በበቀለ ሹሜ
እስከ ዛሬ ድረስ የምናስበውና የምናቅደው ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ቀንድ/ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናችን እያየን፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር መተሳሰርን ነበር፡፡ ውለን እያደርን የምናየቸው ነገሮች የሚነግሩን ግን ከዚህ በላይ ማለፍ (እኛና ደጃችን ግቢ መሆን) እንደሚያሻው፣ ወይም በትክክለኛው አገላለጽ ከኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ቀንድ የሆነው የዕይታና የትልም ማዕዘናችን ከአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ማኅብረሰብነት ወደ ተናጠል አገሮች መዞር እንዳለበት ነው (ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የቀጣናዊ ህልውና የውስጥ አካላት መሆን እንዳላበቸው ነው)፡፡
ይህንን ለማጤን እንዲረዳን አንዳንድ ነገሮችን አፍታተን አንይ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ የኋለኞቹ (ኤርትራ፣ ሶማሊላንድ፣ ደቡብ ሱዳንም ተጨምረው) ስለብቻ ታሪካቸው ማተት ይችላሉ፡፡ በሁሉም የብቻ ታሪክ ሐተታ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እጅ አለ፡፡ ሁሉም የቅኝ ገዥዎች መዳፍ አርፎባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁለቴ ተወራለች፡፡ በ1888 ዓ.ም. በዓድዋ በአንድ ቀን ጦርነት ነጭ ወራሪዋን አሳፍራለች፣ ሙሉ ለሙሉ ባትነቅለውም፡፡ በሁለተኛው መንግሥቷ ፈርሶ ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ አርበኞቿ ተዋድቀው ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ቀሪዎቹም ስለነፃነት ትግልና ነፃነትን ስለመቀዳጀት ማውራት ይችላሉ፡፡ በቅኝ ገዥዎች በነበራቸው የይዞታ ቅርጫ መሠረት ሉዓላዊ አገረ መንግሥት ስለሆኑበት ታሪክም እንዲሁ፡፡ ግን በኢኮኖሚ ነፃ ሆኑ? ድርቅን፣ ረሃብን፣ ድህነትን የውስጥ ብጥብጥን፣ የአሸባሪ እንቅስቃሴን፣ ጦርነትን፣ መፈናቀልና ስደትን አሸነፉ? አላሸነፉም፡፡ የውጭ ወራሪን/ቅኝ ገዥን ድል ከመቱ ወይም ነፃነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ ጥሬ ሀብታቸውንና የገንዘብ ጥሪታቸው ከሰው ኃይል ልማት ጋር አገናኝተው የኢኮኖሚ ግስጋሴ ከማድረግ ምን አገዳቸው? በውጭ ሸር ሊያላክኩ ከሚችሉት በላይ የራሳቸው ውስጣዊ የዘረፋና የሥልጣን ሽሚያ፣ ጎረቤትማማችነትን አዳብሮ አቅምን በልማት ላይ ከማፍሰስ ይልቅ በተለያዩ የቁርቁስ ምክንያቶች/ሰበቦች ጦርነቶች ውስጥ መግባት፣ እነዚህን በመሳሰሉ ጥሪት አድፋፊ ወጥመዶች ተይዘው በቀላሉ መንግሥቶቻቸው ለውጭ አሻንጉሊትነት መመቸት፣ አሻንጉሊት በመሆንም የቅኝ መዋቅርን በእጅ አዙር ማስቀጠላቸው፣ በአጭሩ ዋናዎቹ መሰናክሎች ከውጫዊ ይልቅ ውስጣዊ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ስለደረሰባት የውጭ ከበባ ብዙ ልታወራ ትችላለች፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጵጵስና ሹመት ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረው የሺሕ ተኩል ዓመታት ያህል የተቀጢላነት አንገላች ታሪክ ዓባይን ከመቆጣጠር ውጣ ውረድ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በወታደራዊ መንገድ ዓባይን ለመቆጣጠር ግብፅ ስላካሄደቻቸው ፍልሚያዎችና ከግብፅ ጀርባ ስለነበሩ ኃይሎች፣ ጣሊያኖች ጥሬ ሀብቷን ለመጋጥ ስላካሄዷቸው ወረራዎች ብዙ ማውሳት ትችላለች፡፡ ጂቡቲ ላይ ቱቦዋን የተከለችው ፈረንሣይ የኢትዮጵያ ንግድ ሌላ መግቢያና መውጫ እንዳይኖረው ስታደባ የነበረው፣ እንግሊዝም ጂቡቲ ላይ የነበረችውን ፈረንሣይ በዘይላ ወደብ አማካይነት ልትሻማት የሞከረችው ኢትዮጵያን በመምጠጥ ጥቅም ላይ እንደነበር እንኳ ለእኛ ለጠላትም ግልጽ ነበር፡፡ ጣሊያን ተሸንፎ ሲወጣ የድል አጥቢያ አርበኛዋ ብሪታኒያ የጣሊያን የነበሩ ቴክኒክ ነክ ተቋማትን እየነቃቀለች መውሰዷና የጣሊያን ባለሙያዎችን ብዛት ማመናመኗ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታገኝ መልፋቷ ሁሉ ኢትዮጵያን ባለችበት እንድትረግጥ ከማድረግ ዓላማ አኳያ ብዙ ሊባልለት ይችላል፡፡
ይህንን ሁሉ ደባ ያየችው ኢትዮጵያ ከልምድ ተምራ ምን አቃናች? ሕዝብ ገብ ትግልና ብልህ ዲፕሎማሲ ውጤት አስገኝቶ የኢትዮጵያና የኤርትራ በፌዴሬሽን መያያዝ ከተሳካ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ራሷን ወደ ኤርትራ የዴሞክራሲ ሽታ ከመውሰድ ፈንታ በወለም ዘለምታ ኤርትራን ወደ አሮጌው አፄያዊ ውጦሽ በማስገባቷ ምን አተረፈች? ሰላሳ ዓመታት ጥሪት፣ መሠረተ ልማትና ሰው በበላ የውስጥ ጦርነት ማቅቆ እንደገና የባህር በር የለሽ ወደ መሆን መመለስ፡፡
