቸሪንግ ሆነ የንግድ እንቀስቃሴ በሌሎች አገሮች አሉ እንደሚባሉት በዜጎች በሚንቀሳቀስ በሺዎች ሔክታር በሚቆጠር የእርሻ መሬትን ይዘው በቤተሰብ (Family)፣ በጣምራ (Joint Venture)፣ እንዲሁም በኮርፖሬሽን (Corporate Share Holding) ደረጃ የቢዝነስ ተቋማትን ሊመሠርቱ፣ ሊመሩና ሊከወኑ እንደሚችሉ ማወቅና መገንዘብ፣
  • አንድ አነስተኛ ገበሬ ጥሮና ግሮ ከሚያገኘው ገቢ ቆጥቦ፣ በራሱም ሆነ በፋይናንስ ተቋማት እንደማናቸውም የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ ተዋንያን የብድር ድጋፍ አግኝቶ፣ ወደ መካከለኛ ብሎም ከፍተኛ የእርሻ ይዞታ (በማሳ ስፋት) ወይም ከእርሻ ውጭ የሆነ የግብርና ኢንተርፕራይዝ ባለቤትነት ሊሸጋገር እንደሚችል ማወቅና መገንዘብ፣

እነዚህ መርህዎችና ዕሳቤዎች ጋር ተያይዞ የምሰጣቸው ሙያዊ አስተያየቶች፣ ማብራሪያዎችና ምክረ ሐሳቦች ከማኅበራዊ ሳይንስ  በተለይም ከኢኮኖሚክስ ትምህርት ንድፈ ሐሳባዊና ተግባራዊ ዕውቀቴ፣ ልምድና ተሞክሮ የተቀዱ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር መታወቅ ያለበት የትኛውም አገር ሊያድግ፣ ሊለማና ሊበለፅግ የሚችለው ሦስቱ የሀብት ምንጮች በነፃነት፣ ከፍተኛ የምርታማነት አገለግሎት አሰጣጥ ውጤት ሊያስገኙ በሚችሉ የአገር ግንባታና የልማት ሥራ ላይ እየተዘዋዋሩ በዜጎች  ለዜጎች ጥቅም ላይ ሲውሉ መሆንን ነው፡፡ ሦስቱ የሀብት ምንጮች የሰው ኃይል/ጉልበት፣ መሬትና ካፒታል/ፋይናንስ ናቸው፡፡

ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት ነበር የማኅበራዊ ሳይንስ በተለይም የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚዎችና ተንታኞች እነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶን ጨምሮ ለአንድ ቤተሰብ፣ አካባቢና አገር ዕድገትና ልማት ብሎም ሁለንተናዊ ብልፅግና ወሳኝ የሆኑ ሀብቶች የሰው ኃይል፣ ጉልበትና ካፒታል ናቸው ብለው ፍልስፍናዊና ትምህርታዊ ትንታኔ የሰጡት፡፡ እነዚህ ዘመናትን ያስቆጠሩ መርሆችና ዕሳቤዎችን በወፍ በረር ለማመልከት የፈለግኩት፣ ደምስ የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አሠራርን ‹‹ይቃወማል›› ለሚሉት፣  የማደርጋቸው ትችቶችና የምሰጣቸው አስተያየቶችና ምክረ ሐሳቦች ለመቃወም ሳይሆን ከእነዚህ ሙያዊና ትምህርታዊ ግኝቶች የፈለቁ መሆናቸውን፣  በተለይም የስትራቴጂውን አጠቃቃም በማሻሻል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ለግብርናው ዘርፍ ዘላቂ፣ በዜጎች ግንባር ቀደም ተዋናይነት፣ በማሳ ስፋት መዋቅራዊ ለውጥ ላይ የተመሠረተ ዕድገትና ልማት ያመጣ ዘንድ መደረግ ያለበትን ለመምከርና ለመጠቆም እንደሆነ ለማሳወቅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር አያይዤ ለቀጣዩ ማብራሪያዬም ሆነ  ለወደፊትም ጥናትና ምርምር ያገለግላሉ ብዬ የምገምታቸውን የሚከተሉትን ሦስት መላምታዊ (Hypothetical) ጉዳዮችን አቀርባለሁ፡፡

