ከዓመታት በፊት ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ዩጎቪያ የሚባል የምሽት ክበብ ነበር፡፡ በተለይ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ክበቡ በደንበኞቹ ይጨናነቃል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ዝነኛ የነበሩ ሙዚቀኞች ወደ አዲስ አበባ ከመንጎዳቸው በፊት፣ በዚህ ክበብ ሥራዎቻቸውን ስለሚያቀርቡ ከተለያዩ አካባቢዎች ሐዋሳ የሄዱ ሰዎች ዩጎቪያን ሳያዩ አይመለሱም ነበር፡፡ እኔም ሐዋሳ በሄድኩ ቁጥር ከወዳጆቼ ጋር ዩጎቪያን መታደም የወቅቱ ልማዴ ነበር፡፡ በጣም ከማልረሳቸው ገጠመኞቼ መሀል ዩጎቪያ በራፍ ላይ በሴተኛ አዳሪዎችና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የነበረው ትንቅንቅ ነው፡፡ ዝንጥ ብለው የሚመጡት የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች፣ ከሐዋሳ ሴተኛ አዳሪዎች ይገጥማቸው የነበረው ተቃውሞ ከፍተኛ ነበር፡፡
በአንዱ ቅዳሜ ምሽት ከወዳጆቼ ጋር 4፡00 ሰዓት አለፍ እንዳለ ስንደርስ ዩጎቪያ ክለብ በራፍ ላይ ትርምስ ተነስቶ፣ ሴቶቹ በክለቡ ጥበቃዎችና በፖሊስ ኃይል ሲገላገሉ ነበር፡፡ ሴቶቹ የዚያን ዕለት ምሽት የተለመደው አምባጓሯቸው ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ ፀጉር ለፀጉር ተያይዘው ፊታቸውን፣ አንገታቸውንና እጆቻቸውን ጭምር እየተናከሱና እየተቦጫጨሩ መሬት ላይ ተንከባለው ሲታገሉ በመቆየታቸው ደም በደም ሆነዋል፡፡ በግምት ከአሥር የማያንሱ ሴቶች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሲታዩ ያሳዝኑ ነበር፡፡ ሴተኛ አዳሪዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሥራችንን ሊሻሙ የሚመጡ ጠላቶቻችን ናቸው ስለሚሉ አይግባቡም፡፡ በዚህ የተነሳ ጠላትነታቸው በመክፋቱ ነበር የዚያን ምሽት ጦርነት ደም ያቃባቸው፡፡
የዛሬን ባላውቅም ያን ጊዜ ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ገበታ ላይ እየጠፉ በየጫት ቤቱ፣ በየሺሻ ቤቱና በፔንሲዮኖች ጭምር ጊዜያቸውን ያባክኑ እንደነበር ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ከወንዶቹ መሀል በጫትና በመጠጥ ሱስ፣ ከዚያም ባለፈ የአደገኛ ዕፅ ልክፍት ውስጥ የገቡ ነበሩ፡፡ ሴቶቹም ከሱሱ ባሻገር ገንዘብ ከሚሰጣቸው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለማድረግ በየፔንሲዮኑ መታየታቸው ብርቅ አልነበረም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ማማለያዎች የተነሷቸው ፎቶግራፎች እንደ ካታሎግ ተደርገው፣ ከአዲስ አበባ ጭምር ለሚሄዱ እንግዶች የወሲብ ግብዣ ይቀርብላቸው እንደነበር አይረሳም፡፡ በዩጎቪያ ክለብ በራፍ ላይ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ሁሌም ጠብ ይነሳ የነበረው፣ ከላይ ከተጠቀሰው ውሎ ጋር ተያያዥነት ስላለው ነበር፡፡ በወቅቱ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ይህ ሁሉ ትርምስ ይዘገብ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህንን ከላይ ያነሳሁትን የሐዋሳ ትዝታ መንደርደሪያ ያደረግኩት በምክንያት ነው፡፡ በቀደም ዕለት አንድ ሰው በትዊተር ገጹ ላይ ደብረ ብርሃን ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ፣ የጀበና ቡና የምታፈላ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ማግኘቱን ያጋራል፡፡ ለሆቴሉ ሠራተኞች ‹‹የተከበረች ምሁር›› ናት ሲላቸው መደንገጣቸውንም ያክላል፡፡ እኔም ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ማለትም በፀጉር ማስተካከል፣ በሻምፑ እጥበት፣ በሆቴል መስተንግዶና በራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተመራቂዎችን አግኝቼ አውቃለሁ፡፡ ሥራ ክቡር በመሆኑም አበረታትቻለሁ፡፡ ድሮ ህንድ ውስጥ ሁለትና ሦስት ዲግሪዎች ይዘው ፓስቲ የሚጠብሱ ምሁራን እንደነበሩ ሲነገርም ሰምቼ ነው ያደግኩት፡፡ የሚቆጨው ግን አንድ ሰው በተማረበት የትምህርት ዘርፍ አገሩን እንዳያገለግል ዕድል ማጣቱ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ተምረው ከንቱ ሆነው ከሚቀሩት ይልቅ ያገኙትን እየሠሩ ለነገ ተስፋ የሚሰንቁ በጣም ይሻላሉ፡፡
ተማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲማሩ መልካምም ሆነ መጥፎ የሚባሉ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው ከወላጆች ቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ገቢያቸው ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ የተገኙ ሴት ተማሪዎች፣ ለወር አበባ የሚገለገሉበት የንፅህና መጠበቂያ ፓድ መግዣ ይቸገራሉ፡፡ ይህንንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ሲሉና ከጓደኞቻቸው ላለማነስ ሲሉ፣ ገንዘብ የማግኛ አማራጮችን ሲያማትሩ ሳይወዱ በግድ የወሲብ ንግድ ውስጥ ገብተው ላልተፈለገ ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ ከጉልበት ሥራ ጀምሮ ያገኙትን እየሠሩ ችግራቸውን ለመድፈን ይጣጣራሉ፡፡ ቀበጦቹ ደግሞ ለጫት፣ ለመጠጥና ለሌሎች ሱሶች ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን ይጎዳሉ፡፡
አንድ ጊዜ ከአሜሪካ ከመጡ ሁለት ጓደኞቼ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው በጣም ዝነኛ የተባለ የምሽት ክለብ እንሄዳለን፡፡ እኔ የምሽቱን ዓለም ከተውኩት በጣም ስለቆየሁ፣ ይህንን ስም አይጠሬ ክለብ ሳየው በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ውስጥ ያለ እንጂ፣ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አይመስልም፡፡ ለማንኛውም በራፉን አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀብታሟን ኢትዮጵያ ያየኋት መሰለኝ፡፡ ወዛቸው የሚያብረቀርቅ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና ወጣት መሳይ ሽማግሌዎች የሞሉበት ዝነኛ ክለብ ውስጥ የውብ ሴቶች ብዛት ያስደነግጣል፡፡ አዲስ አበባ እዚህ ደረጃ መድረሷን ባለማወቄ በራሴ አፈርኩ፡፡ ከአሜሪካ የመጡት ጓደኞቼ በቪዲዮም ሆነ በምሥል መረጃው ቢኖራቸውም፣ በአካል በዚህ ደረጃ የጠበቁት ስላልመሰላቸው ነው መሰል በጣም ነበር የተደመሙት፡፡
የእኔው ዳያስፖራዎች አንድ ሁለት ወሰድ ሲያደርጉ ከቆንጆዎቹ መሀል መረጥ አድርገው ወደ ጠረጴዛችን ለማምጣት ጊዜም አልፈጀባቸው፡፡ ሁለቱ ውብ ፍጥረቶች በእንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ ከባለቤቶቹ ባልተናነሰ ቅላፄ ሲናገሩ፣ አንዳቸው ከአሜሪካ አንዳቸው ደግሞ ከፈረንሣይ የመጡ ነበር የሚመስሉት፡፡ እነሱ እንደነገሩን ከሆነ ግን ሃይ ስኩል ጨርሰው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የተዘጋጁ ‹‹ፍሬሾች›› ናቸው፡፡ ቮድካ በብርቱካን ጭማቂ (ስክሩ ድራይቨር ይሉታል) እየጠጡና በሙዚቃ እየተዝናኑ፣ ካሰኛቸው ወንድ ጋር ደግሞ ሌሊቱን ለማሳለፍ ቅር እንደማይላቸው ሲነግሩን እጄን አፌ ላይ አድርጌ ከማዳመጥ የዘለለ ሚና አልነበረኝም፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሁለት ዓለም ሰዎች እየበዛን እንደሆንን ለማሳሰብ ያህል ነው ይህንን ገጠመኝ የጻፍኩላችሁ፡፡
(ሲራክ ሰለሞን፣ ከገርጂ መብራት ኃይል)