የኤርትራ ታጋዮች 30 ዓመታት ተዋግተው ‹‹ነፃ›› አገር መሠረቱ፣ ግን በኢኮኖሚና በልማት ነፃ አገርና የዴሞክራሲ ሕይወት መገንባት ቻሉ? ለሁለገብ ልማትና ለሰው ሕይወት ግስጋሴ የሚያስፈልጉት እንደ ኤሌትሪክና ውኃ ያሉ መሠረታዊ አውታሮች ተገነቡ? ከነፃነት በኋላ ኤርትራ በግብርናና በፋብሪካ ፈካች ወይስ የነበሩትም ተንኮታኮቱ? የኤርትራ ወደቦች ያሽቃብጣሉ ወይስ ቆዝመዋል? በውጭ ያሉ የኤርትራ ዜጎች ከሚከፍሉት የዜግነት ግዴታ ባሻገር ለዘመድ አዝማድ በሐዋላ የውጭ ምንዛሪ ይላካል፡፡ ወደ ኤርትራ የሚገባም ሆነ ከኤርትራ የሚወጣ ሰው የተወሰነ ክፍያ በውጭ ምንዛሪ አለበት፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ መልኮች የሚሰበሰብ የውጭ ምንዛሪ የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ለማሸጋገር ይውላል? ወይስ ኤርትራ ሸምቶ-በል ነች ማለት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ነች? በኤርትራ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ በቀን ሦስቴ የመመገብ አቅም ምን ያህል እየሰፋና እያደገ መጣ? እነዚህ ሁሉ ነፃነትንና ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መሆንን አዳብሎ የጋራ ህልውናቸውን በሥርዓት ካለማነፅ ጋር ይያያዛሉ፡፡ ግንኙነታቸውን እንደሚያዛልቅ አድርገው አለማስተካከላቸው ሳያንስ ጭራሽ ሁለቱ ዘመዳም አገሮች በመሬት ቀረኝ ሰበብ በተከፈተና የሁለቱንም አቅም ባጎበጠ ጦርነት የተራዘመ መኮራረፍ ውስጥ ወድቀው ቆዩ፡፡ መለያየትና መቀያየማቸው የሁለቱንም አገሮች እውነታዊ ጉድ አወጣ፡፡ ከመለያየት ይብስ መጣመዳቸው የመልማት አቅማቸውንና በአካባቢው የመታፋር ጥንካሬቸውን ማጉደሉ ወለል ብሎ ታይቷል (ያወራሁት ከማውቀው ውስጥ ጥቂቱን ነው፡፡ አወራሬም አፍ ከማሸራረም ይልቅ የተቆርቋሪነት ውስጣዊ ዕንባ ያለበት ነው፡፡)
ሶማሊያ ከቀጥተኛ ቅኝ ተገዥነት ነፃ ከወጣች በኋላ ታላቋን ሶማሊያ በመገንባት ወጥመድ ተጠምዳ ከጎረቤቶች በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በመሬት አለኝ ጦርነት ውስጥ በተደጋጋሚ ተዘፈቀች፡፡ ምን አተረፈች? አሜሪካና ሩሲያ በተሳተፉበት ግዙፍ ጦርነት ተደቋቁሳ እስከ ዛሬ ጣጣው ወደ አልተገባደደ መቆራረስና የመተራመስ ችግር ውስጥ ገባች፡፡ ኢትዮጵያም ባትዝረከረክም የደረሰባት በጦርነት መዳቀቅ በልማት የማገገም አቅሟን የጎዳ ነበር፡፡
ሱዳን፣ ‹‹ዓረብ›› እና ‹‹ጥቁር››፣ እንዲሁም ክርስቲያንና ሙስሊም በሚል አንጓላይ ጭቆናና ከዚሁ በተወለዱ የውስጥ ጦርነቶች ተጠመደች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ውዝግብ ፍትጊያ ውስጥ ገባች፡፡ ሄዳ ሄዳ ያተረፈችው በድህነት ወጥመድ ውስጥ መዳህና ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሆኖ መከፈልን ነው፡፡ የነዳጅ ሀብትን ከሱዳን ጋር የተካፈለችው ደቡብ ሱዳን ከኋላ ቀርነት ለማምለጥ ወደ ፖለቲካ ሰላምና ልማት አልፈጠነችም፡፡ ከዚያ ይልቅ የውጭ እጅ ያለበት የሀብት ዘረፋና የሥልጣን መንገብገብ ወደ እርስ በርስ ቁርቁስና ውጊያ ወሰዳት፡፡ ሱዳን ደቡብ ሱዳንን ሸኝታ ከውስጥ ትርምስ አልተገላገለችም፣ ሁሉን ባካተተ መፍትሔ የፖለቲካ ሰላም ፈጥራ የዘይት ሀብቷን የልማት ማፋጠኛ የማድረግ ብልህነት አላሳየችም፡፡ የተዋጊዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ዕርቅና ስምምነት አይረጋላትም፣ ቆመ የተባለ ተኩስና ነውጥ ሳይታሰብ እየፈነዳና ቅዋሜ እየተጋጋመ ይንጣታል፡፡ የሚንጣትን ውስጣዊ ዋና ችግር በመፍታት ላይ ከማተኮር ፈንታ፣ ጥሩ ወዳጇ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ የውስጥ ወረራ በገጠማት ጊዜ፣ የአጋጣሚ ተጠቃሚ የምትሆን መስሏት ጦር አዝምታ የተወሰነ የድንበር አካባቢን የእኔ ነው ብላ ያዘች፡፡ በኃይል የያዘችው መሬት ልማት ጨመረላት? የፖለቲካ ሰላም ለማግኘት መሸንገያ ሆናት? ዛሬም ጣጣው ባላለቀ የሰላም ማጣትና የፖለቲካ አለመረጋጋት እየዳከረች ነው፡፡ በቀጣናው ውስጥ ለጎረቤት አገር የታጠቀ ተቃዋሚ መጠጊያና ማኮብኮቢያ መሆን ወጥመድነቱ አፀፋዊ መሆኑ ይበልጥ እየታወቀና ግንኙነቶች እየተሻሻሉ ቢሆንም፣ ዛሬም ወለም ዘለም የሚባልበት ወጥመድ መሆኑ አልቀረም፡፡
የአፄዎችን አገዛዝ ተክቶ የመጣው ደርግ ከአፄዎች አልተማረም፡፡ ደርግን የተካው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያማቀቀና የአገረ መንግሥቱን መዋቅር ፍልስልስ ያወጣ ነበር፡፡ የዚያ ጦስ ደግሞ፣ አንድ ጎጠኛ ቡድን የአንድን አገር የደኅንነትና የታጠቀ ሠራዊት መዋቅር ተቆጣጥሮ የውስጥ ወራሪ መሆን የሚችልበትን አዲስ ልምድ ለዓለም ሊያስተዋውቅ ችሏል፡፡ በዚሁ መዘዝ ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ የውጭ እጅ በነበረባቸው ሦስት የውስጥ ወረራዎችና የተቀፂላዎች ጭፍጨፋዎች ውስጥ አልፋለች፡፡
ጂቡቲ ከፈረንሣይ ነፃ ከወጣች ወዲያ ከፈረንሣይ ወታደራዊ ጥበቃ አልተላቀቀችም፡፡ ከወደብ ገቢ ጋር ወዝወዝ ስትል ቆይታ፣ መሬት ለልዩ ልዩ አገሮች የጦር ሠፈር ማከራየትን ከመጨመር ያለፈ ዕርምጃም አልተራመደችም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ጥቅም ጥብቅ ወዳጅነት ውስጥ ብትቆይም፣ የሕዝቧ ዋና ምድር ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አስተውላ ዳርቻና ዋና ምድርን ወደ አገናኘ ልማት የኪራይ ገቢዋን የማሸጋገር ትልም ገና ያላበጀች ዳርቻ ‹‹አገር›› ነች፡፡