  1. ከሰው ኃይል/ጉልበት ሀብት አጠቃቃም አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮችን (ገበሬዎች) ነፃ ኢኮኖሚ ተዋንያንነትን ሳያከብር፣ በሌላ አገላላጽ እነሱን እንደ ፖለቲካ መሣሪያነት ብቻ ቆጥሮ ከተሠራ፣ ዘላቂ የሆነ ለገበሬው ገቢና ኑሮ መሻሻል አበርክቶ ያለውና ለሌላውም ኅብረተሰብ ክፍል የሚተርፍ ተጨማሪ ሀብት የሚያስገኝ የምርታማነት ሆነ ምርት ለውጥ የሚያመጣ የግብርና (እርሻም ሆነ እርሻ ያልሆነ ኢኮኖሚ አደረጃጃት) ፖስፕኢ ሊኖር አይችልም፡፡
  2. በእርሻው ንዑስ ክፈለ ኢኮኖሚ ገበሬዎች በማሳ ስፋት ይዘት በሚለካ ከአነስተኛ ወደ መካካለኛ ብሎም ወደ ሰፋፊ እንዲያድጉ በሚያስችል በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ዘላቂነት ባለውና በመዋቅራዊ ለውጥ በዘመንና ንግድ ተኮር በሆነ የምርታማትና ምርት ማሳደግ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገቡ ዘንድ፣ የመሬት ፖሊሲው ተከልሶ የግል ባለቤትነትን በሚያካትት ይዘት መሰነድ አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን የሚጀመር ማናቸውም የማሳ ማሰባሰብ ወይም ማገጣጠም አካሄድ ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ግብ የሚጠቅም፣ መንግሥት መር የኅብረት ሥራ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችል ብቻ እንጂ በዘላቂነት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በማሳ ስፋት በታገዘ መዋቅራዊ ለውጥ እዲያመጣ፣ በተለይም ሰፋፊ መሬት ለሚሹ የሰብል ምርቶች በትራክተራይዜሽንና ሜካናይዜሽን የታገዘ ዘመናዊና ንግድ ተኮር ግብርና መመሥረትና ማስፋፋት አይቻልም፡፡
  3. በወቅታዊ፣ ቅቡልነት ባለውና ውጤታማ በሆነ የተሻሻለ ቴክኖሎጂ (ባዮሎጂካል፣ ኬሚካልና ሜካኒካል) በሚጠቀም በማሳ ይዞታ መዋቅራዊ ለውጥ የዘመንና ንግድ ተኮር የሆነ ግብርና ዘርፍን ለመፍጠር ካፒታል/ፋይናንስ ሊያግዝ የሚችለው ለአነስተኛ ገበሬዎች ተደራሽነቱ ሰፊና ዘላቂነት ባለው መሠረት ላይ ከቆመ ነው፡፡ ለዚህ የፋይናንስ ተቋማት አደረጃጀት፣ የፋይናንስ ሥርዓቱና አገልግሎት አቅርቦት ጥራትና ብቃት መሻሻልና ከአየር ባየር ንግድ እንቅስቃሴ ተላቆ ወደ ግብርና መር፣ ገጠር ተተካይ ወደ ሆኑ የማኑፋክቸሪነግ ኢንዱስትሪ ግንባታ ሥራዎች መመራት አለበት፡፡ (ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የግብርና ኢኮኖሚስትና ከ40 ዓመት በላይ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ልምድና ተሞክሮ ያካበቱ፣ የተለያዩ አካዳሚያዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍት የጻፉ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው demesec2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...