ሶማሌላንድና ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በአምሳያ ሕዝብ መፋሰስ የተያያዙ ቢሆንም፣ እውነታቸውን ያጤነና ከታሪክ የተማረ የጋራ ዕቅድ ያላቸው ስለመሆኑ አለመሆኑ ገና ጠርቶ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሶማሌላንድ ለብቻ አገር ለመሆን ከመጣር በመለስ ከሶማሊያ ጋር እንኳ የተግባባችበት የትስስር ዕቅድ ይኑራት አይኑራት እስካሁን በይፋ አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያ ባድመ ወደ ኤርትራ ስለሄደ ሰማይ አልተደፋባትም፣ ኤርትራም ባድመ ስለተወሰነላት ሰማይ አልተከፈተላትም፡፡ በሁለቱም ልማትና ህልውና ዓይን ባድመ ትርጉመ ቢስ ነው፡፡ ጥቅምን ያስከበረ የህልውና ጉዳይ ብቻውን የአንድ ደረት ሁለት ጡትን ያህል መቆራኘትን ይጠይቃቸዋል፡፡
ከዚህ አኳያም ሁለቱ አገሮች ምን ሐሳብ እንዳላቸው የተነፈሱት ነገር ባይኖርም፣ ሶማሊያ ኢትዮጵያና ኤርትራ ፈጥረውት የነበረው የአጋርነት ስምምነት የይስሙላ እንዳልነበረ የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ ሕወሓት ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎና ቢያንስ ከሻዕቢያ ጋር ተሻርኮ ከኤርትራ ጋር በተቀላቀለ ግዛት ላይ ለመንፈራጠጥ ይሠራ በነበረው ደባ ኤርትራ አልማለለችም፡፡ ከትግራይ መሬትን ወስዶ ከኢትዮጵያ ጋር ከመባላት ይልቅ ከትልቋ ኢትዮጵያ ጋር በወዳጅነት መቀጠልና መተሳሰር ዘላቂ ጥቅሟ እንደሆነ እንደገባት ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈጸመ ጊዜ ያደረገችው ዕገዛ በቂ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ የሦስቱ አገሮች ተደጋግፎ ሰላምና ልማትን የማራመድ ፍላጎት አንዳንድ ትልልቅ አገሮች አላምር ብሏቸውም ይመስላል፡፡ ስምምነት ፈጥረው ለነበሩት መሪዎች አልተኙላቸውም፡፡ በሶማሊያ ውስጥ ‹‹የምርጫ›› ጉዳይ በውስጥም በእነ አሜሪካም የሙጥኝ ተይዞ የነበረው ለዴሞክራሲ ከመቆርቆር አልነበረም፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያ ግዙፍ የሰሜን ሠራዊት ላይ አገር ከማረድ የማይተናነስ ግፍ ሲፈጽምና ይህንኑ በኩራት ሲለፍፍ የኢትዮጵያ ‹‹ወዳጅ›› አሜሪካ አላወገዘችም፡፡ ወረራው አፈር ልሶ አማራና አፋር ላይ በጥላቻና በጭካኔ የደመቀ ግፍ እየፈጸመ ወደ አዲስ አበባ ሲያመራ ፕሮፓጋንዳዊ ጭብጨባ ተደረገለት እንጂ በንፁኃን ላይ ይፈጸም ስለነበረው ጥቃት ኡኡ ያለ አልነበረም፡፡ ሱዳን ወርራ መሬት ስትይዝ እነ አሜሪካ ከኩነና ይልቅ ዝም ዝም ነበር የበለጠባቸው፡፡ እንዲያውም አሜሪካ በጓሮ እየዞረች ከሱዳን ጋር ‹‹ወደጅነትን›› ወደ ማሞቅና ኢትዮጵያ በሌለችበት ዕልፍኝ ስለኢትዮጵያ መንሾካሾክ ውስጥ ነበር የገባችው፡፡ ለምን?
በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ በተነጣጠሉ ዕይታዎች ውስጥ እንዲቆይ፣ ከተቻለም ሌሎች ትንንሽ አገረ መንግሥታት እንዲወለዱ ለምን ተጣረ? ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ጥቅም ሲባል? የአፍሪካ ምሥራቃዊ አገሮች እነዚህን ሁሉ ነገሮች በአግባቡ የመረመረ የጠራ አቋም ገና አልያዙም፡፡ አንዳንዶቹ ችግራቸው ከዚህም ያልፋል፡፡ ውለታ በመሥራት ለምትገኝ ፍርፋሪ ብለው እንደ ኢትዮጵያ ያለ ወዳጃቸውን ገፍተው ከኃያላን ፍላጎት ጋር በፈራ ተባ የሚርመጠመጡ አሉ፡፡ ዓባይ የእኔ ብቻ የሚል አስኳል ያለውን የስስት ፖለቲካ የዓባይ ተፋስስ አገሮች እስካሁን በፍትሐዊነት መከራከሪያ ሳያወላውሉ ሊመክቱት አልቻሉም፡፡
ከዓባይ ፖለቲካ አኳያ፣ የግብፅ ሕዝብ አስተሳሰብ የመተሳስብንና አብሮ የማደግን ፍትሐዊነት ገና ገና አልተቀዳጀም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን በግጭቶችና በውጊያዎች አዙሪት ከውስጥና ከደጅ ጠምዶ በኋላቀርነትና በድህነት ማቃቂ በማድረግ በደል የዓባይን ጥቅም የመቆጣጠር አስተሳሰብ እስረኛ ነው፡፡ ወታደራዊ ገዥዎቹ የረባ ለውጥ እንዳይመጣ በጭቆና መሣሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ሥልጣናቸው ሲንቋቋና የመፈንቀል አደጋ ሲታያቸው፣ ይህን የዓባይን የስስት ወጥመድ እየንቃጨሉ ማስፈራሪያና ከፋፍሎ መቅዘፊያ ያደርጉታል፡፡
የሱዳን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሱዳን መንግሥትም ኢትዮጵያ የያዘችው ዓባይን በጋራ መተሳሰብ እንጠቀም የሚል አቋምና የህዳሴው ግድብ ሱዳንን እንደማይጎዳ ያውቃሉ፡፡ የህዳሴን ግድብ ግንባታ ደግፈው የቆዩትም ጥቅሙን በማወቅ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ከዓባይ ጉዳይ ባሻገር ሱዳን የፖለቲካ መናወጥ በደረሰባት ጊዜ ትርምስና ውድመት በማያስከትል ሰላማዊ መንገድ ለውጥንና የሥልጣን ሽግግርን እንድትመራ የረዳቻትን ኢትዮጵያን በችግሯ ጊዜ ክህደት ፈጸመችባት፡፡ ከመክዳትም በላይ የግብፅ የስስት ፖለቲካ መሣሪያ ሆና ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያዘውን ድርድር አብራ ስታጎሳቁል ቆየች፡፡ ወደ ሱዳን ከገቡ ስደተኞች ሕወሓት ተዋጊዎች እያሠለጠነና መሣሪያ እያስታጠቀ ኢትዮጵያን ማጥቃቱንና በዚህም ውስጥ የግብፅ እጅ መግባቱን የማታውቅ መስላ ፈቀደች፡፡ ሱዳን ከግብፅ ጋር ውን ውን በማለቷ የበለጠ ሕዝቧን ትጠቅማለች? የግብፅ አጀንዳ አስፈጻሚነቷ ሲታሰብ ዕውን ሱዳን በግብፅ አገዛዝ ሥር ከነበረችበት የ19ኛ ክፍለ ዘመን ምን ያህል ርቃለች?
ሶማሊያ በተበጣጠሰችበት ጊዜ ውጤቱን ፌሽታዋ አድርጋ ኢትዮጵያ አንዱን ቁራጭ ደመኛዬ ሌላውን ሽርካዬ አላለችም፡፡ ወይም የሶማሊያን ሽራፊ እንደ ሉዓላዊ አገር ለማወቅ አልሞከረችም፡፡ የሶማሊያን አንድነት ጉዳይ ሳትፃረር ከሁለቱም ጋር ወዳጅነትና የአካባቢውን መረጋጋት ነበር የምትፈልገው፡፡ ሶማሊያ ከትርምስና ከሽብር መናኸሪያነት እንድትወጣ ያደረገችውና እያደረገችውም ያለው ተጋድሎ ለሁለቱም ሕዝቦች ወዳጅነታቸውና ትግግዛቸው አስፈላጊ መሆኑን ያረጋጋጠ ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በ2014 ዓ.ም. ሶማሊያ አዲስ መንግሥት ከቀየረች ወዲያ እንኳ የግብፅንና ያጋዦቿን ተልዕኮ ይዞና ኢትዮጵያን ለማተራመስ ተንጋግቶ መጥቶ የነበረው የአልሸባብ ሠራዊት ኢትዮጵያን ወግቶ የሶማሊያን መንግሥት የሚምር እንዳልነበር (አልሸባብን የመደቆስ ተግባር ተመልካች የማይኖርበት መሆኑ) ወዲያውኑ ነበር የታየው፡፡ ሀቁ ይህን ያህል ፍንትው ያለ ሆኖ፣ የሶማሊያና የኢትዮጵያ መንግሥታት ወዳጃዊ ትምምን በመሪ ለውጥ ሥጋት ወደ እማይገባው ደረጃ ገና አልደረሰም፡፡
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከላይ አስከ ታች ጠረፍ አገሮች ድረስ ውቅያኖሱን ጨምሮ የውጭ ኃያላት ጣቢያዎችና መርከቦች ተሰማርተውበታል፡፡ በዚህ ሥምሪታቸው ውስጥ የቀጣናው አገሮች ሰላምና ተረጋግቶ ማደግ ጉዳያቸው ከሆነ እንደ አልሸባብ ያሉ አተራማሾችን የሚነቅል ዕገዛ መስጠት ከባድ ባልሆነባቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ወዳጅነት ያዝ ለቀቅ ከማድረግ ይልቅ የቀጣናው አገሮች መርምረው መመለስ ያላባቸው አንዱ ጥያቄ ይህ ነው፡፡ በፍትሐዊ የጋራ ጥቅም ተሳስሮና ከንቁሪያ ርቆ በመልማት ድህነትን፣ ድርቅን፣ ረሃብን፣ የተዛማች በሽታዎችንና የተባዮችን ጥቃት የማሸነፍ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ተግባር አልተቀየረም፡፡ አለመቀየር ብቻ ሳይሆን የእውነታው ግዴታ ጥንካሬና ጎትጓችነት ከጊዜ ጊዜ እየጠነከረ እንጂ እየላላ አይደለም የመጣው፡፡ እንዲያም ሆኖ በሕገ መንግሥታዊ መንገድም ሆነ በሕገወጥ መልክ በጎረቤት ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ የፖለቲካ መዋዠቅና የውስጥ ፍርክስ ሲከሰትና ምዕራባዊ ኃያላን ግልምጫቸውን ኢትዮጵያ ላይ ሲያሳርፉ፣ ለተጋገዘ ልማት የተለፋበት የጉርብትና አጋርነት ይቀጥል ይሆን/ያፈተልክ ይሆን የሚል ጥርጣሬ ቀጣናውን ይጎበኘዋል፡፡ ጉድኝት ይሙለጨለጫል፣ ተመልሶ ጥሬ ከመሆንም አልፎ የጠላትነት ሚና ሲይዝ ታይቷል፡፡ በአንዳንድ ሁኔታ ልክ የኢትዮጵያ መንኮታኮት ለጎረቤቶቿ ሰላምና ልማት ጠቃሚ የሚሆን ወይም መዘዝ የለሽ መሬት ይገኝበት ይመስል፣ በሬ ጉያ ውስጥ የሚወዛወዘው ነገር ከአሁን አሁን ወደቀልኝ እያለች ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ አንዳንዶች የእኛን ቀውስ ተቁለጭልጨውበታል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ጂቡቲና ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛታዊ ፅናትና የፖለቲካ ሰላም ለአካባቢ ሰላም አስፈለጊ መሆኑ የማያወላውል አቋም ሊያዝበት የሚገባ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መፈራረስ ጠቅላላ በቀጣናው ውስጥ ሽብርና ጦርነቶች የሚያባዛ፣ በአረንጓዴ ልማት መተጓጎል ድርቅን የሚያባብስ፣ አንበጣን የመሳሰሉ ተባዮችን የመቆጣጠር አቅም የሚያዳክም፣ ድህነትን/ችጋርንና የስደት ማዕበልን የሚያስፋፋ፣ በዚህ ሁሉ መዘዝም የፖለቲካ ቀውሶችንና ትርምሶችን የሁሉም የሚያደርግ አዙሪት የሚያስነሳ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የአዙሪቱ ጉዳት ሰሜን አፍሪካ ድረስ ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ ተበጣጥሳ ሥርዓት አልባነት ውስጥ ብትገባ ጣናና ዓባይ በብክለትና በአረም መጎሳቆላቸው እጅግ ይከፋል እንጂ አይቀልም፡፡ በዚህ ላይ ብቀላ ከተጨመረበት አያድርስ! እናም በኢትዮጵያ መውደም ከማንም በላይ ግብፅና ሱዳን ለአደጋ የሚጋለጡ መሆናቸውን አለማወቃቸው ድፍን ቅልነት ነው (ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ ግብፅ ድረስ የግብርና ውጤቶች ጥቅም ካላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ዓረቦች መሀል አንዳንዶች የግብፅ አማሽነት ጭፍን ደጋፊ በመሆናቸውም እየተፈታተኑ ያሉት የራሳቸውንና የግብፅ ሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ነው)፡፡ ወጣም ወረደ፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገሮች ሰላማቸው፣ ልማትና ዕድገታቸው በጋራ መሥራትንና አብሮ መቆምን ግድ ማለቱ ያዝ ለቀቅ የማያደርጉት የተግባር መንቀሳቀሻቸው (ግብታዊ ንቃታቸው) መሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን በማጤን ረገድ ውራ ደረጃ ላይ ያሉት (የገዛ ስትራቴጅያዊ ጥቅማቸውን በማቁሰል ዛሬ አንደኛ ደረጃን የያዙት) ሱዳንና ግብፅ ናቸው፡፡ ከሱዳን የባሰባት ደግሞ ግብፅ ነች፡፡ በስስት የታወረ ዱልዱም ብልጠትና ኢትዮጵያን የማመስ ተንኮል ይዛ ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ላይ ታች ማለቷና አንዳንድ አባሪ ማግኘቷ ለቀጣናውም ሆነ እሽክርና ለሞካከረው አገር ትልቅ ውርደት ነው፡፡
የዚህ ሁሉ ምንጭ በድንክ ትልም መጠመድ ነው፡፡ የድንክ ትልሞች ዋና አገዳው የአገር ጥቅምና ስኬትን በየብቻ አገርነት ማዕቀፍ ውስጥ አጥብቦ፣ ከጎረቤቶች ጋር ያለውን ግንኙነት (በጋራ ልማትና በሰላም ጭምር) የውጭ ግንኙነት ጉዳይ አድርጎ ማየት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሌሎች ወጥመዶችም አሉ፡፡ ወደ ጎረቤት አልፎ የሄደ መሬት አለኝ የሚል ውዝግብ ወጥመድ ነው፡፡ ድህነትን ለማቃለል አለመትጋትና አለመቻል፣ ዘረፋና ሙስናን ለመቆጣጠር/ለማድከም አለመቻል፣ ከጥፋቶች ተጠያቂነት ለማምለጥ ብለው ገዥዎች ሥልጣን ላይ መሟዘዛቸው፣ የሕዝብን ብሶት ከገዥነት ላይ ዘወር ለማድረግ ከጎረቤት ጋር መናቆርን በስመ ሉዓላዊነት መነገጃ ማድረግ፣ ብሶቶችንና ቅዋሜዎችን ለማፍዘዝ የሚሆን ዕርዳታ ብድር/ወታደራዊ ዕገዛ ባገኝ በማለት ከጎረቤት ጋር ያሉ ግንኙነቶችን ሊያደፈርሱ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች መሸነፍ፣ እነዚህ ሁሉ ወጥመዶች ናቸው፡፡ የቀጣናችን አገሮች እነዚህን በመሳሰሉ ወጥመዶች ከመጠመድ ማምለጫቸው በተቀዳሚ ህልውናቸው መንታ ፈርጅ ያለው (በተናጠል አገርነት ደረጃ በሚያካሂዱት ውስጣዊ ባለ ብዙ ፈርጅ ስኬትና በቀጣና ደረጃ በሚያሳኩት የልማትና የሰላም ስኬት የሚወሰን) መሆኑን ማጤን ነው፡፡ ይህንን ዕውናዊ ግንዛቤ መሠረት በማድረግም ከተናጠል አገርነት ባሻገር በቀጣናዊ ማኅበረሰብነት መደራጀት (በአንድ ጊዜ አገራዊና ቀጣናዊ ሉዓላዊነት ይዘው) ሁለገብ አቅማቸውን ወደ አንቀሳቀሰ ልማት መጓዝ ነው፡፡ የየአገራቸውን ጥቅምና ዕርምጃ ሁሌም በቀጣናዊ (በማኅበረሰበዊ) የህልውናቸው ትልቅ አድማስ ውስጥ ማየትና ማሰብ መቻላቸው ነው፡፡
ይህንን አስቀድመው የተገነዘቡ ምሁራን በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ በቀጣናው ውስጥ ይኖሩ ይሆናል፡፡ አተያዩ በምሁራን ዘንድ ተነስቶ መወያያ ከሆነም በኋላ፣ በቀጣናው ውስጥ ሊቀባበሉት፣፣ ብሎም ወደ ሕዝብ ዘንድ ሊያሰርፁትና ሊያስፋፉት ይችሉ ይሆናል፡፡ በቀጣናው መንግሥታት ደረጃ እየተሰባሰቡ በዚህ ላይ ለመመካከር መሞከር ግን የተቻኮለና ብዙም የማይፈይድ ይመስለኛል፡፡ ወደ ማኅበረሰባዊ ቅንብር ውስጥ የመግባት ነገር አገሮችን በዋና ዋና ዕውናዊ ፈርጆች ማቀራረብን ይጠይቃል፡፡ በመንግሥታት ዘንድ በአሁኑ ደረጃ አንድ ዓይነት ዕይታና ቁርጠኝት ገና የለም፡፡ ከመንግሥት መቀያየር ጋር ሄዶ መለስ የሚል የአቋም መዋዠቅ የማይኖረውም ዓላማው ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት በቀጣናው አገሮች ውስጥ ካገኘ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የቀጣናው መንግሥታት በማኅበረሰብነት የመቀናበር ሐሳብን ገና ማንከባለል ሲጀምሩ፣ ሐሳቡን የጥቅምቸው ጠንቅ አድርገው በመተርጎም የማወላከፍና የሽብልቅ ሥራ ውስጥ የሚገቡ የቅርብና የሩቅ ኃይላት አይጠፉም፡፡ ቱስ የተባለ የትኛውም ረብ ያለው ነገር ለታላላቆቹ አገሮች ጆሮ ባዳ አይሆንም፡፡ ዛሬ ባለው የቴክኖሎጂ አቅም፣ ስለላ የሰው አሾክሿኪ ሳይሻ እንደ አየር የትም የሚገኝ ከሜዳ እስከ ቤተ መንግሥት የዘለቀ ነው፡፡ በፖለቲከኞች፣ በምሁራንና በመንግሥታት ውስጥ የምትተነፈስ ነገር ሁሉ፣ እየተቀለበች ‹‹በሚያስብ›› የመረጃ ቴክኖሎጂ ዕገዛ ሳቢና ትኩረት የሚሹ ወሬዎች በአጭር ጊዜ ይንጓለላሉ፡፡ በፊት ከነበረ መረጃ ጋር ይገናዘባሉ፣ ይተነተናሉ፣ የአሳሳቢነትና የልዩ ክትትል ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡ እናም፣ ‹‹በዳግም ቅኝ ግዛታዊ ፍላጎት አፍሪካን ስለማተራመስና ስለመቦጥቦጥ…›› እየቀባጠሩ ቀጣናዊ ማኅበረሰብነትን ለማሳካት መሞከር እየካቡ ከማፍረስ አይለይም፡፡ ቀጣናዊ ማኅበረሰብነትን ዕውን የማድረግ ተግባር ጠንቃቃ አካሄድን ይጠይቃል፡፡ ሁነኛ ጉዳዮቻችን፣ ወዳጅነት፣ ሰላም፣ የተዋጣ የሕዝብ አስተዳደር፣ በልማትና ግስጋሴ ረሃብንና ሰው ሠራሽ ሰቆቃዎችን ማስቀረት ነው፡፡ በጋራ ዕይታ ውስጥ ሆኖ እነዚህን ለማሳካት፣ በነገረኛ ምላስም ሆነ በመቆነን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ሳይገቡ የሁሉ ወዳጅ በሆነ ሰምና ወርቅ መጠበብ ያስፈልጋል፡፡ በሰምና ወርቅ በመጠበቡ ጉዞም ውስጥ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና አላት፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ ተግባራት ተወራራሽ ሆነው ይመጣሉ፡፡
- ኢትዮጵያ በአገራዊ ምክክርና መግባባት፣ ከዚያም ጋር ተያይዞ በሚመጣ ሕዝቦች የእኔ ብለው ባፀደቁት ሕገ መንግሥት ቤቷን እያደሰች ዳግመኛ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ በአገረ መንግሥቷም ላይ ሆነ በጎረቤት ላይ የሚተኩስ የጠመንጃ ቡድን የማይበቅልበት ታሪክ ዕውንና ዘላቂ እንዲሆን የሚያስችሉ ሁለገብ ሥራዎችን ማካሄድ መሠረታዊ ተግባር ነው፡፡
- ኢትዮጵያን በዓለም ታይቶ የማይታወቅ የውስጥ ወራሪ እንዲያጋጥማት ያደረጉ በሥልጣን አያያዝና በመንግሥት ዓምዶች አወቃቀር ዘንድ የደረሱ ብልሽቶች እንዴት ያሉ ነበሩ? እነዚህ ወረራዎች በተፈጸሙባት ጊዜ ሉዓላዊነቷን የጣሱና የመላ ሕዝቦቿን ህልውናና ሰቆቆ ያከፉ ምን ዓይነት ስህተቶች በቅርብና በሩቅ አገሮችም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች አካባቢ (በአጭበርባሪ መረጃና ፕሮፓጋንዳ አሳሳችነት በወገንተኛ ግለሰቦች ተፅዕኖ ፈጣሪነት) ተፈጸሙ? ልምዱ ለኢትዮጵያም፣ ለአፍሪካም፣ ለሌላው ዓለምም ትምህርት እንዲሆን በደንብ አጥንቶና ሰንዶ ለዓለም ይፋ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ተግባር የሚወጣ ገለልተኛና ተዓማኒ ተቋም ኢትዮጵያ እንደማታጣ ተስፋ አለን፡፡
- ኢትዮጵያ በዚሁ ልምድ ትምህርታዊነት ላይ ተመሥርታ አጥብቃ በምትይዛቸው አቋሞች ውስጥ የሚከተሉት የሚካተቱ ይመስለኛል፡፡
- ለሉዓላዊነቷ ከመቼው ጊዜ በላይ ቀናዒ፣ በዚያው ልክ የሌሎችን ሉዓላዊነት አክባሪ መሆን፣
- ወዳጃዊና ሰላማዊ ግንኙነት ከሁሉም ጋር ጥቅል መርህ ሆኖ፣ ለጋራ ጥቅምና ብልፅግና ከሚሠሩ ጋር አጋርነት ማበጀት፣
- የፀጥታ አውታሯን አሠፋፈርና የቅኝት አካላይነት በሁሉም አድማሶች ኮሽታ የማያመልጠው አድርጎ በማብቃት ረገድ ሁሌም ከዓለም የጥበብ ግስጋሴ ዓይኗን አለመንቀል፣
- በአፍሪካ ውስጥ የጎረቤት አገረ መንግሥትን በቀውስ ውስጥ የመውደቅ አጋጣሚ ጠብቀውና በአጋጣሚው ብንጠቀም ብለው ወታደራዊ ጥቃት/የድንበር መግፋት በሚያካሂዱ ወይም በተቃዋሚ ስም የታጠቀ ኃይል እያሠረጉ ቀውስ በሚያባብሱ ላይ አኅጉራዊ ኅብረቱና ቀጣናዊ ስብስቦች ፍሬያማ የግሰፃ አቅም እንዲኖራቸው መታገል፣
- በማንኛውም ጊዜ ወዳጃዊ ግንኙነት ደፍርሶ ጎረቤታማማቾች አንዳቸው በሌላቸው ላይ ‹‹የተቃውሞ›› ታጣቂ ቡድን ማሠልጠኛና ማኮብኮቢያ ወደ መሆን ከማምራታቸው በፊት ፀብን የማድረቅ ባህል በአኅጉሩ ውስጥ ጠንካራ ሥርዓት እንዲያበጅ፣ መጠቃቃት በተግባር ተከስቶ በግልግል አልቋጭ ባለ ጊዜም በእጅ አዙር ተጠቃቂዎቹ ላይ ቆንጣጭ ዕርምጃ መውሰድ እንዲኖር መሥራት፣
- በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተመድ በኩል ለሰላም አስከባሪነት ሠራዊት ኢትዮጵያ እንድታዋጣ በተጋበዘች ጊዜ ከሁሉ በፊት የሠራዊት ሥምሪቱ ሰላምንና መረጋጋትን የሚጠቅም መሆኑን መገምገም፣
- በጎረቤት አገር ዘንድ፣ መንግሥት ጨንግፎ ሥርዓት አልባነት ያንዣበበት ሁኔታ ተፈጥሮ፣ ቀውሱ በአካባቢውና በአፍሪካ ኅብረት ተጢኖ፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጎረቤት አገርንና ሕዝብን የማዳን አስቸኳይ ተግባር ሲሆን፣ ወይም ሕጋዊ መንግሥት ባለበት ሁኔታ አገረ መንግሥቱና ሕዝቡ በአሸባሪ አውዳሚ እንቅስቃሴ እየታወከ ከሆነና ከሕጋዊ መንግሥቱ የጣልቃ ገብነት ጥሪ ከመጣ፣ ጣልቃ ገብነቱም የታወከውን አገር ሰላም የሚበጅ ሲሆን ብቻ ጣልቃ መግባት፣
- ኢትዮጵያ ከሆነ ጎረቤቷ ጋር ውዝግብ ውስጥ ብትገባ (በወታደራዊ መንገድ ብትተነኮስ እንኳን) ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ችግሮችን በሰላማዊ መንገዶች ለመጨረስ መሥራትን ሁነኛ ፍላጎቷና ጥረቷ ማድረግ፣
- የትኛውም የአፍሪካ አገር ሰላሙንና አገራዊ ህልውናውን የሚያፍረከርክ የጉልበተኛ ጣልቃ ገብነት/ማዕቀባዊ ስነጋ እንዳይዳረስበት የመከላከል፣ ሲቃጣም ተጋግዞ የማምከን አቅም በክፍለ አኅጉርና በአኅጉር ደረጃ እንዲጎለብት መሥራት፣ በዚህ ረገድ መጎልበት ያለበት ዋናው የመከላከያና የማክሸፊያ አቅም፣ ወታደራዊ ሳይሆን በየአገሮች ውስጥ የሕዝብንና የመንግሥታትን ግብብነት/ትምምን የሚያሳድጉ የዘርፈ ብዙ ዕገዛዎች አቅም መሆኑን ማጤንና ማስጤን፣
- የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ በጦርነት የማይታወክ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ ቀጣና እንዲሆን ከሚሠሩ የቅርብና የሩቅ ኃይሎች ጋር ሁሉ ተባብሮ መሥራት፣
- ከድንበርተኛ ጎረቤቶች ጋር የጋራ መሠረተ ልማትና የልማት ትስስር እንዲጎለምስ መሥራት፣
- ከተሳሰረ ጉርብትና ባለፈ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴራላዊ ሉዓላዊነት ተያይዞ ለማንም ሥጋት ከመሆን ይልቅ አርዓያ የሚሆን የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ግስጋሴን ዕውን ማድረግ ከሚሻ ጋር አብሮ መሥራት፡፡
የመጨረሻዎቹ ሁለት አቋሞች አባባይና ተባባይ የሚኖርባቸው ወይም ፕሮፓጋንዳዊ ውስወሳ የሚሹ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ የሚፈለግባት ከመራራ ልምዷ ተምራ በሁለት ነገሮች ምሳሌ መሆን ነው፡፡ ፍላጎትን በጠመንጃ ለማሳካት ጫካ መግባትን እስከ ወዲያኛው የሚያቋርጥ፣ ችግሮችን በምክክርና በዴሞክራሲ መንገዶች የመፍታት ባህልን በመገንባት፣ በተመጣጠነ ልማት፣ ንቅዘትን በተቆጣጠረ ቀልጣፋ የመንግሥት አገልጋይነትና ትምምንን በማይሸፍጥ ጉርብትና የውስጥ ሰላሟን መንከባከብ አንደኛው ነው፡፡ በጎረቤት አገሮች/ሕዝቦች ዓይን ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ሁሉንም የመሀልና ‹‹የዳር›› አካባቢዎቻችንን የኢኮኖሚ መዋቅር ያራመዱና የሕዝብን ኑሮ የነቀነቁ የልማትና የባህል ብልፅግና ስኬቶችን ማሳየት ሁለተኛው ነው፡፡ በሰሜን ከአክሱማዊ ሐውልቶች ምድር፣ ከሉሲ ምድር አንስቶ እስከ ሸበሌ ምድር፣ ከዚያም የእንሰትና ገዳ ነክ ባህልን ይዞ በእነ ጋምቤላ በኩል ዞሮ ሰሜን የሚገባው አካባቢ ‹‹ዳርቻ/ባለ ዳርቻ›› መስሎ የሚታየን፣ ኢትዮጵያን ብቻ ነጥለን ስንመለከት ነው፡፡ በቀጣናው ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያን ከተመለከትን ግን የዳር የመሰሉን/የሚመስሉን ሕዝቦች የመሀል ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ሕዝቦች ሕይወት ውስጥ የሚመጣ የልማት ተዓምርም የቀጣናውን መሀል ማንቃቱ አይቀርም፡፡ ማለትም ዙሪያ ገብ ልማታችን ለተጎራባቾቻችን በተሳሰረ ልማት መፈላለግና መቀጠል ጎትጓችና ጠባቂ ይሆናሉ፡፡ እነዚህም እውነታዎች በመንግሥት አመራር መለዋወጥና መጥመም ለመረበሽ ቀላል አይሆኑም፡፡ ለውጭ ኃይል አድር ብሎም ሆነ በሌላ የፀብ ሰበብ ሊረብሻቸውና ሊያቋርጣቸው የፈለገ መንግሥትም ከአገሩ ጥቅምና ከሕዝቦች ፍላጎት ጋር መጋጨት ይሆንበታል፡፡ የቀጣና ማኅበረሰባዊ ትስስርን መሠረት ለመጣል አስተማማኝ ስንቅ የሚሆነው፣ የዚህ ዓይነት ድንበር አለፍ የዙሪያ ሕዝቦች ንቃት ነው፡፡
ይህ ዕውን እንደሚሆንና ኢትዮጵያ ሳታቅራራና ሳትጠመድ የምትታፈር፣ ዙሪያዋን ተሳስሮ አንድ ላይ ለመመንደግ የምትናፈቅ፣ የአረንጓዴ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ ግስጋሴ ፈርጥ እንደምትሆን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የእርግጠኛነታችንም መሠረት በኢትዮጵያ በየፈርጁ ጎህ እየቀደደ መሆኑና የኢትዮጵያ ልማት የሚንቦገበገው ከእስከ ዛሬው ጊዜ በተለየ ድባብ ውስጥ ስለሚሆን ነው፡፡ ልጠቃቅስ፡፡
1ኛ/ የኦክቶፐሱ ጭንቅላት ሲሞት በሌሎች ሥፍራዎችም የሚተኩሱት ጣቶቹ አብረው ይደርቃሉ፡፡ ከዳር ዳር የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጠመንጃ ቡድን ከዚህ በኋላ በጉያቸው መደበቅ ይቅርና የጥይት ድምፅ መስማት አንገሽግሿቸዋል፡፡ ይህ የሕዝብ ምሬት የጠመንጃ ቡድኖችን እስከ መጨረሻው ለሚያከስም ሁለገብ ሥራ ትልቅ ስንቅ ነው፡፡ ከዚህ ወዲያ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ተመልሶ ጥሬ የሚሆን ችግር ቢኖር ከፖለቲካችንና ከመንግሥት አመራራችን ተጠያቂነት ውጪ ማሳበቢያ አይኖርም፡፡ የሕወሓት-ሸኔ አተራማሽነትን የተጠለሉ ሰውን በሰው እየገፉ ይዞታ የማስፋት ቁርቁሶች እዚያም እዚያም ሞቅ ፈዘዝ እያሉ እስካሁን ድረስ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በድህረ ጦርነት ኢትዮጵያ የሕዝብ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በቶሎና በሚያዛልቅ አኳኋን ለመዝጋት የሚሳነው መንግሥት ከእንግዲህ እያቃሰተ የሚያጎነብስለት ሕዝብ እንደማይኖር ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባል፡፡
2ኛ/ ሰላምን የሚያውኩ ርዝራዦችን በፀጥታ ኃይሎች ከማጠናቀቅ ባሻገር ዋና ማክሱሚያው ሁለገብ ልማት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ የአካባቢ መንግሥታት፣ የከተሞች አስተዳደሮችና ዩኒቨርሲቲዎች በተያያዘ ሥራ ኢትዮጵያን የልማት ተዓምር መፍለቂያ እንደሚያደርጓት ፅኑ ተስፋ አለ፡፡ በዚህ ረገድ የሰው ልማትን የተመረኮዙ ሥራዎች በየዘርፉ እየተስፋፉ ከሕዝብ ኑሮ መሻሻል ጋር መራመድ መቻላቸው የትኩረት አንድ ነጥብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚመጣው የሕዝብ ዕርካታ ሁሉ ሰው በፌዴራል መንግሥት ላይ አማራሪ/አልቃሽ ሆኖ የቆየበትን ሁኔታ ከመቀየር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም እስከ ታች የወረዳና የቀበሌ ማኅበረሰብ ድረስ የአስተዳደር መዋቅሮች በየዕርከናቸው ለሕዝብ ተጠያቂና ለሕዝብ አቤቱታ መልስ ሰጪ የሚሆኑበት ሥርዓት በአግባቡ መዘርጋትና ህያው ሆኖ መሥራትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ በጎደለበት የሕዝብ ሰላም ተጨባጭ አይሆንም፡፡
3ኛ/ የኢትዮጵያ ሰላምና ሁለገብ ልማት ከመንቦግቦጉ ጋር ብሔርተኛ ባህታውያን በኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ የሙዚየም ዕቃ ይሆናሉ፡፡ እነሱ በአስተሳሰባቸው ያጣመሟቸው ወጣቶች ይቃናሉ፡፡ መደዴ የአሉባልታ ‹‹ፖለቲከኛነት›› ደመናና ዝናብ እንዳጣ ሙጃ ይሆናል፡፡ ጥላቻና ቂም ባልሰነከላቸው፣ ኅብራዊ አመለካከትና ባህል ባላቸው ወጣቶች ኢትዮጵያ ትንቆጠቆጣለች፣ ትታነፃለች፡፡ ግዕዝ የእከሌ፣ ገዳ የእከሌ፣ ወዘተ. የሚል የማዶ ለማዶ ክፍፍል በሌለበት አኳኋን የኢትዮጵያ የባህል የታሪክና የቋንቋዎች ሀብቶች ይጠናሉ፣ ይደራጃሉ፣ ለዛሬና ለነገ ሕይወት ባላቸው የቅርስነትና የመኗኗሪያነት ፋይዳ ለአዲሱ ትውልድ ይሸጋገራሉ፣ አዲሶቹ ወጣቶች ብዙ ቋንቋ (ቢያንስ ሁለት የአገር ውስጥ ቋንቋዎችና አፍሪካን ያሰበ የውጭ ቋንቋ/ቋንቋዎች) ተናጋሪነትን በተባ ደረጃ ይዘው ስለሚወጡ ሰብዕናቸው ኢትዮጵያዊነት አፍሪካዊነትም፣ ዓለም አቀፋዊነትም የሚንፀባረቅበት (ኅብራዊ) ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በኪስዋሂሊ፣ በዓረቢኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሣይኛና በመንደሪን፣ ወዘተ የተባ አንደበት ባላቸው ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማሲያዋን የማካሄድ ድርቅ አያገኛትም፡፡
4ኛ/ ኢትዮጵያውያን ከውስጥ ጦርነት ከመገላገላቸው ጋር አብሮ፣ አገረ ኢትዮጵያን በማዕቀብ ለማንበርከክና በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመበርቀቅ ይፈለግ የነበረው ቀዳዳ ሁሉ ሜዳ ላይ ይቀራል፡፡ በሰው ልጆች መብትም ሆነ በሰብዓዊ ርኅራኄ ስም ባለ ብዙ መልክ ዕገዛ ለጦረኞች ሲሰጡ የነበሩ አገሮችና ተቋማት በድጋፋቸው የትግራይን ሕዝብ ሰቆቃና የደም ግብር ምን ያህል እንዳቀለሉና እንዳባባሱ በሒደት ቁልጭ ይላል፡፡ የሰው ልጆችን መብትና ክብር በመንከባከብ ረገድ በአርዓያነት ከሚጠቀሱት መካከል ነን እያሉ ኢትዮጵያን እንደ ደመኛቸው ጠምደው የቆዩ አገሮችና ተቋማትም የፍትሐዊነት ልካቸውን ያውቁታል፡፡ በአያሌ ኢትዮጵያውያን ተደግፎ የአገረ መንግሥቱን ሸፋፋነት እያቃና የመጣው የለውጥ መንግሥት፣ በእነሱ ጥቅም የመጣ መስሏቸው የተቃወሙት አገሮችም የኢትዮጵያን እውነተኛ ፍላጎትና ማንነት ያለ ውዥንብር ለማስተዋል ጥሩ ዕድል ያገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላምንና ፍትሐዊ ልማትን ከማንገሥ በቀር ከማንም ጋር ተናክሳ መኖር የማትሻ፣ ማንንም የመጉዳት ፍላጎትና ትልም የሌላት፣ ለየትኛውም ልዕለ ኃያላዊ ቡድን ሎሌነት መግባት የማትፈልግ፣ ከሁሉም አገሮች ጋር በጋራ ጥቅም መወዳጀት የምትሻ፣ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር ሁሉ የአፍሪካ ኅብረትንና የተመድን መርሆዎች አክብራ የመሥራት በጎ ፍላጎት እንዳላት ውሎ እያደር ወለል ይላል፡፡
አገራችን የሰምና ወርቅ ጉዞዋ የተሳካ ይሁንላት!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